Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, February 28, 2019

ኖኪያ አምስት ካሜራ ያለው ተንቀሳቃሽ ስልክ ሠራ

ኖኪያ9


ኖኪያ አምስት ካሜራዎች ያለው ተንቀሳቃሽ ስልክ ሰርቶ ይፋ አደረገ።
ኖኪያ9 የተባለው አዲሱ የኖኪያ ተንቀሳቃሽ ስልክ ባልተለመደ መልኩ ከስልኩ ጀርባ አምስት ካሜራዎች ተገጥመውለታል። አምስቱም ካሜራዎች በአንድ ጊዜ በመናበብ የላቀ ጥራት ያለው ፎቶ ያነሳሉ።

ሦስቱ ካሜራዎች ቀይ፣ አረንጓዴና ሰማያዊ ቀለምን ለማመጣጠን ያገለግላሉ። ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ መደበኛ ምስል ይወስዳሉ። ካሜራዎቹ በአጠቃላይ በቂ ብርሃን በመስጠት ምስሉ ላይ ጥራትን ከመጨመር ባሻገር በሚነሳዉ ምስል ላይ ምንም አይነት ጥላ እንዳይኖር ያደርጋሉ።
አምስቱም ካሜራዎች እያንዳንዳቸዉ 12 ሜጋ ፒክስል የጥራት መጠን ሲኖራቸዉ በአንድ ላይ ተናበዉ ያለቀለት ምስል እንዲያወጡ ተደርገው ነው የተሠሩት። የስልኩ የጥራት መጠን በአጠቃላይ እስከ 240 ሜጋ ፒክስል ይደርሳል ተብሏል።

ስልኩ በኖኪያ ስም ቢወጣም ሥራው የተከናወነው ከ2016 ጀምሮ በገበያ ላይ በሚገኘዉ ኤች ዲ ኤም ኩባንያ ነው። ኩባንያዉ በእንግሊዝ ብቻ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ3 በመቶ በላይ ድርሻ እንዳለው ይነገራል።
ስልኩ ስፔን ባርሴሎና ላይ በተከሄደ አውደ ርዕይ ለእይታ ቀርቧል። ኖኪያ9 የመነሻ ዋጋ የተቆረጠለት ሲሆን ለጊዜውም በ699 የአሜሪካን ዶላር እየተሸጠ ይገኛል።

Tuesday, February 26, 2019

የምድራችን ትልቋ ንብ ተገኘች




የዓለማችን ትልቁ ንብ ለዓመታት ጠፍቷል ተብሎ ሲታሰብ በድጋሚ ተገኘ።
የሰውን አውራ ጣት የሚያክለው ትልቁ ንብ የተገኘው በጥቂቱ በተጠናው የኢንዶኔዥያ ደሴት ላይ ነው።
የዱር እንስሳት ባለሙያዎች ለቀናት ካደረጉት ፍለጋ በኋላ ነበር በመጠኗ ለየት ያለችውን ትልቋን ሴት ንብ አግኝነው የቀረጿት።

የዋላስ ትልቁ ንብ በመባል የሚታወቀው የዚህን ተመሳሳይ የንብ ዝርያን ለመጀመሪያ ጊዜ እኤአ በ1858 ባገኘው እንግሊዛዊ የተፈጥሮ ተመራማሪ አልፍሬድ ረስል ዋላስ ስም ነው የተሰየመው።
እኤአ በ1981 ሳይንቲስቶች ብዙ የዋላስ ንብ ዝርያን ያገኑ ቢሆንም ከዚያ ዓመት በኋላ ታይቶ አያውቅም ነበር።
ይህንን ትልቅ ተመሳሳይ የንብ ዝርያ ለማግኘት በጥር ወር አንድ የጥናት ቡድን የዋላስን ኮቴ ተከትሎ ፍለጋውን ለማድረግ ወደ ኢንዶኔዥያ አቅንቶ ነበር።

የመጀመሪያውን ምስል የወሰደው የተፈጥሮ ታሪክ ፎቶ አንሺ ክለይ ቦልት እንደተናግረው "በህይወት ይኑር አይኑር የማናውቀውን ትልቁን በራሪ ንብ ከፊት ለፊታችን በደን ውስጥ እየበረረ ማየት በጣም ድንቅ ነበር" ብሏል።
"በአካል ሲታይ ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ ማየት፤ በትልልቅ ክንፎቹ ከራሴ በላይ ሲበር የሚያወጣውን ድምፅ መስማት በጣም ድንቅ ነበር።"

የዋላስ ትልቁ ንብ (ሜጋቺል ፕሉቶ)
• ወደ 6 ሳንቲ ሜትር የሚጠጋ የክንፍ እርዝማኔ ያለው ሲሆን የዓለማችን ትልቁ የንብ ዝርያ ነው
• ሴቷ ንብ ቤቷን የምትሰራው በምስጦች ኩይሳ ነው። በትልልቅ መንጋጋዎቿም የሚያጣብቅ ሙጫ ተጠቅማ ቤቷን ከምስጦች ትከላከላለች።
•ትልቁ የንብ ዘር በዝቅተኛ ቦታ ላይ ባሉ ዛፎች ላይ ሙጫ ለማግኘት እና በዛፍ ላይ በሚኖሩ ምስጦች ላይ መኖሪያቸውን ለመስራት ጥገኛ ናቸው።
• ከቻርልስ ዳርዊን ጋር የዝገመታዊ ለውጥን ንድፈ ሃሳብ በጋራ እንደሰራ የሚነገርለት ዋላስ ይህንን የንብ ዝርያ "ትልቅ ጥቁር ንብ መሳይ ሆኖ እንደ ጢንዚዛ ትልቅ መንጋጋ ያለው" በማላት ገልጾታል።

በኢንዶኔዥያ ደሴት ሰሜን ሞሉካስ የተገኘው የትልቁ ንብ ጫካው የዓለማችንን ጥቂት ነፍሳት መገኛ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ ሰጥቷል።
ወደ ቦታው ያቀናው የምርምር ቡድኑ አባል የሆነው የንብ ተመራማሪ ኢሊ ቂማን እንደሚለው የትልቁ ንብ ዳግም መገኘት ወደፊት ለሚደረገው የንቡ ታሪክ ጥናት እና እንዳይጠፋ ለሚደረገው ምርምር ተስፋ ይሰጣል ብሏል።

ከምድር ለጠፉ ዝርያዎች ዓለም አቀፍ ፍለጋ የጀመረው ግሎባል ዋይልድ ላይፍ ኮንሰርቬሽን የአካባቢ ጥበቃ ቡድን ወደ ኢንዶኔዥያ ለተጓዘው ቡድን ድጋፍ አድርጓል።
"ዝም ከማለት ይልቅ ለጥበቃው እንዲረዳ የተገኘችውን ትልቋን ንብ ምልክት በማድረግ የንቡን ዘር የወደፊት እጣ ተስፋ የሚሰጥ ማድረግ ይቻላል" በማለት ሮቢን ሞሬ ተናግሯል።
በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ንቦችን በማነብ ያለምንም ስጋት የሚኖረው ቤተሰብ።

ትልቋ ንብ

Monday, February 25, 2019

"በወንድሜ ለአምስት ዓመታት ተደፍሬአለሁ"

ጀርባዋ የሚታይ ሴት


መገናኛ አካባቢ የሚገኝ ፀጥ ያለ መንደር ነው። ሰባት ወይም ስምንት የሚሆኑ ልጅ ያቀፉ አፍላ ታዳጊዎች እየተሳሳቁ ከአንድ ትልቅ ግቢ በመውጣት ላይ ነበሩ። ሁሉም ልጅ የያዙና በእድሜም ለእናትነት ገና መምሰላቸው ትኩረት ይስባል። ምን እየተባባሉ እንደሆነ ለመስማትም ያጓጓል።
እነሱን አልፈን ወደ ውስጥ ዘለቅን።
የ23 ዓመት ወጣት ነች። ከገፅታዋ ምንም ነገር ማንበብ አይቻልም። ገፅታዋም ሆነ ሁለንተናዋ ፀጥ ያለ ነው። ከዓመታት በፊት ወደ እዚህ ግቢ ስትመጣ የሥራ ማመልከቻ ለማስገባት ወይም ሥራ ለመጀመር አልነበረም። ይልቁንም በእናቷ ልጅ በወንድሟ ተደፍራ ከደረሰባት ከባድ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ለማገገምና መጠለያ ለመሻት ነበር።
የደረሰባት ነገር ሰው እንድትፈራ አድርጓት ነበርና በሙሉ አይኗ ሰው ማየት ያስፈራት፤ ቃላት አውጥቶ መናገርም ይከብዳት እንደነበር ታስታውሳለች።

"ከባድና እጅግ አሳዛኝ ህይወት አሳልፌአለው" ትላለች ጊዜውን በማስታወስ። የጉዳቷ መጣን በህይወት እየኖርኩ ነው የማያስብል ቢሆንም ያን ቀን አልፋ ዛሬ ቀና ብላ መራመድ ችላለች። ዛሬ የምትፈልግበት መድረስና ህልሟን መኖር እንደምትችልም በእርግጠኝነት ትናገራለች።
ዛሬ ያኔ ተደፍራ የተጠለለችበትና ለተደፈሩ ሴቶች ድጋፍ የሚያደርገው 'የሴቶችና የህፃናት ማረፊያ' ውስጥ ለመሥራት ችላለች።
ምንም እንኳ ያን ጊዜ ማስታወስ ቢያማትም ያለፈችበት መንገድ ሴቶች ለፆታዊ ጥቃት እንዳይጋለጡ አስተማሪ ይሆናል የሚል ፅኑ እምነት ስላላት የሆነችውን ትናገራለች።
ሊያስተምራት አዲስ አበባ ያመጣት ትልቅ ወንድሟ ፖሊስ ነበር። ያኔ እሷ የ16 ዓመት ታዳጊ ነበረች። የሚኖሩት ወንድሟ በተከራየው ቤት ነበር።
"ልጅ ስለነበርኩ ብዙ ነገር አላውቅም፤ መናገርም አልችልም ነበር። ሰው ሳይ ተመሳሳይ ጥቃት ያደርሱብኛል ብዬ ፍራቻ ነበረብኝ" በማለት የነበረችበትን የሥነ ልቦና ስብራት ታስታውሳለች።
ሰው አይቷት ሚስጥሯን የሚያውቅ ይመስላት ስለነበር ትምህርት ቤት መሄድና መመለስ፤ ክፍል ውስጥ መቀመጥም እጅግ ስለከበዳት ትምህርት ቤት መሄድ አቆመች።

ወንድሟ ለአምስት ዓመታት አብረው ሲኖሩ ደፍሯታል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሦስት ጊዜም ፅንስ እንድታቋርጥም እንዳደረጋት ትገልፃለች።
ልጅነትና የሥነ ልቦና ቀውስ እንዲሁም የወንደሟ ማስፈራራት ለማንም ምንም ትንፍስ ሳትል እንድትቆይ አድርጓት ነበር። ይኖሩ ከነበሩበት ቤት ለቅቀው ሌላ የኪራይ ቤት የገቡበት አጋጣሚ ግን ጉዳቷን አውጥቶ ለመናገር እድል ሰጣት።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁኔታዋን ያስተዋሉት አዲሷ የቤት አከራያቸው አንድ ቀን "ለምንድነው ሰው የማትቀርቢው? ዘመዱ ነሽ ወይ?" ሲሉ ድንገት ጠየቋት።
ሁለቱም ጥያቄዎች ለእሷ እጅግ ከባድ ነበሩ። ከምትኖርበት ስቃይ መውጣት ትሻ ነበርና አለባብሶ እንደነገሩ መልስ መስጠት አልፈለገችም። በሌላ በኩል እውነቱን መናገርም መከራ ሆነባት።
እንደምንም ከራሷ ጋር ታግላ የሆነችውን ለአከራይዋ ተናገረች። በነገሩ በጣም የደነገጡት አከራይ ይዘዋት በአቅራቢያ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ለመሄድ ምንም አላመነቱም።
ከፖሊስ ጣቢያ በኋላ ነበር የተደፈሩ ሴቶችን ወደሚያስጠልለውና የሕግ አገልግሎት ድጋፍ ወደሚያደርገው የሴቶች ማረፊያ ልማት ማኅበር የተወሰደችው።

"ቤተሰብ በኔ ፈረደ"
ነገሩ ወደ ሕግ ከሄደ በኋላ ጉዳዩን የሰሙ ቤተሰቦቿ 'እሱ እንዲህ አያደርግም፤ ልጅ ስለሆነች ነው እንዲህ ያለ ነገር የምታወራው' በማለት በፍፁም ሊያምኗት አልቻሉም። በተለይም ትልቅ እህቷ ካለማመን አልፋ የወንድማቸውን ስም ለማጥፋት 'ያልሆነውን ሆነ እያለሽ ነው' በሚል ብዙ ሞግታታለች ዝታባታለችም።
"ከእናቴ ውጪ ቤተሰብ ሁሉ እንደ ቆሻሻ ተፀየፈኝ" በማለት ተበዳይ ሆና እንዴት የበዳይ እዳ ተሸካሚ እንደተደረገች ትናገራለች።
በሌላ በኩል ፖሊስ ጣቢያ በሄደችበት ወቅት ያየችው አቀባበል እንደሷ ያሉ የተደፈሩ ሴቶች ይብስ ፈርተው እንዳይናገሩ የሚያደርግ እንደነበር ታስታውሳለች።
ሃዘኔታ በሌለው አንደበት 'ነይ እዚህ ጋር' 'እዛጋ' 'እስከዛሬ ምን ትሰሪ ነበር?' ተብላለች።

ይህ የእሷ ብቻ ሳይሆን የብዙ ሴቶች አስከፊ እጣ ነው። በማህበረሰቡ እንዲህ ስላደረግሽ ነው፣ እንደዛ ባታደርጊ ኖሮ በሚሉ የምክንያት ድርደራዎች ለመደፈራቸው ራሳቸው ጥፋተኛ ተደርገው አንገታቸውን እንዲደፉ የተደረጉ ሴቶችን ቤት ይቁጠራቸው።
በቀድሞ መጠለያዋ በዛሬው የሥራ ቦታዋ በወንድም፣ በአባት፣ በአያቶቻቸውም ጭምር የተደፈሩና የወለዱ ሴቶችም ጭምር አጋጥመዋታል። ሁሉም በቤተሰባቸውና በማኅበረሰባቸው ለመደፈራቸው ጥፋተኛ የተደረጉና የተወገዙ መሆናቸውን ትናገራለች።
"እኔ ስለ ሕግ ብዙ አላውቅም፤ ግን ካለፍኩበትና ካየሁት በሕግ በኩል ያለው ነገርም ደስ አይልም።"
በተለያዩ ምክንያቶች ደፋሪዎች ነፃ ሆነው የመሄድ እድል ያገኛሉ። በተመሳሳይ በእሷ ጉዳይም ክስ ተመስርቶ የነበረ ቢሆንም ክሱ የትም ሳይደርስ፤ ወንድሟም ሳይጠየቅ መቅረቱን ትናገራለች።
"ህመሜን ተቋቁሜ ችሎት ላይ ብቆምም መጨረሻው አላማረም። እዚህ ላይ ብዙ ማለት አልፈልግም" ትላለች።
"ለመረዳት ፍቃደኛ መሆን አለብን"
ባደረገችው ተደጋጋሚ የፅንስ ማቋረጥ የማህፀን ጉዳት ደርሶባት ለረዥም ጊዜ ህክምና ስትከታተል ቆይታለች። በዚሁ ምክንያት ዛሬም ከባድ የወገብ ህመም ስላለባት ለቃለ መጠይቅ ባገኘናት ወቅትም በሃኪም የታዘዘ የወገብ መደገፊያ ቀበቶ አድርጋ ነበር።
ይህ ሁሉ ቢሆንም ግን "በጣም የተጎዳሁት በሥነ ልቦና ነው። በተለይም የቤተሰቦቼ ነገር በእጅጉ ጎድቶኛል ዛሬም አልወጣልኝም" ትላለች።
ወደ ማረፊያው ከገባች በኋላም ምግብ መብላት፣ ሰው እንዲቀርባትና እንዲያናግራትም አትፈልግም ነበር። ፍላጎቷ አንድና አንድ ነበር። ይቺን ዓለም ለመተው ራሷን ለማጥፋትም ሞክራ ነበር።
በመጨረሻ ከዚህ ያወጣት የተደረገላት የሥነ ልቦና ድጋፍ እንደሆነ ትናገራለች።

ደህና ሆና ወደ ራሷ ከተመለሰች በኋላ ደግሞ የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎችን ወስዳለች። የሴቶች ማረፊያ ልማት ማኅበር ከሙያ ስልጠና በተጨማሪ ለተደፈሩ ሴቶች ራሳቸውን ከጥቃት መከላከል ይችሉ ዘንድ የቴኳንዶ ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን እሷም ይህን ስልጠና ወስዳለች።
ሰዎች በጣም ሲጎዱ ብዙ ነገር አይፈልጉም። ምንም ነገር መስማትም መረዳትም ላይፈልጉ ይችላሉ። "ቢሆንም ግን ሰውን መርዳት የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች ስላሉ መጀመሪያ እኛ ለመረዳትና ወደፊት ለመራመድ ፍቃደኛ መሆን አለብን" ትላለች።
ካጋጠማት አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃትና ሰቆቃ ለመውጣትና ከባዱን ቀን ለማለፍ ብርታት ያገኘችው ከእራሷ ነበር። "ራሴን ማመኔ፣ የተበላሸ ህይወቴን ማስተካክል እንደምችል ማመኔ ረድቶኛል" ትላለች።
ባይናገሩም ከእሷ የበለጠ ከባድ ነገር ያሳለፉ ሴቶች ይኖራሉ ብላ ታስባለች። ማህበረሰቡ የእንደዚህ ያሉ ሴቶችን ታሪክ ሰምቶ መጠቋቆሚያ እያደረገ እንደገና ቁስላቸውን ባያደማ በታሪካቸው ብዙዎች እንዲማሩና የተሰበሩትም ቀና እንዲሉ ማድረግ ይቻል ነበር የሚል እምነት አላት።
"ሻርፕ ጠምጥመው ስብር ብለው የሚሄዱ ሴቶች ሳይ ሁሌም የእኔ ታሪክ ይመስለኛል" የምትለው ወጣቷ በእንደዚህ ያለ አጋጣሚ ለምታገኛቸው ሴቶች ምንም ባታደርግላቸው እንኳ ገፍታ እንደምታናግራቸውና እንደምትሰማቸው ትናገራለች።
ማኅበረሰቡ የሴቶች ጉዳይ ግድ እንደሚለው ከተማረና ካመነ በብዙ መልኩ እንደ እሷ የተደፈሩ ሴቶችን ሊያግዝ የሚችልበት መንገድ እንዳለ ታምናለች። ከሁሉም በላይ ደግሞ በዚህ ጥቃትን መከላከልም እንደሚቻል ይሰማታል።

ህፃናትም ይሁኑ ታዳጊዎች ያሉት ቤተሰብ በሉ፣ ጠጡ፣ ለበሱ እና ትምህርት ቤት ሄደው መጡ፤ ከሚለው ባሻገር ቤት ውስጥም ሆነ ውጪ ልጆቹ ላይ ጥቃት ሊፈፀም እንደሚችል ማወቅ አለበት። ይህም ልጆችን ለመጠበቅ ያስችላል ትላለች።
"ማን ይፈልገኛል?"
የቀድሞው ፆታዊ ጥቃት ተከላካይ ማኅበር የአሁኑ የሴቶች ማረፊያ ልማት ማህበር በደረሰባቸው ጥቃት የተጎዱ፣ የተሰበሩና 'ማን ይፈልገኛል?' ብለው ራሳቸውን ማጥፋት የፈለጉ በርካታ ሴቶችን ለመደገፍ ጥረት ያደርጋል። ለተደፈሩ ሴቶች የሕግ ድጋፍና የሙያ ስልጠና በመስጠት ከ15 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።
የድርጅቱ መስራች ወ/ሮ ማርያ ሙኒር ማን ይፈልገናል? በሚል ራሳቸውን ለማጥፋት ሞክረው የነበሩ ሴቶች ከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለው ህይወታቸው ተቀይሮ ማየት ለሳቸው ትልቅ ነገር እንደሆነ በየጊዜው ምሳሌ የሚሆኑ ሴቶችን ታሪክ ለሚያወጣው 'ተምሳሌት ገፅ' ተናግረዋል።
ማኅበሩ በአዲስ አበባ፣ በደሴና በሌሎች ቅርንጫፎቹ እያገለገሉ የሚገኙ ኢንጅነሪንግ፣ ማኔጅመንትና ሌላ ሌላም ያጠኑ ወጣት ሴቶችን አቅፏል። ታሪኳን የነገረችን ወጣትም አዲስ አበባ ውስጥ በሙያ አሰልጣኝነትና በሃላፊነት እያገለገለች ነው።

Sunday, February 24, 2019

መጠጥ የ130 ሰው ህይወት ቀጠፈ

በመጠጡ ጉዳት የደረሰባቸው ሕንዳውያን ሠራተኞች


በሻይ ቅጠል ልማት ላይ የሚሠሩ ሕንዳዉያን ባለፈዉ ሀሙስ ለደስታ ብለዉ የተጎነጩት አልኮል ህይወታቸዉን አሳጥቷቸዋል።
እቅዳቸዉ የተለያየ መጠን ያለዉ የታሸገ አልኮል ገዝተዉ ከጓደኞቻቸዉ ጋር መደሰት ነበር።
አልኮሉ የተመረዘ በመሆኑ ግን ከጠጡት ሰዎች መካከል ቢያንስ 130 የሚሆኑት እስከ ትናንት እሁድ ድረስ በተለያዩ ሆስፒታሎች እርዳታ ቢደረግላቸዉም መትረፍ አልቻሉም።
ቢቢሲ ጎላግሃት ሆስፒታል ሲታከም ያገኘዉ ተጎጅ እንደሚናገረዉ፤ መጀመሪያ ምንም የተለየ ስሜት አልነበረዉም። ከደቂቃዎች በኋላ ግን የራስ ምታቱ እየጨመረ በመምጣቱ ለመተኛትም ሆነ ለመመገብ ከተቸገረ በኋላ ራሱን ስቷል።

በዛው ሆስፒታል የሚሰሩት ዶ/ር ራቱል ቦርዶሎይ እንተናገሩት፤ ተጎጂዎቹ ወደ ሆስፒታል ሲሄዱ ከፍተኛ ማስመለስ፣ የደረት ህመም እና የመተንፈስ ችግር ገጥሟቸዉ ነበር።
አብዛኛዎቹ ተጎድተዉ ስለነበርና አልኮሉ መርዛማ ስለሆነ ማትረፍ አልተቻለም። ጉዳዩ በተከሰተበት ሰሜናዊ ሕንድ እስካሁን ከሞቱት 130 ሰዎች በተጨማሪ 200 ሰዎችም በዚሁ የተመረዘ አልኮል ሳቢያ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸዉ ይገኛል።
የተመረዘውን አልኮሉን አሰራጭተዋል የተባሉ ግለሰቦችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል።
ከ2011 ወዲህ ይህን ያህል ሰዉ በተመረዘ አልኮል ምክንያት ሲሞት ለመጀመሪያ ጊዜ ነዉ። በ2011 ዌስት ቤንጋል በተባለዉ የሕንድ ግዛት ውስጥ በተመሳሳይ ክስተት 170 ሰዎች መሞታቸዉ ይታወሳል።

Saturday, February 23, 2019

ሳምሰንግ እንደ መጽሐፍ የሚገለጥ ስልክ አመረተ

እንደ መፅሐፍ የሚገለጠው ሳምሰንግ ተንቀሳቃሽ ስልክ


የሳምሰንግ አዲሱ ምርት ዋጋው ከ50ሺህ ብር በላይ ነው። የተንቀሳቃሽ ስልክ አምራቹ ሳምሰንግ ሦስት በዓይነታቸው ልዩ ያላቸውን የስልክ ናሙናዎች ይፋ አድርጓል።
ከነዚህ ውስጥ አነጋጋሪ የሆነው እንደ መጽሐፍ ይገለጣል የተባለለት ስልክ ነው። በሁለት ወር ውስጥ ለገበያ ይቀርባል ተብሏል።
በኅዳር 2010 "ጋላክሲ ኤስ" ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ የጀመረው ሳምሰንግ 10ኛው ኤስ ሰፊ ገበያ ያስገኝልኛል ሲል ተልሞ ነው የተነሳው።
ከዚሁ ታጣፊ ስልክ ጋር አብሮ የቀረበው "ጋላክሲ ኤስ10 5ጂ" ታጣፊ ያልሆነ ቢሆንም ፈጣን ኢንተርኔንትን ለመጠቀም ግብ አድርጎ የተፈበረከ ነው ተብሏል።

ከነዚህ በኤስ10 ስም ከሚቀርቡ ሦስት ምርቶች አንዱ ደግሞ በዋጋ ደረጃ የደንበኞችን ኪስ የማይጎዳ እንዲሆን ታስቧል።
የሳምሰንግ የመጨረሻ ምርት የነበረው 'ኤስ-9" በዋጋው መናር ምክንያት ሽያጩ ከተጠበቀው በታች ስለነበረ ድርጅቱ ትምህርት ወስጃለሁ ብሏል።
ይህ እንደ መጽሐፍ ይገለጣል የተባለለት ቅንጡ ስልክ የሁለት መጠነኛ ስልኮች ስፋት ሲኖረው ወደ ጎን 18.5 ሴ.ሜ ይረዝማል።
ሲዘረጋም ታብሌት እንጂ ስልክ አይመስልም። ዋናው አገልግሎቱ ደንበኞች በአንድ ጊዜ ሦስት መተግበሪያዎችን መጠቀም እንዲችሉ ነው።
እንደ መጽሐፍ የሚገለጥ ሳምሰንግአንድ ሰው በዚህ ታጣፊ ስልክ ዩቲዩብ ቪዲዮ እያየ፣ ማየቱን ሳያቋርጥ ስለፊልሙ ከወዳጁ ጋር በአጭር መልዕክት እየተላላከ ከጎን ሌላ ተጨማሪ መተግበሪያን ከፍቶ ያሻውን ማድረግ ያስችለዋል።
ይህ ታጣፊ ስልክ 6 ካሜራዎች ሲኖሩት ሦስቱ ከጀርባ፣ ሁለት ከጎን አንድ ደግሞ ከፊት ለፊት ይገኛሉ። ይህም ስልኩን በየትኛውም ሁኔታ ይዞ ፎቶ ማንሳት ያስችላል ተብሏል።
ከዚህም ባሻገር አንድን ምሥል አቅርቦና አርቆ ፎቶ ለማንሳት የሚያስችሉ መተግበሪያ ቁልፎች ተዘጋጅተውለታል።
ሳምሰንግ "ኤስ 10" ገመድ አልባ ቻርጀር ስላለው አብረው የሚሸጡትን የጆሮ ማዳመጫዎችንና ሌሎች ባትሪ የሚሹ ቁሶችን ቻርጅ ማድረግ ይችላል።
ይህ ስልክ ዋጋው በብር እስከ 56 ሺህ ይጠጋል። ቁርጥ ያለው ዋጋው በዶላር 1ሺህ 9መቶ 80 እንደሆነ ሲነገር በአዳራሹ የነበሩ ታዳሚዎችን አስደንግጧል።

የዛሬ 74 ዓመት የተሳመው 'ከንፈር' ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

የአውድ ርዕይ ጎብኚ ምሥሉን በተንቀሳቃሽ ስልኩ ሲያነሳ

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ምሥሉ በዓለም ዙሪያ በትልልቅ አውደ ርዕዮች ቀርቦ አድናቆትን አትርፏል
እጅግ ከሚወደዱና ከተጨበጨበላቸው ፎቶግራፎች አንዱ ነው። በአሜሪካ ብቻም ሳይሆን በዓለም ዙርያ ይህ ምስል ተወዳጅ ነው። ዝነኛም ነው። ስሜት ኮርኳሪም ነው። ያለ ምክንያት ግን አይደለም።
2ኛው የዓለም ጦርነት ማብቃቱን ተከትሎ አንድ የአሜሪካ ጦር መርከበኛ ድንገት በኒውዮርክ ጎዳና ላይ የነበረችን ቆንጆ ጎተት አድርጎ ከንፈሯን ጎረሰው። ምንም አላስተረፈም።
ያን ቅጽበት የፎቶ ጥበበኛው አልፍሬድ አይዠንስታድ በካሜራው አስቀረው። ያ ምሥል 'ላይፍ' በተባለው መጽሔትም ታተመ። ከዚያ ወዲህ በመጽሔቱ ብቻ ሳይሆን በሚሊዮኖች ልብ ላይ የታተመ የዓለማችን እጹብ ድንቅ ፎቶ ሆኖ ኖረ።

ያ ጎበዝ ሳሚ መርከበኛ ስሙ ጆርጅ ማንዶሳ ይባላል። በተወለደ በ95 ዓመቱ ትናንት ማረፉ ተሰምቷል።
የ21 ዓመቷ ተሳሚ ቆንጆ ግሬታ ዚመር ፍሬድማን ትባላለች። በ2016 ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው። ኖራ ኖራ በ92 ዓመቷ ማለት ነው።
የፎቶግራፍ ጥበበኛው አልፍሬድ አይዠንስታድ ያኔ ሳሚና ተሳሚዎቹ እነማን እንደሆኑ ሁሉ አልገለጸም ነበር። ኋላ ነው ነገሩ ይፋ የሆነው።
እንደመታደል ኾኖ መርከበኛው የደንብ ልብሱን ለብሶ ድንገት እየበረረ አንዲትን ቆንጆ ሲስም ቅጽበቱን በካሜራ ቀለበው። ነገሩ ችሎታ ከምንለው ዕድል ብንለው ይቀላል። ይህ የሆነው ነሐሴ 14 ቀን 1945 ነበር።
"ድንገት በካሜራዬ ሌንስ ውስጥ አንድ ጉብል [ከሰልፍ መስመር ወጥቶ] ድንገት አንዲት ኮረዳን እንቅ አድርጎ ሲስማት ተመለከትኩ። የካሜራዬን ቁልፍ ተጫንኩት። ኮረዳዋ ነጣ ያለ የነርስ ደንብ ልብስ ነበር የለበሰችው። [ጎልታ ትታየኝ ነበር] እንዲያ ባትለብስ ኖሮ ይህን ምስል ስለማግኘቴ እጠራጠራለሁ" ብሎ ነበር፤ አልፍሬድ።

ወይዘሪት ፍሬድማን ያኔ የጥርስ ሐኪም ረዳት ነበረች። ስለዚያ አስደናቂ ፎቶግራፍ ያወቀችው ግን ምስሉ ከወጣ ከ16 ዓመት በኋላ በ1960 ነበር።
"ያን ያህልም እኮ የፍቅር መሳሳም አልነበረም። እንዲሁ በፈንጠዚያ ላይ ነበርን፤ በቃ ይኸው ነው" ብላ ነበር፤ ስለዚያ ፎቶግራፍ ስትናገር።
ዓለም ግን ይህን ፎቶግራፍ በዚያ መንገድ አልወሰደውም። ከብዙ እልቂት በኋላ ጃፓን ለአሜሪካ ጦር እጅ የሰጠችበትና የአሜሪካ አሸናፊነት የተበሰረበት ዕለትም በመሆኑ የዚያ ፎቶግራፍ ትርጉምና ዝና በአያሌው ገዝፎ ኖሯል።

የኦነግ አባላት ከነበሩባቸው ቦታዎች እየተመለሱ ነው ተባለ


በመንግሥትና በኦነግ መካከል በአባገዳዎችና በሽማግሌዎች አማካይነት የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ የግንባሩ አባላት ከነበሩባቸው ቦታዎች በሰላም እየተመለሱ መሆናቸው ተነገረ።
በምዕራብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሰው የኦነግ ኃይል አዛዥ ኩምሳ ድሪባ ወይም በትግል ስሙ  መሮ በመባል የሚታወቀው ግን ይህንን ለመፈፀም ዝግጁ አይደለም ተብሏል።

በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተሰማርተው የሚገኙ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጦር አባላት የአባገዳዎችን ጥሪ ተከትለው ትጥቅ ፈትተው ወደ ጦር ካምፖች ከመግባታቸው በፊት ወደተዘጋጁላቸው ጊዜያዊ ማቆያ ስፍራዎች እየገቡ መሆኑ ታውቋል።
ለዚሁም አባገዳዎችባ የየአካባቢዎቹ ባለስልጣናት ለውሳኔው ተገዢ  የኦነግ አባላት  ወደተዘጋጁላቸው ስፍራዎች ከነትጥቃቸው ሲመጡ አቀባበል እያደረጉላቸው መሆናቸው ነው የተነገረው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የአባገዳዎችን ጥሪ ተከትሎ ሁሉም የኦነግ ጦር አባላት እየተመለሱ አለመሆናቸው ተነግሯል።
ለዚህም እንደምክንያት የሚጠቀሰው የምዕራብ ኦሮሚያ የኦነግ ጦር አዛዥ የሆነው ኩምሳ ድሪባ ወይም በትግል ስሙ መሮ የአባገዳዎችን ጥሪ አለመቀበሉ ታውቋል።
በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኘው የኦነግ ጦር አዛዥ እንደሆነ በስፋት የሚነገርለት ኩምሳ ድሪባ (መሮ) ከቢቢሲ ጋር የስልክቃለምልልስ ማድረጉ ነው የተነገረው።
በዚሁቃለምልልስም መሮ ባለው ሁኔታ ስምምነቱን ተቀብሎ ለመግባት ዝግጁ እንዳልሆነ ገልጿል።
የአባገዳዎችን ጥሪ ለመቀበል እና እርቅ ለማውረድ ዝግጁ ስለመሆኑ ተጠይቆ “የእርቅ  ኮሚቴው  አባላት እኔን በአካል አግኝተው ለማነጋገር ፍላጎት የላቸውም ብሏል።
ትኩረት ያደረጉት ጦሩን አንድ በአንድ እጁን እንዲሰጥ ማድረግ ላይ ነው” በማለት እሱም እነሱን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አለመሳካቱንም ነው የገለጸው።
እንዲያውም “ጦሩን የመበታተን ዓላማ ይዘው ነው እየተንቀሳቀሱ ነው ሲል የእርቅ ኮሚቴ አባላትን ወቅሷል።
“ወደፊት መራራ ትግል ማድረጋችንን እንቀጥላለን” ያለው መሮ “ብቻዬን ብቀር እንኳ ትግል ማድረጌን እቀጥላለሁ እቅዴም ይሄው ነው” በማለት በትጥቅ ትግሉ እንደሚቀጥል ገልጿል።
በተያያዘ ዜናም የኦነግ አባላት ትጥቅ ፈተው በሰላማዊ መንገድ ወደ ካምፕ እንዲገቡ ለማድረግ ወደ አካባቢው የተጓዙት አባገዳዎች መታገታቸው ተሰምቷል።
ከአባገዳዎቹ መካከልም ድብደባ የተፈጸመባቸው መኖሩም ነው የታወቀው።
ቁጥራቸው በውል ያልታወቀውና ታግተዋል የተባሉት አባገዳዎች ይሄ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ የታወቀ ነገር የለም።

Thursday, February 21, 2019

በለገጣፎ አንድም የተፈናቀለ ዜጋ የለም ተባለ

በለገጣፎ ተፈናቅሎ ሜዳ ላይ የተጣለ አንድም ዜጋ የለም ሲሉ የለገጣፎ ከተማ ከንቲባ ገለጹ።
እስካሁንም ህገ ወጥ በሚል የፈረሰ ቤት የለም፣ የፈረሱትም በመንግስት ቦታ ላይ የተገነቡ ቤቶች ናቸው ብለዋል።

የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው ግን ክልሉ ለከተሞች ልማት ከሰጠው ትኩረት ጋር በተያያዘ በህገወጥ የተገነቡ ቤቶች እየፈረሱ መሆኑን ገልጸዋል።
ሕጋዊ ከሆኑ ደግሞ መራጃ እንዲያቀርቡ አስቀድሞ ተጠይቀዋል ብለዋል።
ተፈናቃዮቹ በበኩላቸው ለሚመለከተው አካል ማስረጃችንን ካቀረብን በኋላ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ቤታቸው መፍረሱን ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል እስካሁን በህገወጥ መንገድ ተገንብተዋል የተባሉ ከ3ሺ ቤቶች በላይ መፈረሳቸውን ነው ከክልሉ ያገኘንው መረጃ ያገኘንው።
በቅርቡ በኮልፌና በኦሮሚያ ክልል መካከል በሚገኘው አካባቢ ህገወጥ ተብለው የተፈናቀሉት ከ1 ሺ በላይ ነዋሪዎች ሰሞኑን ደግሞ በለገጣፎ ሜዳ ላይ እንዲወድቁ የተደረጉትናቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጎች የተፈናቀሉትም ከዚሁ ከህገወጥ ግንባታ ጋር በተያያዘ ነው ተብሏል።
የለገጣፎ ከንቲባ ወይዘሮ ሃቢባ ሲራጅ ደግሞ አንድም ዜጋ በለገጣፎ ሜዳ ላይ አልወደቀም፣ሕገ ወጥ በሚልም የፈረሱ ቤቶች የሉም ብለዋል ለኢሳት በሰጡት ምላሽ።
ቤቶቹ በሰባት ቀን እንዲፈርሱ የተደረገበት ምክንያትም አግባብነት አለው ብለዋል ወይዘሮ ሃቢባ።
የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊው አቶ አድማሱ ዳምጠው ለኢሳት እንዳሉት ደግሞ በህገወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶች ፈርሰዋል። ይሄ ደግሞ ክልሉ በእቅድ ይዞት እያከናወነው ያለ ተግባር ነው።
የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊው አቶ አድማሱ እንደሚሉት ከሆነ ህገወጥ ቤቶቹ ከመፍረሳቸው በፊት ማስጠንቀቂያ ተሰቷል።አማራጭ የሚሆኑ ቦታዎችም ተዘጋጅተውላቸዋል እነሱ ግን ፈቃደኛ አልሆኑም ነው ያሉት።
የተደረጉትን ጥናቶች መሰረት በማድረግ ህገወጥ ግንባታዎችን የማፍረሱ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት አቶ አድማሱ ከዚህ በፊት እንደተደረገው ሁሉ ቤቶቹ ከመፍረሳቸው በፊት ግለሰቦቹ ህጋዊ ማስረጃዎችን እንዲያቀርቡ ጠጠይቀዋል ብለዋል።
ተፈናቃዮቹ በበኩላቸው ህጋዊ ማስረጃ ብናቀርብም ቤታችን ከመፍረስ አልዳነም ይላሉ።

አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ፍርድ ቤት ቀረቡ


አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ለ3ኛ ጊዜ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።
በጥረት ኮርፖሬት ተፈፅሟል በተባለ የሀብት ምዝበራ የተጠረጠሩት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ለሶስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ተጨማሪ የ14 ቀን ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ በጥያቀው ላይ ወሳኔ ለመስጠት ለ ሰኞ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቢ ህግ ተጨማሪ ምርመራዎችን ለማድርግ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።
አቃቤ ህጉ ዳሽን ቢራ ዲዮት ለተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ የአክሲዮን ድርሻ የሸጠበትን 96 ሚሊዮን ዶላር የት እንዳደረሰው አልታወቀም ሲል እነ አቶ በረከትን ሲወነጅል እንደነበር ይታወሳል።
እነ በረከት ስምዖን እና ታደሰ ካሳ የጥረት አመራር በነበሩበት ጊዜ የኩባንያውን ሀብት በማባከንን በሌብነት ተጠርጥረው መታሰራቸው ይታወሳል።
የክልሉ ጸረ ሙስና አቃቤ ህግ ይ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀው የዳሽን ቢራ የሂሳብ ኦዲት አለመጠናቀቅ የጥረት ኮርፖሬት የአክሲዮን ሽያጭ ህጋዊነት በባለሙያ ማስፈትሽ ስላስለፈለገ ነው ብሏል።
ከዢህ ጋር በተያየዘም 2 ዋነኛ ምስክሮች ከሀገር ውጪ ስለሆኑ የሚመለሱበትን ቀን ታሳቢ በማድረግ ጥያቄው መቅረቡንአቃቤ ህግ  በምክንያትነት ገልጿል።
እነ አቶ በረከት ግን ኦዲቱ ባልተጠናቀቀ ጉዳይ ነው ወይ መዝብረዋል በሚል የተከሰስነው ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል ተብሏል።
ይህ ተገቢ አይደለም አቃቢ ህግ ሆን ብሎ እኛን በእስር ለማቆየት የሚያቀርበው ምክንያት ነው ሲሉም ተጨማሪ ይ 14 ቀን የምርመራ ጊዜውን ተቃውመዋል ።
ጉዳዩን እየተመለከተ ያለው ፍርድ ቤት ጉዳዩን መርምሮ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ያስፈልጋል ወይ የሚለውን ለመወሰን ለመጪው ሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።
ይሕ በእንዲህ እንዳለም አቶ በረከት ስምዖን የእስር አያያዛቸውን በተመለከተ ጠባቂዎችን እያሰቸገሩ መሆናቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የታሰረነውም ሆነ ፍርድ አየተሰጠን ያለው በማህበራዊ ሚዲያ ሰለሆነ ይሕንን ለመከታተል እንድንችል ኢንተርኒት ይግብላን የሚሉት አቶ በረከት ጠባቂዎችን ኢሳት ምን አለ እያሉ መረጃ ለማግኘት እንደሚያስቸግሩ ለማወቅ ተችሏል።
አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ በአሁኑ ጊዤ የተፈቀደላቸው  ሬዲዮ ብቻ መሆኑም ምንጮች ገልጸዋል።

Wednesday, February 20, 2019

በምዕራብ ጎንደር 138 ግለሰቦች በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው ታሰሩ

በምዕራብ ጎንደር ዞን ካለው ግጭት ጋር በተያያዘ 138 ግለሰቦች በሕይወት ማጥፋትና በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው መታሰራቸው ተነገረ።
በግጭቱ ሳቢያ 37 ሰዎች በነፍስ ግድያ፣ 101 ግለሰቦች ደግሞ በስርቆትና በሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የ33ኛ ዓባይ ክፍለ ጦር አስታውቋል ።

በምዕራብ ጎንደር  ግጭት ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩ የቡድን የጦር መሣሪያ ጥይቶችና መሳሪያዎች  መያዛቸውም ተነግሯል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን ካለው ግጭት ጋር በተያያዘ 138 ግለሰቦች በነፍስ ግድያና በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው የተያዙት በመከላከያ ሰራዊት አባላት ነው።
ጥይቶቹ የተያዙትማ በመተማ ዮሐንስ ከተማ በተቃጠሉ ግለሰቦች ቤት ውስጥ መሆኑን የ33ኛ ዓባይ ክፍለ ጦር 1ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል አንገሶም አርአያ ተናግረዋል ።
ከጦር መሳሪያ ጥይቶቹ በተጨማሪ ሃሰተኛ የብር ኖቶች፣ አደንዛዥ ዕፆች፣ የቅስቀሳ መሣሪያዎች (ድምጽ ማጉያ) እና የተለያዩ ሰነዶች በቁጥጥር ስር ውለዋል ነው ያሉት ።
ከዚህ ባለፈም የእጅ ቦንብም፣ የቅንቡላ፣ የአርፒጂ (የላውንቸር) እና የብሬንና ጥይቶችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሌተናል ኮሎኔል አንገሶም አንስተዋል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት የጦር መሳሪያ ጥይቶችን ለታንክ እና ለከባድ ምሽግ ማጥቂያ የሚያገለግሉ ሆነው ለሃገር መከላከያ ሠራዊት እና ለተፈቀደላቸው የፀጥታ አካላት ብቻ የሚፈቀዱ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡
ክላሽ፣ ሽጉጦች፣ ስለታማ መሣሪያዎች፣ የፌዴራል ፖሊስና የሀገር መከላከያ የደንብ ልብሶችም በተቃጠሉ ቤቶች ውስጥ መገኘታቸውንም  ሌተናል ኮሎኔሉ አረጋግጠዋል።
አሁን የተገኙት የቡድን መሣሪያዎቹ ጥይቶች ናቸውም ብለዋል።
አሁንም ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎች በግለሰቦቹ እጅ እንዳሉ እንደሚታመን ጠቁመዋል።
በምዕራብ ጎንደር የህብረተሰቡን ሰላም ለመጠበቅ መከላከያ ሰራዊት ከክልሉ ፖሊስና ከአካባቢው የፀጥታ አካላት ጋር  ተቀናጅቶ እየሠራ መሆኑን ነው የገለጹት።
ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር በሚውሉበት ጊዜ መንግሥት በቶሎ ለህግ እያቀረበ አለመሆኑን የአማራ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል ።

በጎንደር የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የሚከልከል መመሪያ ወጣ


በጎንደር በተወሰኑ አካባቢዎች የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የሚከልከል መመሪያ በአማራ ክልል ይፋ ተደረገ።
መመሪያውን ለማስፈጸም ከመከላከያ ሰራዊት ፥ከክልሉ ፖሊስና የጸጥታ ሐይሎች የተወጣጣ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ዘላለም  ልጅአለም ከኢሳት ጋር ባደርጉት ቃለ ምልልስ አስታወቋል።

ይህ ጸጥታን በጥምር ወታደራዊ እዝ የማስከበሩ ስራ በመመሪያ መልክ የወጣ እንጂ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አለመሆኑንም አቶ ዘላለም ገልጸዋል።
በምዕራብ እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች የተከሰተውን ግጭት ለማርገብ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በተመለከተ የ33ኛ ዓባይ ክፍለ ጦር እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጎንደር ላይ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
መግለጫውን የሰጡት የ33ኛ ዓባይ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል አለምነው አየነ እና የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ናቸው፡፡
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ዘላልም ልጅ አለም ለኢሳት እንደገለጹት በጎንደር  በተወሰኑ አካባቢዎች የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የሚከልከል መመሪያ በአማራ ክልል ትግባራዊ መሆን ጀምሯል።
መመሪያውን ለማስፈጸም ከመከላከያ ሰራዊት ፥ከክልሉ ፖሊስና የጸጥታ ሐይሎች የተወጣጣ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ዘላለም  ልጅአለም ከኢሳት ጋር ባደርጉት ቃለ ምልልስ አስታወቋል።
የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ለፌዴራል መንግሥቱ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የመከላከያ ሠራዊቱ የአካባቢውን ሠላም ለማስከበር መሰማራቱን  በመግለጫው ይፋ ተደርጓል፡፡
በዚህም መሠረት ከጎንደር-መተማ መስመር ከመንገድ 5 ኪ.ሜ ክልል በቡድንም ይሁን በግል ትጥቅ ይዞ መንቀሳቀስ አይቻልም፤ በሁመራ መስመርም በተመሳሳይ ክልከላ ተደርጓል፡፡
በጎንደር ከተማ ከፀጥታ አካላት ውጭ ማንኛውም ሰው መሣሪያ ታጥቆ መንቀሳቀስ እንደማይችልም ነው የገለጹት፡፡
የክልሉ አስተዳድር ለፌዴራል መንግሥቱ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የመከላከያ ሠራዊቱ የአካባቢውን ሠላም እንዲያስከብር ተድርጓልም ብለዋል፡፡
የፖሊስ ኮሚሽነሩ አቶ ዘላለም ልጃለም እንዳሉት ማንኛውም በፀጥታ መደፍረስ ተሳትፎ ያደረገ ኃይል እርምጃ እንደሚወሰድበትና ‹‹ሰላም ለማስከበር›› በሚል ሰበብ ማንኛውም ግለሰብ ከኮሚሽኑ ፈቃድ ውጭ መሣሪያ ይዞ እንዳይንቀሳቀስ እገዳ ተላልፏል፡፡
እናም ከኮሚሽኑ ፈቃድ ውጭ መሣሪያ ይዞ እንዳይንቀሳቀስ እገዳ  ነው ያሉት።
በመግለጫው የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጎንደር ወጣቶችና አክቲቪስቶች በጎንደር እና በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ከፀጥታ ኃይሉ ጋር እንዲሠሩ ጥሪ ቀርቦላቸዋልም ብለዋል፡፡

ኦዴፓ በብሔሮች ራስን የማስተዳደር መብት ላይ አልደራደርም አለ


በፌደራል ስርዓቱ በብሄሮች ራስን የማስተዳደር መብት ላይ ከማንም ጋር እንደማይደራደር  የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ገለጸ።
ፓርቲው  ባወጣው መግለጫ በፌደራል ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እየተካሄደ ነው ብሏል።

የአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም እና የአፋን ኦሮሞ ሁለተኛ ብሄራዊ ቋንቋ እንዲሆንም እየተሰራበት  መሆኑን ኦዲፒ ገልጿል።
ኦዴፓ በአጀንዳነት ይዞ ከሚታገልባቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የፌደራል ስርዓቱ ነው ብሏል።
እንደ ድርጅቱ መግለጫ ለፌደራል ስርዓቱ መምጣት ብሄረሰቦች ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል።
እናም የፌዴራል ስርአቱ እና ብሔሮች ራሳቸውን የማስተዳደር መብት ለድርድር አይቀርብም ነው ያለው ።
በአሁኑ ወቅትም በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የፌዴራል ስርዓቱን ሊያፈርስ እንደሆነ ለማድረግም እየተሰራ ነው ብሏል።
ህብረተሰቡ በፌዴራል ስርዓት ላይ ያለውን እምነት እና ተስፋ እንዲቀንስ ከፍተኛ የሆነ የሀሰት ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑንም ገልጿል።
ኦዴፓ እንደሚለው የሀሰት ዘመቻው ሁለት ዓላማ ያለው ነው ።
አንደኛው የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች አሁን ያለውን ለውጥ በጥርጣሬ እንደሚመለከቱ ማድረግ መሆኑን ነው የገለጸው።
ብሔሮችና ብሄረሰቦች የራሳቸውን ባህል፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ታሪክ ማሳደግን በትግል እና በመስዋዕትነት ያገኙት ቢሆንም የፌደራል ስርዓቱ ሊፈርስ ነው በሚል በጥርጣሬ ተቃውሞ እንዲያስነሱ ታስቦ የሚደረግ ሴራ መሆኑንም ገልጿል።
የኦሮሞን ህዝብ “ተጨማሪ መብት ማግኘት ቀርቶ ከዚህ ቀደም የተገኘውን መብት ልታጣ ነው” በሚል በማደናበር እርስ በርስ ለማጋጨት ያለመ መሆኑንም ኦዲፓ አስታውቋል።
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄን በመግለጽ የአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም እና የአፋን ኦሮሞ ሁለተኛ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆንም እየተሰራበት  መሆኑን ኦዴፓ ገልጿል።
ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች ላይም ትኩረት በመስጠት እየሰራበት መሆኑን ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል።
ኦዴፓ ለተጨማሪ ድል ይሰራል እንጂ ከዚህ ቀደም የተገኙ ድሎችን አያከሽፍም ያለው ፓርቲው፥ በፌደራል ስርዓት ጉዳይ ላይ ከማንም ጋር ለድርድር እንደማይቀመጥ በመግለጫው አስታወቋል።

wanted officials