ፌስቡክ ኢንስታግራም ላይ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ በእያንዳንዱ የፌስ ቡክ የተጠቃሚዎች መልዕክት ስር የተሰጡ የመውደድ (ላይክ) ቁጥሮችን አለማሳየት ሙከራ እርምጃውን አውስትራሊያ ውስጥ መጀመሩን አስታወቀ።
ከዛሬ አርብ ጀምሮ አውስትራሊያ ውስጥ ያሉ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች በሌሎች መልዕክት ላይ የተሰጡ የላይክ እንዲሁም የሌሎች ምላሽ ቁጥሮችን መመልከት አይችሉም።
አወዛጋቢ የሆነው ይህ ውሳኔ የፌስቡክ ተዛማጅ ማኅበራዊ መድረክ በሆነው ኢንስታግራም ላይ ከሐምሌ ወር ጀምሮ በበርካታ ሃገራት ውስጥ ተግባረዊ ተደርጓል።
ፌስቡክ ለአንድ መልዕክት የሚሰጡ የላይክ ቁጥሮችን ከባለቤቶቹ ውጪ ሌሎች እንዳያዩ የሚያደርገውን እርምጃውን ለመውሰድ የወሰነው በተጠቃሚዎች ላይ የሚደርሰውን ማኅበራዊ ጫና ለመቀነስ በማሰብ ነው ተብሏል።
ኩባንያው እንዳለው የፌስቡክ ተጠቃሚዎች በራሳቸው መልዕክቶች ስር የሚሰጡ 'የመውደድ' ምላሾችን መመልከት ግን ይችላሉ።
የድርጅቱ ቃል አቀባይ ሚያ ጋርሊክ ለአውስትራሊያ አሶሺየትድ ፕሬስ እንዳሉት "የቁጥርን ነገር ከጉዳዩ ስናወጣ፤ ተጣቃሚው ዋና ትኩረትን በተሰጡ የላይክና የሌሎች ምላሾች ብዛት ላይ ሳይሆን በሚደረጉ ምልልሶችና በቀረቡ መረጃዎች ጥራት ላይ ብቻ ያደርጋል" ብለዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም ድርጅታቸው ይህንን ለውጥ ከማድረጉ በፊት የሥነ አእምሮ ባለሙያዎችንና ማንጓጠጥ እንዲሁም ማስፈራራትን የሚከላከሉ ቡድኖችን ማማከሩን ገልጸዋል።
በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው አንዳንድ ሰዎች ግን በአንድ መልዕክት ላይ የሚታይ የመውደድ አሃዝ ለሚያገኙት ገቢ ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ እርምጃውንተቃውመውታል።
No comments:
Post a Comment