Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, May 30, 2019

የጋጥ ወጦች ድርጊት ትግላችንን እንድናጠናክር ያደርገናል (የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት)



ጋዜጣዊ መግለጫ
የጋጥ ወጦች ድርጊት ትግላችንን እንድናጠናክር ያደርገናል
የአዲስ አበባ በለአደራ ምክር ቤት ከህዝብ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማስፈፀም ላለፉት 35 ቀናት ደፋ ቀና እያለ ይገኛል፡፡ በዚህ ጊዜ 3 ህዝባዊ ስብሰባዎችና አንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ሞክሮ፣ ሁሉም በአዲስ አበባ መስተዳድር ተፅዕኖ ተደርጎባቸው፣ ሁለቱን ለመሰረዝ ተገዷል፡፡ አንዱ ጋዜጣዊ መግለጫም ቢሆን፣ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅም መልኩ ክልከላ ተደርጎበታል፡፡
ይህ ሁሉ መንግስታዊ ህገ ወጥነት አግባብ እንዳልሆነ፣ የምክር ቤቱ ሰብሳቢና ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በተገናኙበት ጊዜ ተማምነዋል፤ በቀጣይነትም፣ መስተዳድሩ ከህገ ወጥ ተግባራቱ ተቆጥቦ ህዝባዊ ስብሰባዎች ያለምንም ተፅዕኖ እንዲደረጉ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር፡፡
ይህ ስምምነት ሰኞ ዕለት ተደርሶ፣ በማግስቱ፣ ማክሰኞ፣ ለመስተዳድሩ በገባ ደብዳቤ፣ በቀጣዩ ቅዳሜ ሚያዚያ 5/2011 ዓ.ም በ24/መገናኛ በሚገኘው ኮከብ አዳራሽ የቦሌና አቃቂ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ እቅድ መያዙን፣ ለዚህም የፖሊስ ጥበቃ እንዲደረግ ተጠይቋል፡፡ ሆኖም፣ እስከ ዓርብ ድረስ የመስተዳድሩ ምላሽ በመጥፋቱ፣ ለራሳቸው ለምክትል ከንቲባው በቴክስት እንዲያውቁት ተደርጓል፡፡ በመጨረሻም፣ ዓርብ ዕለት በተሰጠ የቃል ምላሽ፣ በህጉ መሰረት ስብሰባ ለማድረግ እንደ ማይከለከል፣ የፖሊስ ጥበቃ ለማድረግ ግን መስተዳድሩ ፈቃደኛ አለመሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህ ተስፋ ባለመቁረጥ፣ አዳራሽ ስብሰባውን በራሳችን ኃይል እያስጠበቅን ለማከናወን ወስነን በቦታው ላይ የተገኘን ቢሆንም፣ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት በመኪና ተጭነው የመጡ ኦሮምኛ ተናጋሪ ወጣቶች፣ በቡድን በቡድን ተደራጅተው በአካባቢው ከመሰማራታቸውም በላይ፣ ወደ ስብሰባው በመምጣት ሁከት ለመቀስቀስ ሞክረዋል፡፡ ይህንን ለፖሊስ ብናሳውቅም፣ በመጨረሻ ላይ፣ “ጥበቃ አይደረግላችሁም” የሚል እጅግ አሳፋሪና ኃላፊነት የጎደለው ምላሽ ተሰጥቶናል፡፡ በዚህ የጋጥ ወጦች ስልት ስብሰባ እንዳናደርግ በእጅ አዙር ጋሪጣ ተደቅኖብን፣ ራሳችንን ለመከላከል በቂ ኃይል ቢኖረንም፣ የህዝብ ደህንነትንና የሀገረን ሰላም በማስቀደም ስብሰባውን ሰርዘናል፡፡
እንደዚህ ዓይነቱ ጋጥ ወጥ አካሄድ፣ በባለአንጣነት እየተፈረጀ ላለው ለአዲስ አበባ ህዝብ ብቻ ሳይሆን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተጀመረው የዲሞክራሲ ሽግግር አደገኛ በመሆኑ፣ አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ አጥበቀን እንጠይቃለን፡፡
የማስተካከያው እርምጃ ቢወሰድም ባይወሰድም ግን፣ ሰላማዊ ትግላችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለወዳጆቻችንም ሆነ ለተቀናቃኞቻችን እንወዳለን፡፡ ቁርጠኝነታችንንም በቀጣይነት በምንወስዳቸው ሰላማዊ የተግባር እርምጃዎች እናሳያለን፡፡
የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት
ሚያዚያ 7/2011 ዓ.ም አዲስ አበባ

Monday, May 27, 2019

የዜጎችን ሕይዎት በግፍ የቀፀፉ ፅንፈኞች ለፍትህ ይቅረቡ! ታማኝ በየነ፤Global Alliance


Global Alliance for the Rights of Ethiopians (GARE).
Global Alliance for the Rights of Ethiopians (GARE)
ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት ከተቋቋመበት የዛሬ ስድስት ዓመት ጀምሮ በተከታታይና ባለው አቅም መሰረት ብሄር፤ ኃይማኖት፤ የፖለቲካ ዝንባሌ፤ ጾታ ወይንም እድሜ ሳይለይ በአገር ቤትና በውጭ ለሚኖሩ ለኢትዮጵያዊያን  ወገኖቹ በያሉበት ለሚደርስባቸው ግፍ፤ በደልና ችግር ያልተቆጠበ ጥረት ሲያካሄድ ቆይቷል። በተለያዩ ወቅቶች በተከሰቱ አሰቃቂ ሁኔታዎች ላይ መግለጫዎችን አውጥቷል።
ዛሬም በሰሜን ሸዋ በሚኖሩ ንጹህ ኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈጸመውን ግፍ፤ በደልና እልቂት በተመለከተ ይህን መግለጫ አውጥቷል።
ከድርጅታችን ዋና ተግባሮች መካከል ትኩረት ሰጥተንባቸው የቆዩት ስራዎች ከወገኖቻችን ገንዘብ ሰብስቦ ሰብአዊ የገንዘብ እርዳታ ( Humanitarian Assistance) ለተጎዱ ወገኖቻችን በአስቸኳይና አስተማማኝ በሆነ መንገድ እንዲደርሳቸው ማድረግ፤ ለወገኖቻችን አቤቱታዎችን ለሚመለከታቸው የአገር ውስጥና የውጭ አካላት ማቅረብ፤ በሕግና በሌላ በባለሞያዎች የተደገፈ እርዳታ ለሚመለከታቸው ግለሰቦች ግጋፍ እንዲያገኙ ማመቻቸት፤ እርቅና ሰላም፤ ብሄራዊ መግባባትና ሌሎች የአቅም ግንባታ ስራዎች እንዲሰሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና በዘላቂነት ከቤታቸውና ከቀያቸው የተፈናቀሉትን ወገኖቻችን ራሳቸውን እንዲችሉ ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶችና ከመንግሥት ተቋማት ጋር ሆኖ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይገኙበታል።
ድርጅታችን በተቻለው መጠን ዛሬ በሰሜን ሸዋ በልዩ ልዩ ቦታዎች ለሞቱትና ለቆሰሉት ቤተሰቦችም ተመሳሳይ ድጋፍ ለመስጠት የወሰነ መሆኑን ለደጋፊዎቻችንና ለኢትዮጵያ ሕዝብ እናስታውቃለን።
በአሁኑ ወቅት ድርጅታችንን እጅግ በጣም ያሳሰበው፤ ያስጨነቀውና ድምጹን በመግለጫ እንዲያሰማ ያስገደደው ሁኔታ በሰሜን ሸዋ በሚገኙ ከተሞችና መንደሮች፤ በንጹህ ወገኖቻችን ላይ ከቅዳሜ መጋቢት 28, 2011 ጀምሮ የተካሄደው እልቂት ነው። በሩዋንዳ የተከሰተውን የዜጎች የብሄር ተኮር እልቂት (Genocide) ሃያ አምስተኛ ዓመት እያስታወስን የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተምሳሌት በሆነችው ኢትዮጵያ የብሄር ተኮር እልቂት ሲካሄድ ማየታችን የኢትዮጵያ የፖለቲካና የአስተዳደር ሁኔታ ከፌደራልና ከክልል ባለሥልጣናት አቅም ውጭ መውጣቱን ያሳስበናል።
የጭካኔውን ጥልቀትና ስፋት ስንገመግመው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የዓለም ሕዝብ ቢሰማው የሚዘገንና የሚያሳፍር ድርጊት ነው። አጥፊዎቹ ከፍተኛ መሳሪያ ተጠቅመው፤ መሳሪያውን የተሸከሙ ተሽከርካሪዎችን ይዘው፤ አልሞ ተኳሽዎች፤ የወታደር ልብስ የለበሱ ልዩ ኃይሎች ኢላማ ያደረጓቸው የንጹህ ኢትዮጵያዊያንን ቤቶችና ንብረቶችን፤ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ክርስትና ቤተከርስቲያኖችን ሲሆን፤ ንጹህ ሰርቶ አደር ነዋሪዎቹ በገፍ፤ በከባድ መሳሪያ፤ በጥይትና በቦምብ ተገድለዋል፤ ቆስለዋል፤ ቤትና ንብረታቸው ተደፍሮ ተዘርፏል። ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዲሸሹ ተገደዋል። ይህ ግፍና በደል የደረሰባቸው ኢትዮጵያዊያን “ለመሆኑ መንግሥት አለ ወይ?” ብለው መጠየቃቸው ሕዝብን እያነጋገረ ነው።
ይዘቱ የተለያየ ቢሆንም፤ በንጹህ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ላይ የሚካሄደው ግፍና በደል በቡራዩ፤ በጌድዮ፤  በጉጅ፤ በጎንደር፤ በለገጣፎ፤ በደሴና በሌሎች አካባቢዎች ተከስተዋል።
ኢትዮጵያ በሰላም ከቤት ወጥቶ በሰላም ለመመለስ ብርቅ የሆነባት አገር መሆኗ በጣም ያሳፍረናል። ግራ ያጋባል። ምን አይነት ሁኔታ ተፈጥሮ፤ ማን ተገን ሆኖ ነው እልቂቱ የተካሄደው? የዚህ አይነት አይን ያወጣ፤ ብሄርንና ኃይማኖትን ኢላማ ያደረገ ሽብርተኛነትና ጀሃዲስትነት ሊካሄድ የቻለው በምን ምክንያት ነው? ይህን ለመመለስ አንችልም።
በእኛ የአጭር ጊዜ ምርምርና ዘገባ መሰረት ግን፤ ይህ አደጋ ሕዝብ በራሱ ሕዝብ ላይ ያካሄደው እልቂት አይደለም።
ድርጅታችን ይህን በአገራችን ታሪክ ውስጥ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ኢ-ሰብአዊ፤ የሚዘገንን፤ ጭካኔን፤ እብሪተኛነትን፤ ዘረኝነትን፤ ጠባብ ብሄርተኝነትን፤ ጽንፈኛነትን፤ ሽብርተኛነትንና ጅሃዲስትነት የሚያንጸባርቅ ድርጊት ሙሉ በሙሉ እናወግዛለን።
የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የሚያስታውሰን የመን ወደ ውድቀት ከመሸጋገሯ በፊት የሆነውን ሁኔታ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በአስቸኳይ የችግሮቹን መሰረት (Systemic, Sttructural and Root Causes) ለመቅረፍ ካልቻለ ሁኔታው እየተባባሰ እንደሚሄድ እንገምታለን።
የዚህ አይነቱና ሌላ ተመሳሳይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እንዳይደገም ጥሪ እናደርጋለን። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እልቂቱን ያመቻቹት፤ ሽፋን የሰጡቱና ያካሄዱት ግለሰቦች፤ ልዩ ኃሎችና ድርጅቶች ሳይውል ሳያድር ተይዘው በሃላፊነት በሕግ እንዲጠየቁ የኢትዮጵያን የክልልና የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት እናሳስባለን።
ኢትዮጵያ ሃገራችን ሰላማዊና ዲሞክራሳዊ ለውጥ እያካሄደች በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት ይህን የመሰለ የእብሪተኞችና የጀሃዲስቶች እልቂት መካሄዱ ለኢትዮጵያ 110 ሚሊየን ሕዝብና ለአገሪቱ ሕልውና አስጊ መሆኑን እየጠቆምን፤ የዜጎች ደህንነት፤ ሰብአዊና ዲሞክራሳዊ መብት፤ ሰላምና እርጋታ በአስቸኳይ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጣቸው እንጠይቃለን።
በዚህ አጋጣሚ ዛሬም ሆን ከዚህ በፊት በየአካባቢው ያልተቆጠበ ጥረት ላደረጉት ሁሉ ከፍተኛ ምስጋና እናቀርባለን። ዛሬም እንደ ትላንቱ ለወገኖቻችን እንድረስላቸው ለሚሉትና ለሌሎች ጥሪ የምናደርገው በያላችሁበት የገንዘብ መሰብሰብ ጥረቱን እንድትቀጥሉበት፤ ያልጀመራችሁ እንድትጀምሩና ላልሰሙት እንድታሰሙ አደራ እንላለን።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሄራዊ አንድነት ይለምልም!
ከአክብሮትና ከሰላምታ ጋር
ታማኝ በየነ፤ ፕሬዝደንት ከታላቅ አክብሮት ጋር

Friday, May 17, 2019

የወላይታ ሕዝብን ጥያቄ ያስተናገደው ሕዝባዊ ሰልፍ በሰላም ተጠናቀቀ

በወላይታ ሶዶ የተካሄደውና የወላይታ ሕዝብን ጥያቄ ያስተናገደው ሕዝባዊ ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁ ተገለጸ። ሰልፈኞቹ የክልል እንሁን ጥያቄን ጨምሮ ባለ አምስት ነጥቦችን የያዘ ጥያቄን ለሚመለከተው አካል ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

ሰልፈኞቹ ለኢሳት እንዳሉት ማንነትን መሰረት አድርጎ በወላይታ ህዝብ ላይ የሚደርሰው ጥቃት ይቁም፣ወንጀለኞች ለህግ ይቅረቡ የሚሉና ሃገራዊ ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የህግ የበላይነት ይከበር የሚሉ መልዕክቶች ተላልፈዋል።
የወላይታ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር ዶክተር ብስራት ኤልያስ ለኢሳት እንዳሉት የወላይታ ህዝብ መብቴ ይከበር የሚል ጥያቄ ሲያቀርብ ዛሬ የመጀመሪያው አይደለም።
በዞኑ ለውጥ እንዲመጣ ብዙ ትግሎች ተካሂደዋል የዛሬው ሕዝባዊ ሰልፍም ይህንን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

ማለዳ 12 ላይ ተጀመረ የተባለውና በርካታ መልዕክቶችን አስተላልፎ የተጠናቀቀው የወላይታ ተወላጆች ሰልፍ ባለ አምስት ነጥብ ጥያቄዎችን አንግቦ እንደነበር ከስፍራው ለኢሳት የደረሱት መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከአጎራባች ህዝቦች ጋር ያለን አብሮነታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል፣የክልል ጥያቄያችን በአስቸኳይ ይመለስ፣የወላይታ ህዝብ በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ አንድነትን ይደግፋል የሚሉና ሌሎች ደግሞ በሰልፉ ላይ የተላለፉ መልዕክቶች ናቸው።
የተለያዩ ማህበራት እንዳስተባበሩት የተገለጸው ይሄ ሰልፍ የወላይታ ህዝብ በየጊዜው ለሚደርስበትና እየደረሰብት ላለው በደል መፍትሄም የሚጠይቅ ነው ብለዋል ሰልፈኞቹ ለኢሳት።
የወላይታ ህዝብ በየትኛውም አካባቢው ተዘዋውሮ የመስራት ኢትዮጵያዊ መብቱ ሊከበርለት ይገባል ሲሉ ሰልፈኞቹ መጠየቃቸውም ተገልጿል።

የወላይታ ህዝብ ለረጅም ጊዜ ራሱን በራሱ የማስተዳደርን መብት ከመጠየቅ ጀምሮ የወላይታ ህዝብ የሚፈልጋቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎች ሲያቀርብ ነው የቆየው ያሉት ደግሞ ዶክተር ብስራት ኤልያስ ናቸው የወላይታ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር ከኢሳት ጋር በነበራቸው ቆይታ።
የወላይታ ህዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ዛሬ ላይ የተጀመሩ አይደሉም ዶክተር ብስራት ምላሽ ባለማግኘታቸው ግን እስካሁን የወላይታ ህዝብ እየተሰቃየ ነው ብለዋል።
እንደ ሃገር የመጣው ለውጥ የወላይታ ህዝብ ጋ አልደረሰም ብለዋል ዶክተር ብስራት።
ይሄ በመሆኑም የወላይታ ህዝብ በተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ከማንሳት ወደኋላ አላለም ብለዋል።
አሁንም ቢሆን መመለስ ያለባቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉ ብለዋል ዶክተር ብስራት ኤልያስ

በተለያዩ ከተሞች በህክምና ባለሙያዎች የተቃውሞ ሰልፎች ተደረጉ።


መንግስት ጥያቄችንን ለመፍታት ዝግጁ አይደለም በሚል በአዲስ አበባ፣ በደብረማርቆስ፣ በአክሱምና በሌሎች ከተሞች ተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን የደረሰን መረጃ ያመልክታል።

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አንዳንድ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች የተካሄደው አድማ ለሶስተኛ ቀን ቀጥሏል።
የኢትዮጵያ ህክምና ባለሙያዎች ማህበር አድማው ተገቢ አይደለም ሲል መግለጫ ሰጥቷል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን መመለስ የምንችለውን እየመለስን ነው፣ ከጥቅማጥቅሞች ጋር የተነሱትን ጥያቄዎች ደግሞ እንደመንግስት አቅም ወደፊት የሚታዩ ይሆናል ሲሉ ለኢሳት በሰጡት ቃለመጥይቅ ገልጸዋል።
የህክምና ባለሙያዎች በመንግስት የጤና ፖሊሲና በጥቅማጥቅም አንጻር ያነሷቸው ጥያቄዎች አሁንም ምላሽ ይሻሉ በሚል እያሰሙ ያሉትን ተቃውሞ ዛሬ ቀጥለው ሰላማዊ ሰልፎችን አድርገዋል።
በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚገኙ አንዳንድ ተለማማጅ ሃኪሞችና የድህረምረቃ ተማሪዎች በስራ ማቆም አድማ ሶስተኛ ቀናቸውን በያዙበት በዛሬው ዕለት ባህርዳርና አክሱም የሚገኙ ባለሙያዎች በተቃውሞ ሰልፎች ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
የባህርዳር ፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል ሀኪሞች፣ የጤና ባለሙያዎችና የዩኒቨርስቲው ተለማማጅ ሐኪሞች ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ የአስተዳደራዊ፣ ደመወዝና ጥቅማጥቅም ጥያቄዎችን በማንሳት አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
በአዲስ አበባ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚሰሩ ሀኪሞችም ዛሬ ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ በሽተኞች እየተጎዱ ያሉት በሃኪሞች አድማ ምክንያት ሳይሆን በመንግስት የተበላሸ የጤና ፖሊሲ አማካኝነት ነው ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
በአክሱም፣ በደብረታቦር፣ በመቀሌና በደብረማርቆስም ተመሳሳይ የህክምና ባለሙያዎች የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል።
መብታችንን መጠየቃችን ለጤናው ዘርፍ የተሳካ እንዲሆንና የታካሚዎችን ደህንነት ከመጠበቅ አንጻር ነው ብለዋል ሰልፈኞቹ።
ሃገር አቀፉ የህክምና ባለሙያዎች ማህበር መብታችንን ሊያስከብርልን አልቻለም በሚል ከማህበሩ እውቅና ውጪ ተቃውሞና የስራ አድማ የሚያደርጉት አንዳንድ የህክምና ባለሙያዎችና ተለማማጅ ሃኪሞች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለጥያቄዎቻቸው የሰጡት ምላሽ ክብራችንን የነካ፣መፍትሄ ለመስጠት በመንግስት በኩል ፍቃደኝነት እንደሌለ የሚያመለክት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህክምና ባለሙያዎች ማህበር ጉዳዩን በተመለከተ በአዲስ አበባ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የተነሱትን ጥያቄዎች እንደግፋለን፣ አድማውን አናበረታታም ብለዋል የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ገመቺስ ማሞ።
በህክምና ባለሙያዎች የተነሱትን የመብትና የጥቅማጥቅም ጥያቄዎች በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን መንግስት ምላሽ እየሰጠ ባለበት በዚህን ወቅት አድማና ተቃውሞ ማድረግ ተገቢ አይደለም ብለዋል።
መንግስት የአቅሙን መልስ እየሰጠ እንደሆነም ገልጸዋል።

የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች የስራ ማቆም አድማ መቱ

 መንግስት ጥያቄአችንን ለመመለስ ዝግጁ አይደለም በሚል የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች ከዛሬ የጀመረ የስራ ማቆም አድማ መምታታቸው ተገለጸ።
ፋይል
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር አድማውን ህገወጥ ሲሉ ገልጸውታል።
የድህረ ምረቃ ተማሪዎቹ እስከነገ ወደ ስራቸው የማይመለሱ ከሆነ ርምጃ እንደሚወሰድባቸው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አስተዳደር ውሳኔ ማስተላለፉ ታውቋል።
የስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ድህረ ምረቃ ተማሪዎች ግን ጥያቄዎቻቸው እስኪመለሱ ከድንገተኛ የህክምና አገልግሎቶች ውጪ ያሉትን ስራዎች በማቆም ተቃውሟቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በድህረ ምረቃ ተማሪዎች እየተነሱ ያሉት ጥያቄዎችን ለመመለስ መንግስት የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰደ ባለበት ወቅት ስራ ማቆም ተገቢ አይደለም ሲሉ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው አሰፋ በድጋሚ መጥሪያ እንዲሰጣቸው ትዕዛዝ ተላለፈ

 ለቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ መጥሪያ እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤት በድጋሚ ትዕዛዝ ሰጠ። ለዛሬ እንዲቀርቡ የተላለፈው የመጀመሪያው ትዕዛዝ ተፈጻሚ ያልሆነው መጥሪያው ከፍርድ ቤት ወጪ ሳይደረግ በመቅረቱ መሆኑን በዛሬው ችሎት ላይ ተገልጿል።

የዋስትና መብት ጥያቄ ያቀረቡ ተከሳሾች በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጎባቸዋል። የአቶ ጌታቸው አሰፋን መጥሪያ በተመለከተ የተዛባ ዜና አሰራጭተዋል በተባሉ የሚዲያ ተቋማት ላይም ፍርድ ቤቱ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በአቶ ጌታቸው አሰፋና በሌሎች የቀድሞ የደህንነት መስሪያ ቤት ከፍተኛ ሃላፊዎች ላይ የተመሰረተውን ክስ እየተመለከተ ያለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ድጋሚ ትዕዛዝ በማስተላለፍ አቶ ጌታቸውን ጨምሮ በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች መጥሪያ እንዲሰጣቸው ውሳኔ አስተላልፏል።
የሚያዚያ 30ው ትዕዛዝ ተፈጻሚ ያልሆነው ከፍርድ ቤት መጥሪያ ባለመውጣቱ ነው የሚል ምላሽ ቢሰጥም ፖሊስ ባለመቅረቡ ትክክለኛውም ምክንያት በፖሊስ አልተገለጸም።
አቃቤ ህግ መጥሪያ የመስጠት ስልጣኑ የእኔ አይደለም ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
በዛሬው ችሎት ፌደራል ፖሊስ መጥሪያውን ለተጠርጣሪዎቹ ባሉበት እንዲያደርሳቸው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተሰጠው ሲሆን ጠቅላይ አቃቤ ህግም ጉዳዩን እንዲከታተለው መታዘዙን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ከአቶ ጌታቸው አሰፋ በተጨማሪ በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸው አቶ አጽበሃ ግደይ፣ አቶ አሰፋ በላይና አቶ ሽሻይ ልዑል በድጋሚ መጥሪያ እንዲደርሳቸው እንዲደረግም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
በዛሬው ችሎት ክስ የተመሰረተባቸው የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት 22 አመራሮች የዋስትና ጥያቄቸው ውድቅ ተደርጓል።
የቀድሞ የደህንነት መስሪያ ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ያሬድ ዘሪሁን፣ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ እንዲሁም አቶ መአሾ ኪዳኔና አቶ አማኑዔል ኪሮስ የዋስትና ጥያቄአቸው ውድቅ ሆኖ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መስጠቱን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።
በተያያዘ ዜና የሚያዚያ 30 ችሎት ላይ አቶ ጌታቸው አሰፋ እጃቸውን ይዞ ለፍርድ እንዲያቀርብ ፖሊስ ትዕዛዝ ተሰጠው በሚል ዜና ያስተላለፉ ሶስት የሚዲያ ተቋማት በዳኛው ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ችሎቱን የተከታተሉ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት፣ ፋና ብሮድካስቲንግና ሸገር ሬዲዮ የተዛባ ዜና አሰራጭታችኋል ተብለው ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው በኋላ ይቅርታ መጠየቃቸው ታውቋል።
ቀጣይ ሂደትን በተመለከተ የክሱን ጉዳይ ለመመልከት ፍርድ ቤቱ ለግንቦት 16 ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የዛሬውን ችሎት አጠናቋል።
በሌብነትና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ከባድ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ጌታቸው አሰፋን አሳልፎ ለመስጠት በትግራይ ክልል መንግስት በኩል ፍቃደኝነት አለመኖሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በመቀሌ የሚገኙ ወጣቶች አቶ ጌታቸው አሰፋ መሸለም እንጂ መከሰስ የለባቸውም በሚል ዓላማ ለዛሬ ሰልፍ ጠርተው ነበር።
አቶ ጌታቸው በስውር እስር ቤቶች በርካታ ዜጎችን ከድብደባ ጀምሮ፣ ጥፍር በመንቀልና በማኮላሸት እስከሞት በሚያደርስ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች ፈጽመዋል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን እስካሁንም በትግራይ ክልል መቀሌ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

ቦይንግ የ737 ማክስ ሶፍትዌርን አሻሽያለሁ አለ


ቦይንግ 737 ማክስ ሶፍትዌር ላይ እያደረገ የነበረውን ማሻሻያ መጨረሱን ይፋ አድርጓል። ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰከሰውን አውሮፕላን ጨምሮ በ737 ማክስ ሁለት የከፉ አደጋዎች መድረሳቸው ይታወሳል።
ቦይንግ የሶፍትዌር ማሻሻያ ባደረገባቸው 737 ማክስ አውሮፕላኖች 207 በረራ ማድረጉን አሳውቋል።

አብራሪዎች አውሮፕላኑን ስለሚቆጣጠሩበት መንገድ ለፌደራል አቪዬሽን አድሚንስትሬሽን (ኤፍኤኤ) መረጃ እንደሚሰጥም ተገልጿል። የኤፍኤኤ ባለሙያዎች ቦይንግ ማሻሻያው እንዲጸድቅለት መረጃውን በሚቀጥለው ሳምንት ለኤፍኤኤ እንዲያስረክብ ይጠብቃሉ።
መጋቢት ላይ ኢቲ 302 ቦይንግ 737 ማክስ ሲከሰከስ አውሮፕላኑን ተሳፍረው የነበሩ 157 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል። ከኢቲ በፊት የኢንዶኔዥያው ላየን ኤር ተከስክሶ 189 ሰዎች መሞታቸውም አይዘነጋም።

ሁለቱም አደጋዎች በቦይንግ 737 ማክስ ችግር ምክንያት መከሰታቸው ተገልጿል። የተሻሻለው ሶፍትዌር የቦይንግ 737 ማክስ ላይ የነበረውን ክፍተት የሚሞላ ነው ተብሏል።
ቦይግን እንዳለው፤ አውሮፕላን አብራሪዎች እንዴት በተሻሻለው ሶፍትዌር እንደሚገለገሉ የሚጠቁም መረጃ ለኤፍኤኤ ከሰጠ በኋላ፤ የሙከራ በረራ ያደርጋል። ከዛም ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንደሚያገኝም ቦይንግ ገልጿል።
ባለፈው ወር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 ማክስ ሲከሰከስ አውሮፕላኑን ተሳፍረው የነበሩ 157 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል

ግሎባል አሊያንስ ለሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ


የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግሎባል አሊያንስ እያደረገ ያለውን ሀገራዊ አስተዋጽኦ ታላቅ ተግባር ነው ሲሉ አወደሱት።
ዓለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ግሎባል አሊያንስ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ጋር ውይይት አደረገ።

ባለፈው ረቡዕ ለጌዲዮ ተፈናቃዮች የ31 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገው ግሎባል አሊያንስ በውጭ በሚገኙ ኢትዮጵያውያንና በመንግስት መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር የሚያስችል እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጿል።
የግሎባል አሊያንስ የኢትዮጵያ ተወካይ ወይዘሮ ትዕግስት ካሳ ለኢሳት እንደገለጹት ከመንግስትና ከዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር የተደረጉት ውይይቶች ለግሎባል አሊያንስ ቀጣይ ሀገራዊ ተግባር ከፍተኛ አቅም የሚፈጡ ናቸው።
ዓለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ግሎባል አሊያንስ ዛሬ ከመንግስትና ከዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር በመገናኘት በኢትዮጵያ ተፈናቃዮችን መልሶ በማቋቋም አንጻር ውይይት አድርጓል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የተገኙት የግሎባል አሊያንስ ተወካዮች ከሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ተገናኝተዋል።
በውይይቱ ሚኒስትሩ የግሎባል አሊያንስን ጥረት አድንቀው ምስጋና አቅርበዋል።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር የተገናኙት የግሎባል አሊያንስ አመራር አባል አቶ በትሩ ገብረ እግዚአብሔር ለወገን ደራሽ ወገን ነው የሚለውን አስመስክራችኋል የሚል አድናቆት እንዳገኙ ለኢሳት ገልጸዋል።
ዓለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት በሀገር ቤት መዋቅር ከፍቶ ህጋዊ ሰውነት ለማግኘት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
በኢትዮጵያ የግሎባል አሊያንስ ተወካይ ወይዘሮ ትዕግስት ካሳ በዛሬው ዕለት ከሶስት አካላት ጋር የተደረገውን ውይይት ውጤታማ ሲሉ ገልጸውታል።
ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያና ከመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ መስሪያ ቤት ኦቻ ጋር የተደረጉት ውይይቶች ለግሎባል አሊያንስ ቀጣይ ስራ ግብዓት ይሆናል ነው ያሉት ወይዘሮ ትዕግስት።
ዓለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ግሎባል አሊያንስ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ጋር ያላቸው ቁርኝት እንዲቀጥል እየሰራ እንደሚገኝ አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ገልጿል።
በጎ ፈቃደኛ የዲያስፖራ አባላትን በማሰባሰብ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በሙያቸው የድጋፍና የስልጠና እገዛ እንዲሰጡ እያደረገ መሆኑንም ተናግሯል።
ግሎባል አሊያን ባለፈው ረቡዕ በአዲስ አበባ በተከናወነ ስነስርዓት በጊዲዮ ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ የሚሆን የ31 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ፌስቡክ አፍሪካ ላይ የተቃጡ ገጾችን ዘጋ

የፌስቡክ መለያ ምስል
ፌስቡክ በመቶዎች የሚቆጠሩና አፍሪካ ላይ አነጣጥረዋል ያላቸውን ገጾችና አንድ የእስራኤል ተቋምን ማገዱን ይፋ አድርጓል።
ፌስቡክ ሀሰተኛ ናቸው ያላቸው ገጾች በተለያዩ ሀገሮች ስለሚካሄዱ ምርጫዎችና ስለሌሎችም ፖለቲካዊ ጉዳዮች መረጃ የሚሰራጭባቸው ነበሩ ተብሏል።

ፌስቡክ ያስወገዳቸው 265 ገጾች መነሻቸው እስራኤል ሲሆን፤ በሴኔጋል፣ በቶጎ፣ በአንጎላ፣ በኒጀር፣ በቱኒዝያ እንዲሁም በላቲን አሜሪካና ደቡብ ምስራቅ እስያ ላይ ያተኮሩ መረጃዎች ያሰራጩ ነበር።
ፌስቡክ የተሳሳተ መረጃን ከድረ ገጹ አያስወግድም በሚል በተደጋጋሚ ይተቻል። ከአራት ዓመታት በፊት የመረጃ ትክክለኛነት የሚጣራበት አሠራር መጀመሩ ይታወሳል።

ፌስቡክ ካገዳቸው ገጾች ጀርባ ያሉ ግለሰቦች ሀሰተኛ ገጽ በመጠቀም የተሳሳተ መረጃ ይነዙ እንደነበረ ፈስቡክ ባወጣው መግለጫ አትቷል። በሀሰተኛ ገጾቹ ይሰራጩ የነበሩ መረጃዎች በርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ጋር እንዲደረሱም ተደርጎ ነበር።
የፌስቡክ የደህንንት ፓሊሲ ኃላፊ ናትናዬል ግሌይቸር እንደተናገሩት፤ ግለሰቦቹ በተለያዩ ሀገራት የሚሠሩ መገናኛ ብዙሀንን በመምሰል ስለፖለቲከኞች ተደብቀው የነበሩ መረጃዎች "አጋልጠናል" እያሉ የያሰራጩ ነበር።

'አርቺሜድስ ግሩፕ' የተባለ የእስራኤል ተቋም ከነዚህ እንቅስቃሴዎች ጀርባ እንዳለ በምርመራ እንደደረሱበትም ኃላፊው ተናግረዋል።
የፌስቡክ ገጾቹን የፈጠሯቸው ሰዎች እንደ አውሮፓውያኑ ከ2012 እስከ 2019 ለማስታወቂያ ወደ 812,000 ዶላር ገደማ ከፍለዋል። ገንዘቡ የተከፈለው በብራዚል፣ በእስራኤልና በአሜሪካ መገበያያ ገንዘብ ነው።
ኢላማ ከተደጉት ስድስት የአፍሪካ ሀገሮች አምስቱ በ2010 ሀገር አቀፍ ምርጫ ያካሄዱ ሲሆን፤ የቱኒዝያ ምርጫ በሚቀጥለው ዓመት ይካሄዳል።
ፌስቡክ ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት የሰዎች ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ የተሰሳቱ መረጃዎችን ባለማገዱ ሲተች ቆይቷል።

ሚኖ ራዮላ፡ የአውሮፓን እግር ኳስ የሚዘውረው ቱጃር 'ደላላ'


"ሚኖ" በተሰኘ ቅፅል ስሙ ይታወቃል፤ ሆላንዳዊው ካርሚን ራዮላ። የታዋቂዎቹ ፖል ፖግባ፣ ዝላታን ኢብራሂሞቪች፣ ሄንሪክ ሚኪታሪያንና ዴ ሊት የመሳሰሉ ተጨዋቾች ወኪል ነው።
ጣልያን ተወልዶ በኔዘርላንድስ ሃርለም ከተማ እንዳደገ የሚነገርለት ራዮላ የደች ዜግነት ያለው 'ምርጥ ደላላ' ነው።
በልጅነቱ አባቱ በከፈቱት ሬስቶራንት ውስጥ ደፋ ቀና ብሎ አስተናግዷል። በጎንዮሽ ደግሞ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በሕግ ተመርቋል።
ጣልያንኛ፣ ጀርመንኛ፣ ስፓኒሽ፣ ፈረንሳይኛ፣ ፓርቹጊዝ፣ ደች እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ የሚናገረው ራዮላ ገና የ18 ዓመት ለጋ ሳለ ነበር ኔዝርላንድስ ውስጥ የሚገኝ አንድ የታዳጊዎች እግር ኳስ ኃላፊ ሆኖ ራሱን ያገኘው።
ከዚያም የነብስ ጥሪው ወደሆነው የወኪልነት ሥራ ገባ፤ ለአንድ ወኪል ድርጅት ተቀጥሮ ይሠራም ጀመር። የመጀመሪያው ሥራ የሆነው ደግሞ ተስፋ የሚጣልባቸውን ታዳጊ ደች ተጫዋቾችን ለጣልያኑ ሴሪ ኤ ማሻሻጥ።
ሚኖ ራዮላ
በታዳጊነታቸው በራዮላ ደላይነት ወደ ጣልያን ብሎም ወደ እንግሊዝ ገብተው ስማቸውን በጉልህ መፃፍ ከቻሉ ተጫዋቾች መካከል ዴኒስ ቤርግካምፕ የሚጠቀስ ነው።
ምንም ቢሆን የራሥ የራሥ ነው ያለው ራዮላ ተቀጥሮ ይሠራበት የነበረበትን ድርጅት ለቆ የራሱን የውክልና ድርጅት ሊያቋቁም ቻለ።
ለሃገሩ ቼክ ሪፐብሊክ ባሳየው ብቃት የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች ዓይን አርፎበት የነበረው ፓቬል ኔድቬድ ከስፓርታ ፕራግ ወደ ላዚዮ እንዲዛወር ያደረገው ራዮላ ነበር።
አሁን ላይ አውሮፓ ውስጥ ከሚጫወቱ እግር ኳሰኞች ስም ያላቸው 20 ገደማ ተጨዋቾች ውክልናቸውን ለራዮላ ሰጥተው ይንቀሳቀሳሉ።
እንደ አውሮፓዊያኑ 2016 ላይ ራዮላ 'ታሪክ ሠራ'። ያኔ የዓለም ሬከርድ በነበረ ዋጋ ፖል ፖግባን ከዩቬንቱስ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ እንዲዛወር አደረገ፤ ዋጋው ደግሞ 105 ሚሊዮን ዩሮ።
ጉደኛው ራዮላ ከዚህ ዝውውር 25 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ ወደ ኪሱ እንዳስገባ ይነገራል።
ከዚያ በኋላ ወደ አሜሪካዋ የባህር ዳርቻ ግዛት ማያሚ አቅንቶ 9 ሚሊዮን ዩሮ በማፍሰስ ቤተ-መንግሥት የሚያስንቅ መኖሪያ 'መንደር' ሸመተ።
ፎርብስ የተሰኘው የቢዝነስ ጋዜጣ 2018 ላይ ባወጣው ዘገባ ራዮላ 69 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ገቢ ያለው ሲሆን በእርሱ ውክልና ሥራ ያሉ 70 ተጫዋቾች 629 ሚሊዮን ዶላር ሊያወጡ ይችላሉ ሲል አትቷል።

ታላላቆቹ የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች የራዮላ ስም ሲጠራ ይንቀጠቀጣሉ፤ ይነዝራቸዋል። ምክንያታቸው ደግሞ በእርሱ ውክልና ሥር ያሉ ተጨዋቾችን እንዳሻው ማዟዟር መቻሉ ነው።
ሰውየው ያሻውን ከመናገር ወደኋላ የሚልም አይደለም። በአትንኩኝ ባይነቱ የሚታወቀው ራዮላ በእርሱ ውክልና ሥር ያሉ ተጨዋቾችን የሚተቹ የቀድሞ እግር ኳሰኞችም ሆነ ተንታኞችን በመወረፍ ይታወቃል።
ከሰሞኑ ግን የራዮላን ጠላቶች ፊት ፈገግ ያሰኘ፤ ለጊዜውም ቢሆን ለክለቦችን እፎይታ የሰጠ ዜና ከወደ ጣልያን ተሰምቷል። ራዮላ በጣልያን እግርኳስ ፌዴሬሽን ከውክልና ሥራ መታገዱን የሚያትት። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አካል ፊፋም የጣልያን አቻውን ፈለግ በመከተል ራዮላ ላልተወሰነ ጊዜ ከወኪልነት ሥራው እንዲታገድ ውሳኔ አስተላለፈ።
የጣልያና እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህን ውሳኔ ለምን እንዳስተላለፈ ግልፅ ባይሆንም ራዮላ ግን «እገዳው ብርቅ አልሆነብኝም። እኔ ያልተመቸኝ ውሳኔው ፖለቲካዊ መሆኑ ነው» ሲል ተደምጧል።
አክሎም «የጣልያን እግርኳስ ፌዴሬሽን የሃገሪቱን ኳስ ወደኋላ አስቀርቷል ብዬ የተናገርኳት ነገር ሳትቆረቁራቸው አትቀርም፤ በሃገሪቱ ሳላለው የእግር ኳስ ዘረኝት ጉዳይ አሳስቦኛል ማለቴም ይቅርታ ሳያስነፍገኝ አይቀርም» ሲል ተሳልቋል።
ይህ ውሳኔ ያስደሰታቸው ቢኖሩም እንኳ የራዮላ መታገድ ለአንዳንድ ክለቦች ደግሞ ደንቃራን ይዞ የመጣ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
የአውሮፓ እግር ኳስ የዝውውር ገበያ በሚደራበት በዚህ ሰዓት የሰውዬ መታገድ ፖል ፖግባን መግዛት ይፈልጋሉ ከሚባሉት ማድሪዶች ጀምሮ የአያክስ ወጣቶችን ለመቀራመት ለቋመጡ ክለቦች የራስ ምታት መሆኑ አልቀረም።

የዋትስአፕ ጉድ፡ እውን ደህንነቱ የተጠበቀ 'አፕ' ይኖር ይሆን?


ዋትስአፕ የተሰኘው የማኅበራዊ መገናኛ መተግበሪያ ከሰሞኑ በርባሪዎች አጥቅተውኛል፤ የተጠቃሚዎቼን መረጃም ሰርቀዋል ማለቱ ይታወቃል።
ዋትስአፕ በዓለም ዙሪያ 1.5 ቢሊዮን ተጠቃሚዎች እንዳሉት የሚነገርለት ከቁመቱም ከወርዱም የገዘፈ ተቋም ነው። የደህንነቱ ጉዳይ ግን ድርጅቱን በጥርጣሬ እንድናየው አድርጎናል።
እሺ ዋትስአፕስ አጠገባችን ያለ ሰው እንዳያጮልቅብን በመዳፋችን የሸፈንነው መረጃ ሌላ አገር ባሉ የመረጃ በርባሪዎች እየታየ ሊሆን እንደሚችል አመነ። ሌሎች የእጅ ስልኮቻችን ላይ ያሉ መተግበሪያዎችስ?

ዋትስአፕ ከሚወድድባቸው ባህሪያት አንዱ፤ የምንልከውን መልዕክት ከተቀባዩ ውጭ ማንም በቀላሉ ሊያገኘው አለመቻሉ ነበር። ነገር ግን መልዕክቶቹን ማግኘት የሚችል 'መረጃ በርባሪ' [ሃከር] ሳይኖር እንዳልቀረ ተነግሯል።
ጉዳዩ ወዲህ ነው። በርባሪዎች መልዕክቱ ተቀባዩ ጋር ከመድረሱ በፊት ስልካችንን በስውር ሰብረው በመግባት የምንፃፃፈውን ነገር ማየት ይችላሉ።
አሁን ጥያቄው ይሄ ነው. . . ሌሎች የእጅ ስልክዎት ላይ ባሉ መተግበሪያዎች [አፕ] ላለመሰለልዎ ምን ያህል እርግጠኛ ነዎት? ምላሽዎ "እኔ ምን አውቄ?" ሊሆን እንደሚችል እንገምታለን።በተለያዩ መተግበሪያዎች ከመሰለል ራስዎን የሚጠብቁባቸው መንገዶች አሉ

እንግዲያውስ ቁርጡን እንንገርዎ። የእጅ ስልክዎ ላይ ያለ ማንኛውም 'አፕ' መረጃዎን ለበርባሪ [ግለሰብም ይሁን መንግሥት] አሳልፎ ላለመስጠቱ ምንም ማስረገጫ የለም። ይህን የሰማነው በዘርፉ አሉ ከተባሉ ባለሙያዎች ነው።
የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን ከሚያስቁ ቀልዶች አንዱ «አፓችን ደህንነቱ የተጠበቀ ነው» የሚል ማስታወቂያ ነው። ማንኛውም የእጅ ስልክም ሆነ ኮምፒውተር ለመርበር ዝግጁ መሆኑን ያውቁታልና ነው።

እንደው እዚህ ድረስ አንብበው መከላከያ ሳንጠቁም ብንለያይ ከወቀሳ የምንተርፍም አልመሰለን። እነሆ ከዘርፉ ሰዎች የተሰጠ ምክር።
አንደኛው ኮምፒውተርዎንና ተንቀሳቃሽ ስልክዎን ኢንተርኔት ከሚሉት 'ጋኔን' ማላቀቅ ነው። ነገር ግን በዚህ ዘመን ያለ ኢንተርኔት አንዴት መኖር ይቻላል? አይቻልም! ኋላስ?
• 'አፕ' ከጫኑ በኋላ በየጊዜው 'አፕዴት' በማድረግ የደህንነት መጠኑን ከፍ ለማድረግ ይሞክሩ።
• ለፌስቡኩም፤ ለትዊተሩም ተመሳሳይ የይለፍ ቃል መጠቀምዎን አሁኑኑ ያቁሙ!!! ማስታወሱ አታካች ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን የተለያየ የይለፍ ቃል መጠቀምን የመሰለ ነገር የለም።

• 'ቱ ስቴፕ ቬሪፊኬሽን' ይሉታል። ወደ 'አፑ' ሲዘልቁ አንድ የይለፍ ቃለ ብቻ ከሚጠየቁ ሁለቴ ቢጠየቁ የሚል አማራጭ ሲቀርብልዎች መልስዎ 'እንዴታ' ይሁን።
• ያገኙትን 'አፕ' ባይጭኑ ይመከራል። ቢቻል ስለመተግበሪያው ትንሽ 'ጎገል' ቢያደርጉ።
• የማያውቁትን ማስፈንጠሪያ [ሊንክ] እንዳይጫኑ፤ አደራ! መዘዙ አይታወቅምና።
ላብዎን ጠብ አድርገው በገዙት ወይም ባስገዙት በገዛ ተንቀሳቃሽ ስልክዎ ከመሰለል ይዳኑ!

በአሜሪካ በእርሻ መሣሪያ የተያዘው አርሶ አደር እግሩን ቆረጠ

መሣሪያው አንደ መብሻ (ድሪል) የሚሽከረከር ነው።
በአሜሪካ ኔብራስካ ግዛት በእርሻ ሥራ ላይ ሳለ ሰብል መሰብሰቢያ መሣሪያ ውስጥ እግሩ የተቀረቀረበት አርሶ አደር በስለት የራሱን እግር ቆርጦታል።
የ63 ዓመቱ አርሶ አደር ኩርት ካሴር ምርት ለመሰብሰብ የሚረዳውን ማሽን ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ እያዘዋወረ ነበር፤ ማሽኑ ልክ እንደ መብሻ (ድሪል) ዓይነት ሲሆን የሚሽከረከርም ነው።
ግለሰቡ የግሉ በሆነው 607 ሔክታር መሬት ላይ ብቻውን እየሰራ ሳለ ነበር አደጋው ያጋጠመው። በአቅራቢያው ሰዎች ባለመኖራቸው የሚረዳው አላገኘም። ስልክ በመደወል የሰዎችን እርዳታ ለመጠየቅ ቢያስብም ተንቀሳቃሽ ስልኩን አጠገቡ ሊያገኘው አልቻለም።
ማሽኑ እግሩን እየከረከረ የበለጠ ወደ ውስጥ እየዘለቀና ከፍ እያለ መጣ።
በዚህ ጊዜ ደፋሩ ገበሬ የያዘውን ስለት ሳብ አድርጎ ከማሽኑ የተረፈውንና ከጉልበቱ በታች ያለው የራሱ እግር ላይ እርምጃ ወሰደ።
የእርሻ መሣሪያ

በደቡብ ሱዳን የምሽት ክለቦች ታገዱ

በደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ የሚገኙ የምሽት ክለቦች ሙሉ በሙሉ መታገዳቸውንና መጠጥ ቤቶች ላይ የሰአት እላፊ መጣሉን ቃል አቀባዩ ሜጀር ጀነራል ዳንኤል ጀስቲን ለቢቢሲ ኒውስ ደይ አሳውቀዋል።
" የምሽት ክለቦች ሙሉ በሙሉ እንዲዘጉ የተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ እየሆነ ነው። የከተማው ነዋሪዎች ለከተማው ምክር ቤት የምሽት ክለቦች እየረበሿቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲያማርሩ ነበር" ብለዋል።

የጁባ አስተዳዳሪ አውግስቲኖ ጃዳላ ዋኒ በበኩላቸው ከሳምንት በፊት በፌስቡክ ባስተላለፉት መልዕክት "ያልተገቡ" ተግባራትን ለመከላከል የምሽት ክለቦች እንዲዘጉና በመጠጥ ቤቶችም የሰአት እላፊ አዋጅ እንዲተላለፍ መወሰኑን አሳውቀው ነበር።

በሰአት እላፊው አዋጅ መሰረት መጠጥ ቤቶች የሚሰሩበት ሰአት ከቀኑ ስምንት ሰአት እስከ ምሽቱ 1 ሰአት ድረስ ብቻ እንደሆነ ሱዳን ትሪቢውን ዘግቧል።

ከዚህም በተጨማሪ በሆቴል መቆየት የሚፈልጉ ጥንዶች ባለትዳር መሆን የሚጠበቅባቸው ሲሆን የጋብቻ ማስረጃ ሰርቲፊኬትም ሊያሳዩ እንደሚገባም ተደንግጓል።

ኢትዮጵያ ለሱዳን ሙሉ በሙሉ ፤ ለጅቡቲ በግማሽ ኃይል ማቅረብ ማቋረጧ ተገለፀ


በመላው ሃገሪቱ ሲያጋጥም የሰነበተው በየዕለቱ ለረጅም ሠዓታት የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ምክንያቱ በኃይል ማመንጫ ግድቦች ውስጥ በቂ ውሃ ባለመኖሩ የተከሰተ እንደሆነ የውሃ፣ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጡ ያጋጠመው በተለይ በግልገል ጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ግድብ ላይ ባጋጠመው የዝናብ እጥረት ምክንያት መሆኑም የገለፀው፤ በአሁኑ ወቅትም የ476 ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦት እጥረት መከሰቱን አመልክተዋል።
በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ ለሱዳንና ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ 180 ሚዮን ዶላር ታገኝበት የነበረውን የኃይል አቅርቦት እንደምታቋርጥም ተገልጿል። ስለሆነም ለሱዳን የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ ለሙሉ፤ እንዲሁም ለጂቡቲ ከምታቀርበው ደግሞ ግማሹን ኃይል እንደምታቋርጥ ተነግሯል።

በተከሰተው እጥረት ምክንያትም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በመላው አገሪቱ በሦስት ፈረቃ እንደሚሆንና የፈረቃ አገልግሎቱም እስከ ሰኔ 30 2011ዓ.ም የሚቆይ መሆኑም ተነግሯል።
ባለፉት ሳምንታት በመላው ሃገሪቱ በተከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በተደጋጋሚ ለረጅም ሠዓታት ምክንያት የንግድ ተቋማትና ግለሰቦች ከፍተኛ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ሲናገሩ ቆይተዋል።
የሆቴል ሥራ አስኪያጅ የሆነው ሐይማኖት ልመንህ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በሥራቸው ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንዳለው ይናገራል።
መብራት በሚቆራረጥበት ጊዜ የኃይል መጠን ከፍና ዝቅ ማለት የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች መበላሸት፣ ሥራ መቆምና ሌሎችም እክሎች እንደፈጠሩ ከዚያም ባሻገር "ለምሳሌ ያህል መጠጥ አይቀዘቅዝም፤ ካልቀዘቀዘ አይሸጥም፤ ሽያጫችን ሙሉ በሙሉ ቆመ ማለት ነው" ይላል።
ምንም እንኳን መብራት መቆራረጥ የተለመደ ችግር ቢሆንም ባለፉት ሳምንታት ግን የከፋ መሆኑን ይናገራል።

በልብስ ስፌት ሙያ የሚተዳደረው ሌላኘው የባህርዳር ነዋሪ በበኩሉ መብራት መቆራረጥ ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩና፤ በተደጋጋሚ ቀጠሮዎችን ለመሰረዝ እንደተገደዱም ይናገራል።
ከዚህ ቀደምም መብራት ፈረቃ በነበረበት ወቅት በጄኔረተር ይገለገሉ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግን መብራት በፈረቃ ሳይሆን በዘፈቀደ በመጥፋቱ ከፍተኛ ችግር እንደተፈጠረባቸው ይገልፃል።
በገቢያቸው ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንዳለው የሚናገረው ይኼው ነዋሪ ንግዳቸውን እየጎዳው እንደሆነ አልደበቀም። በተለይም ባለፉት ሦስትና አራት ወራት ውስጥ ችግሩ መክፋቱን ሲናገር "አሁን ወቅቱ የረመዳን ከመሆኑ አንፃር ሌሊት ለመብላትም ሆነ ለመፀለይ ስንነሳ በጨለማ ነው" ይላል።

ከአርባ እስከ ሃምሳ ሰው በቀን የምታስተናግደው አዲስ አበባ አስኮ አካባቢ ሽሮ ቤት ያላት ማኅደር ተስፋዬ በበኩሏ ሁልጊዜም መብራት መቆራረጥ እንዳለና በተለይም በዚህ ሳምንት ሙሉ ቀን ጠፍቶ ወደ አመሻሹ ስለሚመጣ ለሥራዋ አስቸጋሪ እንደሆነባትና "ወደ ኋላ ተመልሰን በእንጨትና በከሰል ለመስራት ተገደናል" ስትል ትገልጻለች።
ምንም እንኳን ሬስቶራንቷ ከተከፈተ ከሁለት ዓመታት ጀምሮ መብራት መቆራረጥ እንዲሁም በፈረቃ መብራት ማግኘት የተለመደ ቢሆንም በዚህ ሳምንት ሙሉ በየቀኑ መጥፋቱ ግራ እንዳጋባት ትናገራለች።
ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ያጋጠመው መደበኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቆራረጥን በተመለከተ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አስፈላጊው ማብራሪያ ባለመሰጠቱ ግራ መጋባት ተፈጥሮ ቆይቷል።
ቅሬታውና ግራ መጋባቱ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት በአሁኑ ወቅት የውሃ፣ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስቴር ለቀጣይ በርካታ ሳምንታት የኤሌክትሪክ አቅርቦት በፈረቃ እንደሚሆን የሚገልጽ መግለጫ ሰጥቷል።

Sunday, May 12, 2019

የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህነንት መስሪያ ቤት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ ዛሬ ክስ መታየት ጀመረ።

በከባድ የሌብነት ወንጀልና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸው የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህነንት መስሪያ ቤት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ ዛሬ  ክስ መታየት ጀመረ። በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ክሳቸው የተሰማው አቶ ጌታቸው አሰፋ በተለያዩ ስውር ቤቶችና በፌደራል መንግስት ስር በሚታወቁ እስር ቤቶች ሰዎችን አፍኖ በመውሰድ ከባድ ግርፊያ፣ ድብደባና ጥፍር በመንቀል ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸምባቸው አስደርገዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ከአቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር በእሳቸው ስር የነበሩ የመምሪያ ሃላፊዎችም በተመሳሳይ ወንጀሎች ተጠርጥረው ክስ እንደቀረበባቸው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በሌሉበት ክሳቸው ዛሬ መታየት የጀመረው የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በስውር ማፈኛ ቤቶች በሚፈጸሙ ከባድ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎች የሚያስጠይቅ የክስ ፋይል እንደተከፈተባቸው ነው የተገለጸው።
በልደታ ምድብ ችሎት መታየት የጀመረው የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት አመራሮች የክስ ሂደት ከአቶ አቶ ጌታቸው አሰፋ ሌላ ፣ አቶ አጽበሃ ግደይ፣ አቶ አሰፋ በላይና አቶ ሺሻይ እንዳልተገኙም ተመልክቷል።
በብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ በተለያዩ መምሪያዎች በሃላፊነት የሰሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ፣አቶ ተስፋዬ ገብረጻዲቅ፣ አቶ ጎህ አጽብሃ ገብረህይወት፣ አቶ ቢኒያም ማሙሸትና አቶ ሸዊት በላይ ላይ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሌብነት ወንጀሎች ክስ ቀርቦባቸዋል።
እነዚህ ሃላፊዎች የጸረ ሽብር መምሪያ፣ የአዲስ አበባ ደህንነት መምሪያ፣ የውስጥ ደህንነት መምሪያና የኦፕሬሽን ክፍል መምሪያ በተሰኙ ከፍተኛ ሃላፊነቶች ላይ በነበራቸው ሚና በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸም ከባድ ወንጀልን በበላይነት መምራታቸው ተገልጿል።
እነዚህ የቀድሞ የደህንነት ሃላፊዎች በኃይል አስገድዶ ምርመራ በማካሄድ፤ የሰብአዊ መብት ረገጣ በመፈጸም፤ በምርመራ ላይ የጥፍር መንቀልን ጨምሮ በድብቅ እስር ቤት ውስጥ ዓይን ሸፍኖ ከባድ ድብደባ መፈጸም የሚሉት ወንጀሎች ተጠቅሰው ክስ ተመስርቶባቸዋል።
በምርመራ ወቅት በድብደባ የተነሳ ህይወቱ ያለፈ ሰውም ተጠቅሶ በክስ መዝገቡ ላይ ተነስቷል።
በአቶ ጌታቸው ላይ የቀረበው ክስ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ያልታወቁ እስር ቤቶች ውስጥ በኦነግና ግንቦት ሰባት ስም የተያዙ ሰዎችን በማሰቃየትና ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል በመፈጸም የሚል ነው።
አቶ ጌታቸው አሰፋ  ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል በተጨማሪ ከባድ የሌብነት ወንጀል መፈጸማቸውን በክሱ ላይ ተመልክቷል።
አቶ ጌታቸው አሰፋ በጠቅላይ አቃቤ ህግ በኩል የእስር ትዕዛዝ ቢወጣም የትግራይ ክልላዊ መንግስት አሳልፎ ላለመስጠት በመወሰኑ በአካል ሊገኙ እንዳልቻሉ ታውቋል።

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት የአፋር ሶስት ቀበሌዎች ይመለሱ ሲል ያሳለፈው ውሳኔ አግባብነት የሌለው ነው ሲል የአፋር ህዝብ ፓርቲ አስታወቀ


የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ኮንቴ ሙሳ ከኢሳት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ከሆነ ከሶማሌ ክልል ተወስደዋል የተባሉት ቀበሌዎች ድንበር ላይ ያሉ ሳይሆኑ 300 ኪሎ ሜትር ወደ አፋር ክልል የገቡ ናቸው።
ይህ ባለበት ሁኔታ አይነቱን ጥያቄ ማንሳት አግባብነት የሌለውና የህዝብን መብት የሚገፍ ነው ብለዋል።
ቀበሌዎቹ ምናልባትም የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባቸው መሆናቸውና ያ ጥቅማቸው የተነካባቸው ሰዎች የቀሰቀሱት ሊሆን ይችላሉም ብለዋል።
የአፋር አርብቶ አደር ሳይገደል ያደረበት ቀን የለም ያሉት ዶክተር ኮንቴ እንዲህ አይነቱ ኢሰብአዊ ድርጊት ሊቆም ይገባዋል ሲሉ ገልጸዋል።
ዶክተር ኮንቴ እንደሚሉት ከሆነ ዋናው ነገር የአካባቢው ሰላም ተጠብቆ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር ሁሉም ወገኖች ችግሩን በሰላም ለመፍታት መጣር አለባቸው ብለዋል።
የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አማካሪ አቶ ጀማል ደርዬ በበኩላቸው እነዚህ ቀበሌዎች ያለህዝብ ይሁንታ ወደ አፋር ክልል እንዲካለሉ ተደርገዋል ነው ያሉት።
ይሄ ውሳኔ ደግሞ የህዝብ ቁጣን ቀስቅሷል በዚህም ምክንያት የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ወደዚህ ውሳኔ ተሸጋግሯል ብለዋል።
አሁን ላይ ግን በሁለቱ ክልሎች መካከል ችግሮች መፈጠራቸውንና እነዛን ችግሮች ለመፍታት ደግሞ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው ብለዋል።

በቤንሻንጉል በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ቁጥር 62 ደረሰ


ኢሳት: በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን በማምቡክና አከባቢው ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ቁጥር 62 መድረሱ ተገለጸ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እንዳስታወቀው በማምቡክ 50 በጃዊ ደግሞ 12 ሰዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው።
ፋይል
ኮሚሽኑ ጨምሮ እንደገለጸው በአሁኑ ወቅት በአከባቢዎቹ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኗል።
ተቋርጠው የነበረው የትራንፖርት አገልጎሎትም መጀመሩን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አድጎ አምሳያ በጃዊው ጥቃት 200 ሰዎች ተገድለዋል ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል።
በጥቃቱ ምክንያት የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥርም 4ሺህ ደርሷል ብለዋል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር እንደገለጹት በሁለት አካባቢዎች የተነሱትን ግጭቶች በመቆስቆስና በማባባስ እጃቸው አለበት የተባሉ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ እንቅስቃሴ በስፋት ቀጥሏል።
በእስከአሁንም 62 ሰዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው። በተጠርጣሪዎች ላይ ማስረጃ የማሰባሰብ ሥራው መቀጠሉንም አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ መተከል ዞን በማምቡክና በአከባቢው ግጭቶች እንዲፈጠሩ ማድረጋቸውና በሂደትም መረጋጋት እንዳይፈጠር በማባባስ የሚጠረጠሩ ግለሰቦች በርካታ መሆናቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ በቀጣይም ሌሎችን በመያዝ ለፍርድ የማቅረቡ ተግባር ይካሄዳል ብለዋል።
ከማምቡክ ሌላ በጃዊ ወረዳ ከተፈጠረው ግጭት ጋር በተያያዘ እጃቸው ያለበት ሰዎች ተለይተው ምርመራ እየተደርገባቸው ሲሆን 12 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።
በማምቡክ ከተያዙት 50 ግለሰቦች ጋር በድምሩ 62 ሰዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚደረግ እንደሚሆን ነው ኮሚሽነሩ ገለጸዋል።
በፌዴራል እና በክልል ፖሊስ የተደራጀው ግጭቱን የሚመረምረው ቡድን ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉን ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል፡፡
ኮሚሽነሩ አቶ መሀመድ ሀምዲል እንዳሉት በአማራና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎችና በመከላከያ ሰራዊቱ ትብብር በተደረገ ጸጥታ የማስከበር እርምጃ ግጭት የተከሰተባቸው አከባቢዎች ወደ መረጋጋት ተመልሰዋል።
በግጭቱ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የአሶሳ- ግልገል በለስ፣ የግለገል በለስ- ማምቡክ፣ የግልገል በለስ-ፓዌ-ጃዊ-ማንኩሽና እና ሌሎችም ከተሞች የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩንም አቶ መሀመድ ገልጸዋል።
በቅርቡ የምርመራ ቡድኑ 200 የሚጠጉ የቀስት ደጋን ከነመወርወሪያው፣ ገጀራ እና መጥረቢያ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ኮሚሽነሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በማምቡክና አካባቢው ግጭት የ21 ሰዎች ህይወት ማለፉን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በሌላ በኩል በጃዊ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት 200 ሰዎች መገደላቸውን የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ገልጸዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ አድጎ አምሳያ ለሪፖርተር እንደገለጹት የእኛ ወገን ተነካ በሚል በተፈጸመ ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ጃዊን ጨምሮ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በመጠለያ የሚገኙ ሰዎች ከ4,000 በላይ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡
በመጠለያ ጣቢያዎች ወላጆቻቸውን ያጡ በርካታ ሕፃናት እንደሚገኙም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
አሁን ሁኔታዎች ተረጋግተዋል። ስጋት ያለባቸውን አከባቢዎች በመለየት ጸጥታ የማስከበሩን ስራ በተቀናጀ መልኩ እየሰራን ነው ማለታቸውን ሪፖርተር ዘግቧል።

የሰባት የፖለቲካ ሃይሎች ውህደት የሆነው አዲሱ ፓርቲ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ በሚል ስያሜውን አጸደቀ።

አዲሱ ፓርቲ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ በሚል ስያሜውን አጸደቀ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 1/2011) የሰባት የፖለቲካ ሃይሎች ውህደት የሆነው አዲሱ ፓርቲ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ በሚል ስያሜውን አጸደቀ።

መስራች ጉባዔውን ዛሬ በአዲስ አበባ የጀመረው አዲሱ ፓርቲ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከ300 በላይ ወረዳዎች በተወከሉ የመስራች ጉባዔ አባላት መተዳደሪያ ደንብ፣ አወቃቀር እና አርማ ላይ ውሳኔ በመስጠት እየተካሄደ መሆኑን የመስራች ጉባዔው አስተባባሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
በድምጽ የሚሳተፉ 1200 የጉባዔ አባላት የአዲሱ ፓርቲ አመራሮችን ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ፓርቲው በማህበራዊ ፍትህ ላይ መሰረት በማድረግ የዜግነት ፖለቲካን እንደሚያራምድም በመስራች ጉባዔው ላይ ተገልጿል።
አቶ አንዱዓለም አራጌ የመስራች ኮሚቴ አባል ጉባዔው ታሪካዊ ነው ሲሉ ገልጸውታል።

ኢዜማ የፓርቲውን መሪዎች በመምረጥ ጉባዔውን አጠናቀቀ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 2/2011) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ኢዜማ የፓርቲውን መሪዎች በመምረጥ የመስራች ጉባዔውን አጠናቀቀ።

የሰባት ፓርቲዎች ውህድ በመሆን የተመሰረተው ኢዜማ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን የፓርቲው መሪ፣ አቶ አንዱዓለም አራጌን በምክትልነት መርጧል።
አቶ የሺዋስ አሰፋን የፓርቲው ሊቀመንበር፣ ዶክተር ከበደ ጫኔን ደግሞ በምክትል ሊቀመንበርነት መምረጡ ታውቋል።
ከ300 በላይ ወረዳዎች ተወካዮቻቸውን በመላክ በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት ጉባዔውን ያካሄደው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ዜግነት ላይ መሰረት ያደረገ የፖለቲካ መስመር እንደሚከተልም ይፋ አድርጓል።

Friday, May 10, 2019

የደቡብ ሱዳን አማጺያን ሰራዊት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንዲጠጋ ትዕዛዝ ተሰጠ


የደቡብ ሱዳን አማጺያን ወታደራዊ አዛዥ ሰራዊት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንዲጠጋ ማዘዛቸው ተሰማ።
የሪክ ማቻር ሰራዊት አባላት እንደሆኑ የሚነገርላቸው ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል ጆር ወረዳ በድብቅ ወታደራዊ ካምፕ መስርተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መሆናቸው ታውቋል።

በአርሶአደሩና በጋምቤላ ልዩ ሃይል በተፈጸመባቸው ጥቃት የኢትዮጵያን ግዛት ለቀው የወጡት የደቡብ ሱዳን አማጺ ታጣቂዎች ተመልሰው ወደ ለመግባት በመሰባሰብ ላይ መሆቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የጋምቤላ ክልል ካቢኔ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በጋምቤላ ክልል አኝዋክ ዞን ጆር ወረዳ በኢትዮጵያ መንግስት ቁጥጥር ስር ያልነበረ ወታደራዊ ካምፕ ለአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ሆኖ ቆይቷል።
ካምፑን የደቡብ ሱዳን አማጺ መሪ ሬክ ማቻር ወታደሮች ይሁኑ ሌሎች ሃይሎች በግልጽ አልታወቀም ነበር።
በካምፑ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ወታደሮች የሚገኙ መሆናቸውን የገለጹት የኢሳት ምንጮች የጋምቤላ ክልል መንግስት ጉዳዩን በተመለከተ በተደጋጋሚ ለፌደራል መንግስቱ ማሳወቁን ጠቅሰዋል።
ከዚህ ምንነቱ ካልታወቀ ወታደራዊ ካምፕ ታጣቂዎች እየተነሱ በአኝዋክ ተወላጆች ላይ ጥቃት ሲፈጸም እንደነበርም መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከሶስት ሳምንት በፊት ከጋምቤላ እስር ቤት ያመለጡ 72 እስረኞች በቀጥታ የተቀላቀሉት በድብቅ ይገኛል የተባለውን ካምፕ መሆኑን በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል።
በጆር ወረዳ የሚገኘውን ወታደራዊ ካምፕ በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡን የመከላከያ ሰራዊት ሃላፊዎችንና የጋምቤላ ክልል ባለስልጣናትን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም የኢሳት ምንጮች ጉዳዩ በሁለቱም ወገኖች በልዩ ትኩረት ክትትል እየተደረገበት እንደሆነ ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት በመጀመሪያ ላይ የአርሶ አደሮችና የጋምቤላ ልዩ ሃይል በወሰዱት የማጥቃት ርምጃ ምንነቱ ካልታወቀ ካምፕ ውስጥ የነበሩትን ታጣቂዎች ማስወጣት መቻሉ ታውቋል።
በጊዜው በተካሄደ ውጊያ ከሁለቱም ወገኖች በድምሩ ስድስት ሰዎች መገዳላቸው የሚታወስ ነው።
የመከላከያ ሰራዊት በካምፑ ውስጥ በሚገኙ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ማስጠንቀቂያ በሰጠ ማግስት በተደረገው በዚሁ ውጊያ ታጣቂዎቹ ካምፑን ጥለው ወደ ደቡብ ሱዳን መሸሻቸው ተገልጿል።
የኢሳት ምንጮች ዛሬ ባደረሱን መረጃ ግን ከኢትዮጵያ ግዛት የተባረሩት የደቡብ ሱዳን አማጺ ወታደሮች እንዲሰባብሰቡና ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንዲጠጉ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።
ኮለኔል ፊሊፕ ጂማ ደንግ የተሰኙ የአማጺያኑ ወታደራዊ መሪ ባስተላለፉት በዚሁ ትዕዛዝ በተለያዩ የደቡብ ሱዳን አካባቢዎች የሚገኙት የአማጺው ወታደሮች ተሰባስበው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንዲጠጉ የሚያደርግ ነው።
ዓላማው በኢትዮጵያ ግዛት ጆር ወረዳ ወደ ሚገኘውና ባለፈው ሳምንት የተነጠቁትን ወታደራዊ ካምፕ መልሶ ለመያዝ እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል።
ጉዳዩን በተመለክተ የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት መረጃው እንዳለውም ምንጮች ጠቁመዋል።
አማጺው ግጭቱን የጎሳ እንዲሆን በማድረግ በአኝዋኮችና ኑዌሮች መካከል ደም ለማፋሰስ እየሰራ መሆኑንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በተያያዘ ዜና በጋምቤላ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች መሳሪያ ይዘው በከተማ ውስጥ የሚዘዋወሩ መሆናቸው የክልሉን ነዋሪ ስጋት ውስጥ መክተቱ ተገልጿል።
ሰሞኑንም በጋምቤላ ከተማ መሳሪያ ይዘው ሲዘዋወሩ የተያዙ ስደተኞች መኖራቸውን የኢሳት ምንጮች ከላኩት መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

Thursday, May 9, 2019

በሃይለ ገብረስላሴና በእንግሊዛዊው አትሌት ሞህ ፋራህ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ተካረረ


 በኢትዮጵያዊው ሃይለ ገብረስላሴና በእንግሊዛዊው አትሌት ሞህ ፋራህ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ መካረሩ ተገለጸ።
በአትሌት ሃይሌ ሆቴል በነበረኝ ቆይታ ዘረፋ ተፈጽሞብኛል ላለው ሞህ ፋራህ ሃይሌ መልስ መስጠቱ ውዝግቡን እንዳከረረው ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘግቧል።
ፋይል
አትሌት ሃይሌ እንደሚለው ሞህ ፋራህ በሆቴል ቆይታው በሰዎች ላይ ድብደባ ፈጽሟል።
በስነምግባር ጉድለት ችግር ፈጥሮብኛል ሲል ሞህ ፋራን ከሷል።
የሁለቱ የዓለማችን ታላላቅ አትሌቶች ውዝግብ አለምዓቀፍ ትኩረት መሳቡን ለማወቅ ተችሏል።
ባለፈው ወር መጋቢት መጨረሻ ላይ ነው። የዓለም የረጅም ርቀት ሯጭና የተለያዩ ክብረወሰኖች ባለቤት እንግሊዛዊው ሞህ ፋራህ ኢትዮጵያ ነበር።
ሱሉልታ በሚገኘውና የአትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ንብረት በሆነው ያያ አፍሪካ አትሌቲክስ መንደር ነበር ያረፈው ሞህ ፋራህ።
መጋቢት 25 ጠዋት ሞ ፋራህ መዘረፉን በመግለጽ ለሆቴሉ አመራሮች ያሳውቃል።
ፋራህ እንደሚለው የሞባይል ስልኩ፣ የእጅ ሰዓቱና 2600 የእንግሊዝ ፓውንድ ገንዘቡ መሰረቁን ይገልጻል።
ሞህ ፋራህ እንደሚለው ሃይሌ መዘረፌን አሳውቄው ምንም ምላሽ አልሰጠኝም።
የለንደኑን የማራቶን ውድድር እንዲስተጓጎልብኝ ሆን ብሎ ያስደረገው ነው ሲል ሞህ ፋራህ አትሌት ሃይሌ ላይ ጠንካራ ክስ ያቀርባል።
ሃይሌ ከትላንት በስቲያ ዴይሊ ቴሌግራፍ ለተሰኘ የእንግሊዝ ጋዜጣ በሰጠው ፣ምላሽ የሞህ ፋራህን ክስ ከበቀል ስሜት የመነጨ ሲል አስተባብሎታል።
ለሶስት ሳምንታት በፖሊስ በተደረገ ምርመራ ምንም ዓይነት የተሰረቀ ንብረት እንደሌለ ተረጋግጧል ያለው አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ጉዳዩ  በክብሬ ላይ የተቃጣ የበቀል ርምጃ ነው ብሏል።
እንደውም ሞህ ፋራህ በሆቴሉ በነበረው ቆይታ በስፖርት ማበልጸጊያ ክፍል ውስጥ በአንድ አትሌት ላይ ድብደባ መፈጸሙንና የሆቴሉን ጸጥታ ማወኩን በመግለጽ ተገቢ ባህሪ የሌለው ሲል ወርፎታል።
የያያ አፍሪካ አትሌቲክስ መንደር ስራ አስኪያጅ አቶ ለሚሳ ቦቴ ለዴይሊ ቴሌግራፍ በሰጡት ምላሽ ሞህ ፋራህ በሆቴሉ በነበረው ቆይታ ሰራተኞችን በመዝለፍና በማዋረድ አስነዋሪ ተግባር ሲፈጽም ነበር።
ለተጠቀመበት የሚፈለግበትን የ2000 ፓውንድ ክፍያ ሳይፈጽም ሄዷልም ሲሉ አቶ ለሚሳ ገልጸዋል።
ሞህ ፋራህ በአትሌት ሃይሌ ምላሽ መበሳጨቱን የገለጸ ሲሆን ጉዳዩን በቀላሉ እንደማይመለከተው አስታውቋል።
የሁለቱ የአለማችን ታላላቅ አትሌቶች የከረረ ፍጥጫ ከቃላት መወራወር ባለፈ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል የታወቀ ነገር የለም።

የብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ የቀብር ስነስርዓት የፊታችን እሁድ ይፈጸማል

 የብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ የቀብር ስነስርዓት የፊታችን እሁድ እንደሚፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በተለያዩ ሃላፊነቶችና ሃይማኖታዊ ተልዕኮዎች ሲያገለግሉ የቆዩት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ህይወታቸው ያለፈው በትላንትናው እለት ነው።
በእምነቱ ከፍተኛ መለኮታዊ የትምህርት ደረጃ ላይ በመድረስ ከሚጠቀሱ አባቶች አንዱ የሆኑት ዶክተር አቡነ ገሪማ ከ፵ዓመታት በላይ ቤተክርስቲያኒቱን ማገልገላቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ እስካለፈው ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2011 ድረስ በፓትርያርኩ ልዩ ጽሕፈት ቤት የውጭ ግንኙነት የበላይ ሃላፊነት፣ ሥራቸውን በማከናወን ላይ እንደ ነበሩም ሃራ ዘተዋህዶ ካወጣው መረጃ ላይ ማወቅ ተችሏል፡፡
በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ተብለው በኤጲስ ቆጶስነት የተሾሙት ሐምሌ 9 ቀን 1973 ዓ.ም በሰሜን ሱዳን – ካርቱም እንደነበር የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ፣ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት፣ ወደ ኋላም የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነውም አገልግለዋል፡፡
በዐበይት በዓላት ላይ በሚያቀርቧቸው፣ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እና ሐዋርያዊ ተልእኮ ላይ በአተኮሩ ጽሑፋዊ ስብከቶችና ትምህርቶች የሚታወቁት ብጹእ አቡነ ገሪማ ከ30 በላይ የትምህርታዊ ጽሑፎች ስብስብን በ2006 ዓ.ም. ለኅትመት ማብቃታቸውም ይታወቃል፡፡
ብጹእ ዶክተር አቡነ ገሪማ የተወለዱት በሰሜን ሸዋ በ1937 ዓ.ም. ነበር፡፡
ማዕርገ ዲቁናን ከግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ፣ ማዕርገ ምንኵስናን መጋቢት 1973 ዓ.ም. በደብረ ሊባኖስ ገዳም እንደተቀበሉም ከሕይወት ታሪካቸው መረዳት ተችሏል፡፡

አዴፖ ህገመንግስቱና ፌደራሊዝሙ እንዲሻሻል መጠየቁን አስታወቀ

ህገመንግስቱና ፌደራሊዝሙ እንዲሻሻል አዴፖ መጠየቁን የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ገለጹ። በፋኖ ስም በየመንገዱ መሳሪያ መያዝና ህገወጥ ስራ መስራት አይቻልም ሲሉም አሳስበዋል።

ፕሬዝዳንቱ ዶክተር አምባቸው መኮንን ዛሬ ጎንደር ላይ በተዘጋጀ ህዝባዊ ስብስባ ላይ እንደገለጹት ህገመንግስቱንና ፌደራሊዝሙን ማሻሻልን በተመለከተ ቀድሞ ጥያቄ ያቀረበው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አዴፓ ነው።
ዶክተር አምባቸው በፋኖ ስም የሚደረገው ህገወጥ ተግባርን በማውገዝ በዚህ ድርጊት ላይ የተሰማሩትን ሃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።
የክልሉ መንግስት ፀጥታ ጉዳዮችን ብቻ ነው እየሠራን መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አዴፓ በህገመንግስቱና በፌደራሊዝም ዙሪያ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ መጠየቁን ነው የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ዶር አምባቸው መኮንን የገለጹት።
በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ ስብሰባ ነው።
በዛሬው ዕለት በተጠናቀቀው በዚሁ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንቱ ዶክተር አምባቸው ሕገመንግሥቱ እና ፌዴራሊዝሙ ጭምር እንዲሻሻል ቅድሚያ የጠየቀው አዴፓ ነዉ ብለዋል።
‹‹ይሄ የአዴፓ አቋሙ ነው፤ አሁንም አንቀፆችን በድጋሚ ከሕዝብ ጥቅም አንፃር ማየት እንደሚያስፈልግ እናምናለን፡፡ እኛ የአማራ እና የኢትዮጵያ መሪዎች ነን፤ የሁሉም ሕዝብ ጥቅም ጠንካራ ኢትዮጵያን ይፈጥራል ብለን ነው የምንሠራው›› ማለታቸው ተገልጿል።
ለኢሳት ከውስጥ ምንጭ በደረሰው መረጃ በቅርቡ በተካሄደው የኢህአዴግ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ይህው ጉዳይ መነሳቱ ታውቋል።
በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና በአብዛኛው የአዴፓ አመራሮች ድጋፍ ያለው የህገመንግስትና የፈደራሊዝም መሻሻል ሀሳብ በተወሰኑ የኦዴፓና በአብዛኛው የህወሃት አመራሮች ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበር ነው የኢሳት የመረጃ ምንጮች የገለጹት።
የህወሀቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ የፌደራሊዝም ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው ለመጪዎቹ ሃምሳ ዓመታት ለውጥ አይደረግበትም ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ጎንደር ላይ እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ በአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ዶክተር አምባቸው መኮንን አጽንኦት የተሰጠው ሌላው ጉዳይ በክልሉ ስጋት እየፈጠረ የመጣው ህገወጥነት ነው።
ከዚህ አንጻርም በፋኖ ስም የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ሃይሎች የሚፈጽሙትን ህገወጥ ተግባር እንዲያቆሙት ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል ።
ፋኖ አባቶቻችን ታሪክ የሠሩበት፣ ይህም ትውልድ ለሌላ ታሪክ የሚጠቀመው ስያሜ ነው፡፡
ነገር ግን በየመንገዱ በፋኖ ስም ሕገ ወጥ ሥራ መሥራትና የጦር መሣሪያ ይዞ መሄድ አይቻልም ነው ያሉት የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ዶክተር አምባቸው መኮንን።
የክልሉ መንግስት ይህን ህገ-ወጥነት ሲያስታምም ቆይቷልም ሲሉ ተናግረዋል።
እነዚህን በፋኖ ስም ህገወጥ ተግባር የሚፈጽሙትን ሃይሎች የምትደግፉ ወገኖች ከድርጊታችሁ ተቆጠቡ ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ዶክተር አምባቸው ለወጣቱም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ራሳችሁን የማህበራዊ ሚዲያ አጀንዳዎች ማስተጋቢያ አታድርጉ ብለዋል ለወጣቶች ።
የጎንደሩ ህዝባዊ ስብሰባ በአማራና በቅማንት ማህበረሰቦች መካከል የተፈጠረውን ችግር በእርቅ በመፍታት ወሳኝ ውጤት ማስመዝገቡንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

Tuesday, May 7, 2019

ጎሰኝነት በህግ ይታገድ በሚል የማህበራዊ ድረ ገጽ ዘመቻ ተከፈተ


ጎሰኝነት በህግ ይታገድ በሚል በማህበራዊ ሚዲያዎች ዘመቻ መከፈቱ ታወቀ።
በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያውያን ግብረሃይል የዘር ፖለቲካ እንዲታገድ የሚጠይቅ ትዕይንተ ህዝብ ሊያደርግ በዝግጅት ላይ መሆኑም ታውቋል።

ከትላንት ጀምሮ በፌስ ቡክ፣ በቲውተርና በሌሎች የማህበራዊ ሚዲያዎች በተጀመረው ዘመቻ ኢትዮጵያን ለአደጋ ያጋለጠ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዜጎቿን ለመፈናቀልና ለግድያ የዳረገው የጎሳ ፖለቲካ በህግ እንዲታገድ የሚጠይቁ መልዕክቶች በመተላለፍ ላይ ናቸው።
በመንግስት የተጀመረው የማሻሻያ ስራ የጎሳ ፖለቲካን ካላገደ ትርጉም የለውም ሲሉ አዘጋጆቹ ባሰራጯቸው መልዕክቶች ገልጸዋል።
በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያውያን ግብረሃይል የተጠራው ሰልፍም በመጪው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ እንደሚካሄድ ታውቋል።
ጎሳን መሰረት ያደረገው የፖለቲካ ስርዓት ኢትዮጵያን ለአደጋ አጋልጧል ነው የሚሉት የዘመቻው አስተባባሪዎች።
ስርዓቱ ባለፉት 27 ዓመታት በመንግስት መዋቅር ህጋዊነትን ተላብሶ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ ሲያጋጭ ነው ለበርካቶች መሞት ምክንያት መሆኑን የሚገልጹት አስተባባሪዎች እንደሀገር ኢትዮጵያ እንዳትቆም ትልቅ እንቅፋት መፍጠሩን ይጠቅሳሉ።
ለጎሳ ፖለቲካ እውቅና በመስጠት የዜግነትን መብት የገፈፈው ህገመንግስቱ በአፋጣኝ እንዲከለስ የሚጠይቀው ዘመቻው በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከዚህ አንጻር ጊዜ የማይሰጠው ሃላፊነት ከፊቱ ይገኛል ሲል ያሳስባል።
መንግስት ማሻሻያ ለማድረግ ቃል ቢገባም የጎሳ ፖለቲካን የማያግድ ማሻሻያ ትርጉም አይኖረውም ሲሉ ዘመቻውን የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን በፌስቡክና በቲዎተር ገጾቻቸው መልዕክቶችን እያሰራጩ ነው።
ዘመቻውን በማስተባበር ላይ ያሉትም የዘመቻው ዓላማ አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ጭምር አላሰራና አላንቀሳቀስ ያለውን የጎሳ ፖለቲካ ለማገድ ወሳኝ እርምጃ እንዲወስድ ግፊት ለማድረግ ነው ብለዋል።
ከአስተባባሪዎቹ አንዱ የሆኑት አቶ ከባዱ በላቸው ሀገሪቱ ላይ እውነተኛና ጠንካራ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት መንግስት ቁርጠኛ ከሆነ ቀጣዩ እርምጃው የጎሳ ፖለቲካን በህግ ማገድ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ለሶስት ቀናት በሚዘልቀው ዘመቻ ተሳታፊዎች የተለያዩ በፎቶግራፎችና በጽሁፎች የታጀቡ መልዕክቶችን በማጋራትና በማሰራጨት ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
በተመሳሳይ በፈረንጆቹ ግንቦት 6 ከአንድ ሳምንት በኋላ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያውያን ግብረሃይል ትዕይነተ ህዝብ መጠራቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በአሜሪካን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የተጠራው ሰልፍ የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ እንዲታገድ የሚጠይቅ ነው።
ለዚህ የጎሳ ፖለቲካ እውቅና የሰጠው ህገመንግስቱም እንዲቀየር በሰላማዊ ሰልፉ እንደሚጠይቅ ታውቋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት መጅሊስ አመራር ተሰናበተ

 የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት መጅሊስ አመራር ዛሬ በይፋ ተሰናበተ።

ዘጠኝ አባላት ያሉበት ጊዜያዊ የባላደራ ምክር ቤት መመስረቱንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ታሪካዊ በተባለው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጉባዔ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አንድነት ለኢትዮጵያ አንድነት ወሳኝ ሚና አለው ሲሉ ገልጸዋል።
ከመላ ሀገሪቱ የተወጣጡ የእምነቱ አባቶችና ምሁራን በተገኙበት እርቅ መፈጸሙንም ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የዘመናት ጥይቄ በሚመልስ መልኩ የተጠናቀቀ ጉባዔ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
አፈጻጸሙ ትኩረት ከተሰጠው የዛሬው ጉባዔ ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታላቅ ድል ነው ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የ2019 የዩኔስኮ ተሸላሚ ሆኑ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የ2019 የዩኔስኮ የሰላም ሽልማት ተሸላሚ ሆኑ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ባደረጉት አስተዋጽኦ ለሽልማት መብቃታቸውን የመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ ይፋ አድርጓል።

በቀድሞ የአይቬሪኮስት ፕሬዝዳንት ፌሊኒክስ ሃፌፍ- ቦኒይ ስም የሚጠራውን የዩኔስኮ የሰላም ሽልማት የተቀዳጁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሀገር ውስጥ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ለመውሰድ በጀመሩት ጥረትም አድናቆትን እንዳገኙ ተመልክቷል።
ባለፈው ሰኞ በፓሪስ የዩኔስኮ የሰላም ሽልማት ሰጪ ኮሚቴ አባላት የዘንድሮውን ተሸላሚ ለመምረጥ ተሰይመዋል።
የቀድሞ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሴርሌፍ፣ የቀድሞ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ሆላንዴ፣ የጆርዳን ልዕልት ሱማያ ቢንት ሀሰን፣ የአይ ኤም ኤፍ የቀድሞ ዳይሬክተር ጄነራል ሚሼል ካምዴሰስ የኮሚቴው አባላት ናቸው።
በቀድሞ የአይቬሪኮስት ፕሬዝዳንት በነበሩት ፌሊክስ ሃፌየት ቦኒየ የተሰየመው የመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት የሳይንስና ባህል ተቋም ዩኔስኮ የሰላም ሽልማት ለሰላምና ለዲሞክራሲ መጎልበት አስተዋጽኦ ለሚያደርጉ ሰዎች የሚሰጥ ሲሆን የዘንድሮው ሽልማት ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዲሆኑ ወስኗል።
የኮሚቴው አባላት በሰጡት ውሳኔ መሰረት ዶክተር አብይ 30ኛው የሰላም ተሸላሚ ሆነዋል።
ተቋሙ ይህን ክብር ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር የሰጠው በአፍሪካ ቀንድ የሰላም አየር እንዲነፍስ ባደረጉት አስተዋጽኦ መሆኑን አስታውቋል።
በተለይም ለ20 ዓመታት የዘለቀውን የኢትዮጵያና የኤርትራ ፍጥጫ እንዲቆም ታሪካዊ የተባለ የሰላም ስምምነት እንዲደርግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጫወቱት ሚና ተጠቅሷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ ዳይሬክተር ኦደሪ አዞውላይ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ በጉብኝት ላይ ሲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን አግኝተው የእንኳን ደስ ያልዎት መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ዘገባዎች ያመለክታሉ።
የፌሊክስ ሃፌየት ቦኒየ የሰላም ሽልማት የተቋቋመው በ1989 እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሲሆን ከ120 በላይ የተባበሩት መንግስታት አባል ሀገራት ድጋፍ ሰጥተው በመካሄድ ላይ ያለ ሽልማት መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።
ሽልማቱ ዓለም አቀፍ ግጭቶችን በመፍታት፣ የውይይትን እና ድርድርን ሚና በማጉላትና በመቻቻል፣ በእኩልነትና በመግባባት ሰላም እንዲሰፍን አስተዋፅኦ ላደረጉ ግለሰቦች ተቋማት በየዓመቱ እንዲሰጥም ሀገራቱ ተስማምተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ ለንባብ በበቃው ታይም መጽሄት ከዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ በመባል ከተመረጡ ታላላቅ ሰዎች አንዱ መሆናቸው የሚታወስ ነው።
ለውጥ በሀገራቸው እንዲመጣ በማድረግ የሚጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሁን ላይ ሀገሪቱን እያሰጋት ያለው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውስ የማሻሻያ ፕሮግራማቸው ላይ ከፍተኛ ችግር መፈጠሩን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተለይ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ላደረጉት አስተዋጽኦ የኖቤል የሰላም ሽልማት እንዲያገኙ ግፊት እየተደረገ ሲሆን መቀመጫውን ኖርዌይ ያደረገው የኖቤል ሽልማት ድርጅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእጩነት እንዲቀርቡ የሚጠይቀው የህዝብ ጥቆማ እንደደረሰው ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

Thursday, May 2, 2019

ለዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ አስክሬን አሸኛኘት ተደረገ

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ አስክሬን ሽኝት ተደረገ።
ህይወታቸው ባለፈበት ጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ዛሬ በተካሄደ የሽኝት ፕሮግራም ከተለያዩ የጀርመን ከተሞችና ከሌሎች ሀገራት የመጡ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ዜጎች መገኘታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል ።
በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄነራል ጽሕፈት ቤት አማካኝነት በተዘጋጀው የስንብትና የሽኝት ፕሮግራም የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የቅርብ ጓደኞችና አብሮ አደጎች ምስክርነቶችን ሰተዋል።
በሃይማኖታዊ ዝማሬና  ጸሎት ሽኝቱ የተከናወነ ሲሆን የተለያዩ እምነት አባቶችም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ አስክሬን በነገው ዕለት ወደ ኢትዮጵያ  እንደሚገባ በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመው ኮሚቴ አስታውቋል።
የቀብር ስነስርዓቱም የፊታችን እሁድ በአዲስ አበባ በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተክርስቲያን እንደሚፈጸም ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል ።

wanted officials