Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, May 17, 2019

አቶ ጌታቸው አሰፋ በድጋሚ መጥሪያ እንዲሰጣቸው ትዕዛዝ ተላለፈ

 ለቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ መጥሪያ እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤት በድጋሚ ትዕዛዝ ሰጠ። ለዛሬ እንዲቀርቡ የተላለፈው የመጀመሪያው ትዕዛዝ ተፈጻሚ ያልሆነው መጥሪያው ከፍርድ ቤት ወጪ ሳይደረግ በመቅረቱ መሆኑን በዛሬው ችሎት ላይ ተገልጿል።

የዋስትና መብት ጥያቄ ያቀረቡ ተከሳሾች በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጎባቸዋል። የአቶ ጌታቸው አሰፋን መጥሪያ በተመለከተ የተዛባ ዜና አሰራጭተዋል በተባሉ የሚዲያ ተቋማት ላይም ፍርድ ቤቱ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በአቶ ጌታቸው አሰፋና በሌሎች የቀድሞ የደህንነት መስሪያ ቤት ከፍተኛ ሃላፊዎች ላይ የተመሰረተውን ክስ እየተመለከተ ያለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ድጋሚ ትዕዛዝ በማስተላለፍ አቶ ጌታቸውን ጨምሮ በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች መጥሪያ እንዲሰጣቸው ውሳኔ አስተላልፏል።
የሚያዚያ 30ው ትዕዛዝ ተፈጻሚ ያልሆነው ከፍርድ ቤት መጥሪያ ባለመውጣቱ ነው የሚል ምላሽ ቢሰጥም ፖሊስ ባለመቅረቡ ትክክለኛውም ምክንያት በፖሊስ አልተገለጸም።
አቃቤ ህግ መጥሪያ የመስጠት ስልጣኑ የእኔ አይደለም ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
በዛሬው ችሎት ፌደራል ፖሊስ መጥሪያውን ለተጠርጣሪዎቹ ባሉበት እንዲያደርሳቸው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተሰጠው ሲሆን ጠቅላይ አቃቤ ህግም ጉዳዩን እንዲከታተለው መታዘዙን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ከአቶ ጌታቸው አሰፋ በተጨማሪ በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸው አቶ አጽበሃ ግደይ፣ አቶ አሰፋ በላይና አቶ ሽሻይ ልዑል በድጋሚ መጥሪያ እንዲደርሳቸው እንዲደረግም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
በዛሬው ችሎት ክስ የተመሰረተባቸው የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት 22 አመራሮች የዋስትና ጥያቄቸው ውድቅ ተደርጓል።
የቀድሞ የደህንነት መስሪያ ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ያሬድ ዘሪሁን፣ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ እንዲሁም አቶ መአሾ ኪዳኔና አቶ አማኑዔል ኪሮስ የዋስትና ጥያቄአቸው ውድቅ ሆኖ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መስጠቱን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።
በተያያዘ ዜና የሚያዚያ 30 ችሎት ላይ አቶ ጌታቸው አሰፋ እጃቸውን ይዞ ለፍርድ እንዲያቀርብ ፖሊስ ትዕዛዝ ተሰጠው በሚል ዜና ያስተላለፉ ሶስት የሚዲያ ተቋማት በዳኛው ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ችሎቱን የተከታተሉ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት፣ ፋና ብሮድካስቲንግና ሸገር ሬዲዮ የተዛባ ዜና አሰራጭታችኋል ተብለው ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው በኋላ ይቅርታ መጠየቃቸው ታውቋል።
ቀጣይ ሂደትን በተመለከተ የክሱን ጉዳይ ለመመልከት ፍርድ ቤቱ ለግንቦት 16 ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የዛሬውን ችሎት አጠናቋል።
በሌብነትና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ከባድ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ጌታቸው አሰፋን አሳልፎ ለመስጠት በትግራይ ክልል መንግስት በኩል ፍቃደኝነት አለመኖሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በመቀሌ የሚገኙ ወጣቶች አቶ ጌታቸው አሰፋ መሸለም እንጂ መከሰስ የለባቸውም በሚል ዓላማ ለዛሬ ሰልፍ ጠርተው ነበር።
አቶ ጌታቸው በስውር እስር ቤቶች በርካታ ዜጎችን ከድብደባ ጀምሮ፣ ጥፍር በመንቀልና በማኮላሸት እስከሞት በሚያደርስ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች ፈጽመዋል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን እስካሁንም በትግራይ ክልል መቀሌ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials