Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, May 17, 2019

ሚኖ ራዮላ፡ የአውሮፓን እግር ኳስ የሚዘውረው ቱጃር 'ደላላ'


"ሚኖ" በተሰኘ ቅፅል ስሙ ይታወቃል፤ ሆላንዳዊው ካርሚን ራዮላ። የታዋቂዎቹ ፖል ፖግባ፣ ዝላታን ኢብራሂሞቪች፣ ሄንሪክ ሚኪታሪያንና ዴ ሊት የመሳሰሉ ተጨዋቾች ወኪል ነው።
ጣልያን ተወልዶ በኔዘርላንድስ ሃርለም ከተማ እንዳደገ የሚነገርለት ራዮላ የደች ዜግነት ያለው 'ምርጥ ደላላ' ነው።
በልጅነቱ አባቱ በከፈቱት ሬስቶራንት ውስጥ ደፋ ቀና ብሎ አስተናግዷል። በጎንዮሽ ደግሞ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በሕግ ተመርቋል።
ጣልያንኛ፣ ጀርመንኛ፣ ስፓኒሽ፣ ፈረንሳይኛ፣ ፓርቹጊዝ፣ ደች እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ የሚናገረው ራዮላ ገና የ18 ዓመት ለጋ ሳለ ነበር ኔዝርላንድስ ውስጥ የሚገኝ አንድ የታዳጊዎች እግር ኳስ ኃላፊ ሆኖ ራሱን ያገኘው።
ከዚያም የነብስ ጥሪው ወደሆነው የወኪልነት ሥራ ገባ፤ ለአንድ ወኪል ድርጅት ተቀጥሮ ይሠራም ጀመር። የመጀመሪያው ሥራ የሆነው ደግሞ ተስፋ የሚጣልባቸውን ታዳጊ ደች ተጫዋቾችን ለጣልያኑ ሴሪ ኤ ማሻሻጥ።
ሚኖ ራዮላ
በታዳጊነታቸው በራዮላ ደላይነት ወደ ጣልያን ብሎም ወደ እንግሊዝ ገብተው ስማቸውን በጉልህ መፃፍ ከቻሉ ተጫዋቾች መካከል ዴኒስ ቤርግካምፕ የሚጠቀስ ነው።
ምንም ቢሆን የራሥ የራሥ ነው ያለው ራዮላ ተቀጥሮ ይሠራበት የነበረበትን ድርጅት ለቆ የራሱን የውክልና ድርጅት ሊያቋቁም ቻለ።
ለሃገሩ ቼክ ሪፐብሊክ ባሳየው ብቃት የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች ዓይን አርፎበት የነበረው ፓቬል ኔድቬድ ከስፓርታ ፕራግ ወደ ላዚዮ እንዲዛወር ያደረገው ራዮላ ነበር።
አሁን ላይ አውሮፓ ውስጥ ከሚጫወቱ እግር ኳሰኞች ስም ያላቸው 20 ገደማ ተጨዋቾች ውክልናቸውን ለራዮላ ሰጥተው ይንቀሳቀሳሉ።
እንደ አውሮፓዊያኑ 2016 ላይ ራዮላ 'ታሪክ ሠራ'። ያኔ የዓለም ሬከርድ በነበረ ዋጋ ፖል ፖግባን ከዩቬንቱስ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ እንዲዛወር አደረገ፤ ዋጋው ደግሞ 105 ሚሊዮን ዩሮ።
ጉደኛው ራዮላ ከዚህ ዝውውር 25 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ ወደ ኪሱ እንዳስገባ ይነገራል።
ከዚያ በኋላ ወደ አሜሪካዋ የባህር ዳርቻ ግዛት ማያሚ አቅንቶ 9 ሚሊዮን ዩሮ በማፍሰስ ቤተ-መንግሥት የሚያስንቅ መኖሪያ 'መንደር' ሸመተ።
ፎርብስ የተሰኘው የቢዝነስ ጋዜጣ 2018 ላይ ባወጣው ዘገባ ራዮላ 69 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ገቢ ያለው ሲሆን በእርሱ ውክልና ሥራ ያሉ 70 ተጫዋቾች 629 ሚሊዮን ዶላር ሊያወጡ ይችላሉ ሲል አትቷል።

ታላላቆቹ የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች የራዮላ ስም ሲጠራ ይንቀጠቀጣሉ፤ ይነዝራቸዋል። ምክንያታቸው ደግሞ በእርሱ ውክልና ሥር ያሉ ተጨዋቾችን እንዳሻው ማዟዟር መቻሉ ነው።
ሰውየው ያሻውን ከመናገር ወደኋላ የሚልም አይደለም። በአትንኩኝ ባይነቱ የሚታወቀው ራዮላ በእርሱ ውክልና ሥር ያሉ ተጨዋቾችን የሚተቹ የቀድሞ እግር ኳሰኞችም ሆነ ተንታኞችን በመወረፍ ይታወቃል።
ከሰሞኑ ግን የራዮላን ጠላቶች ፊት ፈገግ ያሰኘ፤ ለጊዜውም ቢሆን ለክለቦችን እፎይታ የሰጠ ዜና ከወደ ጣልያን ተሰምቷል። ራዮላ በጣልያን እግርኳስ ፌዴሬሽን ከውክልና ሥራ መታገዱን የሚያትት። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አካል ፊፋም የጣልያን አቻውን ፈለግ በመከተል ራዮላ ላልተወሰነ ጊዜ ከወኪልነት ሥራው እንዲታገድ ውሳኔ አስተላለፈ።
የጣልያና እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህን ውሳኔ ለምን እንዳስተላለፈ ግልፅ ባይሆንም ራዮላ ግን «እገዳው ብርቅ አልሆነብኝም። እኔ ያልተመቸኝ ውሳኔው ፖለቲካዊ መሆኑ ነው» ሲል ተደምጧል።
አክሎም «የጣልያን እግርኳስ ፌዴሬሽን የሃገሪቱን ኳስ ወደኋላ አስቀርቷል ብዬ የተናገርኳት ነገር ሳትቆረቁራቸው አትቀርም፤ በሃገሪቱ ሳላለው የእግር ኳስ ዘረኝት ጉዳይ አሳስቦኛል ማለቴም ይቅርታ ሳያስነፍገኝ አይቀርም» ሲል ተሳልቋል።
ይህ ውሳኔ ያስደሰታቸው ቢኖሩም እንኳ የራዮላ መታገድ ለአንዳንድ ክለቦች ደግሞ ደንቃራን ይዞ የመጣ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
የአውሮፓ እግር ኳስ የዝውውር ገበያ በሚደራበት በዚህ ሰዓት የሰውዬ መታገድ ፖል ፖግባን መግዛት ይፈልጋሉ ከሚባሉት ማድሪዶች ጀምሮ የአያክስ ወጣቶችን ለመቀራመት ለቋመጡ ክለቦች የራስ ምታት መሆኑ አልቀረም።

No comments:

Post a Comment

wanted officials