Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, May 17, 2019

ኢትዮጵያ ለሱዳን ሙሉ በሙሉ ፤ ለጅቡቲ በግማሽ ኃይል ማቅረብ ማቋረጧ ተገለፀ


በመላው ሃገሪቱ ሲያጋጥም የሰነበተው በየዕለቱ ለረጅም ሠዓታት የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ምክንያቱ በኃይል ማመንጫ ግድቦች ውስጥ በቂ ውሃ ባለመኖሩ የተከሰተ እንደሆነ የውሃ፣ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጡ ያጋጠመው በተለይ በግልገል ጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ግድብ ላይ ባጋጠመው የዝናብ እጥረት ምክንያት መሆኑም የገለፀው፤ በአሁኑ ወቅትም የ476 ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦት እጥረት መከሰቱን አመልክተዋል።
በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ ለሱዳንና ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ 180 ሚዮን ዶላር ታገኝበት የነበረውን የኃይል አቅርቦት እንደምታቋርጥም ተገልጿል። ስለሆነም ለሱዳን የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ ለሙሉ፤ እንዲሁም ለጂቡቲ ከምታቀርበው ደግሞ ግማሹን ኃይል እንደምታቋርጥ ተነግሯል።

በተከሰተው እጥረት ምክንያትም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በመላው አገሪቱ በሦስት ፈረቃ እንደሚሆንና የፈረቃ አገልግሎቱም እስከ ሰኔ 30 2011ዓ.ም የሚቆይ መሆኑም ተነግሯል።
ባለፉት ሳምንታት በመላው ሃገሪቱ በተከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በተደጋጋሚ ለረጅም ሠዓታት ምክንያት የንግድ ተቋማትና ግለሰቦች ከፍተኛ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ሲናገሩ ቆይተዋል።
የሆቴል ሥራ አስኪያጅ የሆነው ሐይማኖት ልመንህ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በሥራቸው ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንዳለው ይናገራል።
መብራት በሚቆራረጥበት ጊዜ የኃይል መጠን ከፍና ዝቅ ማለት የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች መበላሸት፣ ሥራ መቆምና ሌሎችም እክሎች እንደፈጠሩ ከዚያም ባሻገር "ለምሳሌ ያህል መጠጥ አይቀዘቅዝም፤ ካልቀዘቀዘ አይሸጥም፤ ሽያጫችን ሙሉ በሙሉ ቆመ ማለት ነው" ይላል።
ምንም እንኳን መብራት መቆራረጥ የተለመደ ችግር ቢሆንም ባለፉት ሳምንታት ግን የከፋ መሆኑን ይናገራል።

በልብስ ስፌት ሙያ የሚተዳደረው ሌላኘው የባህርዳር ነዋሪ በበኩሉ መብራት መቆራረጥ ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩና፤ በተደጋጋሚ ቀጠሮዎችን ለመሰረዝ እንደተገደዱም ይናገራል።
ከዚህ ቀደምም መብራት ፈረቃ በነበረበት ወቅት በጄኔረተር ይገለገሉ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግን መብራት በፈረቃ ሳይሆን በዘፈቀደ በመጥፋቱ ከፍተኛ ችግር እንደተፈጠረባቸው ይገልፃል።
በገቢያቸው ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንዳለው የሚናገረው ይኼው ነዋሪ ንግዳቸውን እየጎዳው እንደሆነ አልደበቀም። በተለይም ባለፉት ሦስትና አራት ወራት ውስጥ ችግሩ መክፋቱን ሲናገር "አሁን ወቅቱ የረመዳን ከመሆኑ አንፃር ሌሊት ለመብላትም ሆነ ለመፀለይ ስንነሳ በጨለማ ነው" ይላል።

ከአርባ እስከ ሃምሳ ሰው በቀን የምታስተናግደው አዲስ አበባ አስኮ አካባቢ ሽሮ ቤት ያላት ማኅደር ተስፋዬ በበኩሏ ሁልጊዜም መብራት መቆራረጥ እንዳለና በተለይም በዚህ ሳምንት ሙሉ ቀን ጠፍቶ ወደ አመሻሹ ስለሚመጣ ለሥራዋ አስቸጋሪ እንደሆነባትና "ወደ ኋላ ተመልሰን በእንጨትና በከሰል ለመስራት ተገደናል" ስትል ትገልጻለች።
ምንም እንኳን ሬስቶራንቷ ከተከፈተ ከሁለት ዓመታት ጀምሮ መብራት መቆራረጥ እንዲሁም በፈረቃ መብራት ማግኘት የተለመደ ቢሆንም በዚህ ሳምንት ሙሉ በየቀኑ መጥፋቱ ግራ እንዳጋባት ትናገራለች።
ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ያጋጠመው መደበኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቆራረጥን በተመለከተ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አስፈላጊው ማብራሪያ ባለመሰጠቱ ግራ መጋባት ተፈጥሮ ቆይቷል።
ቅሬታውና ግራ መጋባቱ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት በአሁኑ ወቅት የውሃ፣ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስቴር ለቀጣይ በርካታ ሳምንታት የኤሌክትሪክ አቅርቦት በፈረቃ እንደሚሆን የሚገልጽ መግለጫ ሰጥቷል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials