Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, August 20, 2019

ኬንያዊቷ ሼፍ ለሰባ አምስት ሰአታት ያህል በማብሰል 'ሬኮርድ ሰበረች'

ለሰባ አምስት ሰዓታት ያህል ያለማቋረጥ ምግብ በማብሰል ኬንያዊቷ ማሊሃ ሞሃመድ የአለም የምግብ ማብሰል ሬኮርድን እንደሰበረች ተዘግቧል።
ማሊሃ ሞሃመድ
በባህር ዳርቻዋ በምትገኘው ቦምባሳ ተቀማጭነቷን ያደረገችው ማሊሃ መሀመድ ሙከራዋን የጀመረችው ጥዋት ሐሙስ አራት ሰዓት ላይ ነው።
ምግብ ማብሰሏ ለቀናትም ቀጥሎ እሁድ ሰባት ሰዓት ላይ አቁማለች።

የጊነስ ወርልድ ሬኮርድ የማጣራቱን ስራ ያልጨረሰ ሲሆን ከተረጋገጠም በአሜሪካዊው ምግብ አብሳይ ሪኪ ለምፕኪን ተይዞ የነበረውን የ68 ሰዓት ሬኮርድ ታሻሽላለች ተብሏል።
ማሊሃ አራት መቶ ያህል የኬንያና አለም አቀፍ ምግቦችን ካዘጋጀች በኋላ መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን ላጡ ለግሳለች።
ያለማቋረጥ በሰራችባችው ሰባ አምስት ሰዓታት ውስጥ በየአስራ ሁለት ሰዓቱ ለሰላሳ ደቂቃ ያህል ብቻ አርፋለች።

የምግብ ማብሰሏን በድል ካጠናቀቀች በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገረችው "ጉዞው አድካሚ ነበር። እግሮቼ እየተብረከረኩ ነው፤ አይኖቼም እንቅልፍ በማጣት ብዛት ይቆጠቁጡኛል። ነገር ግን ይህንን በማሳካቴ በጣም ደስተኛ ነኝ"

የሞምባሳ አስተዳዳሪ አሊ ሃሰን ጆሆ የ36 አመቷን ምግብ አብሳይ እንኳን ደስ ያለሽ መልዕክት አስተላልፈውላታል።
በፌስቡካቸውም ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍም "ለሞምባሳና ለኬንያ ብቻ ሳይሆን መላው አፍሪካውያንን አኩርተሻል" ብለዋታል።

Monday, August 19, 2019

የአዲስ አበባ አስተዳደር የጎዳና ልመናና የወሲብ ንግድን ለማገድ ረቂቅ ህግ ማዘጋጀቱን ተከትሎ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው

ከሰሞኑ የአዲስ አበባ አስተዳደር የጎዳና ልመናና የወሲብ ንግድን ለማገድ ረቂቅ ህግ ማዘጋጀቱን ተከትሎ በብዙዎች ዘንድ በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው። ከእግዱ አላማ አንስቶ እስከተደረጉ ዝግጅቶች፣ እንዲሁም የአስተዳደሩ ስልጣን ባሉና በተያያዙ ጉዳዮች ውይይቶች ቀጥለዋል።
ረቂቅ ህጉ በአሁኑ ወቅት ለካቢኔ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን የከተማ አስተዳደሩ ብቻውን መወሰንም ስለማይችል ባለድርሻ አካላት በተለይም የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስተያየት እንዲሰጡበትም እየተደረገ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ፌቨን ተሾመ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ህግ የወሲብ ንግድን የማይከለክል ሲሆን ይህንንም ወንጀል ለማድረግ ጉዳዩ የሚመለከተው የከተማ አስተዳደሩን ሳይሆን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን እንደሆነ የህግ ባለሙያ፣ አማካሪና የስርአተ ፆታ መብት ተሟጋቿ ሰብለ አሰፋ ትናገራለች።
የበርካታ ሃገራት ልምዶች ሲታይም የወሲብ ንግድን ህገወጥ ለማድረግ የሚጠቀሙት የወንጀል ህጉን ሲሆን ይህንንም ኃላፊነት የተሰጠው ማእከላዊው መንግሥት ሲሆን በኢትዮጵያም የወሲብ ንግድን ወንጀል ማድረግ የሚቻለው በወንጀል ህጉ መሰረት ሲሆን ይህም ስልጣን የተሰጠው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሆነም ታስረዳለች።
"ስልጣኑ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰጠበት ምክንያት እንደራሴዎቹ የብዙኃኑ ተወካይ ናቸው። ማህበረሰቡን ያማከለና በጥናት የተመሰረተ ህግ ነው የሚያወጡት የሚል ግንዛቤ ስላለ ነው" ትላለች።

ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የወሲብ ንግድን የሚያግድ ህግ ይውጣ ቢባል እንኳን በዘፈቀደ ሳይሆን በበርካታ ጥናቶች ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥታ የምትናገረው ጉዳይ ነው።
የወሲብ ንግድን መከልከል ጉዳይ ሲነሳ ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ የምትናገረው ሰብለ በተለይም የወንጀል ህጉ በ1997ዓ.ም ሲሻሻል የወሲብ ንግድና ፅንስ ማቋረጥን የመከልከል ጉዳይ በጣም አነጋጋሪ ሁኔታም እንደነበር ትጠቅሳለች።
በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ፈቅደው የሚገቡበት ባለመሆኑ ወደዛ የሚመራቸው ማህበራዊ ችግሮች ባልተፈቱበት ሁኔታ ድርጊቱን ህገወጥ ማድረጉ "ከህመሙ ይልቅ የህመሙ ምልክት ላይ ማተኮር"፤ ከዚህም በተጨማሪ ሰፋ ያለውን የፖሊሲ ጉዳይ እልባት ሳያገኝና ሴቶቹን ወደዛ የሚገፋፋቸውን ውስብስብ ነገሮች መፍትሔ ሳይሰጥና ተገቢውን የማብቃት ስራ ሳይሰራ ዝም ብሎ ማገድ ትክክል አለመሆኑ ግንዛቤ ተወስዶበት በቂ ጥናት ተሰርቶ ህጋዊ እንዲሆን መደረጉንም ትናገራለች።
በወቅቱም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንን ነገር በአግባቡ እንደተመለከተውና ጉዳዩ ይመለከተኛል የሚሉ ባለድርሻ አካላት የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም የሴቶች መብት ተሟጋቾች ጥናት የተሳተፉበት ጥናት መቅረቡን ታስረዳለች። ከዚህም በተጨማሪ በየከተማው ውይይት ተደርጎ ባለው የሃገሪቷ ሁኔታ የሚሻለው ህጋዊ አድርጎ መቀጠል ነው በሚል ተወስኗል ትላለች።
"የከተማ አስተዳደሩ በራሱ ይህንን እከላከላለሁ ሲል ወንጀል እያደረገው ነው ያንን ለማድረግ ስልጣኑ የለውም። ስልጣኑ ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው" ትላለች።
በወሲብ ንግድ ላይ መሰማራት ሴቶቹ መርጠው ይገቡበታል ተብሎ የሚታሰብ ባለመሆኑ ለጎዳና ልጆች እንደታሰበው ለሴቶቹም የገቢ ማግኚያ መንገድ መቀየስ ሲገባው ይህ አለመሆኑ "በጣም አደገኛ አካሄድ ነው፤ የሴቶቹን መብት እየተጋፋ ነው" በማለት ታስረዳለች።
በተደጋጋሚ የፀጥታ ኃይሉ ጎዳና ላይ በወሲብ ንግድ የተሰማሩትን "የሕግ አግባብ" ሳይኖር ለመከልከል እርምጃ መውሰዱን በመጥቀስ አንዳንዶች ትችት ያቀርባሉ።
አሁን ደግሞ መንግሥት ህግ አርቅቆ ለፀጥታ ኃይሉ የማስከበር ኃላፊነቱን የሚሰጥ ከሆነ እነዚህን ተጋላጭ የማህበረሰቡ አባላት ላይ ተገቢ ያልሆነ ኃይል እንዲጠቀሙ በር ይከፍታል የሚሉም አልታጡም።
ለሰብለም ክልከላው ሲደረግ አፈፃፀሙ እንዴት ነው የሚለው ጥያቄ ከበድ ያለ ሊሆን እንደሚችል ትናገራለች። በረቂቅ ህጉ መሰረት የጎዳና ወሲብ ንግድን ለመከላከከል ቅጣጡ ተፈፃሚ የሚሆነው በንግዱ ላይ የተሰማሩት ሴቶች ናቸው።
"የከተማ አስተዳደሩ ፖሊሶችን እየላከ ጎዳና ላይ ያሉ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሴቶችን ከሆነ ኢላማ የሚያደርገው ይሄ ክልከላ ሳይሆን አላማው ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ይህ ከሆነም አፈፃፀሙም ከባድ ነው፤ ለከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የፆታዊ ጥቃት ለመሳሰሉት የሚዳርግ ነው፤ እንደ ወንጀለኛም እንዲቆጠሩ ይዳርጋል። "ትላለች።
ሰብለ እንደምትለው የወሲብን ንግድ ህገ መንግስቱ ስለማይከለክለው በዚያ መሰረት ወንጀል ተደርጎ አልተቆጠረም ማለት ይህ አንድ የስራ መስክ ሊሰማሩበት የሚገባ ጉዳይ ሲሆን መከልከል ደግሞ የሴቶቹን ህገ መንግሥታዊ መብት የሚጣረስ ነው ትላለች።
"ይህ ኢ-ህገ መንግሥታዊ ነው። ህገ መንግሥቱም ስለማይከለክለው እንደ አንድ የገቢ ማግኛ የኢኮኖሚ መስክ የመምረጥ ህገ መንግሥታዊ መብት አላቸው። የከተማ አስተዳደሩም የመከልከል መብት የለውም" የምትለው ሰብለ የከተማ አስተዳደሩ በከፍተኛ ሁኔታ እንደገና ሊያጤነው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አስተያየቷን ሰጥታለች።
ረቂቁ እንዲሁ ከመንግሥት ስለመጣ ብቻ መጫን ሳይሆን ከህብረተሰቡ ጋር ለመተማመን እየተሰራ መሆኑንና ከዚያ በኋላም ወደ ምክር ቤት ተልኮ አዋጁ ሥራ ላይ እንደሚውል የሚናገሩት ፌቨን ተሾመ ናቸው።
የጎዳን ልመናን በተመለከተ አምራች ኃይሉ ወደ ሥራ እንዲገባና በተለይም ለጎዳና ተዳዳሪዎቹ ከዚህ ህይወት እንዲወጡም በዘላቂነት ማቋቋም የሕጉ አላማ እንደሆነ ገልፀዋል።

እንደ ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ከሆነ በአሁኑ ወቅት አስተዳደሩ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለማገዝ የራሱን 'ሶሻል ፈንድ' አቋቁሞ እየሰራ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ማህበረሰቡ በተናጠል የሚሰጠውን ገንዘብ ተቋማዊ አሰራር ዘርግቶ በዚያ መንገድ እርዳታው እንዲገለስና ፕሮጀክቶችም ተቀርፀው እነሱ የሚጠቀሙበት መንገድ ተቀይሷል ይላሉ።
"የማይከለከል ከሆነ አስቸጋሪ ነው። ልመና እንደባህልም እየተወሰደ ስለሆነ ከዚህ ህይወት መውጣት ያለመፈለግ አዝማሚያዎች አሉ። በርካታ ወጣቶችም ከተለያዩ ከተሞች ወደ አዲስ አበባ ለልመና ሲባል ይመጣሉ። ይህ እርምጃም ነገ ተረካቢ ትውልድ ከማፍራት አንፃር ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብሎ አስተዳደሩ ያምናል" ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አዲስ አበባ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ከመሆኗም አንፃር ለሃገር ገጽታም መታሰብ እንዳለበትም አስረድተዋል።
ከዚህም አንፃር የጎዳና ላይ ልመና ብቻ ሳይሆን የጎዳና ላይ የወሲብ ንግድ ልቅ መሆኑ አግባብ እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ በተለይም የወሲብ ንግድ ከባህል አንጻር እንዲሁም ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ አፅንኦት በመስጠት ተናግረዋል።

"የወሲብ ንግድ ኢትዮጵያዊ እሴት ስላልሆነ፤ እንደ ዋና ከተማ ዜጎች ከውጭ ሃገር የሚመጡባት ለሃገሪቷም መውጪያና መግቢያ በር እንደመሆኗ መጠን እንደዚህ አይነት ተግባር ያልተበራከቱባት ብሎም የሌሉባት ከተማ ለማድረግ ታቅዷል" ይላሉ።
ከዚህም በተጨማሪ የወሲብ ንግድ መበራከት በከተማዋ ያለውን የኤች አይ ቪ ስርጭትን እንደሚጨምረው ጥናቶች ስለሚጠቁሙ ይህንንም ለመከላከል የወሲብ ንግድን መቆጣጠርም እንደሚያግዝ ያስረዳሉ።

በዚህ ጉዳይ ላይ የተጠየቁት ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ረቂቅ ህጉ ላይ ከልመና ጋር በተገናኘ ተጠያቂ የሚሆነው ወይም የሚቀጣው ሰጪው እንደሆነ ጠቅሰው የጎዳና ተዳዳሪዎችንም የማገገሚያ ማዕከል ተዘጋጅቶ ወደዚያ ገብተው የሥነ ልቦና ትምህርት፣ የሞያ ስልጠና እንዲያገኙና ወደ ሥራ እንዲገቡ የማቋቋም ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል።
"በመቆጣጠርና በመከልከል የሚፈለገው ላይ ስለማይደረስ፤ ከማስገደዱ በላይ የግንዛቤ ሥራ መቅደም አለበት። በተለይ የሃይማኖት ተቋማት እዚህ ላይ ከፍተኛ ሚና ስላላለቸው መተማመን ላይ መደረስ አለበት" ይላሉ አክለውም።
"በዚህ ሁኔታ የሐይማኖት አባቶች ትብብር ካላደረጉ የሚሳካ ስላልሆነ፤ ተቋማትን ማወያየትና የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ውይይቶች ይደረጋሉ። ከህብረተሰቡ ጋር መተማመን ከተደረሰ በኋላ ነው ወደ ማፅደቁ የምንሄደው" ብለዋል።
የወሲብ ንግድን በተመለከተ ረቂቅ ሕጉ ራሳቸው በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩትን ለመቅጣት ያሰበ ሲሆን፤ ከዚያም በተጨማሪ የምክር አገልግሎት የመስጠት ከሚገኙበት አካባቢ እንዲነሱና ህይወታቸውን እንዲቀይሩ የማድረግ ሥራ ይሰራል ብለዋል።
በቀድሞ የወሲብ ንግድ ትተዳደር የነበረችው ምፅዋ የረቂቅ ሕጉን ሐሳብ ደግፋ "በጣም የሚያስከፋ ሥራ ነው። ግን ለእነዚህ ሰዎች ምንድን ነው የሚደረግላቸው? ብዙዎች የልጆች እናትና የቤተሰብ አስተዳዳሪ እንደመሆናቸው መጠን መንግሥት ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል" በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች።
"እየተገረፉ፣ እየታሰሩ፤ እርቃናቸውን ብርድ ላይ ብዙ ነገር እየደረሰባቸው ነው እያሳለፉ ያሉት" የምትለው ምፅዋ፤ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች የፀጥታ ኃይሎች በደል እንደሚያደርሱባቸው ጠቅሳ መስተካከል እንዳለበትም ትናገራለች።

እንዲህ አይነት ሕግ ሲረቅ መንግሥት የሚጠበቅበትን ማከናወን አለበትና በወሲብ ንግድ ተሰማርተው የነበሩ ግለሰቦች ምንም አይነት እርዳታ እንደማይደረግላቸውም ትጠቅሳለች።
"እኛ አሁን በቀበሌ ደረጃና የተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች ያውቁናል። ግን ምንም የሚደረግልን ነገር የለም፤ እንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ እያለን እርዱን ብለን የምናለቅስበት ጊዜ ነበር፤ በቅድሚያ ማደራጀትና ማስተማር ያስፈልጋል" ትላለች።
ከዚህም በተጨማሪ ብዙዎቹ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሰዎች በሱስ የተጠቁ ከመሆናቸው አንፃር ያንን ነገር ለማስወገድ መጀመሪያ መሰራት እንዳለበትና የትራንስፖርትና የእለት ጉሮሯቸውን ለመሸፈን የሚያስችል ድጎማም ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ተግባር እንደሆነ አበክራ ትናገራለች።
"ረቂቅ ሕጉ ጥሩ ነው፤ ነገር ግን መጀመሪያ የህብረተሰቡን ችግር መረዳት አለበት። እኛም የወጣነው በፈታኝ ሁኔታ ነው" ትላለች።
ለረዥም ዓመታት በወሲብ ንግድ ተሰማርታ የቆየችው ሐይማኖት ከምፅዋ የተለየ ሀሳብ የላትም። እሷም በሁኔታው ተደስታ ነገር ግን የድጋፍ ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ታስረዳለች።
መንግሥት ትኩረት አድርጎ በእውቀት፣ በትምህርት፣ እንዲሁም ሰርተው የሚበሉበትንና የሚደራጁበትን ቦታ በማሰብ ድጋፍ ሊሰጥ እንደሚገባ ገልፃለች።
"ድጋፍ ከሌለ ከዚያ ህይወት መላቀቅ እጅግ በጣም ከባድ ስለሆነ፤ እኔ ራሱ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ነው መውጣት የቻልኩት፤ እኔ ራሱ በድጋፍ ሰጪ ድርጅት ነው መውጣት የቻልኩት" ብላለች።
መንግሥት ይህንን ሕግ ሲያፀድቅ ዝግጅት አድርጎ ሊሆን እንደሚችልም ግምቷን አስቀምጣለች።
"በአንዴ አቁሙ የሚል ነገር የለም። ምን ሊበሉ፣ ምን ሊጠጡስ፤ ቤት ኪራዩስ፤ ቦታ፣ ትምህርት፣ ገንዘብ አዘጋጅቷል ብዬ አስባለሁ። ካለዚያ ግን የታሰበውን ውጤት አያመጣም። ዝግጅት ሳይደረግ ያፀድቁታል ብዬ አላስብም" ትላለች።
በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ግለሰቦች ከተጠቃሚው እስከ ፖሊስ ድረስ ግፍ እንደሚደርስባቸውም ትናገራለች።
"ማንኛውም አይነት ችግር ቢደርስ ተሰሚነት የላቸውም፤ በዳይ እኛ ተደርገን ነው የምንታየው። ስንደበድብ፣ ጫካ ስንጣል፤ በጣም ራቅ ካለ ስፍራ ከአዲስ አበባ ውጪ ይጥሉ ነበር፤ ይህ ሁኔታ በአሁኑ አሰራር ይቀየራል" ብላ ታስባለች።

እውን ኢትዮጵያ በአንድ ቀን 350 ሚሊዮን ችግኞች ተክላለች?


የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ ነበር ኢትዮጵያ '350 ሚሊዮን ያህል ዛፎች ተክያለሁ፤ የዓለም ሪከርድም ሰብሪያለሁ' ስትል ያሳወቀችው። ግን ይህ መረጃ ምን ያህል እውነት ነው? የቢቢሲ 'ሪያሊቲ ቼክ' ቁጥሮችን አገላብጦ ያገኘው መረጃ እነሆ።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የደን መመናመንን ለመከላከል አርባ ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ችግኝ የመትከል ዕቅድ ይዘው የተነሱት በቅርቡ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከሚሊኒዬም በፊት ከነበረው 35 በመቶ ወደ 4 በመቶ ዝቅ ብሏል ይላል።
ሐምሌ 22/2011 ዓ.ም. ኢትዮጵያ በ12 ሰዓታት ውስጥ 200 ሚሊዮን ዛፎችን ለመትከል ቆርጣ ተነሳች። በቀኑ መገባደጃ ላይ የፈጠራ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ ሃገሪቱ 350 ሚሊዮን ዛፎች መትከሏን አሳወቁ።

መንግሥት እንደሚለው ለበጎ ፈቃደኞች የሚተከሉት ዛፎች መታደል የጀመሩት ከሶስት ቀናት በፊት ጀምሮ ነበር። በርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዕለተ ሰኞ ሐምሌ 22/2011 ዓ.ም መደበኛ ሥራቸውን በመተው ዛፍ በመትከል እንዲውሉ ተደረገ።
የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች ጨምሮ የአፍሪቃ ሕብረት እና ሌሎች መንግሥታዊ ያለሆኑ ድርጅቶችም በዛፍ መትከሉ ላይ በፈቃደኝነት ተሳተፉ።
በርካቶቹ ችግኞች ሃገር በቀል መሆናቸውም ተነግሯል፤ እንደ አቮካዶ የመሳሰሉ የፍራፍሬ ዛፎችም መትከላቸው ታውቋል።
በጎ ፈቃደኞቹ የሚተክሉትን ዛፎች ይቆጥሩ ዘንድ በየቦታው ሰዎች መመደባቸውም በዛፍ ተከላው ቀን ተዘገበ።
አሁን ጥያቄው ይህን ያህል ዛፎች በአንድ ቀን መትከል ይቻላል ወይ የሚለው ነው። የዘርፉ ባለሙያዎች 'መቻሉን ይቻላል፤ ነገር ግን በጣም ትልቅ ዝግጅት ይጠይቃል' ይላሉ።
«እርግጥ ነው ይቻላል። ቢሆንም በጣም ዘለግ ያለ ዝግጅት ይሻል» ይላሉ በተባበሩት መንሥታት ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያ የሆኑት ቲም ክሪስቶፈርሰን።
ኤኤፍፒ ለተሰኘው ዜና ወኪል ሃሳባቸውን የሰጡት ቲም አንድ በጎ ፈቃደኛ በቀን 100 ዛፎች መትከል ይችላል ይላሉ።
ጊነስ ዎርልድ ሪከርድስ፡ «ስለተተከሉት ዛፎች ከኢትዮጵያ የደረሰን መረጃ የለም»
ከ23 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በዛፍ ተከላው ላይ እንደተሳተፉ የብሔራዊ ደን ልማት ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ተፈራ መንግሥቱ ይናገራሉ።
ስለዚህ 23 ሚሊዮን ሰዎች በቀን 100 ያህል ዛፎች ከተከሉ ቁጥሩ ከ350 ሚሊዮን በላይ ሊሆን እንደሚችል አያጠያይቅም። ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው ምን ያህል ዛፍ እንደተከለ በውል የሚታወቅ ቁጥር እንደሌለ ተገልጿል።

350 ሚሊዮን ዛፎችን ለመትከል ቢያንስ 346 ሺህ 648 ሄክታር መሬት ይጠይቃል። ነገር ግን ምን ያህል ሄክታር መሬት ዛፎችን ለመትከል ጥቅም ላይ እንደዋለም መረጃ የለም።
አንድ የመንግሥት መሠሪያ ቤት ሠራተኛ መሥሪያ ቤታቸው 10 ሺህ ዛፎችን እንዲተክልና ወጭውንም እንዲሸፍን እንደታዘዘ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
የበጀት እጥረት ስላጋጠማቸው አምስት ሺህ ዛፎችን ብቻ ነው የተከሉት።
5 ሺህ ዛፎችን ተክለው ነገር ግን 10 ሺህ የሚል ቁጥር ገቢ ማድረጋቸውን ነው ለቢቢሲ አስረድተዋል።
አልፎም አንዳንድ ቦታዎች ላይ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ተተከሉ ያሏቸው ዛፎች ቁጥር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረ-ገፅ ላይ ከሰፈረው ጋር ልዩነት እንደታየበት ቢቢሲ ታዝቧል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጠን የጠየቅነው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አላገኘም።
የተባበሩት መንግሥታት ኢትዮጵያ ለዛፍ ተከላው አመስግኖ ጎረቤት ሃገራትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስቧል። ቢሆንም የዛፎቹ ቁጥር ጉዳይ ከበርካታ ወገኖች ትችት አላጣም።
«እኔ በበኩሌ ይህን ያህል ዛፍ ተክለናል ብዬ አላምንም» ይላሉ የኢዜማ ፓርቲ ቃል-አቀባዩ ዘላለም ወርቅአገኘሁ።
ተቺዎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግሥታቸው የገጠመው ብሔር ተኮር እክልን የዛፍ ተከላው ቅስቀሳውን ሽፋን በማድረግ እያደባበሱት ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።

እውን ሪከርድ ተሰብሯል?

የዓለም ድንቃድንቅ ድርጊቶች መዝጋቢው ጊነስ ዎርልድ ሪከርድስ በበኩሉ የዛፍ ተከላ ሬከርድ የመስበር ሙከራውን ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ መንግሥት የደረሰው ምንም ዓይነት ማመልከቻ እንደሌለ ይናገራል።
«እኛ ምንም ዓይነት ሪከርድ ሲሰበር በንቃት እንከታተላለን። የዝግጅቱ አስተናባሪዎች ደግሞ ሪከርዱ ሲሰበር እንድንመዝግብላቸው ማመልከቻ እንዲያስገቡ እንመክራለን» ይላሉ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጄሲካ ዳውስ።
ኢትዮጵያ እውን ሪከርዱን ሰብራ ከሆነ ምን ያህል ሰዎች እንደተሳተፉ፣ የት እና መቼ እንደተከናወነ የሚገልፅ ውል ያለው መረጃ መስጠት ይኖርባታል። አልፎም ሁለት ገለልተኛ ምስክሮች ሪከርዱ መሰበሩን በሥፍራው ተገኝተው ማረጋገጥ ይጠብቅባቸዋል።
በአሁኑ ወቅት ዛፍ በመትከል የዓለም ሪከርድ ይዛ ያለችው ህንድ ናት።
በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ካናዳዊው ኬን ቻፕሊን በአንድ ቀን 15 ሺህ 170 ዛፎችን በመትከል የዓለም ሪከርድ ይዞ ይገኛል።

ብሩክ ዘውዱ፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት አስመዝጋቢ

ብሩክ ዘውዱ ከእናቱ ጋር
በዘንድሮው ዓመት የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ሃገር አቀፍ ፈተና የተመዘገበው ከፍተኛው ውጤት 645 ሲሆን፤ ይህ ውጤትም በአማራ ክልል መመዝገቡን የትምህርት ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃረጓ ማሞ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ውጤቱን ያስመዘገበውም ብሩክ ዘውዱ የተባለ በባህርዳር የአየለች ደገፉ መታሰቢያ (ኃይሌ) ትምህርት ቤት ተማሪ መሆኑን ሰምተናል። ስላስመዘገበው ውጤት ለማነጋገር ወደ ብሩክ ስልክ መታን። ምን ተሰማህ አልነው።
ብሩክ ውጤቱን እንደሚያመጣ ይጠብቅ ስለነበር ብዙም አልደነቀውም። "ደስ ብሎኛል" አለን በአገር አቀፍ ደረጃ ግን ከፍተኛ ውጤት አስመዘግባለሁ ብሎ እንዳላሰበ በመግለፅ።

እርሱ እንደሚለው በትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚያስተምሩ መምህራን ብቃት ፣ በትርፍ ጊዜው [ቅዳሜና እሁድ] መምህራን የሚሰጡትን ማጠናከሪያ ትምህርት መከታተሉ እና የራሱ የንባብ ልምድ ላስመዘገበው ከፍተኛ ውጤት አስተዋፅኦ አድርጎለታል።
"ሁሉም ሰው የራሱ ሆነ የጥናት ስልት አለው፤ የእኔ የንባብ ስልት ለሌላው ላይፈይድ ይችላል" የሚለው ብሩክ በፕሮግራም፣ ብዙም ሳይጨናነቅ እና ደስ እያለው እንደሚያነብ ከዚያም ፈተናን ተረጋግቶ የመፈተን ልምድ እንዳለው ገልፆልናል።

ብሩክ ወላጅ አባቱን በሞት ያጣው የ10 ዓመት ታዳጊ እያለ ነበር። ከዚያም በኋላ እናታቸው የእናትንም የአባትንም ቦታ ተክተው እነርሱን ማሳደግ ያዙ።
ታዲያ እርሱም ሆነ እህትና ወንድሙ በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እናታቸው የሚያደርጉላቸው ድጋፍና ክትትል ከፍተኛ እንደነበር ሳይጠቅስ አላለፈም።
"እናቴ ብዙም አንብቡ ብላ አትጎተጉተንም ፤ እኛ በፈለግንበት ሰዓት አምነንበት ነው እንድናነብ የምታደርገው" ይላል።

ብሩክ እንደሚለው ታላቅ እህቱም የዛሬ ሦስት ዓመት እርሱ በተማረበት አየለች መታሰቢያ (ኃይሌ) ትምህርት ቤት፤ በትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ውጤት እንዳስመዘገበች ያስታውሳል።
የእርሱ ታናሽ ወንድምም ቢሆን የዋዛ አይደለም፤ ጥሩ የትምህርት አቀባበል አለው።
ብሩክ ለጊዜው የትኛውን የትምህርት ዘርፍ ሊያጠና እንደሚችል ውሳኔ አላሳለፈም። በጤና ዘርፍ፣ በኮምፒዩተር ሶፍት ዌር ኢንጅነሪንግ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የመማር ፍላጎት ቢኖረውም ወደ ሕክምናው ዘርፍ ሳያደላ እንደማይቀር ግን ይናገራል።
ብሩክ ወደፊት አንድ ግብ ብቻ አስቀምጦ መጓዙ አያዋጣም ከሚሉት ወገኖች ነው። ወደፊት የተሻለ ነገር ፍለጋ በተለያዩ ዘርፎች እንደሚታትር ነግሮናል።
"ደስታ ያሰክራል፤ ደስታ እንባ እንባ ይላል" ሲሉ በልጃቸው ውጤት እንደተደሰቱ የገለፁልን ደግሞ እናቱ ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ጥላሁን ናቸው።
የልጃቸውን መልካም ውጤት ዜና የሰሙትም ከራሱ ከልጃቸው ነበር።
"ደውሎ፤ እንዳትደነግጭ፤ ስድስት መቶ ምናምን አምጥቻለሁ ብሎ ስልኩን ዘጋው" ይላሉ የስልክ ልውውጣቸውን ሲያስታውሱ። ከዚያ በኋላ ግን ጓደኛው ደውሎ ብሩክ ከኢትዮጵያ ተፈታኞች አንደኛ እንደወጣ ሲነግራቸው ደስታቸውን መቆጣጠር እንዳልቻሉ ይናገራሉ።

በወቅቱ ጓደኛቸው ቤት ነበሩና " እሷን አቅፌ ጮህኩ፤ እሷን አቅፌ አለቀስኩ፣ ተንበረከኩ...ፈጣሪን አመሰገንኩ" ይላሉ።
ወ/ሮ ኤልሳቤት ከ12ኛ ክፍል በላይ በትምህርታቸው አልገፉም- አንድም ውጤት ስላላስመዘገቡ፤ በግልም ለመማር አቅም ስላልነበራቸው፤ በሌላም በኩል በትዳር ኃላፊነት ውስጥ ስለገቡ።
የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ባለቤታቸው በሞት ከተለዩዋቸው በኋላ 'ልጆቼ ናቸው ሥራዎቼ' ብለው የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ እንደሆነ ያስረዳሉ።
"እናንተ የምታስመዘግቡት ውጤት ለእኔ ደመወዜ ነው እያልኩ ስለማሳድጋቸው ተግተው ነው የሚሰሩት " ይላሉ- ወ/ሮ ኤልሳቤት። መልካም ውጤት ሲያመጡም ደመወዝ እንደከፈሉኝ ነው የሚሰማቸው ሲሉ ከልጆቻቸው ጋር ያላቸውን ተግባቦት ይገልፃሉ፤ እንዲያጠኑ ብዙም ጫና አያሳድሩባቸውም።
"በትምህርት ብቻ ሳይሆን ጥሩ ዜጋ እንዲሆኑ ፤ ገንዘብ በምንም መንገድ ይገኛል፤ መማር ስብዕናን ያንጻል፤ ስብዕናን ያሟላ ሰው እንድትሆኑ እፈልጋለሁ እያልኩ ነው ያሳደግኳቸው" ይላሉ።
ለእርሳቸው ብቻ ሳይሆን ለአገር የሚጠቅሙ ዜጎች እንዲሆኑ እንደሚለፉ ይናገራሉ።

"የምንኖረው ሁለት ክፍል ቤቶችን እያከራየን ነው፤ ለልጆቼ የማወርሳቸው ምንም ሀብት የለኝም" የሚሉት ወ/ሮ ኤልሳቤት እነርሱ ላይ ፍሬያቸውን ማየት ይፈልጋሉ።
ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ስለ ብሩክ ሲናገሩም "ብሩክ በተሰማራበት ሁሉ ውጤታማ መሆን የሚችል ልጅ ነው፤ የሞከረው ሁሉ ይሳካል"ሲሉ ብዙ ጊዜ ናሳ የመሄድ ምኞት እንዳለው ገልፀውልናል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ለመውሰድ ከተመዘገቡት 322 ሺህ 717 ተማሪዎች መካከል 319,264 የሚሆኑት ፈተናውን መውሰዳቸውን የትምህርት ሚኒስቴር በይፋዊ ገፁ አስታውቋል።
ፈተና ላይ ከተቀመጡት ውስጥም 59 ተማሪዎች ከ600 በላይ ውጤት ሲያመጡ 48.59 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከ350 በላይ ውጤት አምጥተዋል።
በዘንድሮው ዓመት በፈተናው ወቅት በተፈጸመ የደንብ ጥሰት የ68 ተማሪዎች ውጤት መሰረዙም ተገልጿል።
በመጨረሻም...
አፕቲቲዩድ የትምህርት ዘርፍ የበርካታ ተማሪዎች ውጤት ዝቅ ማለቱ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው። ለብሩክ ይህንኑ ጥያቄ ሰንዝረንለት ነበር። በእርግጥ እርሱ"86 አካባቢ አስመዝግቤያለሁ"ይላል።
ቢሆንም ግን ምክንያቱን ሳንጠይቀው አላለፍንም። እርሱም የትምህርቱ ዘርፍ የተማሪዎችን ጠቅላላ እውቀት ለመመዘን እንደሚሰጥ ጠቅሶ "ትምህርቱ እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ አይሰጥም፤ መምህራን ናቸው በበጎ ፈቃደኝነት እገዛ የሚያደርጉት፤ በዚያ ምክንያት ይሆናል" ሲል የግል አስተያየቱን አካፍሎናል።

በፓሪስ ዝግ ያለው አስተናጋጅ በጥይት ተገደለ



በፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስ አካባቢ በምትገኝ ቦታ ሳንድዊች እንዲያመጣ የታዘዘ አስተናጋጅ በፍጥነት አላመጣም በሚል የተናደደ ደንበኛ በጥይት ተኩሶ ገድሎታል።
ግድያው የተከሰተው አርብ እለት በምስራቃዊዋ ፓሪስ በምትገኘው ኖይሲ ለ ግራንድ ፣ ፒዛና ሳንድዊች መሸጫ ቦታ ነው።
ፖሊስ እንዳሳወቀው ተጠርጣሪው ወዲያው ከአካባቢው ተሰውሯልም ብሏል።

የአምቡላንስ ሰራተኞች ጀርባው አካባቢ በጥይት የተመታውን የ28 አመቱን አስተናጋጅ ለማዳን ጥረት ቢያደርጉም ቦታው ላይ ህይወቱ አልፏል ተብሏል።
የአስተናጋጁ የስራ ባልደረቦች እንደገለፁት ትእዛዙን ለማስተናገድ የወሰደበት ጊዜ ረዘም ያለ በመሆኑ ደንበኛው በከፍተኛ ሁኔታ ተበሳጭቶ ነበር ብለዋል።

ግድያው የሬስቶራንቱን ሰራተኞችን እንዲሁም የአካበባቢውን ነዋሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ አስደንግጧል።
"በጣም አሳዛኝ ክስተት ነው። ከጥቂት ወራት በፊት የተከፈተችው ይህች ሬስቶራንት ፀጥ ረጭ ያለችና ምንም ችግር የሌለባት ነች" በማለት አንዲት የ29 አመት ግለሰብ ለፈረንሳይ ሚዲያ ተናግራለች።

አንዳንድ ነዋሪዎች በበኩላቸው በአካባቢው የወንጀል ተግባራት እየተበራከቱ ሲሆን በተለይም ከአደንዛዥ እፅ ዝውውርና ከመጠጥ ጋር ተያይዞ ችግሮች እንዳሉም ተናግረዋል።

አይፈተሹም የተባሉ የመከላከያ ሰራዊት መኪናዎች በሕዝብ ተቃውሞ እንዲቆሙ ተደርጓል።

አይፈተሹም የተባሉ የመከላከያ ሰራዊት መኪናዎች በሕዝብ ተቃውሞ እንዲቆሙ ተደርጓል።
********
መተማ ላይ አምስት የመከላከያ መኪናዎች ወደሱዳን ለማለፍ ሲሞክሩ "አንፈተሽም" በማለታቸው ከሕዝቡ ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ በሕዝብ ተቃውሞ እንዲቆሙ ተደርገዋል። የመከላከያ ሰራዊት አባላት "ወደ ዳርፉር እየሄድን ነው" ቢሉም ማለፊያም ሆነ ወደ ዳርፉር የሚሄዱበትን ማስረጃ ማቅረብ አለመቻላቸው ተገልፆአል። የመኪናዎቹ ታርጋዎች እንዳይለዩ በግሪስ የተቀቡ መሆናቸው በሕዝብ ጥርጣሬ መፍጠሩን የአካባቢው ምንጮች ገልፀዋል።
የመከላከያ ሰራዊት አባላት መኪናዎቹ እንዲፈተሹ ባለመፍቀዳቸው ሕዝቡ ኬላ ዘግቶ አስቁሟቸዋል ተብሏል። እስካሁን ባለው ሁኔታ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልም ሕዝቡ ያቀረበው ጥያቄ ትክክል መሆኑን መግለፁ ተነግሯል።

Thursday, August 15, 2019

አፋር ውስጥ የሞተችው እስራኤላዊት የገጠማት ምን ነበር?

አያ ናሚህ


አያ ናሚህ አፋር ክልል ውስጥ ወደሚገኘው የምድራችን ሞቃቱና ዝቅተኛው ደናክል አካባቢ ከሄዱት ስድስት እስራኤላዊያን ተማሪዎችና ሁለት ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዷ ነበረች።
የ22 ዓመቷ ወጣት ቅዳሜ ዕለት ግዙፉ በረሃ ውስጥ ከቡድኑ ተነጥላ መጥፋቷ ከታወቀ በኋላ በተደረገ ፍለጋ ሞታ ተገኝታለች።
አያ ለኢንጂነሪንግ ተማሪዎች በተዘጋጀው የአንድ ወር ስልጠና ላይ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተሳታፊ ለመሆን ነበር ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው።

ተማሪዎቹ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ስልጠናቸውን ሲጨርሱ ስድስቱ እስራኤላዊያን ከሁለት ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ወደ አፋር ክልል በመሄድ የኤርታሌ የእሳተ ገሞራ ሐይቅንና የዳሎል አካባቢን ለመጎብኘት እቅድ አውጥተው ነበር ወደዚያው ያቀኑት።
ከቡድኑ ጋር አብረው ከተጓዙት ሁለት ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዷ የሆነችው ጽዴና አባዲ ለቢቢሲ አንደተናገረችው፤ ወደ ኤርታሌ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ሐሙስ ምሽት አብረው እንደነበሩና አያም "በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደነበረች" ገልጻለች።
"ሁሉም ሰው በጉዞው ተደንቆና ደስተኛ ሆኖ ነበር" ስትል ጽዴና ለቢቢሲ ተናግራለች። ቀጣዩንም ቀን አፍዴራ ሐይቅ ላይ እየዋኙና እየተዝናኑ ማሳለፋቸውን ታስታውሳለች።
ቅዳሜ ጠዋትም አያና ጓደኞቿ ወደ ደናክል ዝቅተኛ ቦታ ደርሰው አካባቢውን በደንብ ለመመልከት እንዲችሉ በአቅራቢያው ወዳለ ኮረብታ አቀኑ።

"ከእሳተ ገሞራው ሐይቅ ከሚወጣው ኬሚካል ከያዘ ሽታና በአካባቢው ካለው ከፍተኛ ሙቀት የተነሳ የተወሰኑት ድካም ስለተሰማቸው ወዳመጣቸው መኪና ሲመለሱ ሌሎቹ ደግሞ ጉዟቸውን እንደቀጠሉ ትናገራለች።
ጽዴና እንዳለችው፤ አያ በድካም ከተመለሱት ተማሪዎች መካከል አንዷ የነበረች ስትሆን፤ ወደ መኪናቸው ስትመለስ የነበረውም ቀድማ ነበር።
በኋላ ላይም አያ እንደጠፋችና በተደረገው ፍለጋም ትሄድበት ከነበረው በሌላ አቅጣጫ ሞታ እንደተገኘች ተናግራለች።
ነገር ግን ሲመለሱ ከነበሩት መካከል የጠፋችው አያ ብቻ እንዳልነበረችም ጽዴና ተናግራለች።
"ሌላኛዋን ጓደኛዬን አግኝቼ እሷን በመከተል ወደ መኪናው እስክደርስ ድረስ እኔም ጠፍቼ ነበር" የምትለው ጽዴና "አካባቢው ተመሳሳይ ከመሆኑ የተነሳ አቅጣጫችንን ለማወቅ አስቸጋሪ ነበር" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ጽዴና አክላም ከእሳተ ገሞራው የሚወጣው ሽታና ያለው ከባድ ሙቀት እንዳሳመማትና "የምትሞት እንደመሰላት" አስታውሳለች።
እስራኤላዊቷ መጥፋቷ ከታወቀ በኋላ የአካባቢው ነዋሪዎችና ፖሊስ ለፍለጋ የተሰማሩ ሲሆን፤ አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያም በኋላ ላይ በፍለጋው ላይ ተሳታፊ ሆኗል።
በፍለጋውም አያ ህይወቷ አልፎ የተገኘች ሲሆን፤ አስክሬኗም ትናንት ዕሁድ በአውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ ተወስዷል።
ጽዴና እንደምትለው፤ አያ በሁሉም ሰው የምትወደድና ተግባቢ ነበረች።
ለእስራኤላዊቷ ሕይወት ማለፍ ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

wanted officials