Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, August 19, 2019

የአዲስ አበባ አስተዳደር የጎዳና ልመናና የወሲብ ንግድን ለማገድ ረቂቅ ህግ ማዘጋጀቱን ተከትሎ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው

ከሰሞኑ የአዲስ አበባ አስተዳደር የጎዳና ልመናና የወሲብ ንግድን ለማገድ ረቂቅ ህግ ማዘጋጀቱን ተከትሎ በብዙዎች ዘንድ በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው። ከእግዱ አላማ አንስቶ እስከተደረጉ ዝግጅቶች፣ እንዲሁም የአስተዳደሩ ስልጣን ባሉና በተያያዙ ጉዳዮች ውይይቶች ቀጥለዋል።
ረቂቅ ህጉ በአሁኑ ወቅት ለካቢኔ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን የከተማ አስተዳደሩ ብቻውን መወሰንም ስለማይችል ባለድርሻ አካላት በተለይም የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስተያየት እንዲሰጡበትም እየተደረገ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ፌቨን ተሾመ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ህግ የወሲብ ንግድን የማይከለክል ሲሆን ይህንንም ወንጀል ለማድረግ ጉዳዩ የሚመለከተው የከተማ አስተዳደሩን ሳይሆን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን እንደሆነ የህግ ባለሙያ፣ አማካሪና የስርአተ ፆታ መብት ተሟጋቿ ሰብለ አሰፋ ትናገራለች።
የበርካታ ሃገራት ልምዶች ሲታይም የወሲብ ንግድን ህገወጥ ለማድረግ የሚጠቀሙት የወንጀል ህጉን ሲሆን ይህንንም ኃላፊነት የተሰጠው ማእከላዊው መንግሥት ሲሆን በኢትዮጵያም የወሲብ ንግድን ወንጀል ማድረግ የሚቻለው በወንጀል ህጉ መሰረት ሲሆን ይህም ስልጣን የተሰጠው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሆነም ታስረዳለች።
"ስልጣኑ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰጠበት ምክንያት እንደራሴዎቹ የብዙኃኑ ተወካይ ናቸው። ማህበረሰቡን ያማከለና በጥናት የተመሰረተ ህግ ነው የሚያወጡት የሚል ግንዛቤ ስላለ ነው" ትላለች።

ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የወሲብ ንግድን የሚያግድ ህግ ይውጣ ቢባል እንኳን በዘፈቀደ ሳይሆን በበርካታ ጥናቶች ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥታ የምትናገረው ጉዳይ ነው።
የወሲብ ንግድን መከልከል ጉዳይ ሲነሳ ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ የምትናገረው ሰብለ በተለይም የወንጀል ህጉ በ1997ዓ.ም ሲሻሻል የወሲብ ንግድና ፅንስ ማቋረጥን የመከልከል ጉዳይ በጣም አነጋጋሪ ሁኔታም እንደነበር ትጠቅሳለች።
በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ፈቅደው የሚገቡበት ባለመሆኑ ወደዛ የሚመራቸው ማህበራዊ ችግሮች ባልተፈቱበት ሁኔታ ድርጊቱን ህገወጥ ማድረጉ "ከህመሙ ይልቅ የህመሙ ምልክት ላይ ማተኮር"፤ ከዚህም በተጨማሪ ሰፋ ያለውን የፖሊሲ ጉዳይ እልባት ሳያገኝና ሴቶቹን ወደዛ የሚገፋፋቸውን ውስብስብ ነገሮች መፍትሔ ሳይሰጥና ተገቢውን የማብቃት ስራ ሳይሰራ ዝም ብሎ ማገድ ትክክል አለመሆኑ ግንዛቤ ተወስዶበት በቂ ጥናት ተሰርቶ ህጋዊ እንዲሆን መደረጉንም ትናገራለች።
በወቅቱም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንን ነገር በአግባቡ እንደተመለከተውና ጉዳዩ ይመለከተኛል የሚሉ ባለድርሻ አካላት የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም የሴቶች መብት ተሟጋቾች ጥናት የተሳተፉበት ጥናት መቅረቡን ታስረዳለች። ከዚህም በተጨማሪ በየከተማው ውይይት ተደርጎ ባለው የሃገሪቷ ሁኔታ የሚሻለው ህጋዊ አድርጎ መቀጠል ነው በሚል ተወስኗል ትላለች።
"የከተማ አስተዳደሩ በራሱ ይህንን እከላከላለሁ ሲል ወንጀል እያደረገው ነው ያንን ለማድረግ ስልጣኑ የለውም። ስልጣኑ ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው" ትላለች።
በወሲብ ንግድ ላይ መሰማራት ሴቶቹ መርጠው ይገቡበታል ተብሎ የሚታሰብ ባለመሆኑ ለጎዳና ልጆች እንደታሰበው ለሴቶቹም የገቢ ማግኚያ መንገድ መቀየስ ሲገባው ይህ አለመሆኑ "በጣም አደገኛ አካሄድ ነው፤ የሴቶቹን መብት እየተጋፋ ነው" በማለት ታስረዳለች።
በተደጋጋሚ የፀጥታ ኃይሉ ጎዳና ላይ በወሲብ ንግድ የተሰማሩትን "የሕግ አግባብ" ሳይኖር ለመከልከል እርምጃ መውሰዱን በመጥቀስ አንዳንዶች ትችት ያቀርባሉ።
አሁን ደግሞ መንግሥት ህግ አርቅቆ ለፀጥታ ኃይሉ የማስከበር ኃላፊነቱን የሚሰጥ ከሆነ እነዚህን ተጋላጭ የማህበረሰቡ አባላት ላይ ተገቢ ያልሆነ ኃይል እንዲጠቀሙ በር ይከፍታል የሚሉም አልታጡም።
ለሰብለም ክልከላው ሲደረግ አፈፃፀሙ እንዴት ነው የሚለው ጥያቄ ከበድ ያለ ሊሆን እንደሚችል ትናገራለች። በረቂቅ ህጉ መሰረት የጎዳና ወሲብ ንግድን ለመከላከከል ቅጣጡ ተፈፃሚ የሚሆነው በንግዱ ላይ የተሰማሩት ሴቶች ናቸው።
"የከተማ አስተዳደሩ ፖሊሶችን እየላከ ጎዳና ላይ ያሉ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሴቶችን ከሆነ ኢላማ የሚያደርገው ይሄ ክልከላ ሳይሆን አላማው ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ይህ ከሆነም አፈፃፀሙም ከባድ ነው፤ ለከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የፆታዊ ጥቃት ለመሳሰሉት የሚዳርግ ነው፤ እንደ ወንጀለኛም እንዲቆጠሩ ይዳርጋል። "ትላለች።
ሰብለ እንደምትለው የወሲብን ንግድ ህገ መንግስቱ ስለማይከለክለው በዚያ መሰረት ወንጀል ተደርጎ አልተቆጠረም ማለት ይህ አንድ የስራ መስክ ሊሰማሩበት የሚገባ ጉዳይ ሲሆን መከልከል ደግሞ የሴቶቹን ህገ መንግሥታዊ መብት የሚጣረስ ነው ትላለች።
"ይህ ኢ-ህገ መንግሥታዊ ነው። ህገ መንግሥቱም ስለማይከለክለው እንደ አንድ የገቢ ማግኛ የኢኮኖሚ መስክ የመምረጥ ህገ መንግሥታዊ መብት አላቸው። የከተማ አስተዳደሩም የመከልከል መብት የለውም" የምትለው ሰብለ የከተማ አስተዳደሩ በከፍተኛ ሁኔታ እንደገና ሊያጤነው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አስተያየቷን ሰጥታለች።
ረቂቁ እንዲሁ ከመንግሥት ስለመጣ ብቻ መጫን ሳይሆን ከህብረተሰቡ ጋር ለመተማመን እየተሰራ መሆኑንና ከዚያ በኋላም ወደ ምክር ቤት ተልኮ አዋጁ ሥራ ላይ እንደሚውል የሚናገሩት ፌቨን ተሾመ ናቸው።
የጎዳን ልመናን በተመለከተ አምራች ኃይሉ ወደ ሥራ እንዲገባና በተለይም ለጎዳና ተዳዳሪዎቹ ከዚህ ህይወት እንዲወጡም በዘላቂነት ማቋቋም የሕጉ አላማ እንደሆነ ገልፀዋል።

እንደ ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ከሆነ በአሁኑ ወቅት አስተዳደሩ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለማገዝ የራሱን 'ሶሻል ፈንድ' አቋቁሞ እየሰራ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ማህበረሰቡ በተናጠል የሚሰጠውን ገንዘብ ተቋማዊ አሰራር ዘርግቶ በዚያ መንገድ እርዳታው እንዲገለስና ፕሮጀክቶችም ተቀርፀው እነሱ የሚጠቀሙበት መንገድ ተቀይሷል ይላሉ።
"የማይከለከል ከሆነ አስቸጋሪ ነው። ልመና እንደባህልም እየተወሰደ ስለሆነ ከዚህ ህይወት መውጣት ያለመፈለግ አዝማሚያዎች አሉ። በርካታ ወጣቶችም ከተለያዩ ከተሞች ወደ አዲስ አበባ ለልመና ሲባል ይመጣሉ። ይህ እርምጃም ነገ ተረካቢ ትውልድ ከማፍራት አንፃር ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብሎ አስተዳደሩ ያምናል" ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አዲስ አበባ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ከመሆኗም አንፃር ለሃገር ገጽታም መታሰብ እንዳለበትም አስረድተዋል።
ከዚህም አንፃር የጎዳና ላይ ልመና ብቻ ሳይሆን የጎዳና ላይ የወሲብ ንግድ ልቅ መሆኑ አግባብ እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ በተለይም የወሲብ ንግድ ከባህል አንጻር እንዲሁም ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ አፅንኦት በመስጠት ተናግረዋል።

"የወሲብ ንግድ ኢትዮጵያዊ እሴት ስላልሆነ፤ እንደ ዋና ከተማ ዜጎች ከውጭ ሃገር የሚመጡባት ለሃገሪቷም መውጪያና መግቢያ በር እንደመሆኗ መጠን እንደዚህ አይነት ተግባር ያልተበራከቱባት ብሎም የሌሉባት ከተማ ለማድረግ ታቅዷል" ይላሉ።
ከዚህም በተጨማሪ የወሲብ ንግድ መበራከት በከተማዋ ያለውን የኤች አይ ቪ ስርጭትን እንደሚጨምረው ጥናቶች ስለሚጠቁሙ ይህንንም ለመከላከል የወሲብ ንግድን መቆጣጠርም እንደሚያግዝ ያስረዳሉ።

በዚህ ጉዳይ ላይ የተጠየቁት ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ረቂቅ ህጉ ላይ ከልመና ጋር በተገናኘ ተጠያቂ የሚሆነው ወይም የሚቀጣው ሰጪው እንደሆነ ጠቅሰው የጎዳና ተዳዳሪዎችንም የማገገሚያ ማዕከል ተዘጋጅቶ ወደዚያ ገብተው የሥነ ልቦና ትምህርት፣ የሞያ ስልጠና እንዲያገኙና ወደ ሥራ እንዲገቡ የማቋቋም ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል።
"በመቆጣጠርና በመከልከል የሚፈለገው ላይ ስለማይደረስ፤ ከማስገደዱ በላይ የግንዛቤ ሥራ መቅደም አለበት። በተለይ የሃይማኖት ተቋማት እዚህ ላይ ከፍተኛ ሚና ስላላለቸው መተማመን ላይ መደረስ አለበት" ይላሉ አክለውም።
"በዚህ ሁኔታ የሐይማኖት አባቶች ትብብር ካላደረጉ የሚሳካ ስላልሆነ፤ ተቋማትን ማወያየትና የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ውይይቶች ይደረጋሉ። ከህብረተሰቡ ጋር መተማመን ከተደረሰ በኋላ ነው ወደ ማፅደቁ የምንሄደው" ብለዋል።
የወሲብ ንግድን በተመለከተ ረቂቅ ሕጉ ራሳቸው በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩትን ለመቅጣት ያሰበ ሲሆን፤ ከዚያም በተጨማሪ የምክር አገልግሎት የመስጠት ከሚገኙበት አካባቢ እንዲነሱና ህይወታቸውን እንዲቀይሩ የማድረግ ሥራ ይሰራል ብለዋል።
በቀድሞ የወሲብ ንግድ ትተዳደር የነበረችው ምፅዋ የረቂቅ ሕጉን ሐሳብ ደግፋ "በጣም የሚያስከፋ ሥራ ነው። ግን ለእነዚህ ሰዎች ምንድን ነው የሚደረግላቸው? ብዙዎች የልጆች እናትና የቤተሰብ አስተዳዳሪ እንደመሆናቸው መጠን መንግሥት ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል" በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች።
"እየተገረፉ፣ እየታሰሩ፤ እርቃናቸውን ብርድ ላይ ብዙ ነገር እየደረሰባቸው ነው እያሳለፉ ያሉት" የምትለው ምፅዋ፤ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች የፀጥታ ኃይሎች በደል እንደሚያደርሱባቸው ጠቅሳ መስተካከል እንዳለበትም ትናገራለች።

እንዲህ አይነት ሕግ ሲረቅ መንግሥት የሚጠበቅበትን ማከናወን አለበትና በወሲብ ንግድ ተሰማርተው የነበሩ ግለሰቦች ምንም አይነት እርዳታ እንደማይደረግላቸውም ትጠቅሳለች።
"እኛ አሁን በቀበሌ ደረጃና የተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች ያውቁናል። ግን ምንም የሚደረግልን ነገር የለም፤ እንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ እያለን እርዱን ብለን የምናለቅስበት ጊዜ ነበር፤ በቅድሚያ ማደራጀትና ማስተማር ያስፈልጋል" ትላለች።
ከዚህም በተጨማሪ ብዙዎቹ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሰዎች በሱስ የተጠቁ ከመሆናቸው አንፃር ያንን ነገር ለማስወገድ መጀመሪያ መሰራት እንዳለበትና የትራንስፖርትና የእለት ጉሮሯቸውን ለመሸፈን የሚያስችል ድጎማም ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ተግባር እንደሆነ አበክራ ትናገራለች።
"ረቂቅ ሕጉ ጥሩ ነው፤ ነገር ግን መጀመሪያ የህብረተሰቡን ችግር መረዳት አለበት። እኛም የወጣነው በፈታኝ ሁኔታ ነው" ትላለች።
ለረዥም ዓመታት በወሲብ ንግድ ተሰማርታ የቆየችው ሐይማኖት ከምፅዋ የተለየ ሀሳብ የላትም። እሷም በሁኔታው ተደስታ ነገር ግን የድጋፍ ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ታስረዳለች።
መንግሥት ትኩረት አድርጎ በእውቀት፣ በትምህርት፣ እንዲሁም ሰርተው የሚበሉበትንና የሚደራጁበትን ቦታ በማሰብ ድጋፍ ሊሰጥ እንደሚገባ ገልፃለች።
"ድጋፍ ከሌለ ከዚያ ህይወት መላቀቅ እጅግ በጣም ከባድ ስለሆነ፤ እኔ ራሱ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ነው መውጣት የቻልኩት፤ እኔ ራሱ በድጋፍ ሰጪ ድርጅት ነው መውጣት የቻልኩት" ብላለች።
መንግሥት ይህንን ሕግ ሲያፀድቅ ዝግጅት አድርጎ ሊሆን እንደሚችልም ግምቷን አስቀምጣለች።
"በአንዴ አቁሙ የሚል ነገር የለም። ምን ሊበሉ፣ ምን ሊጠጡስ፤ ቤት ኪራዩስ፤ ቦታ፣ ትምህርት፣ ገንዘብ አዘጋጅቷል ብዬ አስባለሁ። ካለዚያ ግን የታሰበውን ውጤት አያመጣም። ዝግጅት ሳይደረግ ያፀድቁታል ብዬ አላስብም" ትላለች።
በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ግለሰቦች ከተጠቃሚው እስከ ፖሊስ ድረስ ግፍ እንደሚደርስባቸውም ትናገራለች።
"ማንኛውም አይነት ችግር ቢደርስ ተሰሚነት የላቸውም፤ በዳይ እኛ ተደርገን ነው የምንታየው። ስንደበድብ፣ ጫካ ስንጣል፤ በጣም ራቅ ካለ ስፍራ ከአዲስ አበባ ውጪ ይጥሉ ነበር፤ ይህ ሁኔታ በአሁኑ አሰራር ይቀየራል" ብላ ታስባለች።

No comments:

Post a Comment

wanted officials