Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, August 15, 2019

አፋር ውስጥ የሞተችው እስራኤላዊት የገጠማት ምን ነበር?

አያ ናሚህ


አያ ናሚህ አፋር ክልል ውስጥ ወደሚገኘው የምድራችን ሞቃቱና ዝቅተኛው ደናክል አካባቢ ከሄዱት ስድስት እስራኤላዊያን ተማሪዎችና ሁለት ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዷ ነበረች።
የ22 ዓመቷ ወጣት ቅዳሜ ዕለት ግዙፉ በረሃ ውስጥ ከቡድኑ ተነጥላ መጥፋቷ ከታወቀ በኋላ በተደረገ ፍለጋ ሞታ ተገኝታለች።
አያ ለኢንጂነሪንግ ተማሪዎች በተዘጋጀው የአንድ ወር ስልጠና ላይ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተሳታፊ ለመሆን ነበር ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው።

ተማሪዎቹ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ስልጠናቸውን ሲጨርሱ ስድስቱ እስራኤላዊያን ከሁለት ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ወደ አፋር ክልል በመሄድ የኤርታሌ የእሳተ ገሞራ ሐይቅንና የዳሎል አካባቢን ለመጎብኘት እቅድ አውጥተው ነበር ወደዚያው ያቀኑት።
ከቡድኑ ጋር አብረው ከተጓዙት ሁለት ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዷ የሆነችው ጽዴና አባዲ ለቢቢሲ አንደተናገረችው፤ ወደ ኤርታሌ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ሐሙስ ምሽት አብረው እንደነበሩና አያም "በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደነበረች" ገልጻለች።
"ሁሉም ሰው በጉዞው ተደንቆና ደስተኛ ሆኖ ነበር" ስትል ጽዴና ለቢቢሲ ተናግራለች። ቀጣዩንም ቀን አፍዴራ ሐይቅ ላይ እየዋኙና እየተዝናኑ ማሳለፋቸውን ታስታውሳለች።
ቅዳሜ ጠዋትም አያና ጓደኞቿ ወደ ደናክል ዝቅተኛ ቦታ ደርሰው አካባቢውን በደንብ ለመመልከት እንዲችሉ በአቅራቢያው ወዳለ ኮረብታ አቀኑ።

"ከእሳተ ገሞራው ሐይቅ ከሚወጣው ኬሚካል ከያዘ ሽታና በአካባቢው ካለው ከፍተኛ ሙቀት የተነሳ የተወሰኑት ድካም ስለተሰማቸው ወዳመጣቸው መኪና ሲመለሱ ሌሎቹ ደግሞ ጉዟቸውን እንደቀጠሉ ትናገራለች።
ጽዴና እንዳለችው፤ አያ በድካም ከተመለሱት ተማሪዎች መካከል አንዷ የነበረች ስትሆን፤ ወደ መኪናቸው ስትመለስ የነበረውም ቀድማ ነበር።
በኋላ ላይም አያ እንደጠፋችና በተደረገው ፍለጋም ትሄድበት ከነበረው በሌላ አቅጣጫ ሞታ እንደተገኘች ተናግራለች።
ነገር ግን ሲመለሱ ከነበሩት መካከል የጠፋችው አያ ብቻ እንዳልነበረችም ጽዴና ተናግራለች።
"ሌላኛዋን ጓደኛዬን አግኝቼ እሷን በመከተል ወደ መኪናው እስክደርስ ድረስ እኔም ጠፍቼ ነበር" የምትለው ጽዴና "አካባቢው ተመሳሳይ ከመሆኑ የተነሳ አቅጣጫችንን ለማወቅ አስቸጋሪ ነበር" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ጽዴና አክላም ከእሳተ ገሞራው የሚወጣው ሽታና ያለው ከባድ ሙቀት እንዳሳመማትና "የምትሞት እንደመሰላት" አስታውሳለች።
እስራኤላዊቷ መጥፋቷ ከታወቀ በኋላ የአካባቢው ነዋሪዎችና ፖሊስ ለፍለጋ የተሰማሩ ሲሆን፤ አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያም በኋላ ላይ በፍለጋው ላይ ተሳታፊ ሆኗል።
በፍለጋውም አያ ህይወቷ አልፎ የተገኘች ሲሆን፤ አስክሬኗም ትናንት ዕሁድ በአውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ ተወስዷል።
ጽዴና እንደምትለው፤ አያ በሁሉም ሰው የምትወደድና ተግባቢ ነበረች።
ለእስራኤላዊቷ ሕይወት ማለፍ ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

No comments:

Post a Comment

wanted officials