Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, August 19, 2019

እውን ኢትዮጵያ በአንድ ቀን 350 ሚሊዮን ችግኞች ተክላለች?


የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ ነበር ኢትዮጵያ '350 ሚሊዮን ያህል ዛፎች ተክያለሁ፤ የዓለም ሪከርድም ሰብሪያለሁ' ስትል ያሳወቀችው። ግን ይህ መረጃ ምን ያህል እውነት ነው? የቢቢሲ 'ሪያሊቲ ቼክ' ቁጥሮችን አገላብጦ ያገኘው መረጃ እነሆ።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የደን መመናመንን ለመከላከል አርባ ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ችግኝ የመትከል ዕቅድ ይዘው የተነሱት በቅርቡ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከሚሊኒዬም በፊት ከነበረው 35 በመቶ ወደ 4 በመቶ ዝቅ ብሏል ይላል።
ሐምሌ 22/2011 ዓ.ም. ኢትዮጵያ በ12 ሰዓታት ውስጥ 200 ሚሊዮን ዛፎችን ለመትከል ቆርጣ ተነሳች። በቀኑ መገባደጃ ላይ የፈጠራ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ ሃገሪቱ 350 ሚሊዮን ዛፎች መትከሏን አሳወቁ።

መንግሥት እንደሚለው ለበጎ ፈቃደኞች የሚተከሉት ዛፎች መታደል የጀመሩት ከሶስት ቀናት በፊት ጀምሮ ነበር። በርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዕለተ ሰኞ ሐምሌ 22/2011 ዓ.ም መደበኛ ሥራቸውን በመተው ዛፍ በመትከል እንዲውሉ ተደረገ።
የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች ጨምሮ የአፍሪቃ ሕብረት እና ሌሎች መንግሥታዊ ያለሆኑ ድርጅቶችም በዛፍ መትከሉ ላይ በፈቃደኝነት ተሳተፉ።
በርካቶቹ ችግኞች ሃገር በቀል መሆናቸውም ተነግሯል፤ እንደ አቮካዶ የመሳሰሉ የፍራፍሬ ዛፎችም መትከላቸው ታውቋል።
በጎ ፈቃደኞቹ የሚተክሉትን ዛፎች ይቆጥሩ ዘንድ በየቦታው ሰዎች መመደባቸውም በዛፍ ተከላው ቀን ተዘገበ።
አሁን ጥያቄው ይህን ያህል ዛፎች በአንድ ቀን መትከል ይቻላል ወይ የሚለው ነው። የዘርፉ ባለሙያዎች 'መቻሉን ይቻላል፤ ነገር ግን በጣም ትልቅ ዝግጅት ይጠይቃል' ይላሉ።
«እርግጥ ነው ይቻላል። ቢሆንም በጣም ዘለግ ያለ ዝግጅት ይሻል» ይላሉ በተባበሩት መንሥታት ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያ የሆኑት ቲም ክሪስቶፈርሰን።
ኤኤፍፒ ለተሰኘው ዜና ወኪል ሃሳባቸውን የሰጡት ቲም አንድ በጎ ፈቃደኛ በቀን 100 ዛፎች መትከል ይችላል ይላሉ።
ጊነስ ዎርልድ ሪከርድስ፡ «ስለተተከሉት ዛፎች ከኢትዮጵያ የደረሰን መረጃ የለም»
ከ23 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በዛፍ ተከላው ላይ እንደተሳተፉ የብሔራዊ ደን ልማት ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ተፈራ መንግሥቱ ይናገራሉ።
ስለዚህ 23 ሚሊዮን ሰዎች በቀን 100 ያህል ዛፎች ከተከሉ ቁጥሩ ከ350 ሚሊዮን በላይ ሊሆን እንደሚችል አያጠያይቅም። ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው ምን ያህል ዛፍ እንደተከለ በውል የሚታወቅ ቁጥር እንደሌለ ተገልጿል።

350 ሚሊዮን ዛፎችን ለመትከል ቢያንስ 346 ሺህ 648 ሄክታር መሬት ይጠይቃል። ነገር ግን ምን ያህል ሄክታር መሬት ዛፎችን ለመትከል ጥቅም ላይ እንደዋለም መረጃ የለም።
አንድ የመንግሥት መሠሪያ ቤት ሠራተኛ መሥሪያ ቤታቸው 10 ሺህ ዛፎችን እንዲተክልና ወጭውንም እንዲሸፍን እንደታዘዘ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
የበጀት እጥረት ስላጋጠማቸው አምስት ሺህ ዛፎችን ብቻ ነው የተከሉት።
5 ሺህ ዛፎችን ተክለው ነገር ግን 10 ሺህ የሚል ቁጥር ገቢ ማድረጋቸውን ነው ለቢቢሲ አስረድተዋል።
አልፎም አንዳንድ ቦታዎች ላይ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ተተከሉ ያሏቸው ዛፎች ቁጥር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረ-ገፅ ላይ ከሰፈረው ጋር ልዩነት እንደታየበት ቢቢሲ ታዝቧል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጠን የጠየቅነው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አላገኘም።
የተባበሩት መንግሥታት ኢትዮጵያ ለዛፍ ተከላው አመስግኖ ጎረቤት ሃገራትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስቧል። ቢሆንም የዛፎቹ ቁጥር ጉዳይ ከበርካታ ወገኖች ትችት አላጣም።
«እኔ በበኩሌ ይህን ያህል ዛፍ ተክለናል ብዬ አላምንም» ይላሉ የኢዜማ ፓርቲ ቃል-አቀባዩ ዘላለም ወርቅአገኘሁ።
ተቺዎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግሥታቸው የገጠመው ብሔር ተኮር እክልን የዛፍ ተከላው ቅስቀሳውን ሽፋን በማድረግ እያደባበሱት ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።

እውን ሪከርድ ተሰብሯል?

የዓለም ድንቃድንቅ ድርጊቶች መዝጋቢው ጊነስ ዎርልድ ሪከርድስ በበኩሉ የዛፍ ተከላ ሬከርድ የመስበር ሙከራውን ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ መንግሥት የደረሰው ምንም ዓይነት ማመልከቻ እንደሌለ ይናገራል።
«እኛ ምንም ዓይነት ሪከርድ ሲሰበር በንቃት እንከታተላለን። የዝግጅቱ አስተናባሪዎች ደግሞ ሪከርዱ ሲሰበር እንድንመዝግብላቸው ማመልከቻ እንዲያስገቡ እንመክራለን» ይላሉ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጄሲካ ዳውስ።
ኢትዮጵያ እውን ሪከርዱን ሰብራ ከሆነ ምን ያህል ሰዎች እንደተሳተፉ፣ የት እና መቼ እንደተከናወነ የሚገልፅ ውል ያለው መረጃ መስጠት ይኖርባታል። አልፎም ሁለት ገለልተኛ ምስክሮች ሪከርዱ መሰበሩን በሥፍራው ተገኝተው ማረጋገጥ ይጠብቅባቸዋል።
በአሁኑ ወቅት ዛፍ በመትከል የዓለም ሪከርድ ይዛ ያለችው ህንድ ናት።
በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ካናዳዊው ኬን ቻፕሊን በአንድ ቀን 15 ሺህ 170 ዛፎችን በመትከል የዓለም ሪከርድ ይዞ ይገኛል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials