Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, August 19, 2019

ብሩክ ዘውዱ፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት አስመዝጋቢ

ብሩክ ዘውዱ ከእናቱ ጋር
በዘንድሮው ዓመት የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ሃገር አቀፍ ፈተና የተመዘገበው ከፍተኛው ውጤት 645 ሲሆን፤ ይህ ውጤትም በአማራ ክልል መመዝገቡን የትምህርት ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃረጓ ማሞ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ውጤቱን ያስመዘገበውም ብሩክ ዘውዱ የተባለ በባህርዳር የአየለች ደገፉ መታሰቢያ (ኃይሌ) ትምህርት ቤት ተማሪ መሆኑን ሰምተናል። ስላስመዘገበው ውጤት ለማነጋገር ወደ ብሩክ ስልክ መታን። ምን ተሰማህ አልነው።
ብሩክ ውጤቱን እንደሚያመጣ ይጠብቅ ስለነበር ብዙም አልደነቀውም። "ደስ ብሎኛል" አለን በአገር አቀፍ ደረጃ ግን ከፍተኛ ውጤት አስመዘግባለሁ ብሎ እንዳላሰበ በመግለፅ።

እርሱ እንደሚለው በትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚያስተምሩ መምህራን ብቃት ፣ በትርፍ ጊዜው [ቅዳሜና እሁድ] መምህራን የሚሰጡትን ማጠናከሪያ ትምህርት መከታተሉ እና የራሱ የንባብ ልምድ ላስመዘገበው ከፍተኛ ውጤት አስተዋፅኦ አድርጎለታል።
"ሁሉም ሰው የራሱ ሆነ የጥናት ስልት አለው፤ የእኔ የንባብ ስልት ለሌላው ላይፈይድ ይችላል" የሚለው ብሩክ በፕሮግራም፣ ብዙም ሳይጨናነቅ እና ደስ እያለው እንደሚያነብ ከዚያም ፈተናን ተረጋግቶ የመፈተን ልምድ እንዳለው ገልፆልናል።

ብሩክ ወላጅ አባቱን በሞት ያጣው የ10 ዓመት ታዳጊ እያለ ነበር። ከዚያም በኋላ እናታቸው የእናትንም የአባትንም ቦታ ተክተው እነርሱን ማሳደግ ያዙ።
ታዲያ እርሱም ሆነ እህትና ወንድሙ በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እናታቸው የሚያደርጉላቸው ድጋፍና ክትትል ከፍተኛ እንደነበር ሳይጠቅስ አላለፈም።
"እናቴ ብዙም አንብቡ ብላ አትጎተጉተንም ፤ እኛ በፈለግንበት ሰዓት አምነንበት ነው እንድናነብ የምታደርገው" ይላል።

ብሩክ እንደሚለው ታላቅ እህቱም የዛሬ ሦስት ዓመት እርሱ በተማረበት አየለች መታሰቢያ (ኃይሌ) ትምህርት ቤት፤ በትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ውጤት እንዳስመዘገበች ያስታውሳል።
የእርሱ ታናሽ ወንድምም ቢሆን የዋዛ አይደለም፤ ጥሩ የትምህርት አቀባበል አለው።
ብሩክ ለጊዜው የትኛውን የትምህርት ዘርፍ ሊያጠና እንደሚችል ውሳኔ አላሳለፈም። በጤና ዘርፍ፣ በኮምፒዩተር ሶፍት ዌር ኢንጅነሪንግ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የመማር ፍላጎት ቢኖረውም ወደ ሕክምናው ዘርፍ ሳያደላ እንደማይቀር ግን ይናገራል።
ብሩክ ወደፊት አንድ ግብ ብቻ አስቀምጦ መጓዙ አያዋጣም ከሚሉት ወገኖች ነው። ወደፊት የተሻለ ነገር ፍለጋ በተለያዩ ዘርፎች እንደሚታትር ነግሮናል።
"ደስታ ያሰክራል፤ ደስታ እንባ እንባ ይላል" ሲሉ በልጃቸው ውጤት እንደተደሰቱ የገለፁልን ደግሞ እናቱ ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ጥላሁን ናቸው።
የልጃቸውን መልካም ውጤት ዜና የሰሙትም ከራሱ ከልጃቸው ነበር።
"ደውሎ፤ እንዳትደነግጭ፤ ስድስት መቶ ምናምን አምጥቻለሁ ብሎ ስልኩን ዘጋው" ይላሉ የስልክ ልውውጣቸውን ሲያስታውሱ። ከዚያ በኋላ ግን ጓደኛው ደውሎ ብሩክ ከኢትዮጵያ ተፈታኞች አንደኛ እንደወጣ ሲነግራቸው ደስታቸውን መቆጣጠር እንዳልቻሉ ይናገራሉ።

በወቅቱ ጓደኛቸው ቤት ነበሩና " እሷን አቅፌ ጮህኩ፤ እሷን አቅፌ አለቀስኩ፣ ተንበረከኩ...ፈጣሪን አመሰገንኩ" ይላሉ።
ወ/ሮ ኤልሳቤት ከ12ኛ ክፍል በላይ በትምህርታቸው አልገፉም- አንድም ውጤት ስላላስመዘገቡ፤ በግልም ለመማር አቅም ስላልነበራቸው፤ በሌላም በኩል በትዳር ኃላፊነት ውስጥ ስለገቡ።
የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ባለቤታቸው በሞት ከተለዩዋቸው በኋላ 'ልጆቼ ናቸው ሥራዎቼ' ብለው የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ እንደሆነ ያስረዳሉ።
"እናንተ የምታስመዘግቡት ውጤት ለእኔ ደመወዜ ነው እያልኩ ስለማሳድጋቸው ተግተው ነው የሚሰሩት " ይላሉ- ወ/ሮ ኤልሳቤት። መልካም ውጤት ሲያመጡም ደመወዝ እንደከፈሉኝ ነው የሚሰማቸው ሲሉ ከልጆቻቸው ጋር ያላቸውን ተግባቦት ይገልፃሉ፤ እንዲያጠኑ ብዙም ጫና አያሳድሩባቸውም።
"በትምህርት ብቻ ሳይሆን ጥሩ ዜጋ እንዲሆኑ ፤ ገንዘብ በምንም መንገድ ይገኛል፤ መማር ስብዕናን ያንጻል፤ ስብዕናን ያሟላ ሰው እንድትሆኑ እፈልጋለሁ እያልኩ ነው ያሳደግኳቸው" ይላሉ።
ለእርሳቸው ብቻ ሳይሆን ለአገር የሚጠቅሙ ዜጎች እንዲሆኑ እንደሚለፉ ይናገራሉ።

"የምንኖረው ሁለት ክፍል ቤቶችን እያከራየን ነው፤ ለልጆቼ የማወርሳቸው ምንም ሀብት የለኝም" የሚሉት ወ/ሮ ኤልሳቤት እነርሱ ላይ ፍሬያቸውን ማየት ይፈልጋሉ።
ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ስለ ብሩክ ሲናገሩም "ብሩክ በተሰማራበት ሁሉ ውጤታማ መሆን የሚችል ልጅ ነው፤ የሞከረው ሁሉ ይሳካል"ሲሉ ብዙ ጊዜ ናሳ የመሄድ ምኞት እንዳለው ገልፀውልናል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ለመውሰድ ከተመዘገቡት 322 ሺህ 717 ተማሪዎች መካከል 319,264 የሚሆኑት ፈተናውን መውሰዳቸውን የትምህርት ሚኒስቴር በይፋዊ ገፁ አስታውቋል።
ፈተና ላይ ከተቀመጡት ውስጥም 59 ተማሪዎች ከ600 በላይ ውጤት ሲያመጡ 48.59 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከ350 በላይ ውጤት አምጥተዋል።
በዘንድሮው ዓመት በፈተናው ወቅት በተፈጸመ የደንብ ጥሰት የ68 ተማሪዎች ውጤት መሰረዙም ተገልጿል።
በመጨረሻም...
አፕቲቲዩድ የትምህርት ዘርፍ የበርካታ ተማሪዎች ውጤት ዝቅ ማለቱ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው። ለብሩክ ይህንኑ ጥያቄ ሰንዝረንለት ነበር። በእርግጥ እርሱ"86 አካባቢ አስመዝግቤያለሁ"ይላል።
ቢሆንም ግን ምክንያቱን ሳንጠይቀው አላለፍንም። እርሱም የትምህርቱ ዘርፍ የተማሪዎችን ጠቅላላ እውቀት ለመመዘን እንደሚሰጥ ጠቅሶ "ትምህርቱ እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ አይሰጥም፤ መምህራን ናቸው በበጎ ፈቃደኝነት እገዛ የሚያደርጉት፤ በዚያ ምክንያት ይሆናል" ሲል የግል አስተያየቱን አካፍሎናል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials