የሪክ ማቻር ሰራዊት አባላት እንደሆኑ የሚነገርላቸው ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል ጆር ወረዳ በድብቅ ወታደራዊ ካምፕ መስርተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መሆናቸው ታውቋል።
በአርሶአደሩና በጋምቤላ ልዩ ሃይል በተፈጸመባቸው ጥቃት የኢትዮጵያን ግዛት ለቀው የወጡት የደቡብ ሱዳን አማጺ ታጣቂዎች ተመልሰው ወደ ለመግባት በመሰባሰብ ላይ መሆቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የጋምቤላ ክልል ካቢኔ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በጋምቤላ ክልል አኝዋክ ዞን ጆር ወረዳ በኢትዮጵያ መንግስት ቁጥጥር ስር ያልነበረ ወታደራዊ ካምፕ ለአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ሆኖ ቆይቷል።
ካምፑን የደቡብ ሱዳን አማጺ መሪ ሬክ ማቻር ወታደሮች ይሁኑ ሌሎች ሃይሎች በግልጽ አልታወቀም ነበር።
በካምፑ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ወታደሮች የሚገኙ መሆናቸውን የገለጹት የኢሳት ምንጮች የጋምቤላ ክልል መንግስት ጉዳዩን በተመለከተ በተደጋጋሚ ለፌደራል መንግስቱ ማሳወቁን ጠቅሰዋል።
ከዚህ ምንነቱ ካልታወቀ ወታደራዊ ካምፕ ታጣቂዎች እየተነሱ በአኝዋክ ተወላጆች ላይ ጥቃት ሲፈጸም እንደነበርም መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከሶስት ሳምንት በፊት ከጋምቤላ እስር ቤት ያመለጡ 72 እስረኞች በቀጥታ የተቀላቀሉት በድብቅ ይገኛል የተባለውን ካምፕ መሆኑን በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል።
በጆር ወረዳ የሚገኘውን ወታደራዊ ካምፕ በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡን የመከላከያ ሰራዊት ሃላፊዎችንና የጋምቤላ ክልል ባለስልጣናትን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም የኢሳት ምንጮች ጉዳዩ በሁለቱም ወገኖች በልዩ ትኩረት ክትትል እየተደረገበት እንደሆነ ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት በመጀመሪያ ላይ የአርሶ አደሮችና የጋምቤላ ልዩ ሃይል በወሰዱት የማጥቃት ርምጃ ምንነቱ ካልታወቀ ካምፕ ውስጥ የነበሩትን ታጣቂዎች ማስወጣት መቻሉ ታውቋል።
በጊዜው በተካሄደ ውጊያ ከሁለቱም ወገኖች በድምሩ ስድስት ሰዎች መገዳላቸው የሚታወስ ነው።
የመከላከያ ሰራዊት በካምፑ ውስጥ በሚገኙ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ማስጠንቀቂያ በሰጠ ማግስት በተደረገው በዚሁ ውጊያ ታጣቂዎቹ ካምፑን ጥለው ወደ ደቡብ ሱዳን መሸሻቸው ተገልጿል።
የኢሳት ምንጮች ዛሬ ባደረሱን መረጃ ግን ከኢትዮጵያ ግዛት የተባረሩት የደቡብ ሱዳን አማጺ ወታደሮች እንዲሰባብሰቡና ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንዲጠጉ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።
ኮለኔል ፊሊፕ ጂማ ደንግ የተሰኙ የአማጺያኑ ወታደራዊ መሪ ባስተላለፉት በዚሁ ትዕዛዝ በተለያዩ የደቡብ ሱዳን አካባቢዎች የሚገኙት የአማጺው ወታደሮች ተሰባስበው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንዲጠጉ የሚያደርግ ነው።
ዓላማው በኢትዮጵያ ግዛት ጆር ወረዳ ወደ ሚገኘውና ባለፈው ሳምንት የተነጠቁትን ወታደራዊ ካምፕ መልሶ ለመያዝ እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል።
ጉዳዩን በተመለክተ የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት መረጃው እንዳለውም ምንጮች ጠቁመዋል።
አማጺው ግጭቱን የጎሳ እንዲሆን በማድረግ በአኝዋኮችና ኑዌሮች መካከል ደም ለማፋሰስ እየሰራ መሆኑንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በተያያዘ ዜና በጋምቤላ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች መሳሪያ ይዘው በከተማ ውስጥ የሚዘዋወሩ መሆናቸው የክልሉን ነዋሪ ስጋት ውስጥ መክተቱ ተገልጿል።
ሰሞኑንም በጋምቤላ ከተማ መሳሪያ ይዘው ሲዘዋወሩ የተያዙ ስደተኞች መኖራቸውን የኢሳት ምንጮች ከላኩት መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
No comments:
Post a Comment