ይህ ግን ለሃይማኖታዊ አገልግሎት ብቻ አይደለም። ከአገልግሎቱ ጎን ለጎን ቅርሱን እያስጎበኙ ኑሯቸውን ስለሚመሩ ጭምርም ነው።
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት በ12ኛው ክፍለ ዘመን ከአንድ አለት ተፈልፍለው የተሠሩ ናቸው።
በቁጥር 11 የሆኑት አብያተ ክርስቲያናት፤ በ1970 ዓ. ም. በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ ተብለው ተመዝግበዋል።
ዲያቆን ፈንታ እነዚህን ድንቅ ቅርሶች ሲያስጎበኙ ከጊዜ ወደ ጊዜ አደጋ ላይ እየወደቁ መሆኑን መገንዘብ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል።
"ዕድሜ ተጨምሮበት፣ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያትም እየተጎዱ ነው" ይላሉ።
በዚህ ሀሳብ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም አስተዳዳሪ የሆኑት አባ ጽጌሥላሴ መዝገቡም ይስማማሉ።
"ከ800 ዓመት በላይ ዕድሜ በማስቆጠራቸው እርጅና ይታይባቸዋል። አልፎ አልፎም ተሰነጣጥቀዋል። ችግሮቹ ሁለት ናቸው። አንዱ በእድሜ ምክንያት የደረሰባቸው ጫና ሲሆን ሁለተኛው ሰው ሠራሽ ጉዳት ነው" ይላሉ።
ችግሮቹን ለመቅረፍ ሲባል በተለያዩ ወቅቶች የጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል።
"የተለያዩ ባለሙያዎች ሊጠገኑት ሞክረዋል። በግብጻዊያን እና በጣልያናዊያን መሃንዲሶች የተሠሩ ሥራዎች አሉ። አንዳንዶቹ ጥሩ ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ ችግሮቹን ያባባሱ ናቸው" ሲሉ አባ ጽጌሥላሴ ያስረዳሉ።
ቤተ ገብርኤል የተሻለ እድሳት እንዳገኘ የሚገልጹት ዲያቆን ፈንታ፤ በዕድሳቱ ምክንያት ተጨማሪ ጉዳት የደረሰባቸው አብያተ ክርስትያናት መኖራቸውንም ይጠቁማሉ።
ቤተ አማኑኤል የተቀባው ቀለም ከፍተኛ ሽታ በማምጣቱ፤ ቀለሙን ፍቆ ለማስለቀቅ የተደረገው ሙከራ የህንጻው ግድግዳ ላይ ጉዳት አድርሷል። ቤተ ጎልጎታ ደግሞ፤ የዝናብ ውሃ ለማውረድ ጣራው ላይ በተለያዩ አቅጣጫዎች ቦይ መሳይ ማፍሰሻ ቢሠራለትም፤ በአራት በኩል ተሰባስቦ የሚወርደው ውሃ ታችኛውን የቅርሱን አካል በመቦርቦር ላይ ይገኛል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ከዚህ ሁሉ በላይ አሳሳቢ የሆነው የአብያተ ክርስትያናቱ መጠለያ ነው።
በ2000 ዓ. ም. አብያተ ክርስትያናቱን ከአደጋ ለመከላከል ሲባል መጠለያ እንዲሠራላቸው ተደርጎ ነበር። ይህ መጠለያ ደግሞ ቅርሶቹ ላይ ጫና በማሳደሩ የብዙዎች ስጋት ከሆነ ሰነባብቷል።
"እነዚህ ቅርሶች ህልውናችን ናቸው" የሚሉት የላሊበላ ከተማ ነዋሪው አቶ ተገኘ ዋሲሁን፤ "ቅርሶቹ ለእኛ ሃብታችን እና ህልውናችን ናቸው። ሰማያዊ ስጦታ፤ ምድራዊ ርስታችን ናቸው። በተወሰነ የጊዜ ገደብ ለቅርሱ ተብሎ መጠለያ ቢሠራለትም፤ እስካሁን ባለመነሳቱ ለከፋ አደጋ ሊያደርሰው ይችላል" ሲሉ ስጋታቸውን ለቢቢሲ አስርድተዋል።
ሌላው የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ ቀለሙ ገላው በበኩላቸው፤ "የተሰቀለው ብረት ካለው ክብደት እንጻር ስጋት ደቅኗል። በተደጋጋሚ ብንጠይቅም እስካሁን ምላሽ አላገኘም" ይላሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ከብረት የተሠራው መጠለያ በአምስት ዓመት ውስጥ ይነሳል ቢባልም ለ12 ዓመታት ያህል አልተነሳም። "ብረቱ ካለመነሳቱ በተጨማሪ ብረቱ ያረፈበት ከቤተክርስትያናቱ መሠረት ጋር ተመሳሳይ መሆኑም ስጋት ፈጥሯል" ይላሉ።
ዲያቆን ፈንታ በበኩላቸው ብረቱ ላይ ፍተሻ እንዳልተደረገ ይናገራሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ከ10 ሜትር በላይ የሚረዝመው ብረት የቆመው ከህንጻው በላይ ነው። ለምሶሶነት የሚያገለግለው ብረት መሬት ውስጥ ተቆፍሮ የተቀበረ መሠረት የለውም። ስለዚህም ብረቱ ቢንቀሳቀስ ቅርሱ ላይ ቢወድቅ ይችላል። "ዓለም ሁለተኛ ሊሠራው ይቅርና እንዲህ ተብሎ ተሠራ ለማለት የሚከብደውን ቅርስ አደጋ ላይ ጥሏል" ይላሉ።
በተለይ ቤተ አማኑኤል ላይ ያለው መጠለያ፤ ሸራው በስብሶ፣ ቀዳዳ በመፍጠሩ ዝናብ ሰርጎ እየገባ ቅርሱ ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።
"ቤተ መስቀል መሃል ለመሃል ተሰንጥቋል። ቤተ መድኃኒዓለም ጣርያው አፈር ብቻ ሆኗል። ውስጡ ላይም ጉዳት አድርሶበታል" ይላሉ ዲያቆን ፈንታ ስለችግሩ ሲያስረዱ።
በዚህ ሐሳብ አባ ጽጌሥላሴም ይስማማሉ። አሁን ያለው መጠለያ ለአራተኛ ጊዜ የተቀየረ መሆኑን ይናገራሉ።
"የብረቱ እግር የቆመው ዋሻ ወይም ቤተ መቅደስ ላይ ነው። መጠለያው ሲሠራ የነበረው የንፋስ መጠን አሁን በእጥፍ ጨምሯል። ንፋስ ሲኖር ብረቱ ይንቀሳቀሳል። ከባድ ንፋስ ቢመጣና ብረቱ ቢወድቅ ቤተክርስትያኑን ያፈርሰዋል። እግሩ ቢሰምጥም ከስር ያለው መቅደስ ላይ ሊወድቅ ይችላል" ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።
የአማራ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ግዛት አብዩ፤ "ከዕድሜ እና ከአያያዝ ጋር በተያያዘ ጉዳት እየደረሰ በመሆኑ ጊዜያዊ መፍትሔ ሲሰጥ ነበር። አሁን ሲባባስ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል" ብለዋል።
ጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት እንዲያገኝ መስከረም 27፣ 2011 ዓ. ም. ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጎ ነበር። ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ልዑካንም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ሄደው አቤት ብለዋል።
ችግሩን ቦታው ድረስ በመሄድ የተመለከቱት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ፤ ጉዳዩን ለፈረንሳይ መንግሥት አቅርበው ድጋፍ በጠየቁት መሠረት አዎንታዊ ምላሽ አግኝተዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም ቅርሱን ጎብኝተዋል። በጎ ምላሽም ሰጥተዋል።
"የፈረንሳይ መንግሥት ለቅርሱ ጥበቃ አድርገው መሥራት እንደሚችሉ ቃል ገብተዋል። ሙሉ ለሙሉ የፈረንሳይ መንግሥት የሚሰራው ሲሆን፤ የአገር ውስጥ እና የፈረንሳይ ባለሙያዎችን ያካተተ የቴክኒክ ቡድን ኮሚቴ ተዋቅሯል" ብለዋል አቶ ግዛት።
አባ ጽጌሥላሴ ከዚያ በኋላ ተስፋ እንዳላቸው ይናገራሉ። "ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ አለ። የተለያዩ ባለሙያዎች ተካተውበታል። ከመስከረም ጀምሮ ጥናቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል። እኛም ጥገና ይካሄዳል የሚል ተስፋ ነው ያለን" ብለዋል።
ለሥራው የፈረንሳይ መንግስት ከአንድ ሚሊዮን ዩሮ በላይ መድቧል። አቶ ግዛት አብዩ፤ ከመስከረም ጀምሮ የቴክኒክ ሥራ እንደሚጀመር፣ የአማራ ክልልን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ገንዘብ በመመደብ ከቅርሱ ውጭ ያሉ ነገሮች እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
ዲያቆን ፈንታ እንደሚሉት፤ እንደ ላሊበላ አይነት ቅርስ ባለመኖሩ ባለሙያዎች ቅርሱን ለመጠገን ሲቸገሩ ይስተዋላል።
"ቅርሱ ከምድር ውስጥ አለት ተፈልፍሎ ዓለም ከሚሠራው ጥበብ በተለየ ነው የተሠራው። ይህን ለመጠገን ባለሙያዎች ሲጨነቁ እናያለን። ጥበቡን ግለጽላቸው ነው የምንለው። እንደዚህ ዓይነት ሥራ በሌላው ዓለም ስለሌለ አንዳንዶቹ ቅርሶቹን መሞከሪያ ነው የሚያደርጓቸው። አንዱ መጥቶ ሠርቶ ይሄዳል፤ ሌላው መጥቶ ትክክል አይደለም በሚል ያንን ያነሳል፤ የራሱን ይቀይራል። በዚህ መልኩ በአብዛኛው ሰው ሠራሽ ችግር ነው የጎዳው" ይላሉ።
አባ ጽጌሥላሴ እንደሚሉት፤ በቤተ መድኃኒዓለም እና በቤተ አማኑኤል ትልቁ ጉዳት አንዱ ባለሙያ መጥቶ የሠራውን ሌላው መጥቶ በመዶሻ እና መቆርቆሪያ ማንሳቱ ነው።
አቶ ግዛት እንደሚናገሩት፤ ቅርሶቹ ላይ መጠለያው ስጋት ቢደቅንም፤ ማንሳቱ የሚወስነው በባለሙያዎች የተቋቋመው የቴክኒክ ቡድን ነው።
"ጉዳት የማያደርስ ከሆነ ይቆያል። የሚጎዳ ከሆነ ደግሞ ያነሳል" ሲሉ ያስረዳሉ።
ዲያቆን ፈንታ "ባይናገር እንኳን እንደ መምህር የሚያስተምር፣ እንደዳቦ እየተቆረሰ የተሠራ፣ በዚህ ዘመን ማንም ሰው ሊሠራው የማይችል ድንቅ ጥበብ በመሆኑ፤ እንጠግናለን ተብሎ የተጀመረው ሃሳብ በአጭር ጊዜ ውስጥ መከናወን አለበት። አንዴ ከፈረሰ ከሃዘን ውጭ የሚጠቅመን ነገር የለም" ይላሉ ።
የዲያቆን ፈንታ ሕልም ሁለት ነው። አንድም ጥንታዊ የሆነውን ቅርስ መጠበቅ። በሌላ በኩል ደግሞ ቅርሱን በማስጎብኘት የሚያገኙትን ጥቅም ማስቀጠል