አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ሥፍራዎች የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት ላይ የነበሩ የተባሉ የአል-ሸባብና የአይ ኤስ ቡድን አባላት መያዛቸው ተገለጸ።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ቅዳሜ ምሽት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው አልሸባብ እና አይ ኤስ ኢትዮጵያ ውስጥ የሽብር ጥቃት በመፈፀም በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ በዝግጅት ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት፤ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በርካታ የጽንፈኛው እስላማዊ ቡድን-አይኤስ አባላትን በቁጥጥር ሥር አዋልኩ ማለቱን መዘገባችን ይታወሳል።
የኢታማዦር ሹሙ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ኮለኔል ተስፋዬ አያሌው ከአንድ ሳምንት በፊት የጽንፈኛ ቡድኑ አባላት ናቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች ጅግጅጋ፣ ድሬዳዋ፣ ሞያሌ እና ዶሎ ከተማዎችን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ውስጥ መያዛቸውን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሶማሊያ፣ የሶሪያ እና የየመን ዜጎች እንደሚገኙበት ኮለኔል ተስፋዬ ተናግረዋል። "አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች አማርኛ ቋንቋ ተምረው የተላኩ ናቸው" ሲሉም አክለው ነበር።
ህዝብ የሚበዛባቸውን ቦታዎች እንዲሁም የሀይማኖት ክብረ በዓል የሚካሄድባቸውንና የተለያዩ ሆቴሎችን የመለየትና የፎቶግራፍ መረጃዎችን የመሰብሰብ ጥናት ካደረገ በኋላ ጥቃት ለመፈጸም በጅቡቲ በኩል ወደ አዲስ አበባ የገባው አንደኛው የአልሸባብ የሽብር ቡድን አባል ሙሐመድ አብዱላሂ ዱለት፤ ክትትል ሲደረግበት ቆይቶ በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ መያዙን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ገልጿል።
ከግለሰቡ በተጨማሪ ሌሎች ተባባሪዎች ለተለያዩ የጥቃት ተልዕኮዎች ከጅቡቲና ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውንና ከሃገራቱ የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ስር እንደዋሉም ተነግሯል።
ከአል-ሸባብ በተጨማሪ የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባላት ከቦሳሶ በሶማሌላንድ ሃርጌሳ በኩል ወደ አዲስ አበባ በመግባት የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ በብሔሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በአዲስ አበባና በአዋሽ አካባቢ መያዛቸው ተገልጿል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የቡድኖቹ አባላት በተጨማሪ የሚጠቀሙባቸው የግንኙነት መሳሪያዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች መያዙም ተጠቅሷል።
ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በቁጥጥር ስር የዋሉትን ግለሰቦች ማንነት እና የት በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ይፋ አድርጓል። በዚህም መሰረት፤
የአል-ሸባብ የሽብር ቡድንን የሚመራው ሙሐመድ አብዱላሂ ዱለት በሀሰተኛ ስሙ ያህያ አሊ ሃሰን በጅቡቲ በኩል ወደ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ቦሌ አካባቢ በቁጥጥር ስር ውሏል።
የሙሐመድ አብዱላሂ ዱለት ግብረ አበሮች የሆኑት አብደክ መሃመድ ሁሴን፣ ሬድዋን መሃመድ ሁሴን እና በቅፅል ስሙ ስመተር መሀመድ ኢማን ዩሱፍ በመባል የሚታወቀው ጅቡቲ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ከደቡባዊ ሶማሊያ በመነሳት ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ዝግጅት ሲያደርጉ የነበሩት ይሳቅ አሊ አደን እና አደን ሙሃሙድ መሃመድ በቅፅል ስሙ አደን ቦራይ ሱማሊላንድ ውስጥ ተይዘዋል። ይሳቅ አሊ አደን ከሶማሌ ክልል ቦህ ወረዳ ጨርቃን ቀበሌ የተሰጠ የነዋሪነት መታወቂያ ይዞ የተገኘ ሲሆን፤ አደን ሙሃሙድ መሃመድ የሚባለው ተጠርጣሪ ደግሞ በስሙ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2.5 ሚሊዮን ተቀማጭ ብር ተገኝቷል።
መካከል ዒድ መሃመድ ዓሊ የተባለ ተጠርጣሪ በሶማሌ ክልል ጨርጨር ዞን አራርሶ ወረዳ፣ በሽር ዑስማን አብዲ በሶማሌ ክልል ፊቅ አከባቢ እንዲሁም ዑስማን አሊ ሁሴን በኦሮሚያ ክልል በሞያሌ ከተማ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የአይ ኤስ አባል የሆነው ፋዕድ አብሽር የሱፍ ከቦሳሶ ሶማሊያ በሃርጌሳ ፑንትላንድ በኩል አድርጎ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በቁጥጥር ሥር ውሏል። ሙህመድ ጉሀድ ቡዲል የተባለው ተጠርጣሪ ደግሞ ሶማሌ ክልል በአፍዴር ዞን ምዕራብ ኢሚ ወረዳ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዉሏል።
ሌላ የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባል የሆነ ሰይድ ዑመር ሸበሺ የተባለው ተጠርጣሪ በፀጥታ አካላት በአዋሽ አካባቢ በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል።
የሸብር ቡድኖችን በመከታተል በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ለማድረግ በተካሄደው የኦፕሬሽን የጁቡቲ፣ የሶማሊላንድ፣ የፑንትላንድ፣ የአሜሪካ፤ የጣሊያን፣ የፈረንሳይና የስፔን የመረጃ ተቋማት እገዛ ማድረጋቸውን ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በመግለጫው አሳውቋል።
ከዚህ ቀደም አይኤስ በአማርኛ ቋንቋ የጽሑፍ መልዕክቶችን በቴሌግራም አማካኝነት ማስተላለፍ እንደሚጀምር ማስታወቂያ አሰራጭቶ እንደነበረ ይታወሳል።
የኢታማዦር ሹሙ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮለኔል ተስፋዬ "የአገራችን የደህንነት ጥበቃ ጠንካራ ስለሆነ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው መግባት ባለመቻላቸው፤ ፕሮፖጋንዳ ብቻ ነው የሚነዙት። ድንበር አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ጥበቃ እያደረግን ነው" ብለው ነበር።
No comments:
Post a Comment