Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, November 27, 2018

የብርቱኳን ዉለታ አለብን ከሳዲቅ አህመድ

ከሳዲቅ አህመድ
ብርቱኳንን የተዋወኳት የሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊዎች በታሰሩበት ሰሞን ነው።እራሷ ናት የደወለችልኝ። ስለታሰሩት ኮሚቴዎች ጠየቀችኝ።ስለ እስር ቤት አሰከፊነትም አጫወተጭኝ።ከድምጿ አዘኔታን፣ ርህራሄን ሰምቻለሁ። አቅሟ በቻለው መጠንም ማድረግ የሚገባትን እንደምታደርግ ቃል ገብታ ነበር።

አምንስቲ ኢንተርናሽናል ዋሽንግተን ዲሲ መጥተን በህገወጥ መንገድ ስለታሰሩት የሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች እንድናስረዳ ብርቱኳን ሁናቴዎችን አመቻቸች። በቀነ ቀጥሮውም መሰረት እኔና አብዱሰላም (የደስደስ) ያሲን ቦታው ላይ ተገኘን። ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ከብርቱኳን ጋር በግል ተወያየን።በወቅቱ ስለ ኮሚቴው የምንሰማው ነገር እንዳለ ጠየቀችን።እኔ ማስረዳቱን ስቀጥል ብርቱኳን ድንግጥ አለች።ስቅጥጥ ሲላትም አየሁ።በጣም የምትንሰፈሰፍ ሆና አገኘኋት። እስር ቤት የሚጎዳና የሚሰብር ነው። ብርቱኳን ሚደቅሳ ላሸባሪዎቹና ለማፍያዎቹ ህወሃቶች ሳትሰበር የነርሱን የተፈረካከሰ እኩይ ተግባር ለማድቀቅ የበቃች ጀግና ሴት በመሆኗ ሁሌም አክባሪዋ ነኝ። የህግ ባለሙያ የሆነው አብዱሰላም (የደስደስ) ከህግ አንጻር የኮሚቴውን እስርና በፍትህ ስርአት ዉስጥ የተፈጸመውን ሸፍጥ በተዋጣለት መልኩ አስረዳ።ተሰብሳቢው በተመስጥኦ አዳመጠ።አብዱሰላም (የደስደስ) ንግግሩን ሲጨርስ ጭብጨባው ጎላ ያለ ነበር።
በግዜው የአሸባሪነት ትርክት ( narrative) በአለም የመገናኛ ብዙኋን ላይ ናኝቷል።አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያዊ ዉስጥ አሸባሪነትን ፈብርኮ የኢትዮጵያን ሙስሊሞችን ለማስመታት ይጥራል።ያሰራቸውን ኮሚቴዎች ጂሃዳዊ ሐረካት በሚባል የሐሰት ዘጋቢ ፊልም ባሸባሪነት ፈርጆ የምእራብን ምጽዋት ለማግኘት ይንደፋደፍ ነበር-ህወሃት። ዛሬ መቀሌ በሽፍታነት የገባው የነ ጌታቸው አሰፋ ቡድን ከዚህ እኩይ ተግባር ያንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ይህንን ሴራ ለማክሸፍ ብርቱኳን ሚደቅሳ ባደባባይ ወጥታ ባትናገርም በውስጥ የተቻላትን አድርጋለች።ከተለተለያዩ አለምአቅፍ ተቋማትም ጋር ትገናኝ ነበር።በተለያቱ ግዜያትም ብርቱኳን እየደወለች ስለኮሚቴው ስትጠይቅኝ ኮሚቴዎቹ በእስር ቤት ውስጥ የሚተነፍሱትን የስቃይ ትንፋሽ እየተነፈሰች እንደሆነ ይሰማኝ ነበር።

ብርቱኳን ከህወሃት እስር ቤትና የሽብር ጥቃት ተርፋ፣ መንፈሷን በለውጥ እሳቤ አጎልብታ፣ አሜሪካ በቆየችባቸው አመታቶች በትምርቷ ተራቃ የመጠቀች ድንቅ ሴት ናት።ብርቱኳን ለብዙ ሴት እህቶች #የይቻላል መንፈስን የለገሰች፣በትግል ጣራ ላይ ወጥታ ሌሎች ሴቶችን የሳበች የሴት ተምሳሊት ናት።ዛሬ ሴቶች አገሪቷን ለመምራት ግማሹን ካቢኔ ሲረከቡ፣ሴቶች በተለያየ የስልጣን እርከን ላይ ሲቀመጡ በውስጣቸው ብርቱካናዊ ቁርጠኝነት፣ብርቱካናዊ የአላማ ጽናት አለ ቢባል የእብለት አይሆንም።ብርቱኳን የምርጫ ቦርድን መምራቱ ቢያንሳት እንጂ አይበዛባትምና ልብ ያለው ልብ ይበል።
ይህ ብርቱካናዊ የትግል ጥላ አሁንም ባሉ፣ገና በሚወለዱ ሴት ልጆች ላይ አርፎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች እርሷን መስለው ከርሷ በላይ ይሆኑ ዘንድ ምኞቴ ነው።እኛም ወንዶች ከርሷ ጥንካሬ ብዙ የምንማረው ነገር አለ ስል ብርቱዋን ብርቱካን መልካም የስራ ዘመን ይሁንልሽ እያልኩ ነው።
በዚህ አጋጣሚ ከላይ የጠቀስኩትን የአምኒስቲ ኢንተርናሽናል ስብሰባም ይሁን ሌሎች የዲፕሎማሲና የላቢ (lobby) ስራዎች ላይ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ጥያቄ የኔ ብሎ ሚዲያ ላይ ሳይወጣ በውስጥ ብዙ ስራዎችን ሲሰራ የነበረውን ዝምተኛውን ጀግና ከባዱ በላቸው ሳላመሰግን አላልፍም።

No comments:

Post a Comment

wanted officials