መገናኛ
አካባቢ የሚገኝ ፀጥ ያለ መንደር ነው። ሰባት ወይም ስምንት የሚሆኑ ልጅ ያቀፉ አፍላ ታዳጊዎች እየተሳሳቁ ከአንድ
ትልቅ ግቢ በመውጣት ላይ ነበሩ። ሁሉም ልጅ የያዙና በእድሜም ለእናትነት ገና መምሰላቸው ትኩረት ይስባል። ምን
እየተባባሉ እንደሆነ ለመስማትም ያጓጓል።
እነሱን አልፈን ወደ ውስጥ ዘለቅን።
የ23 ዓመት ወጣት
ነች። ከገፅታዋ ምንም ነገር ማንበብ አይቻልም። ገፅታዋም ሆነ ሁለንተናዋ ፀጥ ያለ ነው። ከዓመታት በፊት ወደ
እዚህ ግቢ ስትመጣ የሥራ ማመልከቻ ለማስገባት ወይም ሥራ ለመጀመር አልነበረም። ይልቁንም በእናቷ ልጅ በወንድሟ
ተደፍራ ከደረሰባት ከባድ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ለማገገምና መጠለያ ለመሻት ነበር።
የደረሰባት ነገር ሰው እንድትፈራ አድርጓት ነበርና በሙሉ አይኗ ሰው ማየት ያስፈራት፤ ቃላት አውጥቶ መናገርም ይከብዳት እንደነበር ታስታውሳለች።
"ከባድና
እጅግ አሳዛኝ ህይወት አሳልፌአለው" ትላለች ጊዜውን በማስታወስ። የጉዳቷ መጣን በህይወት እየኖርኩ ነው የማያስብል
ቢሆንም ያን ቀን አልፋ ዛሬ ቀና ብላ መራመድ ችላለች። ዛሬ የምትፈልግበት መድረስና ህልሟን መኖር እንደምትችልም
በእርግጠኝነት ትናገራለች።
ዛሬ ያኔ ተደፍራ የተጠለለችበትና ለተደፈሩ ሴቶች ድጋፍ የሚያደርገው 'የሴቶችና የህፃናት ማረፊያ' ውስጥ ለመሥራት ችላለች።
ምንም እንኳ ያን ጊዜ ማስታወስ ቢያማትም ያለፈችበት መንገድ ሴቶች ለፆታዊ ጥቃት እንዳይጋለጡ አስተማሪ ይሆናል የሚል ፅኑ እምነት ስላላት የሆነችውን ትናገራለች።
ሊያስተምራት አዲስ አበባ ያመጣት ትልቅ ወንድሟ ፖሊስ ነበር። ያኔ እሷ የ16 ዓመት ታዳጊ ነበረች። የሚኖሩት ወንድሟ በተከራየው ቤት ነበር።
"ልጅ ስለነበርኩ ብዙ ነገር አላውቅም፤ መናገርም አልችልም ነበር። ሰው ሳይ ተመሳሳይ ጥቃት ያደርሱብኛል ብዬ ፍራቻ ነበረብኝ" በማለት የነበረችበትን የሥነ ልቦና ስብራት ታስታውሳለች።
ሰው አይቷት ሚስጥሯን የሚያውቅ ይመስላት ስለነበር ትምህርት ቤት መሄድና መመለስ፤ ክፍል ውስጥ መቀመጥም እጅግ ስለከበዳት ትምህርት ቤት መሄድ አቆመች።
ወንድሟ ለአምስት ዓመታት አብረው ሲኖሩ ደፍሯታል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሦስት ጊዜም ፅንስ እንድታቋርጥም እንዳደረጋት ትገልፃለች።
ልጅነትና
የሥነ ልቦና ቀውስ እንዲሁም የወንደሟ ማስፈራራት ለማንም ምንም ትንፍስ ሳትል እንድትቆይ አድርጓት ነበር። ይኖሩ
ከነበሩበት ቤት ለቅቀው ሌላ የኪራይ ቤት የገቡበት አጋጣሚ ግን ጉዳቷን አውጥቶ ለመናገር እድል ሰጣት።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁኔታዋን ያስተዋሉት አዲሷ የቤት አከራያቸው አንድ ቀን "ለምንድነው ሰው የማትቀርቢው? ዘመዱ ነሽ ወይ?" ሲሉ ድንገት ጠየቋት።
ሁለቱም ጥያቄዎች ለእሷ እጅግ ከባድ ነበሩ። ከምትኖርበት ስቃይ መውጣት ትሻ ነበርና አለባብሶ እንደነገሩ መልስ መስጠት አልፈለገችም። በሌላ በኩል እውነቱን መናገርም መከራ ሆነባት።
እንደምንም ከራሷ ጋር ታግላ የሆነችውን ለአከራይዋ ተናገረች። በነገሩ በጣም የደነገጡት አከራይ ይዘዋት በአቅራቢያ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ለመሄድ ምንም አላመነቱም።
ከፖሊስ ጣቢያ በኋላ ነበር የተደፈሩ ሴቶችን ወደሚያስጠልለውና የሕግ አገልግሎት ድጋፍ ወደሚያደርገው የሴቶች ማረፊያ ልማት ማኅበር የተወሰደችው።
"ቤተሰብ በእኔ ፈረደ"
ነገሩ
ወደ ሕግ ከሄደ በኋላ ጉዳዩን የሰሙ ቤተሰቦቿ 'እሱ እንዲህ አያደርግም፤ ልጅ ስለሆነች ነው እንዲህ ያለ ነገር
የምታወራው' በማለት በፍፁም ሊያምኗት አልቻሉም። በተለይም ትልቅ እህቷ ካለማመን አልፋ የወንድማቸውን ስም ለማጥፋት
'ያልሆነውን ሆነ እያለሽ ነው' በሚል ብዙ ሞግታታለች ዝታባታለችም።
"ከእናቴ ውጪ ቤተሰብ ሁሉ እንደ ቆሻሻ ተፀየፈኝ" በማለት ተበዳይ ሆና እንዴት የበዳይ እዳ ተሸካሚ እንደተደረገች ትናገራለች።
በሌላ በኩል ፖሊስ ጣቢያ በሄደችበት ወቅት ያየችው አቀባበል እንደሷ ያሉ የተደፈሩ ሴቶች ይብስ ፈርተው እንዳይናገሩ የሚያደርግ እንደነበር ታስታውሳለች።
ሃዘኔታ በሌለው አንደበት 'ነይ እዚህ ጋር' 'እዛጋ' 'እስከዛሬ ምን ትሰሪ ነበር?' ተብላለች።
ይህ
የእሷ ብቻ ሳይሆን የብዙ ሴቶች አስከፊ እጣ ነው። በማህበረሰቡ እንዲህ ስላደረግሽ ነው፣ እንደዛ ባታደርጊ ኖሮ
በሚሉ የምክንያት ድርደራዎች ለመደፈራቸው ራሳቸው ጥፋተኛ ተደርገው አንገታቸውን እንዲደፉ የተደረጉ ሴቶችን ቤት
ይቁጠራቸው።
በቀድሞ መጠለያዋ በዛሬው የሥራ ቦታዋ በወንድም፣ በአባት፣ በአያቶቻቸውም ጭምር የተደፈሩና
የወለዱ ሴቶችም ጭምር አጋጥመዋታል። ሁሉም በቤተሰባቸውና በማኅበረሰባቸው ለመደፈራቸው ጥፋተኛ የተደረጉና የተወገዙ
መሆናቸውን ትናገራለች።
"እኔ ስለ ሕግ ብዙ አላውቅም፤ ግን ካለፍኩበትና ካየሁት በሕግ በኩል ያለው ነገርም ደስ አይልም።"
በተለያዩ ምክንያቶች ደፋሪዎች ነፃ ሆነው የመሄድ እድል ያገኛሉ። በተመሳሳይ በእሷ ጉዳይም ክስ ተመስርቶ የነበረ ቢሆንም ክሱ የትም ሳይደርስ፤ ወንድሟም ሳይጠየቅ መቅረቱን ትናገራለች።
"ህመሜን ተቋቁሜ ችሎት ላይ ብቆምም መጨረሻው አላማረም። እዚህ ላይ ብዙ ማለት አልፈልግም" ትላለች።
"ለመረዳት ፍቃደኛ መሆን አለብን"
ባደረገችው
ተደጋጋሚ የፅንስ ማቋረጥ የማህፀን ጉዳት ደርሶባት ለረዥም ጊዜ ህክምና ስትከታተል ቆይታለች። በዚሁ ምክንያት
ዛሬም ከባድ የወገብ ህመም ስላለባት ለቃለ መጠይቅ ባገኘናት ወቅትም በሃኪም የታዘዘ የወገብ መደገፊያ ቀበቶ አድርጋ
ነበር።
ይህ ሁሉ ቢሆንም ግን "በጣም የተጎዳሁት በሥነ ልቦና ነው። በተለይም የቤተሰቦቼ ነገር በእጅጉ ጎድቶኛል ዛሬም አልወጣልኝም" ትላለች።
ወደ ማረፊያው ከገባች በኋላም ምግብ መብላት፣ ሰው እንዲቀርባትና እንዲያናግራትም አትፈልግም ነበር። ፍላጎቷ አንድና አንድ ነበር። ይቺን ዓለም ለመተው ራሷን ለማጥፋትም ሞክራ ነበር።
በመጨረሻ ከዚህ ያወጣት የተደረገላት የሥነ ልቦና ድጋፍ እንደሆነ ትናገራለች።
ደህና
ሆና ወደ ራሷ ከተመለሰች በኋላ ደግሞ የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎችን ወስዳለች። የሴቶች ማረፊያ ልማት ማኅበር ከሙያ
ስልጠና በተጨማሪ ለተደፈሩ ሴቶች ራሳቸውን ከጥቃት መከላከል ይችሉ ዘንድ የቴኳንዶ ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን እሷም
ይህን ስልጠና ወስዳለች።
ሰዎች በጣም ሲጎዱ ብዙ ነገር አይፈልጉም። ምንም ነገር መስማትም መረዳትም
ላይፈልጉ ይችላሉ። "ቢሆንም ግን ሰውን መርዳት የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች ስላሉ መጀመሪያ እኛ ለመረዳትና ወደፊት
ለመራመድ ፍቃደኛ መሆን አለብን" ትላለች።
ካጋጠማት አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃትና ሰቆቃ ለመውጣትና ከባዱን ቀን ለማለፍ ብርታት ያገኘችው ከእራሷ ነበር። "ራሴን ማመኔ፣ የተበላሸ ህይወቴን ማስተካክል እንደምችል ማመኔ ረድቶኛል" ትላለች።
ባይናገሩም
ከእሷ የበለጠ ከባድ ነገር ያሳለፉ ሴቶች ይኖራሉ ብላ ታስባለች። ማህበረሰቡ የእንደዚህ ያሉ ሴቶችን ታሪክ ሰምቶ
መጠቋቆሚያ እያደረገ እንደገና ቁስላቸውን ባያደማ በታሪካቸው ብዙዎች እንዲማሩና የተሰበሩትም ቀና እንዲሉ ማድረግ
ይቻል ነበር የሚል እምነት አላት።
"ሻርፕ ጠምጥመው ስብር ብለው የሚሄዱ ሴቶች ሳይ ሁሌም የእኔ ታሪክ
ይመስለኛል" የምትለው ወጣቷ በእንደዚህ ያለ አጋጣሚ ለምታገኛቸው ሴቶች ምንም ባታደርግላቸው እንኳ ገፍታ
እንደምታናግራቸውና እንደምትሰማቸው ትናገራለች።
ማኅበረሰቡ የሴቶች ጉዳይ ግድ እንደሚለው ከተማረና ካመነ
በብዙ መልኩ እንደ እሷ የተደፈሩ ሴቶችን ሊያግዝ የሚችልበት መንገድ እንዳለ ታምናለች። ከሁሉም በላይ ደግሞ በዚህ
ጥቃትን መከላከልም እንደሚቻል ይሰማታል።
ህፃናትም
ይሁኑ ታዳጊዎች ያሉት ቤተሰብ በሉ፣ ጠጡ፣ ለበሱ እና ትምህርት ቤት ሄደው መጡ፤ ከሚለው ባሻገር ቤት ውስጥም ሆነ
ውጪ ልጆቹ ላይ ጥቃት ሊፈፀም እንደሚችል ማወቅ አለበት። ይህም ልጆችን ለመጠበቅ ያስችላል ትላለች።
"ማን ይፈልገኛል?"
የቀድሞው
ፆታዊ ጥቃት ተከላካይ ማኅበር የአሁኑ የሴቶች ማረፊያ ልማት ማህበር በደረሰባቸው ጥቃት የተጎዱ፣ የተሰበሩና 'ማን
ይፈልገኛል?' ብለው ራሳቸውን ማጥፋት የፈለጉ በርካታ ሴቶችን ለመደገፍ ጥረት ያደርጋል። ለተደፈሩ ሴቶች የሕግ
ድጋፍና የሙያ ስልጠና በመስጠት ከ15 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።
የድርጅቱ መስራች ወ/ሮ ማርያ ሙኒር ማን
ይፈልገናል? በሚል ራሳቸውን ለማጥፋት ሞክረው የነበሩ ሴቶች ከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለው ህይወታቸው ተቀይሮ
ማየት ለሳቸው ትልቅ ነገር እንደሆነ በየጊዜው ምሳሌ የሚሆኑ ሴቶችን ታሪክ ለሚያወጣው 'ተምሳሌት ገፅ' ተናግረዋል።
ማኅበሩ
በአዲስ አበባ፣ በደሴና በሌሎች ቅርንጫፎቹ እያገለገሉ የሚገኙ ኢንጅነሪንግ፣ ማኔጅመንትና ሌላ ሌላም ያጠኑ ወጣት
ሴቶችን አቅፏል። ታሪኳን የነገረችን ወጣትም አዲስ አበባ ውስጥ በሙያ አሰልጣኝነትና በሃላፊነት እያገለገለች ነው።