Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, February 16, 2019

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ዳንኤል በቀለ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር እንዲሆኑ አቶ ዳንኤል በቀለ መንግሥት ያቀረበላቸውን ጥያቄ ተቀበሉ


በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ  አቶ ዳንኤል በቀለ  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር እንዲሆኑ መንግሥት ያቀረበላቸውን ጥያቄ መቀበላቸው ተሰማ።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች  እንዳረጋገጡት አሜሪካን የሚገኙት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ዳንኤል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን በኮሚሽነርነት እንዲመሩ መንግሥት ላቀረበላቸው ጥያቄ ፈቃደኛ ሆነዋል።

ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ለሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ኮሚሽነሮች የሚሾሙት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያቋቁመው ኮሚቴ ዕጮዎችን ተቀብሎና መዝኖ ከመረጠ በኋላ ለምክር ቤቱ በማቅረብ ሲፀድቅ ነው።
በዚህም መሠረት ዕጩዎችን የሚያቀርበው ኮሚቴ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ  አቶ ዳንኤል በቀለን  በዕጩ ኮሚሽነርነት እንደመዘገባቸው ገልጸዋል።
አቶ ዳንኤል በቀለ በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ማግሥት መንግሥት ባቀረበባቸው ክስ ከዓመት በላይ ታስረው እንደነበር ይታወሳል።
በወቅቱ አክሽን ኤድ ተብሎ የሚታወቀው ዓለም አቀፍ የሲቪክ ማኅበር ባልደረባ ነበሩ።
ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ከአገር በመውጣትና መቀመጫቸውንም በኬንያ በማድረግ፣ አምነስቲ ለተባለው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የምሥራቅ አፍሪካ ተወካይ በመሆን የኢትዮጵያንም የሰብዓዊ መብት አያያዝ ይከታተሉ ነበር።
በመቀጠልም ዋና መቀመጫውን በአሜሪካ ላደረገው ታዋቂው ‹‹ሂውማን ራይትስ ዋች›› የተባለ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር በመሆን፣ ለረዥም ዓመታት ኒውዮርክ በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤቱ ሲያገለግሉ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአንድ ወር እረፍት ከመበተኑ አስቀድሞ ጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ፣ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዕጩ ኮሚሽነር አቅራቢ ኮሚቴ አቋቁሟል።
ምክር ቤቱ 11 አባላት የያዘ ኮሚቴ ማቋቋሙ ነው የተነገረው።
ኮሚቴውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ በሰብሳቢነት ይመሩታል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተወካይ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጉባዔ ተወካይ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ተወካይ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ተወካይ ለኮሚቴው በአባልነት ከተመረጡት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
የተቀሩት ደግሞ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል የተመረጡ መሆናቸውን ሪፖርተር ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials