Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, February 16, 2019

አምስት ነጥቦች ስለቀጣዩ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ

የሰው ስብስብ


ኢትዮጵያ አራተኛውን አጠቃላይ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ከመጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም አንስቶ ልታካሂድ ሽር ጉድ ላይ ናት። የሕገ መንግሥቱ 103ኛ አንቀፅ ቆጠራው በየአስር ዓመቱ መከናወን እንዳለበት ይደነግጋል። ይሁንና በ1999 ዓ.ም እንደተካሄደው ሦስተኛው ቆጠራ ሁሉ ይሄኛውም አስቀድሞ ከተተለመለት ጊዜ ከአንድ ዓመት በላይ ተራዝሟል።
1. ሕዝብ እና ቤት ቆጠራው ለድብልቅ ማንነቶች እውቅና ይሰጣል?
ሦስተኛው የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ውጤት ይፋ በሆነበት ወቅት ከተለያዩ አካላት ነቀፌታዎችን ማስተናገዱ ይታወሳል። በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ እና የአማራ ክልል ሕዝቦች ቁጥሮች ጋር በተያያዘ የቆጥራውን ውጤት የመጠምዘዝ ሥራ ተከውኗል ሲሉ የሚያጣጥሉት አሉ።
አራተኛው ቆጠራ የሚከናወነው ከፍ ባለ ጉጉት ከሚጠበቀው ከቀጣዩ ምርጫ አንድ ዓመት በፊት እንዲሁም በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ራስን የማስተዳደር ጥያቄዎች በተበራከቱበት ወቅት ነው። ቆጣሪዎች የሚመለመሉት ደግሞ በየአካባቢው ባለስልጣናት ነው።

የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ እና የብሔራዊ ስታትስቲክስ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ቢራቱ ይገዙ ቆጠራው ፖለቲካዊ ግብ ባይኖረውም፤ ለፖለቲካ ውሳኔዎች እና ፍላጎቶች ግብዓት መሆኑ ስለማይቀር የሚሰበሰበውን መረጃ ለራስ ፍላጎት እንደሚመች አድርጎ የመነካካት ዝንባሌ አንዱ ስጋታቸው መሆኑን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ይህን ለመቆጣጠር በዚህ ቆጠራ ላይ ተግባራዊ የሚደረጉ በቴክኖሎጂ የታገዙ አሠራሮች አንድ መላ እንደሚሆኑ ይናገራሉ። ለቆጣሪዎቻቸው ይህን የሚመለከት ስልጠና እንደሚሰጡ፤ ተጠያቂነት እንደሚኖርባቸውም አስረግጠው እንደሚያሳውቋቸውም አቶ ቢራቱ አክለው ያስረዳሉ።
ከሚጠበቀው በተለየ የተጋነነ ለውጥ ካለ "በወረዳና በቀበሌ ያሉ የመስክ ታዛቢዎችን ለምን እንዲህ ያለ ልዩነት እንደመጣ ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ እንጠይቃለን፤ በጣም የተለየ ከሆነ ደግሞ ገለልተኛ ታዛቢ እንዲላክ ይደረጋል" ብለዋል።
በምርጫ መጠይቅ ከሚሞሉ መረጃዎች አንደኛው የተቆጣሪዎቹ ብሔር ሲሆን፤ ድብልቅ የብሔር ማንነቶች ያሏቸው ተቆጣሪዎች አንደኛውን የመምረጥ ግዴታ እንደሌለባቸው የሚያስረዱት አቶ ቢራቱ "ብሔርን፣ ኃይማኖትን በተመለከተ መልስ ሰጭው የሰጠው ብቻ ነው የሚሞላው" ይላሉ። መረጃውን የሚሞላው ሰው በዚህ ጉዳይ ላይ የራሱን ብያኔ የመስጠት ስልጣን የለውም።
ድብልቅ የብሔር ማንነት ያላቸውም ሆነ፤ የብሔር ማንነታቸውን መግለፅ የማይፈልጉ ሰዎች ይህንኑ ለቆጣሪያቸው ቢናገሩ፤ ቆጣሪያቸው የሚሞላው ወይንም የምትሞላው ኮድ አለ ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።
2. ለሕዝብ እና ቤት ቆጥራው ምን ያህል ዝግጅት ተደርጓል?
ኢትዮጵያ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራውን ለመጀመሪያ ጊዜ በዲጂታል መሣሪያዎች የምታከናውን ሲሆን ለዚሁ ተግባር ያገለግላሉ የተባሉ 180 ሺህ ታብሌቶች ከአንድ ዓመት በፊት ተገዝተዋል።
ታብሌቶቹ ከኃይል መቆራረጥ ጋር በተያያዘ ችግር እንዳይገጥማቸው ታስቦም በመጠባበቂያነት የሚያገለግሉ 126 ሺህ ተንቀሳቃሽ የኃይል ማከማቻዎች (ፓወር ባንኮች) እንዲሁም 30 ሺህ በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ የባትሪ አቅም መሙያዎች (ቻርጀሮች) ግዥ ተፈፅሟል።
አቶ ቢራቱ ይገዙ ቆጠራውን በዲጂታል መሣርያዎች ማድረጉ "ለጥራት ቁጥጥርም፣ ለክትትልም፣ በጊዜ ለማድረስም፣ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍም" የተሻለ አማራጭ እንደሚሆን ታምኖበት የተወሰነ ነው ይላሉ።

ሌላኛው የተከናወነው ሥራ የቆጠራ ክልል ማዘጋጀት ሲሆን እርሱም ሁለት ዓመታትን ወስዷል እንደ አቶ ቢራቱ ገለፃ። በዚህም መሠረት በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም ቀበሌዎች በቆጠራ ክልልነት ተሸንሽነዋል።
በገጠር ቤቶች ዘርዘር ብለው እንደመገኘታቸው ከአንድ መቶ እስከ አንድ መቶ ሃምሳ ቤተሰቦች በአንድ የቆጠራ ክልል የተጠቀለሉ ሲሆን በከተማ ደግሞ የቤቶቹ ቁጥር ከአንድ መቶ ሃምሳ እስከ ሁለት መቶ ከፍ ይላል። የቆጠራ ክልሎቹ መገኛ በዓለም አቀፍ የአቀማመጥ ሥርዓት (ጂፒኤስ) ነጥባቸው ተወስዷል።
እያንዳንዱ ቆጣሪ ከተሰጠው የቆጠራ ክልል ውጭ ቢንቀሳቀስ ዲጂታል መሣርያው አይሰራለትም ሲሉ አቶ ቢራቱ ገልፀዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ አንደኛው ስጋት የሳይበር ጥቃት ሊፈፀም ይችላል የሚል እንደሆነ የተናገሩት አቶ ቢራቱ ይህን በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራን ነው ብለዋል።
3. ውጤቱ መቼ ይፋ ይሆናል?
በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ የሚስተዋለው ያለመረጋጋት የቆጥራውን ሒደት ሊያወከው ይችል እንደሆነ በቢቢሲ የተጠየቁት አቶ ቢራቱ፤ ስጋቱ ቢኖርም ሥራችንን ሊያውከው ይችላል ብለን አንጠብቅም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በአስረጂነት የሚያነሱትም የቆጠራ ክልል ሲዘጋጅ በነበረበት በ2009 ዓ.ም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ተቃውሞ እና ያለመረጋጋት የነበረ ቢሆንም፤ ሥራቸው ላይ እንቅፋት የተፈጠረባቸው አጋጣሚዎች ያለመኖራቸውን ነው።

አቶ ቢራቱ ቆጠራውን ለማካሄድ ከሰባት እስከ አስር ቀናት እንደሚወስድ ይገልፃሉ።
ቆጠራው ከተከናወነ በኋላ የተሰበሰበውን መረጃ የመተንተን ሥራ የሚቀጥል ሲሆን፤ ውጤቱን ሕጉ የሚያስገድዳቸውን ሒደቶች አልፎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀ በኋላ ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ ስድስት ወር ገደማ ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል።
4. ማን ምን ይጠየቃል?
ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራው መጠይቆች በአምስት ቋንቋዎች ተዘጋጅተዋል። ከአማርኛ በተጨማሪም ኦሮምኛ፣ ሶማሊኛ፣ ትግርኛ እና አፋርኛ መጠይቁ የተሰናዳባቸው ቋንቋዎች ናቸው።
መሠረታዊ መረጃን ከሚያመላክቱ ዕድሜ፣ ፆታ፣ ኃይማኖት፣ ብሔር፣ የሥራ ስምሪትና የመሳሰሉ ጥያቄዎች በተጨማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ የአካል ጉዳት መረጃ እና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ደረጃ ማለትም የተንቀሳቃሽ ስልክ እና ኢንተርኔት ተጠቃሚነት መረጃዎችም ይጠየቃሉ።
በኢትዮጵያ የሥነ ምድር ክልል ውስጥ የሚገኙ ዜጎችም ሆኑ ስደተኞች የሚቆጠሩ ሲሆን የሕግ ታራሚዎችን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችን እና የጎዳና ተዳዳሪዎችን የሚመለከቱ ልዩ የመጠይቅ ዓይነቶችም አሉ ሲሉ የቆጠራ ኮሚሽኑ ዋና ጸሐፊ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ከዓለም ቀዳሚ ያደረጓትን ቁጥራቸው በሚሊዮን የሚቆጠር ተፈናቃዮችን አስመልክተውም፤ መንግሥት በሚቀጥሉት ሁለት ወራት በተቻለ መጠን ወደቀያቸው "ለቆጠራውም፣ ለሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሲባል" እንዲመለሱ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል። ይህ ሁሉ ተደርጎም ግን ፍልሰትን የተመለከተ "የአቆጣጠር ዘዴ አለ" ይላሉ።
ተፈናቃዮቹ የቆጠራው ውጤት ይፋ ከመሆኑ በፊት ወደቀያቸው ለመመለሳቸው ማረጋገጫው ሲገኝም "መረጃውን ተከታትለን የምናስተካለው ነው የሚሆነው" ብለዋል ዳይሬክተሩ።
ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን ለቅቆ ወደውጭ አገር የሄደ የቤተሰብ አባል አለ ወይ? የሚለው ሌላኛው በአራተኛው የሕዝብ ቆጠራ ውስጥ የተካተተ አዲስ ጥያቄ ነው።
5. ቆጥራውን የሚያካሂዱት እነማን ናቸው?
ቆጠራውን በበላይነት የመምራቱ እና የማስተባበሩ ስልጣን የሕዝብ ቆጥራ ኮሚሽን ነው። በሕገ መንግሥቱ መሠረት ኮሚሽኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እጩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚፀድቁ አባላት ይኖሩታል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሚሽኑ የበላይ ሲሆኑ፤ ይመለከታቸዋል የሚባሉ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች እንዲሁም የክልል እና የከተማ መስተዳደር ኃላፊዎችን በአባልነት ያካትታል።
አጠቃላይ ዕቅዶችን መገምገም፣ አቅጣጫዎችን መስጠት፣ በከፍተኛ ደረጃ መፍትሄ የሚፈልጉ ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅት መፍትሄ መስጠት ከኮሚሽኑ ኃላፊነቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ሆኖም የቆጠራውን ቴክኒካዊ ሥራዎች የሚያከናውነው ቆጠራ በሚኖርበት ወቅት ተጠሪነቱ ለኮሚሽኑ የሚሆነው ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጄንሲ ነው።

ኤጄንሲው የቆጠራ ካርታ የማዘጋጀት ኃላፊነት አለበት። የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ያቀርባል። ለተመለመሉ ቆጣሪዎች ስልጠና ይሰጣል። የቆጠራ መረጃውን ይሰበስባል። መረጃውን ይተነትናል። ከዚያም ለኮሚሽኑ ያቀርባል። ኮሚሽኑ መረጃውን ካፀደቀው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ያስፀድቃል።
ኤጄንሲው በተጨማሪም የኮሚሽኑ ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ለቆጠራ የሚሰማሩ ሰራተኞችን መልምለው የሚያቀርቡት የክልል እና የከተማ አስተዳደሮች ናቸው። ተመልማይ ቆጣሪዎቹ የመንግሥት ሰራተኞች ሲሆኑ በአብዛኛው መምህራን፣ የግብርና ልማት ሰራተኞችና የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ይሆናሉ።

No comments:

Post a Comment

wanted officials