የኩላሊት መድከም የገጠማቸው ሰዎች ተቸግረው፣ ሕመማቸው
በርትቶ፣ ጎዳና ወጥተው ተመልክተናል፤ በየመገናኛ ብዙሃኑ የድረሱልኝ ጥሪያቸውን ሰምተናል። በአደባባዩች ፎቷቸውን
ሰቅለው ለህክምና ምፅዋት ሲጠይቁ አድምጠናል።
ሰርተው ይበሉ የነበሩ እጆች ተይዘው፣ ያስተዳድሩት
የነበረው ቤተሰብ ተበትኖ የነገን ፀሐይ ለመሞቅ ማሰብ ቅንጦት ሲሆንባቸው ማጣታቸውን ቆርሰው ያካፈሉ፣ በሙያቸው
የቻሉትን አስተዋፅኦ ያበረከቱትንም ተመልክተናል። ድምጻውያን "እኔ ነኝ ደራሽ" ሲሉም አቀንቅነው ልባችንን ነክተው ኪሳችንን እንድንዳብስ አድርገዋል። ይህ ትናንት የሚመስለው የኩላሊት መድከም ወሬ ዛሬ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል።
"እኛ ብቻ አይደለንም፤ ዘመዶቻችንም ታመዋል"
መሪማ መሐመድ ጦይብ የተሻለ ኑሮን ለመምራት በማሰብ ነበር ወደ አረብ ሀገር ያቀናችው፤ ነገር ግን ብቸኛ ሀብቴ ያለችው ጤናዋ ከዳት። ዘወትር ከብርታት ይልቅ ድካም በጎበኛት ቁጥር ሕክምና ወደ ምታገኝበት ስፍራ ሄደች።
የሰማችው ነገር ግን ጆሮን በድንጋጤ ጭው የሚያደርግ ዜና ነበር። "ሁለቱም ኩላሊቶችሽ ከጥቅም ውጪ ሆነዋል" ተባልኩኝ ትላለች። ስለዚህ ቢያንስ ሞቴን በዘመዶቼ መካከል፣ በሀገሬ አፈር ብላ ብላ ጓዟን ጠቅልላ ወደ ሀገሯተመለሰች።
አቶ አለነ ወልደማሪያም ደግሞ የስኳር ሕመምተኛ ናቸው። የስኳር ሕመምተኛ ሲኮን ካሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች መካከል የኩላሊት መድከም አንዱ እንደሆነ ያውቁ ስለነበር ሁሌም ስጋት ሽው ይላቸው ነበር።
አንዳንድ የህመም ምልክቶቻቸው ደግሞ ስጋታቸው እውን እንደሆነ እንዲሰማቸው ያደርጉ ጀመር። ወደህክምና ተቋም ሄደው ሲመረመሩ ስጋታቸው ልክ እንደሆነ አረጋገጡ፤ ኩላሊታቸው ደክሟል።
የስኳር በሽታው እና የኩላሊት ህመሙ ተደራርቦ አልጋ ላይ ጣላቸው። ሌሎች የጎንዮሽ ህመሞች መደራረብ ደግሞ አልጋ ላይ የሚቆዩበትን ጊዜ አረዘመው።
መሪማ ሀገሯ ስትመለስ ዘመድ ወዳጆች ተረባርበው ወደ ግል ሆስፒታል ወሰዷት። የሄደችበት የግል ሆስፒታል ለአንድ ቀን ለመታጠብ፣ ለመድሃኒት፣ ለታክሲና ለአንዳንድ ነገሮች እስከ ሦስት ሺህ ብር ያስወጣን ነበር ትላለች።
"ይህንን ወጪ በየቀኑ ማሰብ ከሕመሙ በላይ የሚሰማ ሕመም ነው። ይህ የሌላቸው የዘመድ እጅ ወደ ማየት ንብረት ወደመሸጥ ይሄዳሉ" ትላለች መሪማ።
አቶ አለነም ቢሆኑ ለእጥበቱ የሚወጣውን ወጪ ለመሸፈን ወደ ጎዳና ላለመውጣት ቤተሰቦቻቸው አግዘዋቸዋል። ለተከታታይ ስምንት ወራት የኩላሊት እጥበት ሲያደርጉ ቤተሰቦቻቸው ያላቸውን ንብረት ለመሸጥ ሃሳብ አቅርበውላቸው እንደነበር ይናገራሉ።
ጥሪት አሟጠው፣ ቤተሰቦቻቸውን ያለ መጠለያ አስቀርተው፣ ጤናቸውን መመለስ ግን አልፈለጉም። "ሞት እንኳ ቢመጣ አንድ ነፍሴን ይዤ እሄዳለሁ" በማለት አሻፈረኝ አሉ።
መሪማ ሰዎች የኩላሊት እጥበት ለማድረግ የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈን አቅቷቸው ሲሞቱ ስታይ ነገም የእኔ እጣ ይህ ነው በማለት የፍርሃት ቀዝቃዛ ዳና ይሰማት ጀመር።
መሪማ ሞትና ሕይወት እጣ እየተጣጣሉባት እንደሆነ ታስብ እንደነበር ትናገራለች።
ሐኪሞች በኩላሊት እጥበት መዳን እንደማይቻል፣ ኩላሊት የሚሰጥ ዘመድ ካገኙ ንቅለ ተከላ ማካሄድ ብቸኛ መፍትሄ እንደሆነ ለሁለቱም እንደነገሯቸው ያስታውሳሉ።
መሪማ እህቶቿ ወደ ህንድ ሄዳ ንቅለ ተከላ እንድታካሄድ ሃሳብ አቀረቡ። ነገርግን እህቶቿን አስቸግራ፣ አንገት ማስገቢያ ቤታቸውን ሸጠው፣ ወደ ውጪ ሄዶ የመታከም ሀሳብ በጭራሽ አልነበራትም። ስድስት ሰባት ሰው የሚጠለልበትን ቤት ለሽያጭ ማቅረብ ቤተሰቡን እንደመበተን ተሰማት።
ከዘመዶቿ ውጪም የማንንም እጅ ላለማየት ለራሷ ቃል ገብታለች። ያላት ተስፋ እጥበቱን እያካሄደች ከነገ ማህፀን የሚወለድ ተስፋን መጠበቅ ብቻ ሆነ።
ተስፋ ጠፍቶ ሐዘን ባጠላበት አንድ ቀን ጆሮዎቿ መልካም ወሬ ሰሙ።
ሕይወት በክር ጫፍ
መሪማ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት ንቅለ ተከላ እንደሚያካሂድ ስትሰማ ጆሮዎቿን ማመን አልቻለችም። ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታሉ በመምጣት ህክምና ለማግኘት ተመዘገበች።ወዳጅ ዘመድ ሁሉ ይህንን ዜና ሲሰማ ኩላሊቱን ለመስጠት ተሽቀዳደመ። አብድሩሃማን መሐመድ የመሪማ መሐመድ ልጅ ነው። ኩላሊታቸውን ለመለገስ ከተስማሙ ቤተሰቦች መካከል ቀዳሚው ነበር። ነገር ግን በተደረገለት ምርመራ እንደማይችል ተነገረው።
በዚህ ቀን እንኳ ለእናቱ ያለውን ማካፈል ባለመቻሉ አዘነ። አካሏን ከደፍላ ያኖረችው እናቱን አካሉን ከፍሎ ማኖር ባለመቻሉ ከፋው። የአክስት ልጅ የአጎት ልጅ እኛ አለን ሲሉ ተረባረቡ። የሚመረመሩት ሁሉ በአንድም በሌላም ምክንያት መስጠት እንደማይችሉ እየተነገራቸው ተመለሱ። ለመሪማ መሐመድ ኩላሊት የሚለግስ ሳይጠፋ ኩላሊቱ ግን ጠፋ።
በዚህ መሀል የአክስቷ ልጅ ሙና መሀመድ ስትመረመር መስጠት እንደምትችል ታወቀ። "ለአክስቴ መዳን ምክንያት በመሆኔ ደስተኛ ነኝ" ትላለች ሙና። መሪማ ግን "ለአቧቷ አንድ ሴት ልጅ፣ ያልወለደች፣ ያልከበደች እንዴት ኩላሊቷን ወስጄ በአንድ አስቀራታለሁ" ስትል አሻፈረኝ አለች።
አቶ አለነ ወልደማሪያም ከሐኪማቸው ንቅለ ተከላ በሐገር ውስጥ ማግኘት እንደሚችሉ ሲነገራቸው 'እራሴን ለማኖር የሌላ ሰው ኩላሊት እንዴት እወስዳለሁ' የሚል ሀሳብ ፈትሮ ያዛቸው። በሕይወት መንገድ ላይ ራሳቸውን አስቀድመው ያዩ ስለመሰላቸው አንገራገሩ።
ሐኪሙ ግን በአንድ ኩላሊት መኖር እንደሚቻል በመንገር ለማሳመን ሞከሩ። እህት ወንድሞቻቸውም እኛ እያለን ወንድማችን አልጋ ይዞ አይቀርም በሚል ተረባረቡ።
የመኖር ዋጋው፣ የነገን ፀሐይ ማየት፣ በወዳጅ ዘመድ መካከል በፈገግታ ታጅቦ የመገኘት ዋጋ ውድ ነው የሚሉት አለነና መሪማ የዘመዶቻቸውን ስጦታ ተቀብለው ንቅለ ተከላው ተካሄደላቸው።
ህክምናው ደግሞ በአብዛኛው በነፃ የሚሰጥ መሆኑ የበለጠ ደስታቸውን አድልቦታል። ሁለቱም መድሃኒቱን ለመግዛት ብቻ ገንዘብ እንደሚያወጡ ተናግረዋል።
"በአንድ ኩላሊት የሚኖር ሰው ስጋት ሊኖረው አይገባም"
ዶ/ር ብርሃኑ ወርቁ የኩላሊት ስፔሻሊስት ሲሆኑ በጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማዕከል ይሰራሉ። በሆስፒታሉ ማንም ሰው የኩላሊት መድከም ካጋጠመው መጥቶ በነፃ መታከም ይችላል የሚሉት ዶ/ር ብርሃኑ ነገር ግን ታማሚው ኩላሊት የሚለግሰው፣ ዘመድ የሆነ አንድ ሰው ሊኖረው ይገባል ሲሉ ያስረዳሉ። ዝምድና ካላቸው ሰዎች ብቻ የኩላሊት ልገሳውን የሚቀበሉት በዋናነት ህገወጥ የአካል ሽያጭን ለመከላከል እንደሆነ ያስረዳሉ።
የኩላሊት ንቅለ ተከላ እንዲካሄድላቸው የሚፈልጉ ሕሙማን ማሟላት ካለባቸው ነገሮች መካከል አንዱ ኩላሊቱን ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ፣ እድሜው በራሱ ለመወሰን የሚያስችለው ደረጃ ላይ የሚገኝ ሰው ማምጣት እንደሆነ ዶ/ር ብርሃኑ ይናገራሉ።
ሌላው የኩላሊትም ሆነ ሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች የሌሉበት፣ በተለይ በረዥም ጊዜ በራሳቸው የኩላሊት መድከም ሊያመጡ የሚችሉ ህመሞች የሌሉበት ግለሰብ መሆን አለበት ይላሉ። አክለውም ኩላሊት የሚሰጡ ሰዎች ከመስጠታቸው በፊት አስፈላጊው ምርመራ ሁሉ እንደሚደረግላቸውም ያስረዳሉ።
በአንድ ኩላሊት የሚኖሩ ሰዎች የተለየ ስጋትና ፍራቻ ሊኖራቸው አይገባም የሚሉት ዶ/ር ብርሃኑ ለጋሾችምሆኑ ተቀባዮች ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ መምራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ይመክራሉ።
ኩላሊታቸውን የሚለግሱም ሆኑ የሚቀበሉ በአግባቡ የህክምና ክትትላቸውን ማድረግና የሕክምና ባለሙያዎችን ምክር መከተል ያስፈልጋቸዋል የሚሉት ዶ/ር ብርሃኑ፤ ንቅለ ተከላውን ያደረጉ ሰዎች ደግሞ አዲሱ ኩላሊታቸው ከእነርሱ ጋር አብሮ የሚቆየው መድሃኒታቸውን በአግባቡ መውሰድ እስከቻሉ ድረስ ብቻ ስለሆነ የሐኪሞችን ምክር መከተል የግድ ነው ይላሉ።
"የኩላሊት መድከም ገጥሟቸው ንቅለ ተከላ የሚካሄድላቸው ሕሙማን የወሰዱት የሌላ ሰው ኩላሊት ስለሆነ ሁሌም አዲሱ ኩላሊት ሰውነታቸው ውስጥ እንግዳ ሆኖ ነው የሚኖረው" የሚሉት ዶክተሩ መድሃኒታቸውን ካልወሰዱ አካላቸው ኩላሊቱን እንደባዕድ ስለሚቆጥረው ይታመማሉ ይላሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ የኩላሊት ንቅለ ተከላ በብቸኝነት የሚሰጠው የመንግሥት የጤና ተቋም ቅዱስ ጳውሎስ ሲሆን አገልግሎቱን መስጠት ከጀመረ ሦስት ዓመት እንደሆነው ዶ/ር ብርሃኑ ይናገራሉ። እስከ አሁን ድረስ በማዕከሉ አንድ መቶ ያህል ሰዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላውን አካሂደዋልም ይላሉ።
No comments:
Post a Comment