እጅግ ከሚወደዱና ከተጨበጨበላቸው ፎቶግራፎች አንዱ ነው። በአሜሪካ ብቻም ሳይሆን በዓለም ዙርያ ይህ ምስል ተወዳጅ ነው። ዝነኛም ነው። ስሜት ኮርኳሪም ነው። ያለ ምክንያት ግን አይደለም።
2ኛው የዓለም ጦርነት ማብቃቱን ተከትሎ አንድ የአሜሪካ ጦር መርከበኛ ድንገት በኒውዮርክ ጎዳና ላይ የነበረችን ቆንጆ ጎተት አድርጎ ከንፈሯን ጎረሰው። ምንም አላስተረፈም።ያን ቅጽበት የፎቶ ጥበበኛው አልፍሬድ አይዠንስታድ በካሜራው አስቀረው። ያ ምሥል 'ላይፍ' በተባለው መጽሔትም ታተመ። ከዚያ ወዲህ በመጽሔቱ ብቻ ሳይሆን በሚሊዮኖች ልብ ላይ የታተመ የዓለማችን እጹብ ድንቅ ፎቶ ሆኖ ኖረ።
ያ ጎበዝ ሳሚ መርከበኛ ስሙ ጆርጅ ማንዶሳ ይባላል። በተወለደ በ95 ዓመቱ ትናንት ማረፉ ተሰምቷል።
የ21 ዓመቷ ተሳሚ ቆንጆ ግሬታ ዚመር ፍሬድማን ትባላለች። በ2016 ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው። ኖራ ኖራ በ92 ዓመቷ ማለት ነው።
የፎቶግራፍ ጥበበኛው አልፍሬድ አይዠንስታድ ያኔ ሳሚና ተሳሚዎቹ እነማን እንደሆኑ ሁሉ አልገለጸም ነበር። ኋላ ነው ነገሩ ይፋ የሆነው።
እንደመታደል ኾኖ መርከበኛው የደንብ ልብሱን ለብሶ ድንገት እየበረረ አንዲትን ቆንጆ ሲስም ቅጽበቱን በካሜራ ቀለበው። ነገሩ ችሎታ ከምንለው ዕድል ብንለው ይቀላል። ይህ የሆነው ነሐሴ 14 ቀን 1945 ነበር።
"ድንገት በካሜራዬ ሌንስ ውስጥ አንድ ጉብል [ከሰልፍ መስመር ወጥቶ] ድንገት አንዲት ኮረዳን እንቅ አድርጎ ሲስማት ተመለከትኩ። የካሜራዬን ቁልፍ ተጫንኩት። ኮረዳዋ ነጣ ያለ የነርስ ደንብ ልብስ ነበር የለበሰችው። [ጎልታ ትታየኝ ነበር] እንዲያ ባትለብስ ኖሮ ይህን ምስል ስለማግኘቴ እጠራጠራለሁ" ብሎ ነበር፤ አልፍሬድ።
ወይዘሪት ፍሬድማን ያኔ የጥርስ ሐኪም ረዳት ነበረች። ስለዚያ አስደናቂ ፎቶግራፍ ያወቀችው ግን ምስሉ ከወጣ ከ16 ዓመት በኋላ በ1960 ነበር።
"ያን ያህልም እኮ የፍቅር መሳሳም አልነበረም። እንዲሁ በፈንጠዚያ ላይ ነበርን፤ በቃ ይኸው ነው" ብላ ነበር፤ ስለዚያ ፎቶግራፍ ስትናገር።
ዓለም ግን ይህን ፎቶግራፍ በዚያ መንገድ አልወሰደውም። ከብዙ እልቂት በኋላ ጃፓን ለአሜሪካ ጦር እጅ የሰጠችበትና የአሜሪካ አሸናፊነት የተበሰረበት ዕለትም በመሆኑ የዚያ ፎቶግራፍ ትርጉምና ዝና በአያሌው ገዝፎ ኖሯል።
No comments:
Post a Comment