በመስቀል አደባባይ የተሰነዘረው የቦምብ ጥቃት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመግደል ነው ተባለ
በአዲስ አበባ ከተማ ሰኔ 16/2010 በመስቀል አደባባይ የተሰነዘረው የቦምብ ጥቃት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን ለመግደል የተቀነባበረ መሆኑን አቃቤ ሕግ ገለጸ።
ድርጊቱን የፈጸሙትም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/ ደጋፊዎች መሆናቸውም ተመልክቷል።
በተጠርጣሪዎቹ ላይ ዛሬ በይፋ ክስ መመስረቱም ታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹ ከሱሉልታ ተነስተው ጥቃቱን መፈጸማቸውም ተመልክቷል።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ላይ ግድያ ለመፈጸም የተንቀሳቀሱት ግለሰቦች ኬንያ ላይ የተቀነባበረውን ርምጃ ሱሉልታ ላይ መክረው አዲስ አበባ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ መንቀሳቀሳቸውን ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሪፖርት መረዳት ተችሏል።
ጌቱ ግርማ፣ብርሃኑ ጃፋር፣ጥላሁን ጌታቸው፣ባህሩ ቶላና ደሳለኝ ተስፋዬ የተባሉት ግለሰቦች ዛሬ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአሸባሪነት ክስ የተመሰረተባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመግደል በተቀነባበረው ሒደት ውስጥ በተለያየ ደረጃ ተሳታፊ ሆነው በመገኘታቸው ነው ተብሏል።
ሰኔ 16/2010 በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተቃጣውን ግድያ ያቀነባበረችው ኬንያ የምትገኝ ገነት ታምሩ በቅጽል ስሟ ቶሎ ሺ ታምሩ የምትባል እንደሆነችም በክሱ ተመልክቷል።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ላይ ግድያ በመፈጸም በሃገሪቱ በመታየት ላይ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ ተንቀሳቀሱ የተባሉት ሰዎች “ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የድጋፍ ሰልፍ መካሄድ የለበትም፣ሰልፉን የጠራው ገለልተኛ ወገን ሳይሆን ኢሕአዴግ ነው፣ሰልፉ በአሜሪካ ኮንግረስ የጸደቀውን ኤች አር 128 ተግባራዊ እንዳይሆን ያደርጋል”የሚሉ መነሻዎችን ይዘው መንቀሳቀሳቸውን አቃቤ ሕግ ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸውና እንደማይፈለጉ አድርጎ ለማሳየትም ጥቃቱ መቀነባበሩ ተመልክቷል።
በዚህም መነሻነት አንደኛው ተከሳሽ ጌቱ ግራም ኬንያ ከምትገኘው ገነት ታምሩ ጋር በመገናኘት ሰልፉ እንዳይካሄድና እንዲበተን መሞከራቸውን አቃቤ ሕግ ገልጿል።
ጌቱ ግርማ ከገነት ታምሩ መመሪያውን ከተቀበለ በኋላ ከ2ተኛው ተከሳሽ ብርሃኑ ጃፋር ጋር ሱሉልታ ላይ ስለተልዕኮው አፈጻጸም መምከራቸው ተገልጿል።
በዚህም ብርሃኑ ጃፋር ቦምብ እንዲያዘጋጅና ቦምቡንም የሚወረውር ሰው እንዲያፈላልግ በተሰጠው መመሪያ መሰረት ሶስተኛውን ተከሳሽ ጥላሁን ጌታቸውን ሒደቱ ውስጥ ማስገባቱን አቃቤ ሕግ ገልጿል።
2ኛው ተከሳሽ ብርሃኑ ጃፋር ሁለት ኤፍ ዋን አንድ የጭስ ቦምቦችን በማዘጋጀት በአንደኛው ተከሳሽ ጌቱ ግርማ ቤት ማስቀመጣቸው ተገልጿል።
በሰልፉም ዕለት ተከሳሶቹ ከሱሉልታ በመነሳት በጌቱ ግርማ አማካኝነት የቦምብ ጥቃቱን መፈጸማቸው ተዘርዝሯል።
እነዚህ ግለሰቦች ሐገሪቱ መመራት ያለባት በኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/ነው በሚል አላማ መንቀሳቀሳቸውም ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ የተያዙት ቦምብ ወርዋሪዎችም ሆኑ በኬንያ ያለችው አቀነባባሪ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ ጋር ግንኙነት ይኑራቸው አይኑራቸው በክሱ ውስጥ የተጠቀሰ ነገር የለም።
በጥቃቱ 2 ሰዎች ሲገደሉ ከ150 በላይ መቁሰላቸው ይታወሳል።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ከዚህ የቦምብ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው መታሰራቸው የተገለጸ ቢሆንም በዚህኛው ክስ ውስጥ ግን አልተካተቱም።
አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ድርጊቱን ያቀነባበሩት ካልተያዙ የበላይ አለቆቻቸውና ከሌሎች ግለሰቦች ጋር መሆኑን ፖሊስ ፣መግለጹ ይታወሳል።
አቃቤ ሕግ በእኚህ የቀድሞ ባለስልጣንና በኬንያ በምትገኘው ገነት ታምሩና በሌሎች መካከል ያለውን ግንኙነት መሰረት አድርጎ በቀጣይ ክስ ሊመሰርት እንደሚችልም የህግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
አቶ ተስፋዬ ኡርጌ የወንጀል ሒደቱን በዝርዝር አጋልጠው ከተናዘዙ በተያዙና ባልተያዙ ግለሰቦች ላይ በአቃቤ ሕግ ምስክርነት ከቀረቡ ከክሱ ሊወጡ እንደሚችሉ የሕግ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።
No comments:
Post a Comment