የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/አብን/በመላ ሃገሪቱ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ጥሪ አቀረበ።
ንቅናቄው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ ከሕግ አግባብ ውጭ ከአማራ ክልል የተወሰዱ መሬቶች እንዲመለሱ፣እንዲሁም ይህንን የመብት ጥያቄ ባነሱ ወገኖች ላይ የሚደርሰው እስር፣እንግልትና ማፈናቀል ይቁም ሲልም ጥሪ አቅርቧል።
በመተከል፣በጅጅጋ፣በቡራዩና አካባቢው እንዲሁም በጉራጌ ዞን ማረቆና ወለኔ ለተከሰተው ግጭትና እልቂት መንግስት ህግና ስርአት የማስከበር ግዴታውን ባለመወጣቱ የተከሰተ ነው ሲልም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ገልጿል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ መሪዎች ትላንት አዲስ አበባ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሊቀመንበሩ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ለአማራነት መታገል ከኢትዮጵያዊነት ጋር ግጭት የለውም ብለዋል።
አማራ በአማራነቱ ባለመደራጀቱ ግን ባለፉት 50 አመታት በይበልጥም በ27ቱ አመታት ከፍተኛ በደል እንደደረሰበትም ዘርዝረዋል።
ድርጅቱ ባወጣው ባለ 8 ነጥብ የአቋም መግለጫም መንግስት የአማራ ሕዝብ የሕልውና ጥያቄዎችን በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ፣የዜጎች ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ግዴታውን እንዲወጣ፣ ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎችና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፉ ድርድሮችን እንዲያካሂድም ጥሪ አቅርቧል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከርዕዮት አለምና ከጎሳ አጥር ወጥተው፣ሕዝቦችን በእኩልነትና በፍትሃዊነት የምታስተናግድ ኢትዮጵያን የመገንባት ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል።
መንግስት እርቅ ከማድረጉ በፊት እውነታን የማጥራት ስራ እንዲሰራ የጠየቀው የአማራ ብሔራኢ ንቅናቄ/አብን/ በዘር ማጥፋት፣በጅምላ ጭፍጨፋ፣ሃገር በማፍረስና ከፍተኛ ዘረፋ የፈጸሙ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል።
ተጎጅዎችም በመንግስት በኩል ይቅርታ እንዲጠየቁና ካሳ እንዲከፈላቸም ጥሪ አቅርቧል።
No comments:
Post a Comment