Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, September 27, 2018

የናሱ እባብ የክርስቶስ ምሳሌ እንደሆነ ሁሉ በፓትርያርኩ እጅ የምናየው “በትረ ሙሴ” ትምህርት ነው



፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል “ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ” ። ዘኍ 21፣ 8- 9 ። ይኼ ምሳሌ መሆኑን ክርስቶስ ሲያስተምር “ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል” ። ዮሐ 3 ፣ 14 በማለት ምሳሌና ጥላ የነበረውን አማናዊ ለማድረግ፣ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ ያዩት ሁሉ እንደሚድኑ አመሳስሎ አስተማረበት ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የናሱን እባብ ከራሱ ስቅለት ጋራ ሲያነጻጽረው ያላፈረበትን፤ የእኛ አባቶች የናሱን እባብ ምሳሌ “በትረ ሙሴ” የሚባለውን በግራ እጃቸው፣ የተሰቀለበትን መስቀል በቀኝ እጃቸው ቢይዙ የሚያሳፍር አይሆንም፡፡
በዘመነ ብሉይ እግዚአብሔር ሕዝቡ ሲበድሉት “እባቦችን ሰደደ፥ ሕዝቡንም ነደፉ ከእስራኤልም ብዙ ሰዎች ሞቱ” ። ዘኍ 21፡6 በእባብ መርዝ ተነድፈው የታመሙ ሁሉ መርዝ በሌለው የናሱን እባብ በማየት እንዲድኑ አድርጓል። ይህም ምሳሌው ለእኛ ነው፡፡ የበደሉት እስራኤላውያን የእኛ የሰዎች ምሳሌ ሲሆኑ፤ መርዝ ያለው እባብ የዲያብሎስ ምሳሌ ነው፤ የናስ እባብ መርዝ እንደሌለው ሁሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ያለ በደሉ ተሰቅሎ ስለ እኛ ኃጢአት እርሱ የመሞቱ ምሳሌ ነው፤ “እባብን ሠርተህ በዓላማ ላይ ስቀል የተነደፈውም ሁሉ ሲያያት በሕይወት ይኖራል” ዘኍ 21፣8 መባሉ፣ የናሱን እባብ ሲያዩ የዳኑ፣ ጌታ ተሰቅሎ አይተው የዳኑ ሰዎች ምሳሌ ሲሆን፣ ከሩቅ ያሉት ሰዎች ምሳሌነት ወንጌልን ከመምህራን በመስማት ሳያዩ ቃሉን ብቻ ሰምተውና አምነው የዳኑ ክርስቲያኖች ምሳሌ ነው፡፡ ምክንያቱም በስብከታቸው “በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር” ገላ 3፣1 እንዳሉት ማለት ነው፡፡
በፓትርያርኩ እጅ የምናየው “በትረ ሙሴ” ትምህርት ነው የሚሰጠው፤ ምክንያቱም የሚታይ ሥዕልና ቅርጽ ትምህርት እንደሚሆን ሁሉ በቤተ ክርስቲያናችን አማኝ ሁሉ ጠባቂ መልአክ እንዳለው እንዲያውቅ እንዲረዳ “ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ” ዘጸ 25፣18 ባለው አምላካዊ ቃል መሠረት በቤተ ክርስቲያናችን ግንቦች ላይ ሁሉ ሥዕል ይሳላል፤ የሚመለከት ጠባቂ መልአክ ይባላሉ ብሎ እንዲያስታውስ ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው ንጉሥ ሰሎሞን “በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው አሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት ሁለት ኪሩቤል ሠራ በወርቅም ለበጣቸው" ተብሎ በዚሁ እንድንቀጥል የተሠራው የተጻፈልን 1ኛ ነገሥ 6 ፣23-35፣ 2ኛ ዜና 3፣7-13
የብሉይ ኪዳን ምሳሌ የሆነውን የናሱን እባብ ስናይ እስራኤላውያን የዳኑት በዚህ በፓትርያርኩ በግራ እጃቸው ባለው የናስ እባብ ነው ብለን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈልንን እንድናስታውስና፣ እኛ ግን የዳንነው በቀኝ እጃቸው ባለው መስቀል ላይ በተሰቀለው በኢየሱስ ክርስቶስ ነው በማለት ለመመስከር ሁለቱንም ማለትም ብሉዩንም አዲሱንም፤ የናሱን ምስልና የክርስቶስን መስቀልን ይዘው ይታያሉ፡፡ ሌላው መሪው ሙሴ የናሱን እባብ ይዞ በዓላማ ላይ ሲሰቅለው እንዳዳናቸው፤ እግዚአብሔር አብ ልጁን በመስቀል ላይ ሰቅሎ ዓለሙን ለማዳኑ መስካሪዎች ስለሆንን “በትረ ሙሴ” የሚል ስያሜ ያለውን በትር የኤጲስ ቆጶሳቱ አለቃ በእጃቸው ይዘው ይታያሉ፡፡ ሙሴ የእስራኤላውያን መሪ ነው፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ ደግሞ የሃይማኖት መሪ ናቸውና ይህን በትር ይይዛሉ፡፡
ሙሴ በትር ይይዝና ተአምራት ያደርግ ነበረ፤ “ይህችንም ተአምራት የምታደርግባትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ” ዘጸ 4፣17 ያለው እግዚአብሔር ያለ በትር ተአምር ማድረግ ተስኖት ሳይሆን አንተ መሪያቸውና ቤዛ ሆነህ የምታወጣቸው ነህ ሲለው ነው በትሩን አስይዞ የላከው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ እስጢፋኖስ “ይህን ሙሴን በቍጥቋጦው በታየው በመልአኩ እጅ እግዚአብሔር ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው” ሐዋ 7፣35 ብሎ የመሰከረለት፡፡ ለክርስቲያኖች ጠባቂና የበላይ አባት የሆኑት ቅዱስ ፓትርያሪኩም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” ተብለው አደራ የተቀበሉ ስለሆነ፣ የመሪነታቸው ምልክት ይህን በትር ይይዛሉ፡፡ ዘንግ በትር መያዝ የአባትነትና የጠባቂነት ምልክት ነው፡፡
የዕብራዊያን ሁሉ አባት ያዕቆብ ዘንግ ይይዝ እንደነበረና፣ ልጁ ዮሴፍ “በዘንጉም ጫፍ ተጠግቶ ሰገደ” ተብሎ የተጻፈው አባቱ ዘንግ ስለሚይዝ ነው ዕብ 11፣21 ፡፡ በተጨማሪም እረኛው ዳዊት “በትር ይዞ” 1ኛ ሳሙ 17፣43 በጎቹን እንደሚጠብቅና በኋላም የሕዝብ ጠባቂ ንጉሥ ሲሆን በትረ መንግሥት እንደሚይዝ ዘፍ 49፣10 ፤ የአዲስ ኪዳን እረኞችም ጠባቂነታቸውን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ተቀብለዋል “...ግልገሎቼን አሰማራ ...ጠቦቶቼን ጠብቅ ...በጎቼን አሰማራ።” ባላቸው መሠረት ከሌሎች ብፁዐን ጳጳሳት ለየት ብለው ለጠባቂነታቸው ምልክት በግራ እጃቸው “በትረ ሙሴ” እና በቀኝ እጃቸው የወርቅ መስቀል ጨብጠው ይታያሉ፡፡
የናሱ እባብ የክርስቶስ ምሳሌ እንደሆነ ሁሉ፣ በትርም የፈጣሪያችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌና ጥላ ነው፡፡ “ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፥ ከሥሩም ቍጥቋጥ ያፈራል።” ኢሳ 11፣1 ስላለ የእሴይና የዳዊት ልጅ የሆነውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ የመያዛቸው ምልክት ነው፡፡ “በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ” ሉቃስ 9፣23 ብሏልና፤ በየጊዜው መስቀለ ክርስቶስን በእጃቸው ይዘው፤ በሕይወታቸው ደግሞ መከራ መስቀልን ታግሠው እረኛነታቸውን የሚያሳዩበት ተግባራዊ ምልክት ይህ ነው፡፡
ባጠቃላይ መጽሐፍ ቅዱስ የሚባለው ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን እንደሆነ ሁሉ፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ የብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳን ምሳሌ የሆነውን፤ በግራ እጃቸው ጥንታዊቷን ያረጀችውን (ብሉይ)ን “በትረ ሙሴ”ን ተመርኩዘው፤ በቀኝ እጃቸው የተሰቀለውን የክርስቶስን መስቀል ይዘው፤ መከራ ቢመጣም መከራን ታግሰው እረኝነታቸውን በንቃት እንደሚወጡ ያሳያል፡፡እንዳንድ ወገኖች በፓትርያርኩ እጅ ያለውን በትር ከባዕድ አምልኮና ከ 666 አምልኮ ጋር አያይዘው ይጠይቃሉ ለጥያቄው መልስ የመሪነታቸውን ምልክት በግራ እጃቸው የሚይዙት “በትረ ሙሴ” ይባላል፡፡ ይህም የአባትነታቸው፣ የመሪነታቸው ምልክት እንጂ በትሩ አይመለክም፤ቢመለክ ሰባብረን እንጠለዋለን፤ የሚስመውም ሆነ የሚሰግድለት ማንም የለም፤በትሩ ለመሪነታቸው ብቻ ምልክትነት ነው የሚያገለግለው፡፡ደግሞ መዘንጋት የሌለብን አንድ ምሥጢር አለ ሰይጣን ዲያብሎስ ሁልጊዜ የእግዚአብሔር የሆነውን ነገር ሁሉ እያስመሰለ ሰዎችን ወደ እርሱ መሳብና ማሰናከል ይፈልጋል።ይህ በትረ ሙሴ በሺ ለሚቆጠሩ ዓመታት አባቶች ሲጠቀሙበት የቆየ ምልክት ነው።የ 666 አምላኪዎች ደግሞ አስመስለው በቅርብ የፈጠሩት ምልክት አለ፤ ዓላማቸው የእግዚአብሔርን ነገር ማስረሳት ነው።ሌላው ቀስተ ደመና/ሬንቦ/ እግዚአብሔር ለኖኅ ቃል የገባበት የምህረት ምልክት ነው፤ ዛሬ ግን ሰዶማውያን ያንን ምልክት የራሳቸው አስመስለው ባንዲራ ሰርተው ያውለበልባሉ ይህንን ባንዲራ ሰው ሲመለከት የእግዚአብሔርን የምህረት ኪዳን ሳይሆን የሰዶማውያንን ክብር እንዲያስብ ሰይጣን እየፈጠረ ያለው የተንኮል መንገድ ነው።ይህንን ጠንቅቀን ልናውቅ ይገባል።ዛሬም ከአባቶች ለመለየትና ከመስቀሉ ፍቅር ለማራቅ፣ከቤተመቅደስ ለማስኮብለል ዲያብሎስ በሶሻል ሚዲያ ተላላኪዎቹን አሰማርቶ የጥላቻ ዘመቻውን ቢከፍትም ድሉ ግን የእኛ የእውነተኞቹ የክርስቲያኖች ነው ክብር ለክርስቶስ ይሁን።
ስንጠቀልለው፡-
የመጀመሪያው ሙሴና እስራኤላውያን ያስታውሰናል፡፡
ኦሪት ዘኁልቁ 21፡5-9 ሕዝቡም በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ። በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? እንጀራ የለም፥ ውኃ የለም፤ ሰውነታችንም ይህን ቀላል እንጀራ ተጸየፈ ብለው ተናገሩ። እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ እባቦችን ሰደደ፥ ሕዝቡንም ነደፉ፤ ከእስራኤልም ብዙ ሰዎች ሞቱ። ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው። በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ ስለ ተናገርን በድለናል፤ እባቦችን ከእኛ ያርቅልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን አሉት።ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ። እግዚአብሔርም ሙሴን። እባብን ሠርተህ በዓላማ ላይ ስቀል፤ የተነደፈውም ሁሉ ሲያያት በሕይወት ይኖራል አለው፡፡ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ፤ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ።
በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደተረዳነው ሙሴ እስራኤላውያንን እግዚአብሔር ያድናቸው ዘንድ ከጠየቀ በኋላ እግዚአብሔር አድርግ ብሎ የሰጠው ትእዛዝ በዓላማ የናስ እባብ እንዲሰቅል ነበር፡፡ መቼም ለስሙ ክብር ይግባውና እግዚአብሔር ይህን አድርጉ ሲል የሰይጣንን ዓላማና ተግባር ፈፅሙ ለማለት ፈልጎ እንዳልሆነ የምንረዳ ይመስለኛል ፡፡ የዚህ ታሪክ ምሳሌውንና ትርጉሙን ስናየው የእባቡ መርዝ የኃጢአታችን የናሱ እባብ የመስቀሉ ምልክት ሲሆን ፣ እስራኤላውያን የናሱን እባብ አይተው እንደዳኑ ሁሉ በዘመነ ሐዲስ ክርስቲያኖች ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ከዘለዓለማዊ ኃጢአትና ሞት እንዳዳነን ያሳያል፡፡
የዮሐንስ ወንጌል 3፣14 …ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል።በመሆኑም ልክ ሙሴ የናሱን እባብ ይዞ ሕዝቡን እንዳደነበት ሁሉ የኦርቶዶክሳውያን አባቶች ደግሞ የተሰቀለውን ክርስቶስንና የክርስቶስን አዳኝነት ከፍ አርገው ይሰብኩበታል ፡፡
ሌላው ድንቅ ምሥጢር ሁለት እባብ በመስቀሉ ግራና ቀኝ መታየታቸው ከብሔሞት እስከ ሌዋታን ያለውን ዓለም፣ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ያለውን ፍጥረት ሁሉ ፈጥሮ የሚገዛው በመስቀል ላይ ለዓለሙ ሁሉ ቤዛ የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ መሆኑን ማስተማሪያ ነው።
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ መረዳት የሌላቸው ግለሰቦች በጥራዝ ነጠቅ እውቀት በመነዳት ቅድስት ቤተክርስቲያንን ለመንቀፍና ለመተቸት ሲንጠራሩ እናያለን መጽሐፍ አባትህን ጠይቅ ይነግርሃል አለ እንጂ አባትህን ስደብ አላለም።
እንደ መከራከሪያ የሚጠቅሱትም የ25 ዓመቱ ንጉሥ ሕዝቅያስ ለእሥራኤል በነገሠ ጊዜ በኮረብቶች ላይ የነበሩ የተለያዩ የማምለኪያ አፀዶችን ሲሰባብር የናሱን እባብም ሰብሮታል ስለዚህ ከዚህ በኋላ ሊታይ አይገባውም ይላሉ።ይህ ፈጽሞ ስህተት ነው ምክንያቱም ንጉሥ ሕዝቅያስ በወቅቱ የሰባበራቸው ነገሮች ሁሉ ሕዝበ እስራኤል እንደ አምላክ ያመልኳቸው የነበሩ ነገሮችን ነው ።ከግብጽ ያወጣቸው፣ባህር የከፈለላቸው፣ከዓለት ላይ ውሃ ያፈለቀላቸው ፣ሲታመሙ የፈወሳቸው እግዚአብሔር እንጂ የነሐሱ እባብ አልነበረም እነርሱ ግን እግዚአብሔርን ማምለክ ትተው የናሱን በትር ማምለክ ስለ ጀመሩ አምልኳቸውን እንዲያስተካክሉ ንጉሡ ከፊታቸው አስወግዶታል።እግዚአብሔር አምላክ ራሱ የሙሴን መቃብር ከሕዝበ እሥራኤል የሰወረባቸው መቃብሩ ላይ ሄደው ሙሴን እንዳያመልኩት ነው።እኛ ኦርቶክሳውያን ግን የምናመልከውን ጠንቅቀን እናውቃለን።
የተሰበረ ነገር ሁሉ ተሽሯል አያስፈልግም ማለት አይደለም።ለምሳሌ ጽላት ሲሰበር እግዚአብሔር ሙሴን ደግመህ ቅረጽ ብሎታል።የሰሎሞን ቤተመቅደስ ሁለት ጊዜ ፈርሶ እግዚአብሔር ግን ድጋሜ ወደ ተራራ ውጡ ቤትንም ሥሩልኝ በእርሱ ደስ ይለኛል እያለ ሕዝቡን ያዛቸው ነበረ።ስለዚህ ቅድስት ቤተክርስቲያን ለዘመናት ይዛ የቆየችው ስርዓት በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንጂ ድንገት የመጣ ነገር ስላልሆነ በማስተዋል ልንረዳ ይገባል።
እባካችሁ ሼር በማድረግ ሰዎችን ከስህተት እንመልስ።
ለበረከት ሁኑ

No comments:

Post a Comment

wanted officials