Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, December 20, 2019

''ለ 12 ዓመታት ባልተደፈረው ቦክስ ኢትዮጵያን በኦሎምፒክ መወከል እፈልጋለሁ'' ተመስገን ምትኩ



ተመስገን ምትኩImage copyrightተመስገን ምትኩ
ተመስገን ምትኩ ይባላል። ባሳለፍነው ዓመት የኢትዮጵያ ቦክስ ፌደሬሽን ባዘጋጀው የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮና በ75 ኪሎ ግራም አጠቃላይ አሸናፊ ሲሆን የዓመቱ ምርጥ ቦክሰኛ ተብሎም ተመርጧል።
ገና የ22 ዓመት ወጣት ነው። በቅርቡ ሃገሩን ወክሎ ኦሎምፒክ ላይ እንደሚሳተፍ ተስፋ ተጥሎበታል።
2005 ዓ.ም. ክረምት ላይ በታላቅ ወንድሙ ገፋፊነት በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶስት ወጣቶች ማዕከል ቦክስ የጀመረው ተመስገን ከቦክስ ይልቅ ለቴኳንዶ ፍቅር እንደነበረው ይገልጻል።
''ሰፈር ውስጥ አስቸጋሪ ልጅ ስለነበርኩ ወንድሜ ቦክሱንም እየሰራሁ ስነምግባሬም እንዲስተካካል በማሰብ ቦክስ ወስዶ አስመዘገበኝ።''
ክረምቱ መጨረሻ ላይ የውድድር ዕድል አግኝቶ አሰልጣኙ ለመወዳደር ፍላጎት እንዳለው ሲጠይቁት በደስታ ነበር የተቀበለው፤ ተመስገን።
''ድፍረትና ከነበሩት ልጆች የተሻለ ጉልበት ስለነበረኝ ለግጥሚያው ተስማማሁ። ነገር ግን ብዙም ልምድ ስላልነበረኝ በዝረራ ተሸንፌ ወጣሁ። በጣም እልህ ይዞኝ ስለነበር ያሸነፈኝን ልጅ መልሼ ለማግኘት ስል በቦክሱ በርትቼ ቀጠልኩበት።''
ምንም እንኳን በዝረራ ያሸነፈውን ቦክሰኛ ለመግጠም ብሎ በቦክሱ ቢቀጥልም ጭራሽ ክረምቱ ሲያበቃ ሁለቱም በተመሳሳይ ክለብ ውስጥ ተቀጠሩ።
በወቅቱ በ57 ኪሎ ይወዳደር የነበረ ሲሆን በ60 እንዲሁም በ 63 ኪሎም ጭምር ተወዳድሯል።
የቀድሞው ኒያላ የአሁኑ ማራቶን ክለብ ተወዳዳሪው ተመስገን በ 2006 ዓ.ም. የክፍለ ከተማዎች ውድድር አሸናፊ በመሆን አዲስ አበባን ወክሎ አዳማ ላይ በተካሄደው የሀገር አቀፍ ፕሮጀክቶች ውድድር ተካፈለ።
በውድድሩም በ 63 ኪሎ ግራም የተወዳደረው ተመስገን የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያውን ማግኘት ችሏል።
በ2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተካሄደው 'ሴሚ ፕሮፌሽናል' (የከፊል ፕሮፌሽናል) ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበረው ተመስገን በ 64 ኪሎ ግራም ወርቅ ሜዳሊያ አገኘ። በተመሳሳይ ውድድር 2010 ዓ.ም. ደግሞ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነ።
የኢትዮጵያ ቦክስ ፌደሬሽን በዓመት አራት ጊዜ የሚያዘጋጀው ብሄራዊ የክለቦች ሻምፒዮና በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ይካሄዳሉ። በ2011 ዓ.ም ድሬዳዋ ላይ በተደረገው የመጀመሪያው ዙር ውድድርም ተመስገን በ63 ኪሎ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ነበር።
ሁለተኛው ዙር ወላይታ ላይ ተካሂዶ እዛም ተመሳሳይ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ ሲሆን በደሴ በተካሄደው ሶስተኛው ዙርም አሸናፊ በመሆን ጨርሷል። የዓመቱ የመጨረሻውና አራተኛው የአዲስ አበባ ክለቦች አቋም መለኪያ ላይ ደግሞ አሁንም የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት ያለመሸነፍ ጉዞውን ቀጠለ።
በሀገር ውስጥ ውድድሮች ሁሉንም በሚባል ደረጃ አብዛኛውን በድል ማጠናቀቅ የቻለው ተመስገን በአፍሪካና በዓለም ደረጃ ሃገሩን የመወከል እድሎችንም አግኝቷል።
2010 ዓ.ም. ላይ በአፍሪካ ምድብ ሞሮኮ በተካሄደው የዓለም ወጣቶች ማጣሪያ ጨዋታ ላይ ሀገሩን ወክሎ በመሳተፍ ሶስተኛ ወጥቶ የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚም ነበር።
ተመስገን ምትኩImage copyrightተመስገን ምትኩ
በዚሁም ሃንጋሪ ለሚካሄደው የዓለም ወጣቶች ውድድር አለፈ። ነገር ግን ከውድድሩ በኋላ አንድ ያልጠበቀው ነገር ተፈጠረ። የኢትዮጵያ ቦክስ ፌደሬሽን በወቅቱ በጀት የለኝም በማለት ተመስገን ወደ ሀንጋሪ እንደማይሄድ ተነገረው።
'' ሀገሬን ወክዬ ውጤት እንደማመጣ እርግጠኛ ነበርኩ፤ የሚቆጨኝ ነገር ቢኖር እሱን ማሳካት አለመቻሌ ነው። እርግጠኛ የሆንኩበት ምክንያት በሞሮኮው ውድድር በትንንሽ ስህተቶች ነበር የተሸነፍኩት። ከአብዛኛዎቹ ተወዳዳሪዎች የተሻልኩ ነበርኩኝ፤ ነገር ግን ሀገር ውስጥ ብቻ ካገኘሁት ስልጠና አንጻር ብዙ የዓለማቀፍ ህጎችን ስለማላውቅ አንደኛ መውጣት አልቻልኩም።''
ላለፉት 12 ተከታታይ ዓመታት ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድረክ በቦክስ የሚወክላት አላገኘችም። ተመስገን ምትኩ ግን ያሉበትን ማጣሪያዎች በድል አጠናቅቆ ሀገሩን በቦክስ ወደ ኦሎምፒክ መድረክ መመለስ እንደሚፈልግ ይናገራል።

ለመሆኑ በኢትዮጵያ ያለው የቦክስ ስልጠና ምን ይመስላል?

እስከዛሬ በሄደባቸው ውድደሮችና ስልጠናዎች በሙሉ ብዙ ታዳጊ ልጆች ከፍተኛ የሆነ ተፈጥሮአዊ አቅም ቢኖራቸውም የሚያገኙት ስልጠና ግን ከልምድ የመጣ ብቻ እንደሆነ ተመስገን ያስረዳል።
''በተፈጥሮ ያገኙት አካላዊ ብቃት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መዳበር ሲገባው እንደነገሩ ስለሆነ ስልጠና የሚሰጣቸው፤ በዓለማቀፍ ደረጃ መፎካከርም ሆነ ብቃታቸውን ማሳደግ አይችሉም።'' ይላል
ከዚህ በተጨማሪም በጣም ከባድ ስልጠናዎችን ከሰሩ በኋላ የሚያገኙት ምግብ ለሰውነት ግንባታ የማይጠቅምና የላብ መተኪያ እንኳን አለመሆኑ ችግር እንደፈጠረባቸው ያስረዳል።
በአሁኑ ሰአት ለብሄራዊ ቡድን ሲመረጡ በቀን ሶስት ጊዜ ስልጠና የሚሰሩ ሲሆን፤ እያንዳንዱ ስልጠና ሶስት ሰአት የሚፈጅ ሲሆን ከሌሊቱ 11 ሰአት፣ ጠዋት ሶስት ሰአት እና ከሰአት በኋላ ዘጠኝ ሰአት ላይ ስልጠናቸውን ይሰራሉ።
''ነገር ግን ከስልጠና በኋላ እዚህ ግባ እንኳን የማይባል ወጥ ነው የሚቀርብልን። ያው ሁሌም በጀት የለንም ነው የምንባለው። እንደዚህ ደክመን ሰልጥነን ተገቢውን ምግብ ካላገኘን እንዴት ነው ከሌሎች ተወዳዳሪዎች ጋር መፎካካር የምንችለው?'' በማለት ይጠይቃል።
ከዚህም በተጨማሪ በብሄራዊ ቡድን ደረጃም ሆነ በክለብ ስልጠና የሚሰሩበት ቦታ አዳራሽ ብቻ እንጂ ተገቢው የስልጠና መሳሪያዎች እንኳን ያልተሟሉለት እንደሆነም ተመስገን ይናገራል።
''ሌላው ቀርቶ ፌደሬሽኑ ለስልጠና ጓንት ብቻ ነው የሚያቀርብልን። እንደ ቁምጣ እና ሌሎች ትጥቆችን የምናሟላው በራሳችን ነው። አንዳንዴም ባለን ልብስ ስልጠና እንሰራለን።'' በማለት ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ይናገራል።
ተመስገን ሌላው በኢትዮጵያ ያለውን የቦክስ ስፖርት ወደኋላ እየጎተተው ያለው የዳኝነት ችግር እና ከክፍያ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንደሆኑ ያስባል።
''ዳኞች ተገቢውን ዓለማቀፍ ስልጠና አያገኙም፤ ከዚህ በተጨማሪም የማዳላት ነገር ይስተዋላል። በሌላ በኩል አድካሚ ስልጠና ለሚሰሩ ቦክሰኞች የሚቀርበው ክፍያ በጣም ትንሽ ነው።'' ይላል።
በብሄራዊ ቡድን ደረጃ እንኳን ምንም አይነት ክፍያ እንኳን እንደሌለ የሚገልጸው ተመስገን ሃገር ወክለው በውጪ ሃገራት የሚሳተፉ ቦክሰኞች ምናልባት እስከ 5 ሺ ብር የሚደርስ ለተሳትፎ እንደሚሰጣቸው ያስታውሳል።
ተመስገን በ 2020 በጃፓን አዘጋጅነት ለሚካሄደው ኦሎምፒክ ሀገሩን ወክሎ ለመሳተፍ በደቡብ አፍሪካና በካሜሩን የኦሎምፒክ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ይጠብቁታል።
ተጋጣሚዎቹን በማሸነፍ በቦክስ ውድድር ሀገሩን በኦሎምፒክ ለመወከል ተስፋ ሰንቆ በአሁኑ ሰአት ስልጠናውን እያከናወነ ይገኛል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials