Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, December 24, 2019

የሞጣ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰው ቃጠሎ

የኢትዮጵያ ካርታ
ትናንት ማምሻውን በአማራ ክልል፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ የሚገኘው ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፣ ጀሚዑል ኸይራት ታላቁ መስጊድ እና አየር ማረፊያ መስጊድ ላይ ቃጠሎ መድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገለጹ።
ሆቴሎች እንዲሆም ሌሎች የንግድ ተቋሞች ላይም ጉዳት መድረሱንም በስልክ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎቹ ገልጸውልናል።
የአማራ መገናኛ ብዙሀን፤ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሰኢድ አሕመድን ጠቅሶ እንደዘገበው ትናንት አራት መስጊዶች የተቃጠሉ ሲሆን፤ የሙስሊሞች ሱቆችና ድርጅቶችም ተዘርፈዋል።
11:00 ሰዓት አካባቢ በሞጣ ጊዮርጊስ ሠርክ ጸሎት በሚደረግበት ሰዓት መነሻው ምን እንደሆነ ባልታወቀ ሁኔታ በቤተክርስቲያኑ አናት ላይ ጭስ መታየቱን የነገሩን ሞጣ ከተማ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ነዋሪ የሆኑ አንድ ግለሰብ ይህን ተከትሎ እሳት ለማጥፋት ርብርብ ነበር ይላሉ።
ቤተክርስቲያኒቱ ላይ የታየው እሳት ከጠፋ በኋላ ግን ወጣቶች በስሜት መስጊድ ወደ ማቃጠል መሄዳቸውን እኚሁ ምንጭ ለቢቢሲ አብራርተዋል።
ሕዝቡ ውሃ በማቅረብ የጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ቃጠሎውን መቆጣጠር መቻሉን የነገሩን ነዋሪው፤ ቤተ ክርስቲያኑ መትረፉን ተከትሎ ሰዓቱም መሽቶ ስለነበር ስሜታዊ የነበሩ ወጣቶች ከቁጥጥር ውጭ ሆነው በመስጊድ ላይ ጥቃት እንዳደረሱ ሰምቻለሁ ብለዋል።
እርሳቸው ግን ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ መቅረታቸውንና ከዚያ በኋላ ስለሆነው ነገር በወሬ እንጂ በዝርዝር እንደማያውቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአካባቢው ሰበካ ጉባኤ በተፈጠረው ሁኔታ ላይ ነገ ማብራሪያ ለመስጠት ቀጠሮ መያዙን፣ ሆኖም ግን በትክክል የጊዮርጊስ በቤተክርስቲያን የታየው እሳት ከምን እንደመነጨ በመጣራት ላይ እንደሆነም ገልጸውልናል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሙስሊሙና በክርስቲያኑ መካከል ቅራኔ እንዳልነበረና ሆኖም ግን ነባር ሙስሊሞችና ውሃቢ የሚባሉት ቡድኖች ጋር ቅራኔዎች እንደነበሩ ያስታወሱት እኚሁ ምንጭ ከዚህ በፊት በነበረ ስብሳባ "እኛን ሊያለያዩ ነው ብለው ደብዳቤ ጽፈውባቸው ያውቃሉ" ይላሉ። ይህ እንዴት ወደ እምነት ተቋማት ቃጠሎ ሊያመራ እንደቻለ ግን ያሉት ነገር የለም።
ሞጣ ላይ ሙስሊምና ክርስቲያኑ አንድ ቤተሰብ እንደነበረና ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተነሳውን እሳት ለማጥፋትም ቢሆን በርካታ ሙስሊም ወንድሞች መረባረባቸውን እኚሁ ግለሰብ ገልጸዋል። "ዛሬ ራሱ ጄሪካን ስጡን ብለው እየመጡ ነበር። ሁሉም ነገር ሰላም ነበር" ይላሉ።
የትናንቱ ክስተት ወጣቶች ስሜታዊ ሆነው በመሄዳቸው የተከሰተ አጋጣሚ እንደሆነ የሚናገሩት ነዋሪው፤ "መስጊድ ማቃጠሉ ታልሞበት፣ ታስቦበት የተገባ ጉዳይ አልነበረም" ሲሉ ያስረዳሉ።
ነዋሪው እንደሚሉት፤ አሁን ልዩ ፖሊስ ገብቶ ሁኔታዎችን ለማረጋጋት እየሞከረ ሲሆን በተከሰተው ነገር አንድ ግለሰብ መጎዳቱን እንደሰሙና የሰው ሕይወት ግን አልጠፋም ይላሉ።
በተከሰተው ነገር የሙስሊሙም የክርስቲያኑም ንብረት መጥፋቱን ገልጸው፤ "ወጣቱ በስሜት ተነሳስቶ እዚህ ውስጥ መግባት የለበትም። አሁንም ቢሆን የጋራ እምነታችንን ነገ በእርቅ እንዘጋለን። ከዛ ውጪ ግን በስሜት መሄድ ራሳችንንም ማውደም ነው" ብለዋል።
የሞጣ ከተማ አስተዳደር የምክር ቤት አባል የሆኑት ሀጂ ዩኑስ ኢድሪስ፤ የቃጠሎው መንስኤው ምን እንደሆነ ግራ እንደሆነባቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
"የተቃጠሉት በብዛት የሙስሊም ሱቆች እየተመረጡ ነው፤ አራት በአራት በተባለው ሸቀጥ ተራ ሁለት ፎቅ ሙሉ ሱቆች ተቃጥለዋል፤ ተዘርፈዋል። የሙስሊም መድኃኒት ቤቶች እና ኮንቴነሮች ተቃጥለዋል፤ ተዘርፈዋል" ብለዋል። ይህ ለምን እንደተከሰተ ግን ሳይጣራ በመላምት እንዲህ ነው እንዲያ ነው ማለት አልፈልግም ብለዋል።
የአየር ማረፊያ ታላቁ መስጊድ እሳቱ አሁንም (ዛሬ ረፋድ ድረስ) እንዳልተዳፈነና ወደ 100 የሚደረሱ ሰዎች ተሰባስበው እሳቱን ለማጥፋት እየሞከሩ እንደሆነ ገልጸውልናል።
እርሳቸው እስከሚያውቁት ደረስ ትናንት ወደተከሰተው ነገር ሊያመራ የሚችል በሙስሊሙና በክርስቲያኑ ማኅበረሰብ መካከል የተፈጠረ ምንም ችግር እንዳልነበረ ሀጂ ዩኑስ ነግረውናል። በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ በሁለት ወገን መካከል የተከሰተ ነገር ቢኖርም፤ ከትናንቱ ክስተት ጋር ሊገናኝ እንደማይችልም አክለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌላ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፤ በአካባቢው ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ለዘመናት ተሳስሮ እንደኖረ ሲያስረዱ፣ "የክርስቲያን ልጅ እናት ገበያ ስትሄድ የሙስሊም እናት ጡት ጠብቶ ነው ያደገው" በማለት በማኅበረሰቡ መካከል የነበረውን ጥብቅ ግንኙነት ያስረዳሉ።
ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኮረፊ በሚባሉ ነባር ሙስሊሞችና ወሀቢ በሚባሉት መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ለማርገብ ውይይት እየተደረገ እንደነበር ያብራራሉ።
ነባር ሙስሊሞች ከወሀቢዎች ጋር ለማስታረቅ ሂደቶች እንደነበሩና ይህን ተከትሎ ግን ነባር ሙስሊሞች "ከዚህ በኋ ክርስቲያኖች ላይ ለሚደርሰው ነገር ተጠያቂ እንዳልሆኑ የሚገልጽ ደብዳቤ ጻፉ መባሉን፣ "ይህ ደብዳቤም የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ በመድረሱ ውጥረት እንደፈጠረ ያስረዳሉ።
ሞጣ ከተማImage copyrightMOTTA CITY COMMUNICATION OFFICE
ከዚህ ደብዳቤ በኋላ ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ዘንድ "ሙስሊሞች ሊያጠቁን ይችላሉ" የሚል ስሜት ማደሩን እንደሚያውቁ ይናገራሉ።
ይህ ሁኔታ፣ አሁን ካለው አገራዊ ሁኔታ ጋር ተደማምረው ወደትናንቱ ክስተት እንዳመሩም ያምናሉ። ከዚህ መላምት ባለፈ ግን በሞጣ ከተማ እስከ ትናንት 11፡00 ድረስ ከሙስሊም ወንድሞቻችን ጋር በአንድ መዓድ ስንበላ ስንጠጣ እንደነበረ ነው የማውቀው ይላሉ።
"እስኪ አስበው ቀን 11፡00 ቤተ ክርስቲያን መቅደስ ገብቶ እሳት የሚለኩስ እንዴት ይኖራል?" ሲሉም ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተነሳ ስለተባለው እሳት በሰው የተነሳ ነው ብለው ለማመን እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሞጣ ምርጫ ክልል ተወካይ ለሆኑት አቶ ኃይሉ ያዩት ደውለንናለቸው እርሳቸው ለጊዜው ከአካባቢው ርቀው እንደሚገኙና ያላቸው መረጃ በወፍ በረር ያገኙት ብቻ እንደሆነ ነግረውናል።
አቶ ኃይሉ እንዳሉት በስልክ ከአካባቢው ባገኙት መረጃ መሠረት እስካሁን ሁለት መስጊድና የተወሰኑ ሱቆች መቃጠላቸውን፣ አሁን ንብረት የማስመለስ ሂደት እንዳለና አንድ ትልቅ ሆቴል ላይ እሳት ተለኩሶ በርብርብ መትረፉን እንደሰሙ ነግረውናል። አሁን አካባቢው ልዩ ፖሊስ በመግባቱ ሰላማዊ ነው ብለዋል።
መምህር ሲሳይ የተባለ የሞጣ ከተማ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ ትናንት አስተምሮ ከትምህርት ቤት ሲወጣ ተኩስ እንደሰማና ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተቃጠለ መባሉን ይናገራል። ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ካመራ በኋላ ቤተ ክርስቲያኑ ጉልላት ላይ ጢስ እንደነበረና በመሰላል ወጥተው ተረባርበው እንዳጠፉት ይናገራል። "እሳቱ በምን ምክንያት እንደተነሳ አልታወቀም" ሲልም መንስኤው አለመታወቁን ያስረዳል።
ከዛ በኋላ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች ሱቆች ወደሚገኙበት አካባቢ እንደሄዱና እነሱን ለማስቆም ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም ከቁጥጥር ውጪ መውጣታቸውን ይናገራል። "የተቃጠለው የሙስሊሞች ሱቅ ብቻ አይደለም፤ ለምሳሌ የባለቤቴ ቤተሰቦች ሱቅም ተቃጥሏል" የሚለው ሲሳይ፤ ወጣቶቹ ከሱቆቹ በኋላ ወደ መስጊዶቹ እንደሄዱና ርብርብ ቢደረግም ማስቆም እንዳልተቻለ ያክላል።
ከተቃጠሉት መካከል ማርዘነብ ህንጻ እንደሚገኝበት ጠቅሷል። ከሳምንታት ቀደም ብሎ "ማርዘነብ ህንጻ ውስጥ የተሰበሰቡት ሙስሊሞች ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን ከፍለው ሊያቃጥሉ ነው" የሚል ወሬ በማኅበራዊ ሚዲያና በሻይ ቤቶች ጨምር ውስጥ ውስጡን ይነዛ እንደነበር ሲሳይ ይናገራል። "እንደዚህ ያሉ ወሬዎች የእርስበርስ ግጭት ለማስነሳት የሚፈልጉ ኃይሎች የሚነዙት ነው ብንልም የሚሰማን አጣን"
"ወጣቶቹን ለማስቆም ከፍተኛ ጥረት አድርገን ነበር። ግን አልሆነም። የሕዝብ ማዕበሉን ማን ያቁመው። ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ወጣ። አድማ በታኞችም 3፡00 ሰዓት አካባቢ ነው የደረሱት" ይላል።
መምህር ሲሳይ፣ "ዛሬ ለሞጣ የሐዘን ቀን ነው፤ ማኅበረሰባዊ ኪሳራ ነው የደረሰብን፤ ሙስሊም ወንድሞቻችንን አሳዝነናል" ሲልም በደረሰው ነገር የተሰማውን ገልጿል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ኮማንደር ጀማል መኮንን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ትናንት የሞጣ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውን ቃጠሎ ህብረተሰቡ ተረባርቦ ካጠፋው በኋላ፤ የተሰባሰው ነዋሪ ወደ መስጊዶች በመሄድ ጥቃት አድርሰዋል።
አንድ መስጊድ ሙሉ በሙሉ በቃጠሎ እንደወደመና ሁለት መስጊዶች ደግሞ በከፊል እንደተቃጠሉ ኮማንደር ጀማል ተናገረዋል። ማርዘነብ የሚባል የመኝታና የሱቅ አገልግሎት የሚሰጥ የአክሲዮን ህንጻ መስታወቱ እንደተሰበረና፣ ቃጠሎ እንደደረሰበትም ጨምረው ገልጸዋል።
"አሁን ኅብረተሰቡን የማወያየትና የማረጋጋት ሥራ እየተሠራ ነው፤ በኋላ ለደረሱት ጥፋቶች ምክንያት ተብሎ የሚጠቀሰው በቤተ ክርስቲያኑ ላይ የደረሰው የቃጠሎ ሙከራ ነው" ሲሉም አብራርተዋል።
እስካሁን ምንም ተጠርጣሪ እንዳልተያዘ ዞኑ ሪፖርት እንዳደረገም ኮማንደር ጀማል ገልጸዋል። "በአካባቢው ያለው የጸጥታ ኃይል ባደረገው ርብርብ ነው እንጂ ከዚህ በላይም ትልቅ ስጋት እንደነበረ ነው የሰማነው" ሲሉም ተናገረዋል።
በአካባቢው ስለሆነው ነገር ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጡን የደወልንላቸው የሞጣ ከተማ ከንቲባ፣ የከተማዋ የጸጥታ ኃላፊ እና የድርጅት ኃላፊ ሁሉም ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ልናገኛቸው አልቻልንም።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ሕዝብ ግንኙትን ደውለንላቸው ያልተጣራ መረጃ ልሰጣችሁ አልችልም፤ አጣርተን የደረስንበትን ጊዜው ሲደር እንነግራችኋለን ብለዋል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials