Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, December 5, 2019

በዶዶላ ቤተክርስቲያናት ተጠልለው የሚገኙ ምዕመናን ስጋት ላይ መሆናቸውን ገለፁ



የኢትዮጵያ ካርታ፤ ዶዶላ
ባሳለፍነው ረቡዕ በተለያዩ ቦታዎች የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በምዕራብ አርሲ፤ ዶዶላ ከተማ በተፈጠረ ግጭት ለከፍተኛ ህክምና ወደ ሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል የተላኩ ሁለት ግለሰቦችን ጨምሮ የ8 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ከነዋሪዎችና ከሆስፒታል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የዶዶላ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ልሳናት ቀሲስ እየበሩ ዓለሙ ላለፉት አራት ቀናትም በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በከተማዋ በሚገኙ ቤተክርስቲያናት ተጠልለው እንደሚገኙ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
በዚህም ጨቅላ ሕፃናት፣ እናቶች፣ ነፍሰጡር ሴቶች፣ አረጋዊያን እና ሕሙማን የከፋ ችግር ላይ መውደቃቸውን ይናገራሉ።
የቤተ ክህነቱ ፀሐፊ ዲያቆን ደለለኝ ማሞ በበኩላቸው ባነጋገርናቸው ወቅት በሚገኙበት ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ውስጥ ሁለት እናቶች ያለ ህክምና እርዳታ መውለዳቸውን ነግረውናል።
"ጭንቀት ውስጥ ነን ያለነው"
በዶዶላ ከተማ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው ከሚገኙት መካከል ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀችን የሦስት ቀን አራስ ትገኛለች።
ይህች እናት ረቡዕ ዕለት ወጣቶች ከፊት ለፊታቸው የነበሩ ቤቶችን ሲያቃጥሉ አይተው እግሬ አውጭኝ ብለው እንደሸሹና ሕይወታቸውንም ለማቆየት ቤተክርስቲያኗ ውስጥ እንደተጠለሉ ታስረዳለች።
"ወደኛ በኩል ድንጋይ ሲወረውሩ፤ በጓሮ በኩል አጥር ቀደን ወጣን፤ ምንም ሳንይዝ እያለቀስን ነው የወጣነው፤ በሰው ግቢ በኩል እየተረማመድን ወደ ቤተክርስቲያኗ መጣን" ትላለች።
የነበረው ሁኔታ በጣም አስፈሪ ነበር የምትለው አራሷ የተገላገለችውም ቤተክርስቲያኗ ውስጥ ነው።
"በልምድ የሚያዋልዱ ሰዎች ረድተውኝ በሰላም ተገላግያለሁ፤ ጡቴ ወተት እምቢ ብሎ፤ ውሃ በጡጦ እያጠባሁ ነው ያለሁት" ትላለች።
እርሷ እንደምትለው ከፍተኛ የሆነ የውሃ ችግር በመኖሩም ችግሩን አባብሶታል።
ከሐዋሳ እናቷ ጋር ለመታረስ ብትመጣም በነበረው ብጥብጥ እናቷን ጨምሮ የሰባት ወር ህፃን የያዘች የአክስቷ ልጅ፤ በአጠቃላይ ሦስት ህፃናትና አራት አዋቂዎች ሆነው እንዳመለጡ ታስረዳለች።
በቤተክርስቲያኗ ውስጥ በከፍተኛ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ እንደሆነ የምትናገረው እናት ቢቢሲ ከቀኑ 7፡35 አካባቢ ባናገራት ወቅት ምግብ እንዳልቀመሰችና ሻይ ብቻ እንደጠጣች ተናግራለች።
ወደቤት ሄደውም ሆነ ውጭ ወጥተው ለመመገብ ለደህንነታቸው ስለሰጉ ችግር ላይ መሆናቸውን ታስረዳለች።
ረቡዕና ሐሙስ ዕለት የተቃውሞ ሠልፍ በተካሄደባቸው የኦሮሚያ፣ ሐረርና ድሬዳዋ ከተሞች በክልሎችና በአስተዳደሩ ጥያቄ መሠረት የመከላከያ ሠራዊት መሰማራቱንና ሁኔታዎች እንደተረጋጉ ቢገለፅም አራሷ በዚህ ሃሳብ አትስማማም።
"ተረጋግቷል የሚባለው መንቀሳቀስ ሲቻል ነው። ያሉት ወታደሮች ቤተ ክርስቲያኗን በመጠበቅ ላይ ናቸው" ትላለች።
አክላም "ያለነው በመከራ፣ በስቃይ ነው፤ ከፍተኛ ብርድ አለ፤ አራስ ሆነን ውጭ እያደርን ነው፤ የታመሙ ህፃናት አሉ፤ አንዲት የአምስት አመት ልጅ ቶንሲል ታማ ስታለቅስ ነበር ግን ምን ማድረግ ትችላለች" ስትል መንግሥት እንዲደርስላቸው ተማፅናለች።
ዲያቆን ደለለኝም በኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ከሁለት መቶ በላይ አባወራዎችም ልጆቻቸውንና ቤተሰባቸውን ይዘው በመቃብር ቤቶች እንዲሁም ድንኳን ውስጥ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
የሦስት ቀጠና ማህበረሰብ፤ ቀጠና 4፣ 5 እና 7 በዚችው ቤተክርስቲያን ተጠልለው እንደሚገኙና ሌሎች ደግሞ በቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ይገኛሉ ብለዋል።
በዛሬው ዕለት በአንፃሩ ከተማው እንደተረጋጋና ከቤተክርስቲያኗም በቅርብ ርቀት የሚገኙ ሰዎች ከቃጠሎ የተረፈ ንብረትም በመሰብሰብ ላይ የሚገኙ እንዳሉም ገልፀዋል።
በቤተክርስቲያኗ ዙሪያ አንድ ፓትሮል፣ አስራ አምስት የማይሞሉ የመከላከያ ኃይል በአካባቢው እንዳለ ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጅ ተጠልለው የሚገኙት ምዕመናንም በምግብና ውሃ እጥረት እየተሰቃዩም እንደሆነ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
"አንዳንድ ግለሰቦች ከውጭ ምግብ እያመጡ በሚረዱት ነው እየተዳደርን ያለነው። በጣም የተቸገርነው ደግሞ ውሃ መቅዳት ባለመቻሉ ነው።"ይላሉ።
ወደ ቤተ ክርስቲያኗ የሚመጣው የውሃ መስመር በመቋረጡ እንዲሁም ወንዝ ሄደው እንዳይቀዱ ለደህንነታቸው በመስጋታቸው በውሃ ጥም እንዲሰቃዩ ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ።
ፍትህ የሚጠይቁ ወጣቶች ስብስብImage copyrightALEMAYEHU DEMISSIE
ቤተክርስቲያኗን ለቀው ቢወጡ አካባቢውን የሚጠብቀው ኃይል ለደህንነታቸው ዋስትና ስላልሰጣቸው አሁንም ስጋት እንዳደረባቸውና በጭንቀትም ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
"ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ነው" የሚሉት ዲያቆን ደለለኝ ከሰባት ቤት በላይ ተቃጥሏል፣ የተዘረፈና የወደመ ንብረት አለ ይላሉ። ረቡዕ ዕለት በቤተክርስቲያኗ አባቶች ላይ ድብደባ እንደደረሰም ይናገራሉ።
እስካሁን ባለው ስድስት ሰዎች እንደተቀበሩና በዛሬው ዕለትም ከሃዋሳ የመጣች የአንዲት ሴት ሥርዓተ ቀብር መፈፀሙን ይገልፃሉ።
"በሞትና በሕይወት ስላለው ሰው በቁጥር ልናገር አልችልም፤ ሦስት ሰዎች በሞትና በሕይወት መካከል ሆነው አሁንም በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ነው ያሉት" ሲሉም ጉዳት ያጋጠማቸው በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ያስረዳሉ።
በከተማዋ ገብረ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን እንደሚገኙ የገለፁልን የዶዶላ ወረዳ ቤተክህነት ኃላፊ ሊቀ ልሳናት ቀሲስ እየበሩም በበኩላቸው እንደ ኃይማኖት መሪ በግምት ለመናገር ቢቸገሩም በዚች ቤተክርስቲያን ብቻ 2ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ገልፀውልናል።
ከረቡዕ ዕለት አንስቶ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ህፃናት ፣ ሴቶች፣ አረጋዊያን ተጠልለው እንደሚገኙ ገልፀው፤ የተጎዳ ሰው ለመጠየቅ ትናንት ወደ ሆስፒታል በማምራት ላይ ሳለች ድብደባ የተፈፀመባት አንዲት ሴትም ሕይወቷ በማለፉ ዛሬ የቀብር ሥነ ሥርዓቷ እንደተፈፀመ ነግረውናል።
በርካታ ሰዎች ላይ 'ዘግናኝ ጥቃት' እንደተፈፀመ የተናገሩት ቀሲስ እየበሩ፤ የ8 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ ቤቶች መቃጠላቸውን ፣ ንብረቶች መውደማቸውን ያክላሉ።
"ዛሬ ጠዋት ላይ መንገድ ተከፍቷል በሚል ከተለያየ ቦታ ለለቅሶና ለሌላ ጉዳይ የመጡ ነበሩ፤ እነርሱም ላይ የማዋከብና የማሰር ድርጊት እየተፈፀመ ነው" ብለዋል።
እስካሁን ድረስ በሥፍራው ተገኝተቶ የጎበኛቸው የመንግሥት ባለሥልጣናትም እንደሌሉ ይናገራሉ።
"በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው የተፈፀመው፤ ሰው መረጋጋት አልቻለም። እናቶችና ሕፃናት እየተራቡ ናቸው፤ ውሃ ወጥቶ መቅዳት አልቻልንም። ወደ ፈጣሪ ከመጮህ ውጭ ሌላ የምናደርገው ነገር የለም" ይላሉ።
"በቤተክርስቲያኗ ውስጥ አንድ መፀዳጃ ቤት ነው ያለው፤ ውሃ የለም ፤ ምግብ የለም" ሲሉም በዚሁ ከቀጠለ ለበሽታ ሊዳረጉ እንደሚችሉ ስጋት አላቸው።
ግጭቱም ከብሔር ጋር የተገናኘ ቢሆንም መልኩን ቀይሮ ወደ ሃይማኖት እንደዞረ በማስረዳትም በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙት የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ስብጥር ያለውና በአብዛኛው የኦርቶዶክስ አማኞች መሆናቸውን ያስረግጣሉ።
ዛሬ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዶዶላ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ቶላ ቢዮ ለከፍተኛ ህክምና ወደ ሀዋሳ ሆስፒታል ተልከው የነበሩትን ሁለት ሰዎች ጨምሮ የሟቾች ቁጥር 8 መድረሱን ነግረውናል።
የተጎዱትን ለማስታመም ወደ ሆስፒታል ያመሩ ሰዎች ላይ ጥቃት ተፈፅሟል ስለመባሉ ያነሳንላቸው ዶክተር ቶላ፤ ዝርዝር መረጃ ባይኖራቸውም ሀሙስ እለት ግን ሆስፒታሉ ግቢ ውስጥም ግጭቶች እንደነበሩ ገልፀውልናል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ በአዲስ አበባ የሚገኙ የዶዶላ ተወላጆች፣ የሟቾች ቤተሰቦች በመሰባሰብ ለሚዲያዎች ፣ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አቤት ለማለት እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆነ የዶዶላ ተወላጅ እና በአዲስ አበባ በሥራ ላይ የሚገኘው አስተባባሪ አቶ አለማየሁ ደምሴ ገልፆልናል።
ዜጎች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴያቸው እንዲገቡም መንግሥት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቋል።
"ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው የሚገኙት በርሃብ ሊያልቁ ነው፤ ሕፃናት፣ የሚያጠቡ እናቶች አሉ፤ ትናንትና እና ከትናንት ወዲያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ንፍሮ ቀቅለው ነው የበሉት" ይላል።
ግጭት በተፈፀመባቸው አካባቢዎች መከላከያ እንደተሠማራ መንግሥት ቢገልፅም አሁንም ድረስ በከተማዋ ጥቃት እየተፈፀመ እንደሆነም ለቢቢሲ ገልጿል።
በጉዳዩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ከፍያለው ተፈራን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ብንደውልም ጥረታችን ሳይሳካ ቀርቷል።
የተቃውሞ ሠልፍ በተካሄደባቸው የኦሮሚያ፣ ሐረርና ድሬዳዋ ከተሞች በክልሎችና በአስተዳደሩ ጥያቄ መሠረት በአምቦ፣ ቢሾፍቱ፣ ባሌ ሮቤ፣ አዳማ፣ ሞጆ እንዲሁም በድሬዳዋ እና ሐረር የመከላከያ ሠራዊት እንደተሠማራ መገለፁ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials