ናታልያ እስኩድሮ አርቲቪኢ ለተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ የምትሰራ ሲሆን፤ የቀጥታ ስርጭት ላይ እያለች ሎተሪ እንደደረሳት ስታውቅ በደስታ ተሞልታ እየጮኽች በነጋታው ወደ ሥራ ገበታዋ እንደማትመጣ ተናግራለች።
ነገር ግን ቆየት ብላ የደረሳት ሎተሪ በጠቅላላ 4 ሚልዮን ዩሮ ከሚያስገኘው ዕጣ ናታልያ የደረሳት 5ሺህ ዩሮ ብቻ መሆኑን ተረድታለች።
የገና ሎተሪው ከፍተኛ ሽልማት 4 ሚሊዮን ዩሮ ቢሆንም ብሩ ግን ለበርካታ አሸናፊዎች የሚከፋፈል ነበር። ናታልያ ይህንን እንዳወቀች ለድርጊቷ ይቅርታ ጠይቃለች።
ናታልያ እንዳለችው እንደዛ "ስሜታዊ" ሆና በመናገሯ እንደተፀፀተችና ባደረገችው ነገር ጥሩ ስሜት ላልተሰማቸው ተመልካቾቿም ስለሁኔታው እንደምታብራራ ገልፃለች።
የናታልያ ምላሽ የመጣው የቴሌቪዥን ምስሉ በሰፊው ማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ ሲሰራጭ 'ሙያዊ ስብዕና ይጎድላታል' የሚል ክስ ከቀረበባት በኋላ ነው።
በሎተሪው ዕጣ የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ሻምፓኝ ተከፍቶ፣ ትልቁ የዕጣ መጠን በሚነገርበት ግዜ ናታልያ በደስታ ስትዘል በቀጥታ በቴሌቪዥን ተላልፏል።
ተመልካቾችም ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንዳሸነፈችና ሥራዋንም እንደምታቆም የገለፀችበት አኳኋንን እንደነቀፉት የስፔን መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።
ይህ የእርሷን ስሜት የያዘው ስርጭት ከተላለፈ በኋላ እስኩድሮ ዳግመኛ በቴሌቪዥን መስኮት ላይ ብትቀርብም ብዙም አላወራችም።
ለቀረበባት ትችት ትዊተር ላይ የሰጠችው ምላሽ እንደሚለው በጊዜው ለወራት ያክል ግላዊ በሆነ ምክንያት ችግር ገጥሟት የነበረ ቢሆንም በ25 ዓመት ብቁ በሆነ የጋዜጠኝነት ህይወቷ በቅንነት ተግታ እንደሰራችና እንደምትኮራበትም ተናግራለች።
"ናታሊያ እስኩድሮ አደናጋሪና ውሸታም የአርቲቪኢ ጋዜጠኛ" ተብላ ትዊተር ላይ ለተፃፈው ክስና ለተፈጠረው ግራ የሚያገባ ድርጊቷ ይቅርታ በመጠየቅ አሰትባብላለች።
No comments:
Post a Comment