Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, December 24, 2013

የጋምቤላ በደን የተሸፈነ 3012 ሄክታር በሊዝ የገዛው የህንድ ኩባንያ ቃጠሎ ደረሰበት

የጋምቤላ በደን የተሸፈነ 3012 ሄክታር በሊዝ የገዛው የህንድ ኩባንያ ቃጠሎ ደረሰበት

ሻይ ቅጠል ለማልማት የተፈጥሮ ጥብቅ ደን እንዲያወድም የተፈቀደለት ቬርዳንታ ሀርቨስት የተባለ ኩባንያ በከፍተኛ ወጪ ያለማውና ለመለቀም በደረሰ ምርት ላይ ማንነታቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች እሳት ለቀውበታል። ጥቅምት 12 ቀን 2006 ዓም ደረሰ በተባለው ቃጠሎ ኩባንያው የደረሰበት ሊሳራ እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ስለ ጉዳዩ የሚያውቁ አስታውቀዋል።
አንጋፋ እድሜ ጠገብና ረዣዥም የተፈጥሮ ደን በመጨፍጨፍ ጣውላ እያመረተ ሲቸበችብ የነበረው ኩባንያ ሙሉ ንብረቱና ከፍተኛ መጠን ያለው የጣውላ ምርት ከተለያዩ ማሽኖች ጋር ወድሞበታል። የአካባቢው ምንጮች እንዳሉት ኩባንያው ላይ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ ለመሰብሰብ የደረሰውን የሻይ ቅጠል ማሳ አጋይቶታል።ውድመት የደረሰበት የህንድ ኩባንያ በልማት ባንክ ላይ ኪሳራ ሊያስከትል እንደሚችል ስጋት አለ::
በጋምቤላ ክልል በመዠንግር ዞን፣ በጎደሬ ወረዳ በጉማሬና በካቦ ቀበሌዎች የሚገኝ 5000 ሄክታር በደን የተሸፈነ መሬት በኢንቨስትመንት ስም እንዲሸጥ መወሰኑን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ አሰምተው ነበር። በወቅቱ ውሳኔውን “በባዕድ ወራሪ ሃይል እንኳን የማይፈጸም” በማለት የተቹና ቅሬታቸውን የገለጹ ነበሩ።
ሙሉ በሙሉ በደን የተሸፈነ 3012 ሄክታር ድንግል ለም መሬት በሄክታር111 ብር ሂሳብ ለ50 ዓመት የሊዝ ኮንትራት የተሸጠለት ይህ ኩባንያ ጥብቅ ደኑን ከማውደሙ በፊት ውሳኔው እንዲጤን የአካባቢው ህዝብ በወኪሎቹ አማካይነት ለፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ጥያቄ አቀርበው ነበር።
በወቅቱ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ድርጊቱን በመቃወም የሚከተለውን ጽሁፍ አትሞ ነበር። ሰሚ ባለመገኘቱ የተፈራው ደረሰ። http://www.solidaritymovement.org/amharic/110103GambellaVillagizationLeakedInfo.pdf
ጡረተኛው ፕሬዚዳንት ለአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በሰጡት ትዕዛዝ መሰረት የተፈጥሮ ደኑ ከመጨፍጨፉ በፊት ውሳኔው እንዲመረመርና እንዲጠና ሚያዚያ 28 ቀን 2002 ዓ ም ለክልሉ ደብዳቤ ልኮ ነበር። ሟቹ ጠ/ሚኒስትር በወቅቱ የአፍሪካ የተፈጥሮ ጥበቃና የአየር ንብረት ተሟጋች ነኝ ያሉበት ወቅት መሆኑንን በማስታወስ፣ የፕሬዚዳንቱን መመሪያ በመጠቆም ባለስልጣኑ የጻፈውን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የክልሉ ፕሬዚዳንት ህዳር 10 ቀን በተጻፈ ደብዳቤ ደመሰሱት። ከላይ የተጠቀሰው ኩባንያ የ50 ዓመቱን ውል ቅድሚያ ክፍያ የአንድ ዓመት 19 ሺህ ዶላር ስለከፈለ ቦታውን እንዲረከብ ዞኑንን አዘዙ።
የበላይና የበታቹ በማይታወቅበት የመለስ አወቃቀር ጥብቅ ደኑ ያለበት መሬት ለህንዱ ኩባንያ ተላለፈ። ህዝብ ያነሳውን ጥያቄ እስከ ፕሬዚዳንቱ ያደረሱት ሊቀመንበር እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው ከሃላፊነታቸው ተባረሩ። ህዝብ የኑሮው መሰረትና የህይወቱ ያህል የሚንከባከበው ደን ተጨፈጨፈ። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ደኑ ሲጨፈጨፍ የነበረው ሃዘን በቃል የሚገለጽ አልነበረም።
ባገኘው ከፍተኛ የደን ምርት ጣውላ ማምረት የጀመረው ኩባንያ መጋዘን ገንብቶ የጣውላ ንግድ ውስጥ ገባ። አሁን ድረስ ንዴቱና የበደል ስሜቱ ያለቀቀቃቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የተካሄደባቸውን ግፍ “ዝርፊያ” እያሉ ነው የሚጠሩት።
ህግን ጠብቀው ኢህአዴግን ያሳሰቡት የአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም ቢሆን በእስርና በድብደባ በማሰቃየት ኢንቨስትመንትን /ነዋሪዎቹ ዝርፊያ ነው የሚሉት/ በክልሉ ቀጣይ ማድረግ አይቻልም። አስቀድሞ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ኢህአዴግና ኩባንያው ጆሮ ሰጥተዋቸው ቢሆን ኖሮ እንዲህ ያለ አደጋ ሊፈጠር እንደማይችል አስተያየት ሰጡ አሉ።
92 ሚሊዮን ብር በላይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እዳ ያለበት የእርሻ ድርጅት፣ ንብረቱ በእሳት ከወደመ በኋላ የተሸከመው እዳ አጀንዳ ሆኗል። የደረሰበት ውድመት ከፍተኛ በመሆኑ ክልሉንና ኢህአዴግን ካሳ እንደሚጠይቅም ከወዲሁ ተሰምቷል። ዜናውን ያቀበሉ ክፍሎች “ህዝብ ላልተቀበለው ኢንቨስትመንት ካሳና የልማት ባንክ ላይ ለደረሰው ኪሳራ ተጠያቂው ኢህአዴግ ነው” የሚል ጥያቄ መነሳቱን አመልክተዋል።
ለአበባ እርሻ ላስቲክና ኬሚካል በማስያዝ ልማት ባንክን እያለቡ የተሰወሩ በርካታ ድርጅቶችና ለስርዓቱ ቅርበት ያላቸው ሸሪኮቻቸው መኖራቸውን በማስታወስ በጋምቤላ ተመሳሳይ ድርጊት ሊፈጸም እንደሚችል የዜናው ምንጮች ጠቁመዋል። ካራቱሪ በኪሳራ መንገዳገዱን፣ ሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ በ”ውክልና” ለሳዑዲ አረቢያ ቀለብ እንዲያመርት የተከሉት ሳዑዲ ስታርና ሌሎች የህወሃት ሰዎች ከተለያዩ የአገር ውስጥ ባንኮች ከፍተኛ ገንዘብ መበደራቸውን ገልጸዋል።
“ህዝብን ያለፈቃዱ በማፈናቀልና መሬቱን በመቀማት የሚከናወን ኢንቨስትመንት ሁሌም አደጋ ላይ መሆኑ አያጠራጥርም” በማለት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ አኢጋን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ለጎልጉል ገልጸዋል። “ኢንቨስትመንት እንኳን ደህና መጣህ በሚል ህዝብ ካልተቀበለው ዘረፋ ነው” ያሉት አቶ ኦባንግ “በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ድምጹን ሲያሰማ ጆሮ ያጣ ህዝብ ተቃውሞውን ገለጸ” በማለት በደረሰው ውድመት ባይደሰቱም ለውድመቱ ተጠያቂው ኢህአዴግና ከኢህአዴግ ጋር ተሻርኮ ዝርፊያ ያከናወነው ድርጅት እንደሆነ አመልክተዋል።
ካሩቱሪና ሳዑዲ ስታርን ጨምሮ ህዝብ ላይ በተፈጸመ ግፍ ሃብት ለማፍራትና ለመበልጸግ የሚያስቡ ትልቅ ግንዛቤ ሊወስዱ እንደሚገባ ያሳሰቡት አቶ ኦባንግ “ኢህአዴግ ዝርፊያና ኢንቨስትመንትን ለይቶ መሔድ ካልቻለ ስጋቱ እየጨመረ ይሄዳልና ከስህተት በመመለስ ህዝብ በሚፈቅደው መልኩ ማስተናገድ ግድ ነው” ሲሉ አሁንም ጆሮ የለውም ለሚባለው ኢህአዴግ ማሳሰቢያ አዘል ምክር ለግሰዋል። ባለሃብት የሚባሉትም ከዚህ ታላቅና አሳዛኝ ውድመት ሊማሩና ህዝብ “እንኳን ደህና መጣችሁ እንዲላቸው ህዝብ ከሚቃወመው ዝርፊያና አሰራር ራሳቸውን ሊያገሉ ይገባል” ብለዋል።
የክልሉ ፕሬዚዳንት ቃጠሎውን ማመናቸውን ሪፖርተር በእሁድ እትሙ ያስታወቀ ሲሆን አጣሪ ኮሚቴ ተቃቁሞ አደጋውን ያደረሱት እነማን ናቸው የሚለው እየተመረመረ እንደሆነ ጠቁሟል። የክልሉ የጎልጉል ምንጮች በርካታ ሰዎች እሳት አስነስታችኋል በሚል መታሰራቸውና በፌዴራል አንጋቾች እየተመረመሩ መሆኑን አረጋግጠዋል። እሳት ያስነሱትን ለማጋለጥ በሚል በየመንደሩ በሚደረግ ማዋከብ ነዋሪዎቹ መማረራቸውን ተናግረዋል። ለጊዜው የእስረኞች ቁጥር ባይታወቅም ወደ ማዕከል የተላኩ በርካታ እንደሆኑም ገልጸዋል።
Source http://www.goolgule.com

No comments:

Post a Comment

wanted officials