የትግራይዋን 'አልባንያ' በደቡባዊ አውሮፓ ባልካን በሚባለው አካባቢ በስተምዕራብ ከምትገኘው አልባንያ ጋር የሚያመሳስላት አንዳች ነገር የለም።
ምናልባትም የ'ትግራይዋ አልባንያ' ያለምንም የአቋም ለውጥ ለረዥም ዓመታት የህወሓት ተቃዋሚ መሆኗ ከቀሪው የትግራይ ክፍል የተለየች ሊያስብላት ሲችል፤ አልባንያም በአስቸጋሪ መልክዓ ምድሯ እንዲሁም በውስብስብ የታሪክ፣ የባህልና ማህበራዊ ሁኔታዎች ተለይታ የምትኖር መሆኗ ካላመሳሰላቸው በስተቀር።
ከመቐለ በስተምሥራቅ 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውና ቀድሞ በእንደርታ ወረዳ አስተዳደር ስር የነበረችው 'እግሪ ሃሪባ' በብዙዎች ዘንድ 'አልባንያ' በመባል ትጠራለች።
ይህ ግን በሌላ ሳይሆን፤ ይደርስብናል የሚሉትን ኢፍትሀዊነት አምርረው በመቃወማቸው፣ በደል የሚሸከም ጫንቃ የለንም በማለታቸው መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢዋ ነዋሪዎች ያስረዳሉ።
የእግሪ ሃሪባ 'አልባኒያ' ኗሪዎችህወሓትን ለምን አምርረው ይቃወማሉ?
"ስንቱን እናገረዋለሁ . . . እስር ላይ በነበርንበት ወቅት፣ ሌሊት ስድስት ሰዓት ላይ በየቀኑ በሚቀያየሩ ሰዎች እንመረመር ነበር። ራሳቸው በፈጸሙት ጥፋት የተከሰስንበት ጊዜም ነበር፤ ከባድ በደል ደርሶብናል። ህወሓት እያታለለ የሚኖር ፓርቲ ነው" ይላሉ የእግሪ ሃሪባዋ የሦስት ልጆች እናት አርሶ አደር አልጋነሽ ገብረሕይወት።
ወ/ሮ አልጋነሽ ቀድሞ የህወሓት ደጋፊ የነበሩ ቢሆንም የአካባቢያቸው ነዋሪ ለሚያነሳው ጥያቄ የፓርቲው ምላሽ 'ጆሮ ዳባ ልበስ' ሲሆንባቸው "ጥያቄያችንን እና መብታችንን እናስመልሳለን" ካሉ የእግሪ ሃሪባ አርሶ አደሮች ጋር አብረው ተሰልፈዋል።
አብዛኛው የአካባቢው ሰው ብዙ ችግር ማሳለፉን፤ ስብሰባ ላይ ሃሳባቸውን እንዳይገልፁ ይደረጉ እንደነበር የሚናገሩት ወ/ሮ አልጋነሽ፤ ተናገራችሁ ተብለው የታሰሩበት ጊዜም እንደነበር ያስታውሳሉ።
'አልባንያዎች'ና ህወሓት የተካረሩት በ2003 ዓ.ም የመቀሌ ከተማ አስተዳደር ትንሽዋን የገጠር ከተማ እግሪ ሃሪባ [አልባንያ] በመቀለ ከተማ አስተዳደር ስር መግባት አለባት የሚል ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ነው።
በወቅቱ ነዋሪዎቿ አስፈላጊው መሰረተ ልማት ሳይሟላ እንዴት በከተማ አስተዳደር ስር እንገባለን ሲሉ አሻፈረን አሉ። ወ/ሮ አልጋነሽ እና ሌሎች ስድስት የአካባቢው ኗሪዎች የተቃውሞው መሪዎች ነበሩ።
ያነጋገርናቸው የእግሪ ሃሪባ ነዋሪዎች እንደገለፁልን አካባቢው በከተማ አስተዳደር ስር እንዲሆን ሲወሰን፤ ውሃ፣ መብራት፣ መንገድና ሌሎች መሰረታዊ የልማት አቅርቦቶች አልነበሩም።
የሕክምና ባለሞያዎችና የሕክምና መሳሪያ ባልተሟላበት የጤና ተቋም ልጆቻችንን አናስከትብም፣ አስተማሪ ባልተሟላበትና የትምህርት መሳሪያ እጥረት ወዳለበት ትምህርት ቤትም ልጆቻችንን አንልክም በማለት የእግሪ ሃሪባ ነዋሪዎች ሰላማዊ ተቃውሟቸውን ያደርጉ ነበር።
በዚህ ተቃውሟቸውም 'የአልባኒያ ተቋማዊዎች' የሚል መጠሪያ እንደተሰጣቸው ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።
ወ/ሮ አልጋነሽ ከእስር ከተፈቱ በኋላ በወቅቱ ብቸኛው የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲ የነበረው አረናን እንደተቀላቀሉ ይገልጻሉ።
ከአምስት ዓመት በፊት በተካሄደው አራተኛው አገራዊ ምርጫ፤ ከወ/ሮ አልጋነሽ ጋር የህዝብ ጥያቄ ይመለስ ሲሉ ድምፃቸውን ያሰሙ ተቃዋሚዎች በምርጫው ዋዜማ በሽብር ተከስሰው ታሰሩ።
"እኔን ጨምሮ መሬታችንን አትቀሙንም ብለን ያልን ሰዎች ታሰርን" የሚሉት ወ/ሮ አልጋነሽ፤ ለሦስት ዓመታት ልጆቻቸው ማረሚያ ቤት እየተመላለሱ እሳቸውን በመጠየቅ እንደተንገላቱ በቁጭት ያስታውሳሉ።
ወ/ሮ አልጋነሽ ከመቀለ ከተማ አፍንጫ ስር የምትገኘው መንደራቸውን በመጥቀስ "አካባቢያችን ላይ ውሃ ስለሌለ የሁለት ሰዓት መንገድ ተጉዘን ውሃ እንቀዳለን፤ መብራት የለም፤ ለአምቡላንስ የሚመችም መንገድም የለም፤ ከተማ ላይ ሆነን ሁሉም የራቀብን ሰዎች ነን። በቃ! 2003 ላይ የወደቀችው አካባቢ እንደወደቀች ናት፤ እስከ አሁን አምነን የተቀበልነው አስተዳዳሪ'ኳ የለንም፤ ቢኖርም አናውቀውም" ይላሉ።
የእግሪ ሃሪባ አርሶ አደሮች ዛሬም የክልሉ መንግሥት የሚልካቸው አስተዳዳሪዎችን 'የህወሐት ካድሬ' ናቸው በሚል በሙሉ ልቡ አይቀበሏቸውም። ትግራይ ውስጥ ያለው ሰው ባለው ወቅታዊ የፖለቲካ ምክንያት ለህወሓት ልቡ የራራ ቢመስልም 'አልባንያዎች' ግን ህወሓትን ይቅር ያሉት አይመስሉም።
አቶ መኮንን አብርሃ [ለዚህ ታሪክ ሲባል ስማቸው ተቀይሯል] አርሶ አደር ናቸው።
"2003 ላይ መብታችን ይከበር፣ መሰረተ ልማት ይሟላልን በማለታችን፤ ለሦስት ወይም አራት ዓመት ገደማ አስተዳዳሪ አልተመደበልንም ነበር" ይላሉ።
በ2008 ህዳር ወር ላይ አሸባሪዎች ተብለው በክልሉ መንግሥት ታስረው ለ14 ወራት የክስ ሂደታቸውን በውጪ ሲከታተሉ ቆይተው በመጨረሻ የተወሰኑት አራት፤ ሌሎቹ ደግሞ ሦስት ዓመት ተፈርዶባቸው መታሰራቸውን ያስረዳሉ።
ልጆቻንን አናስከትብም፤ ወደ ትምህርት ቤትም አንልክም ማለትስ ምን አይነት ተቃውሞ ነው? የሚል ጥያቄ በቢቢሲ የተጠየቁት አቶ መኮንን፤ ጥያቄው ያስቆጣቸው ይመስላል፤ ለህወሓት የሚሰሩ ናቸው ያሏቸው መገናኛ ብዙሃን ጉዳዩን የዘገቡት በተሳሳተ መልኩ መሆኑን በማስረዳት ነገሩ እንደዚያ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።
"ልጆቻችን አናስከትብም ሳይሆን፤ የሚከተቡት በቀደመው አስተዳደር ስር ስንሆን ነው፤ የትምህርት ቤቱ ጉዳይም ወላጆቻችሁ ወደ ከተማ አስተዳደሩ ገብተናል ብለው ሲፈርሙ ነው የምናስተምራችሁ በማለታቸው እራሳቸው የፈጠሩት ችግር ያመጣው ነው።"
ወ/ሮ አልጋነሽም በበኩላቸው "የክልሉ መንግሥት ክትባት የሚለው ምን ዓይነት የጤና ተቋም ሰርቶ ነው?" የሚል ጥያቄ በማንሳት "መጀመሪያ አላስከትብ፤ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት አልልክ አሉ ብሎ ለመውቀስ የክልሉ መንግሥት ተቋማቱን በቅጡ መች ሰርቷቸው ነው?" ሲሉ ለጉዳዩ ምላሽ ይሰጣሉ።
ህወሓት ያቀረብኩለትን ጥያቄ መመለስ ስላልቻለም "ፓርቲዬን ቀየርኩ" የሚሉት ወ/ሮ አረጋሽ፤ "እውነት በመጉደሉ ከህወሓት እንድንርቅ ተገደናል" ብለዋል።
የ'አልባኒያዎች' ተቃውሞ ሰላማዊ ሊባል የሚችል የነበረ ቢሆንም እነሱ እንደሚሉት ግን የህወሓት ጠንካራ እጅ ከብዶባቸው ነበር።
እነርሱ እንደሚያስረዱት በወቅቱ የአካባቢው ገበሬዎች የሰበሰቡት እህል በእሳት ጋይቶ ያድር ነበር።
ይህ በአካባቢው ነዋሪና በአካባቢው የመንግሥት ተሿሚዎች መካከል ውጥረትን ፈጥረ። ውጥረቱ እየተካረረ በሄደበት ወቅት እንደ ወ/ሮ አልጋነሽ ያሉ የአካባቢው ተቃውሞ መሪዎች ታሰሩ። ቤተሰባቸው እንደተበተነና ልጆች ከትምህርታቸው እንደተስተጓጎሉ ይናገራሉ።
"እኔ ስታሰር፤ ልጄ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን አቋርጣ ጠላ እየሸጠች፣ ወንድሞችዋን ተታሳድግ ነበር። የአካባቢው ህብረተሰብም መሬት ያርስላቸው፣ እህል ያጭድላቸው ነበር። ሁላችንም ግን ፍላጎታችን ለውጥ እንጂ ሌላ አልነበረም" ይላሉ።
የእግሪ ሃሪባ ገበሬዎችንና የከተማዋ አስተዳደርን ለማሸማገል የሀገር ሽማግሌዎችና ቀሳውስት በመካከል ገቡ፤ ነገር ግን አልተሳካም።
የአጽቢ ወንበርታ ወረዳ
የ'አልባኒያዎች'፣ የእነ ወ/ሮ አልጋነሽ እና የህወሓት ጉዳይ በዚህ አላበቃም ወደ ኋላ እንመለስበታለን።
አሁን ደግሞ ከመቀለ በ50 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቃ ወደምትገኘው የአጽቢ ወንበርታ ወረዳ እንሂድ።
ያነጋገርነው በወረዳዋ ኗሪ የሆነው ሕድሮም ኃይለሥላሴ የተባለ አርሶ አደር፤ ህወሓት የትግራይ ህዝብ ትግልን መንገድ ላይ 'ክዶታል' ይላል። ለዚህም ማስረጃ ሲል የሚጠቅሰው ህወሓት ደርግ ከመውደቁ በፊት የነበረ ባህሪውን ከደርግ መውደቅ በኋላ ቀይሯል በማለት ነው።
ሕድሮም የታጋይ ልጅ ሲሆን እርሱም በአፍላ ወጣነት እድሜው በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ሚሊሻ ነበር። በትምህርት ደግሞ 10ኛ ክፍል ደርሷል።
ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ህወሓት ላይ የነበረውን እምነት እያጣ መምጣቱን የሚናገረው ሕድሮም፤ 2002 ላይ አረና ትግራይን ተቀላቅሎ ህወሓትን መቃወም ጀመረ። 'ህወሓትን የመቃወም ጉዞው' ግን ቀላል አልሆነም፤ ከባድ ዋጋ ያስከፍለው ጀመር።
ተቃዋሚ መሆኑ ሲታወቅ፤ ወደ እሱ እርሻ የሚሄደው የመስኖ ውሃ 'የህወሓት ካድሬዎች' በሚላቸው ሰዎች ተዘጋ፤ ከማህበራዊ ህይወት እንዲገለል በብዙ መልኩ ጫና ደረሰበት በመጨረሻም ታሰረ።
ይህን ታሪኩን ይዞ ወደ ማህበራዊ ሚዲያ የመጣው ሕድሮም፤ ብዙ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ባደረጉት ከፍተኛ ጫና የተዘጋበት የመስኖ ውሃ መስመር ከዓመታት በኋላም ቢሆን ተከፈተለት።
"ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነኝ፤ እናቴ ማረሚያ ቤት ተጠርታ ልጅሽ ትግራይን የካደ፣ የአማራ ተላላኪ ነው ስትባል አዝና ማየቴ ነው" ይላል።
ሰው በምንም መልኩ እንዳይረዳው፣ ቀብር ላይ እንዳይገኝ፣ እስር ላይ ሳለም እንዳይጠየቅ ክልከላዎች ተደርገውበት እንደነበር ህድሮም በተሰበረ አንደበት ይገልፃል።
እናቱ "በጉያሽ ጠላት እያሳደርሽ ነው" በመባላቸው ሲጨነቁ በዚሁ ምክንያት ከአማቾቹ ጋር እንዲለያይ መሆኑም ለእሱ ከባድ ስቃይ እንደነበር ይናገራል።
ምንም እንኳ የተለያየ አካባቢ ነዋሪዎች ቢሆኑም የ'አልባንያዎቹ' እነ ወ/ሮ አልጋነሽና ህድሮም ህወሓትን በመቃወም የደረሰባቸው የቅጣት እጣ ተመሳሳይ ነው። በብዙ መልኩ አካላዊም ሥነ ልቦናዊም ዋጋ ከፍለዋል።
"በወሬ መሃል እኛ ስንቀላቀል ዝም ይባላል፤ አሁን ሰልችቶን ትተነው ነው እንጂ ልጆቻችንንም አትናገሩ፤ ብትመቱም አንገታችሁን ደፍታችሁ ቤታችሁ ግቡ ብለናቸዋል። የሕዝብ ሁኔታ እንዲሻሻል የማደርገው ጥረት የለም፤ አርፌ ኑሮዬን እየኖርኩኝ ነው" ይላሉ ወይዘሮ አልጋነሽ።
ያለፈው ነገር የአካባቢያቸውን አርሶ አደር በፍርሀት የሥነ ልቦና ጫና ውስጥ እንዲገባ ማድረጉንም ይገልጻሉ።
'የእገሌ ወንድም እኮ ነው' እየተባለ ከማህበራዊ ኑሮ ተገለናል የሚሉት አቶ መኮንን፤ ፍትህና ለውጥ እስኪገኝ የሚደረገው ትግል ዋጋ እንደሚያስከፍል ይናገራሉ።
የትግራይዋ 'አልባኒያ' ህወሓትን ይቅር ብላዋለች?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ በተለያዩ የለውጥ ሂደቶች ውስጥ ብትሆንም አለመረጋጋት በዚህም በዚያም እየናጣት ነው።
በአንድ ግንባር ስር የቆየው በኢህኢዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት፤ በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል ያለው ፍትጊያም ከጊዜ ወደ ጌዜ እየተካረረ ሄዷል።
ይህ መካረር ለህወሓት በክልሉ ውስጥ ድጋፍ እያስገኘለት መምጣቱን በክልሉ የሚኖሩ ሰዎች ይናገራሉ።
"ይህ ሕዝብ እኮ ትዕግስተኛ ስለሆነ ነው እንጂ፤ የተሸከመው ችግር ቀላል አይደለም" የሚሉት ወ/ሮ አልጋነሽ፤ ህወሓት በስመ ይቅርታ እየኖረ ነው ይላሉ።
"አሁን ጊዜው ጨለም ስላለ ይነጋ ይሆናል ብለን ሁሉንም በሆዳችን ይዘነዋል። ሌላ ቦታ ቤትም ንብረትም ተቃጠለ ሲባል እንሰማለን፤ ይህ እኛ ጋርም እንዳይፈጠር ልጆቻችንን ረጋ ብለን እየገራን ነው። ለዚህ ድርጅት አስበን ሳይሆን ለራሳችን . . ."
አክለውም "አዲሱ ትውልድ የራሱን ርዕስ ፈጥሮ እንዲሄድ እንሻለን እንጂ ህወሓትን ተቀይሞ ጠብና ግጭት እንዲያነሳ አንፈልግም" ይላሉ።
በትግራይ ፍትህ የሚባል አለመኖሩ የሚናገሩት አቶ መኮንን በበኩላቸው፤ አሁን ያለንበት ጊዜ የትግራይ አስተዳደር እንዲህ አድርጎናል ብለን "ክልላችንን ለአደጋ የምናጋልጥበት አይደለም" ይላሉ።
"ባለፈው የምቀየም ሰው አይደለሁም፤ በትግራይ ብዙ ደምና አጥንት ተከፍሏል። ይህ በማንም ሰው እንዲረገጥና እንዲደፈር አንፈልግም። ፍትህ ባይኖርም ትግራይን እንጠብቃለን፤ ከህወሓት ጋር ያለንን ሂሳብ ኋላ ላይ እንተሳሰባለን" ቢሉም መልሰው ደግሞ ጥያቄ ያነሳሉ።
"ህወሓት አሁን ለትግራይ እሰራለሁ ካለ፤ ለምን ታድያ አሁን ዞር ብሎ አያየንም? ስለምን ችግራችንን አይፈታልንም?"
የትናንቱ ህወሃት
ከተመሰረተ 45 ዓመታት ያስቆጠረው ህወሓት፤ በሂደት የሚገነባው ሥርዓት ዲሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ይሆናል የሚል የብዙዎች ተስፋና የድርጅቱ ቃል ነበር።
ይሁን እንጂ፤ ህወሓት ከበረሀ ወጥቶ "ሥልጣን ከተቆናጠጠ በኋላ መርሆቹን ጥሷል" ብለው የሚተቹት የድርጅቱ አባላት የነበሩ ጭምር ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ፤ በጅግጅጋና አምቦ ከተሞች ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ወደ መቀለ በመሄድ ለነዋሪዎች ንግግር ሲያደርጉ፤ በእያንዳንዷ ንግግራቸውም ነዋሪው በድጋፍ ሲያጨበጭብ ነበር።
ያኔ በህወሓት አስተዳደር የተገፉ የክልሉ ነዋሪዎች ሌላ መሪ በማግኘታቸው ሸክማችን ይቀላል ብለው፤ ተስፋ አድርገው እንደነበር ይናገራሉ። ተስፋው ግን ብዙ አላስኬደም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወሰዷቸው የለውጥ እርምጃዎች ደስተኛ አልሆኑም።
የአገሪቷ አንዳንድ መገናኛ ብዙኀንም በሰሯቸው 'ሙስናና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጋልጡ ናቸው' በተባሉ ዘጋቢ ፊልሞች 'ትግርኛ ተናጋሪ' የሚለውን ማስተጋባታቸው የትግራይን ሕዝብ እንዳስኮረፈም ይጠቅሳሉ።
ሕዝቡም ተቀባይነቱ እየተመናመነ መጥቶ ለነበረው ህወሓት የራራለት መሰለ።
"ይህ ሁሉ፤ ሃገሪቷ ላይ ያለው ሁኔታ የፈጠረው ስጋት እንጂ፤ ህወሓት ተመችቶት አይደለም" የሚለው ስሙ ሊጠቀስ ያልፈለገ የፖለቲካ ተንታኝ፤ ህወሓት ዛሬ ትግራይ ላይ ያገኘው ድጋፍ "ዘላቂ ነው ወይ?" በሚለው እርግጠኛ መሆን አይቻልም ይላል።
በትግራይ፤ ሰላማዊ ትግል ማካሄድ ከባድ መሆኑን የሚናገረው ሕድሮም፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለይ በክልሉ መንግሥት ላይ ትንሽ ለውጥ ቢመጣም፤ አሁንም እኛ በምንፈልገው መንገድ እየሄድን፣ ሃሳባችን እየገለጽን ግን አይደለም ይላል።
"ቢሆንም፤ ቢያንስ ፖሊስ መጥቶ አያስረንም፣ ገበያ ላይም ሰው አይሸሸንም።"
የህወሓት ሊቀ መንበርና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት ድርጅት፤ የህዝብ ጥያቄ ለመመለስም ሆነ የተሻለ የፖለቲካ ምህዳር ለመፍጠር እንደሚሰራ በተለያዩ መድረኮች ገልጸዋል።
"ድርጅቱ አሁን ጠቅልሎ ቢመጣም [ወደ ትግራይ] መጨረሻው ግን የት ነው? የሚለውን ማወቅ አስቸጋሪ ነው" የሚለው ሕድሮም፤ አገሪቷ ላይ ባለው ፖለቲካዊ ሁኔታ በማመካኘት ለግል ጥቅሙ ህዝብ ላይ የፍርሀት ሥነ ልቦና እየፈጠረ ነው" ይላል።
ህወሓት በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን ምላሽ ለማወቅ የታሪኩ መነሻ ወደሆነችው የእንደርታ ወረዳ ተመለስን፤ የወረዳው የህወሓት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደም ዓለም ድርጅታቸው "ህወሓትን የሚቃወም ሆነ ጥያቄ የሚያቀርብ አካል ላይ በደል አልተሰራም" ብለዋል።
"ስላለፈው የአርሶ አደሮቹ ታሪክ የማውቀው ነገር የለም፤ ለአካባቢው አዲስ ብሆንም እንዲህ የሚል መረጃም ግን አላገኘሁም። በአጠቃላይ ግን፤ ከሥርዓት ውጪ የሆነ በሥርዓት ይጠየቃል እንጂ ተቃዋሚ ስለሆነ የሚያስርና የሚገርፍ ድርጅት [ሕወሓት] አይደለም።"
በዚህ ወቅት እንዲህ አይነት ታሪክ የሚያነሱ ሰዎችንም "በአገር ደረጃ እየደረሰ ካለው ጥላሸት የመቀባት ዘመቻ ለይቼ አላያቸውም" ያሉት ኃላፊው፤ "ህወሓት በሃሳብ የሚታገል ድርጅት" ነው በማለት ይናገራሉ።
እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ ፓርቲው ቀደም ብሎ ባካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ፤ ጸረ ዲሞክራሲያዊ ባህሪይ ሲያሳይ መቆየቱን ማመኑ ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment