Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, September 11, 2017

ራያ ቢራና መስቀል - ሰላም ተስፋዬና "አመለጥኩኝ" - ማህበረ ቅዱሳንና ፈራጆቹ

Image may contain: 2 people, people standing and textራያ ቢራና መስቀል - ሰላም ተስፋዬና "አመለጥኩኝ" - ማህበረ ቅዱሳንና ፈራጆቹ 🍾🍾 
ከሁኔታዎች አለመመቻቸት የተነሳ ወቅታዊያችንን በያዙት ጉዳዮች ላይ የተሰማኝን ለማካፈል ሳልችል ብቆይም ዛሬ ግን አስተያየቴን ይዤ መጥቻለሁ። .
🔥🔥🔥 ራያ ቢራና የመስቀል ምልክት ማስታወቂያ 🔥 🔥🔥
አዲሱን ቢራ ለማስተዋወቅ የራያ ቢራ ማስታወቂያ ሲለቀቅ ወቅታዊውን የማህበረሰብ በዓል አሸንዳን በማስመልከት "መልእክቴን ያደምቁልኛል" ብሎ ባሰበበት ልክ በቢራው የቆርኪ ጫፍ ላይ ባህላዊ ክርን፥ ከወገቡ ላይ ቄጤማን ከአንገቱ ላይ ደግሞ የታሰረ መስቀልን ተጠቅሞ አሳይቶናል (በርግጥ የክሩና የቄጤማ እሳቤ በራሱ ደስ የሚያሰኝና መስእብነት ያለው መሆኑን መካድ አይቻልም) የማስታወቂያ ክፍሉ ጥሩ መነሻ ሃሳብ ይዞ እንደተነሳ ማወቅ ይቻላል። ፋብሪካው በተነሳው ተቃውሞ ላይ "ምንም ማሻሻያ እንዳማያደርግ"ም አሳውቋል። ታዲያ ለተፈጠረው ቅሬታ ምን መፍትሔ ያሻል? አንድ ማስታወቂያ ምን መልክ ሊኖረው ይገባል የሚለውን ብናይ ወደድኩ።
🔥 ማስታወቂያ ስንል ሳይንሱ ዘርፈ ብዙ ቢሆንም እንደ መግባቢያ ቀለል ካለው ከወሰድን ግን ማስታወቂያ መነሻ መድረሻ አድርጎ ውጤታማ የሚሆነው የማህበረሰቡን እሴት ባህል ልማድ /society believes, opinion, values, religion/ ሳይንድ መተላለፍ ሲችል ነው። የራያ ቢራ የማስታወቂያ ክፍል ባለሙያዎች ይህን እውቀትይጠፋቸዋል ብዬ ማሰብ አልችልም። ከማህበረሰብ እሴት፥ እምነት፥ ባህል ጋር ሊጋጭ እንደሚችል አስቀድሞ መረዳትና መተንበይ የባለሙያነት አንዱ መስፈርት ነው። ራያ ቢራ የሕዝብ ማስታወቂያ (public advertisement) ሲጠቀም ጥንቃቄ ማድረግ የማስታወቂያ ሳይንሱም ሆነ ነባራዊው ሃቅ ግድ ይለዋል።
🔥 ፋብሪካው ካልጠፋ ምልክት ስለምን መስቀልን መረጠ ተብሎ ሲጠየቅ “በዓሉ ላይ ሴቶች በተዋበ ሁኔታ መስቀል አስርተው ስለሚታዩ ነው” ብሎ መግለጫ ሰጥቷል። ይህ እውነት ነው! ግና በወዲሁ በኩል ደግሞ መስቀሉ በአማኞች ዘንድ ያለው ክብርና ቦታስ ከሚዛን ላይ መቀመጥ አይገባም ወይ የሚለው ጥያቄ አብሮ መመለስ ይገባል። 🔥 ማስታወቂያ ክፍሉ “ባወጣው ያውጣው” ብሎ ካልተጠቀመበት በስተቀር መስቀሉ ቢቀር አሊያም በሌላ ምልክት ቢተካ ኖሮ የተሻለ አማራጭ ሆኖ መቅረብ ይችል ነበር። የራያ ቢራንም ተፈላጊነት በአንዳች ሁኔታ አይቀንስም።
🔥 እንደ ምክረ ሀሳብ አሁንም ቢሆን ማስታወቂያ የድርጅታችንን ምርት ግዙን ብለን በአድማጮች ዘንድ ጥሩ ምስል የምንክስትበት ዘርፍ /promotion undertakes to communicate and promote it's' products to the target market/ እንደ መሆኑ መጠን ከዚህ እውነት ተጋጭቶ ተቃራኒ መልእክት እንዳያስተላልፍብን ትኩረት ማድረግ ተገቢነት አለው።
🔥 አንዳንድ ለራያ ቢያ ያዘኑ የመሰሉ ሰዎች "ምነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራስ አለላችሁ አይደለምን" ብለው ጭብጥ የሌለው ነገር ያቀርባሉ። በ19 መጀመርያዎቹ በንጉሱ የባለድርሻነት ባለቤትነት የተመሰረተው ቢራ ከነበረው አስተሳሰብ ተነስቶ ያንን ትክክል ያልሆነ ምልክትና ስያሜ ተጠቅሟል። እኛ በተሻለ እውቀት መረዳት ግንዛቤና በሰለጠነ ዘመን ላይ ተቀምጠን ካለፈው ስህተት ጋር ራሳችንን ማወዳደራችን ትክክል አይሆንም። ራያ ቢራንም ቢሆን የሚጠቅመው ነገር የለም። ይልቁንስ ለራያ ቢራ ያለንን አጋርነት መግለጽና እድገቱን የምንናፍቅ ከሆነ ራያ ራሱን መመዘን ማየት እና ማደራጀት ያለበት ከዘመኑ እውቀት ፍልስፍና እና ጥበብ ጋር መሆን እንዳለበት አምነን የተሻለው አስተያየት ብንሰጠው ይሻላል ባይ ነኝ።
ሰይጣን ደም ባይኖረውም “ራያ ቢራን የጠጣ የሰይጣን ደም የጠጣ ነው” የሚሉ አካላትም መጀመርያ መጠጣትን እንደዜግነት ግዴታ እና እንደ መንፈሳዊነት መገለጫ ትክክለኛ መስመር አድርጎ መቀበላቸው ላይ እርምት መውሰድ እንዳለባቸው እረዳለሁ።
🦋 🦋 1. - ሰላም ተስፋዬና የመስቀል ምልክት ማስታወቂያ 🦋🦋
ይህን በአጭሩ ባልፈው ይሻለኛል። ተዋናይቷ በራሷ ገጽ ላይ ያሰፈረችውን እንመልከት። "እኔ በትወና መሳተፌን እንጂ ስለተሰራው ተጨማሪ ማስታወቂያ የማውቀው ነገር የለኝም። በዚህም የተቀየማችሁኝን ይቅርታ" ብላለች። (ከዚህ በኃላ ያለው የሰላም ማስታወቂያውን አስቀድማ ማወቅና አለማወቅ ከእኛ እሩቅ ስለሆነ እርሷ ባለችው በይቅርታ ማለፉ የተሻለ አማራጭ ይሆናል) እንደ ባለሙያ ግን የምትሰራው ማስታወቂያ ከህብረተሰቡ ሁሉን አቀፍ ግንዛቤ አኗኗርና አመለካከት ጋር እንዴት ይዛመዳል ብላ በኃላፊነት ስሜት መከታተል ይገባታል ባይ ነኝ
🦋🦋 2. - ሰላም ተስፋዬና “አመለጥኩኝ” 🦋 🦋
ሰላም ተስፋዬ "አመለጥኩኝ" ብላለች ብሎ ከኦርቶዶክስ ወደ ፕሮቴስታንት መግባቷን አስመልከቶ መልካሙ የተባለ ፓስተር በራሱ ቲዮብ ላይ ለጥፎ ሰላምም ከተለያዩ የፕሮቴስታንት አጋልጋዮች ጋር ፎቶ መነሳቷን እንደ ዋቢ አድርጎ ለቆታል። ከዚህ በኃላ የተሰጡ ያሉት አስተያየቶች ግን ግርምትን እንደፈጠረብኝ መደበቅ አልችልም።
🦋 የእምነት መስመሯን ቀየረች ተብሎ ልጅቱን ጥንብ እርኩሱዋን አውጥቶ ማንቋሸሽ መሳደብ መዝለፍ ብሎም ማዋረድ ኢ-ክርስቲያናዊ መንገድ መሆኑን ለመጠቆም ተገድጃለሁ።
አንድ ሰው ከእኛ ጋር ካልሆነ የተሳሳተ ነው ብሎ ከድምዳሜ መነሳት ተገቢ አይደለም። ማንም ሰው የሚፈለገውን የመከተል የማይፈልገውን የመተው መብቱ የተረጋገጠ ነው።
🦋 እንኳን በክርስትና ውስጥ ባለ እምነት ይቅርና ከክርስትናም ወጥቶ ወደ እስልምና ቢገባ (ከእስልምና ወደ ክርስትና ቢመጣ) የዚያን ሰው መብት ልናከብርለት ይገባል። አመለጥኩኝ ማለቷ የእኛን እምነት ማሳጣትና ማወረዷ ነው ብሎ ከመደምደም ይልቅ ልበ ሰፊ ሆኖ ማየቱ ሳይሻል አይቀርም። በአንድ ወቅት በሐረር አካባቢ የነበረ ሳሙኤል የተባለ የፕሮቴስታንት እምነት ፓስተር ወደ ኦርቶዶክስ ተመልሶ በየአድባራቱ እየዞረ ምስክርነት ሲሰጥ አዲስ አበባን አጨናንቋት ነበር። በወቅቱ ፓስተሩ ከጨለማው አሰራር "አመለጥኩ" እያለ ሲናገር በአካልም በካሴት ሰምተነዋል። አንድ ሰው ከእስልምና ወደ ክርስትና ሲመጣ ወይም ከክርስትና ወደ እስልምና ሲገባ ቀርባችሁ ብትጠይቁት አመለጥኩ እንደሚላችሁ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ
🦋 ሰላምም (በርግጥ እምነቷን ትቀይር አትቀይር በራሷ የገለጸችው ነገር ባይኖርም) ብትቀይርስ የኛ ምላሽ ስድብ ዛቻ ማጥላላት ማንቋሸሽ ተገቢነቱ ምን ላይ ነው?
እርሷን በመስደባችን የምናተርፈው ጽደቅ የለም። የተማርነው ወንጌል ፍቅርን እንጂ ጥላቻን አይደለም። በርግጠኝነት እግዚአብሔር የስድባችን አድናቂም ሆነ ተባባሪ አይደለም። በርግጠኝነት ቤተክርስቲያንም የኛን ክፉ ንግግርና ቃላት አትደግፈውም።
💢💢 ....... ማህበረ ቅዱሳንና ፈራጆች ......... 💢 💢
ከሰሞኑ ጉዳዮች አንዱ ያለቦታው ስሙ የተደነቀረውና ባልዋለበት ሜዳ ኩበት ልቀም ሲባል የነበረው ማህበረቅዱሳን ነው። በራያ ቢራ ላይ በተነሳው ተቃውሞ ክብሪት ለኳሹ ይህ ማህበር ነው ብለው ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲያ የሚያስብል ጽሁፍ ያስነበቡን ጥቂት ሰዎች አግኝቻሁ። (የመጻፍ መብታቸውን ባከብርም ስሁት መንገዳቸውን ማረም ግን ግዴታዬ ነው)
💢 ማህበረ ቅዱሳን የዜማ የመጽሐፍት የንባብ የቋንቋ ዲፓርተመንት እንጂ የመጠጥ ዲፓርተመንት አቋቁሞ ስራ የሚሰራበት ዘርፍ የለውም። ታዲያ ከራያ ቢያ ጋር ምን መድረክ ምን አጀንዳ ያገናኘዋል? ወይስ ማህበሩ በይፋ የሰጠው መግለጫ አለ? .. ከዚያም አልፎ ማህበሩን ከዘር ግጭት ጋር ለማላተምም ተሞክሯል። በመሰረቱ እንኳን ማህበረ ቅዱሳን ይቅርና ክርስትንም ከዘር ምደባ የወጣ እምነት ነው። የክርስትና ዘሩ ክርስቶስ እንጂ ሰዎች በምድር የተቧደኑበት ክፍልፋይ አይደለም። ማህበሩም ከሞላ ጎደል በኢትዮጽያ ውስጥ አሉ የሚባሉ ብሔሮችና ብሔረሰቦች አባላት ያሉበት ስብስብ ሆኖ ማን ላይ ቆሙ ነው የትኛውን ዘር ለማጥቃት የተነሳው ተብሎ ቢታሰስ ለትዝብት የሚጥለን ሆኖ የሚቀር ጉዳይ ነው።
💢 በስያሜ ደረጃም “ማህበረ ቅዱሳን” ተብሎ መጠራቱ የማይመጥነው ስያሜ ነው ብሎ መነሳትም ወንጌልን አለማወቅና የመንፈሳዊ ትምህርት ጨዋነትን ከማሳየት የዘለለ ፋይዳ የለውም። ማንም ሰው በክርስቶስ ደም ቅዱስና ንፁህ ነው። (የገዛ በደሉ ቢፈታተነውም) በርካቶች ሆነው ማህበር ቢመሰርቱ ደግሞ የቅዱሳን ስብስብ ወይም ማህበር ከመባል አንዳች የሚያግደው አስተምህሮ የለም። በሌላኛው እውነት ደግሞ ይህ ማህበረ ቅዱሳን በዚህ ስም የተሰየመው “እኛ አባላቱ ልዩ፥ የበቃን፥ የነቃን ቅዱሳን ነን” ብሎ ሳይሆን በማህበሩ የሐዋርያት የጻድቃን የሰማዕታት የቅዱሳን አስተምህሮ ይነገርበታል ከሚል እንደሆነ ከዓመታት በፊት ያነበብኩት ጽሁፋቸውን ማስታወስ እችላለሁ።
💢 ስናጠቃልለው የፈጣሪን መኖር የካደውና የሙሴን ህግጋት የማይቀበለው ታዋቂው ፋላስፋ ኒቼ “ጥርጣሬ በጭንቀት ገደለኝ” እንዳለው ከጥርጣሬ ብዛት ህሊናን ለዝለት አሳልፎ መስጠት ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። በሌላ መልኩ ዋናውን ነጥብን ትተን በሌላ ተያያዠ ባልሆነ ጉዳይ ላይ ማተኮር (missing the point of the argument) ስለሚሆንብን በሚገናኙ ነገሮች ላይ ተመስርተን መነጋገር ለሁሉ ይጠቅማል ባይ ነኝ ...
(((( የሰላም ተስፋዬን - የፓስተር መላኩን መልእክቶች ፓስት አድርጌላችኃለሁ ))))
.................................... ነፃነት አምሳሉ ......................... 02/13/09

No comments:

Post a Comment

wanted officials