አሪክ የተባለው የናይጄሪያ አየር መንገድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሳሳተ መግለጫ ደርሰብኝ ላለው ጉዳት 56 ሚሊየን ዶላር ይከፈለኝ ሲል በፍርድ ቤት ክስ አቀረበ።
አየር መንገዱ ለናይጄሪያ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ባቀረበው የጉዳት ካሳ ክስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣የናይጄሪያ ትራንስፖርት ሚኒስቴርና የናይጄሪያ አቃቢ ህግ ተጠያቂ እንደሆኑ አመልክቷል።
20 አንቀጾች ባለው የክስ አቤቱታ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የፌዴራሉ የናይጄሪያ ትራንስፖርት ሚኒስቴር የአሪክ አየር መንገድ አስተዳደርን ለመውሰድ ጀመርን ያሉትን ድርድር ፍርድ ቤቱ እንዲያስቆምም ተጠይቋል።
በአሪክ አየር መንገድ የቀረበው ክስ እንዳመለከተው አምኮን የተባለ ድርጅት ቀደም ሲል የተቋሙን አስተዳደር እንዲወስድ በመደረጉ ይህንኑ በመቃወም ሁለት የፍርድ ቤት አቤቱታዎች ቀርበው በሂደት ላይ ይገኛሉ።
እነዚህ ክሶች መቋጫ ሳያገኙ የናይጄሪያ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የአሪክ አየር መንገድ አስተዳደርን ለመረከብ ተደራድሬያለሁ ማለቱ ሕገወጥና ለኪሳራ የሚዳርግ ነው ብሏል። _ የአሪክ አየር መንገድ።
እናም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሌላ ተወዳዳሪ ተቋም ጉዳይ ጣልቃ በመግባትና ባደረሰው ጉዳት የናይጄሪያ አቃቤ ህግ ምርመራ እንዲጀምር ፍርድ ቤቱ እንዲያደርግ አሪክ አየር መንገድ አቤቱታ አቅርቧል።
የአሪክ አየር መንገድ ለናይጄሪያ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ክስ ቢያቀርብም ለየትኛው ዳኛ እንደተመራና በመቼ ጊዜ ቀጠሮ እንደተሰጠ ገና የታወቀ ነገር አለመኖሩን የአፍሪካ ፕሬስ ኤጀንሲ ዘግቧል።
No comments:
Post a Comment