Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, September 17, 2017

የአሜሪካ ብሔራዊ የደህንነት ኤጀንሲ የኢትዮጵያው አገዛዝ ዜጎቹን እንዲሰልል የቴክኖሎጂ እገዛና ስልጠና እየሰጠ መሆኑ ተጋለጠ


(ኢሳት ዜና–መስከረም 4/2010)
የአሜሪካ ብሔራዊ የደህንነት ኤጀንሲ የኢትዮጵያው አገዛዝ ዜጎቹን እንዲሰልል የቴክኖሎጂ እገዛና ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ኢንተርሴፕት የተባለ ተቋም አጋለጠ።
ብሔራዊ የደህንነት ኤጀንሲው በኢትዮጵያ የስለላ መረብ እንዲዘረጋ ትልቅ እገዛ ማድረጉን መረጃዎቹን ያሰባሰበው ይሄው ተቋም ገልጿል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በየአመቱ የሀገራትን ሰብአዊ መብት አያያዝ በማስመልከት በሚያወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ዜጎቿን መሰለሏንና ማፈኗን ቢያወግዝም የዚሁ ድርጊት ተባባሪ መሆኑ ግን ትክክል አለመሆኑን ተቋሙ ተችቷል።
አሜሪካ የኢትዮጵያ ዜጎች እንዲሰለሉና እንዲታፈኑ በሚያስችለው የደህንነት ቴክኖሎጂ መረብ ዝርጋታ እጇ አለበት መባሉ ጉዳዩን ውስጡን ለቄስ አስብሎታል።
በአንድ በኩል ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ረገጣ ትፈጽማለች በማለት የምታወግዘው ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ በሌላ በኩል የጉዳዩ ተባባሪ ሆና መገኘቷ ብዙዎችን አስገርሟል።
ኢንተርሴፕት የተባለው ተቋም ሚስጥራዊ ሰንዶችን በመመርመር ይፋ እንዳደርገው የአሜሪካ ብሔራዊ የደህንነት መስሪያ ቤት ኢትዮጵያ የዜጎቿን የስልክ ግንኙነትና ንግግሮችን የሚጠልፍ የቴክኖሎጂ መረብ እንድትዘረጋ ከፍተኛ የቴክኖሎጂና የስልጠና ድጋፍ አድርጓል።
በአንድ በኩል በልማትና በጤና እንዲሁም በሰብአዊ ጉዳይ ላይ ብቻ እርዳታ እሰጣለሁ እያለች የምትፎክረው አሜሪካ በሌላ ሁኔታ የኢትዮጵያውያን መብት እንዲጣስና እንዲታፈን በሚያደርግ ወንጀል ተባባሪ መሆኗ ትልቅ ችግር መሆኑን ኢንተርሴፕት ዘርዝሯል።
እንደ ተቋሙ ገለጻ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የስለላ መረብ መረጃ የቴክኖሎጂና የስልጠና አገልግሎት ስትሰጥ የቆየችው ሽብርተኝነትን ለመከላከል በሚል ሰበብ ነው።
ይህም ሆኖ ግን የኢትዮጵያ አገዛዝ ይህን ቴክኖሎጂ ለሰብአዊ መብት ረገጣና ለአፈና እየተጠቀመበት መሆኑን አሜሪካ እያወቀች ይህን ማድረጓ አግባብነት የለውም ብሏል።
ኢትዮጵያ የተቃዋሚ መሪዎችንና ጋዜጠኞችን በማሳደድና በማሰር እንዲሁም ዜጎችን በመግደል ወንጀል እየፈጸመችበት መሆኑንም ኢንተርሰፕት የተባለው ተቋም ገልጿል።
አሜሪካ ለኢትዮጵያ መንግስት የስለላ መረብ የሰጠችው የቴክኖሎጂ መረብ የአንበሳው ኩራት ወይም ላየንስ ፕራይድ የተሰኘ ነው።
ይህም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2002 በትንሽ የሰው ሃይል ጀምሮ በ2005 ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያደገ ነው ተብሏል።
በዚህ ፕሮጀክት 8 አሜሪካውያንና 103 ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል ተብሏል።
ፕሮጀክቶቹም በአዲስ አበባ፣በድሬደዋና በጎንደር ከተሞች የተዘረጉ መሆናቸው ነው የተገለጸው።
በእነዚህ ፕሮጀክቶችም 7 ሺ 700 ሰንዶችና 900 ሪፖርቶች ከስለላ ስራው በኋላ የተዘጋጁ መሆናቸውን ኢንተርሴፕት አጋልጧል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials