(ኢሳት ዜና–ጳጉሜ 2/2009)
ኢትዮጵያ ያልተረጋጉ ሐገራት ምድብ ውስጥ ደረጃዋ ማሽቆልቆሉን በአሜሪካ የተካሄደ ጥናት አመለከተ።
የምስራቅና የማእከላዊ አፍሪካ ሐገራት በአለም ላይ ካሉና ጥናቱ ካካተታቸው 178 ሐገራት ያልተረጋጉና ሰላም የደፈረሰባቸው ከተባሉ ሀገራት በመጀመሪያው ረድፍ ላይ ተቀምጠዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ከአፍሪካ የሰላምና የደህንነት ካውንስል ጋር በጣምራ ሆነው በአፍሪካ የሰላም ችግር ላይ ለመምከር ትላንት ረቡእ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ምስራቅ አፍሪካና መካከለኛው የአህጉሪቱ ሀገራት ሰላም የደፈረሰባቸውና ያልተረጋጉ መሆናቸውን መሰረቱን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው የጥናት ተቋም ይገልጻል።
በዚሁም መሰረት ደቡብ ሱዳን ሶማሊያን ቀድማ በአንደኛ ደረጃ ያልተረጋጋች ሀገር ስትባል ኢትዮጵያ ደግሞ በፊት ከነበረችበት 19ኛ ደረጃ ወደ 15ኛ ደረጃ ዝቅ በማለቷ ሰላም እየራቃት የመጣች ሀገር ተብላለች።
ይህም ሁኔታ የተሰላው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2016 ከነበረው አሁን ባለው የ2017 አመት ጋር በማነጻጸር እንደሆነ በጥናቱ ተመልክቷል።
ጥናቱ ካካተታቸው 178 ሀገራት ማእከላዊ አፍሪካ 3ኛ ስትሆን ሱዳን 5ኛ ዲሞክራቲክ ኮንጎ 7ኛና ኬንያ 22ኛ ሆናለች።
በጥናቱ ያልተረጋጉ የተባሉት ሀገራት በዚህ መልኩ የተፈረጁት በኢኮኖሚ ክፍተት፣ በቤትና በስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም በውስጣቸው ባለው የግጭት ሁኔታ እንደሆነም ነው የተገለጸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ከአፍሪካ የሰላምና የደህንነት ካውንስል ጋር በአህጉሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ለመምከር ትላንት ረቡእ አዲስ አበባ ገብተዋል።
የጣምራ ስብሰባው በተለይ በሶማሊያ፣ደቡብ ሱዳንና በቻድ ሐይቅ ሰርጥ ዙሪያ ይመክራል ተብሏል።
No comments:
Post a Comment