ጉዳዩ በአዲስ አበባ እንዲታይና ዋስትና እንዲሰጣቸው ያቀረቡት ጥያቄም በፍርድ ቤቱ ውድቅ ሆኗል፡፡
አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ በጥረት ኮርፖሬት ውስጥ አመራር በነበሩ ጊዜ በተጠረጠሩበት የሌብነት ወንጀል በባህር ዳር በሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
ሁለቱም ተጠርጣሪዎች የጤና ችግርና የቤተሰብን ድጋፍ በቅርበት ለማግኘት በሚል የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ በውጭ ሆነው እንዲከራከሩና ጉዳዩ አዲስ አበባ እንዲታይላቸውም ፍርድቤቱን ጠይቀው ነበር።
ተጠርጣሪዎቹ ካለባቸው የጤና ችግር አንጻር በጥንቃቄ የተዘጋጀ ምግብ እንደሚመገቡ ገልጸው፤ ይሁንና በማረፊያ ቤቱ ምግብ በአግባቡ እና በሰዓቱ እንደማይቀርብላቸው ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም ትናንት ምሳ በ10፡00 እንደቀረበላቸው ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የሰብአዊ መብት አያያዛቸው እንዲከበርም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የኢኮኖሚ ችግር እንዳለባቸው እና ጡረታ በአግባቡ እንደማይወስዱም ነው ተጠርጣሪዎቹ የገለጹት፡፡
በባህር ዳር ቤት እና ዘመድ ስለሌለን ቤተሰቦቻችን ከአዲስ አበባ ተመላልሰው ምግብ ለማብሰልም ሆነ ለማገዘ አይመቻቸውም ነው ያሉት ፡፡
በተጨማሪ በማረፊያ ጣቢያው ዙሪያ የተሰበሰቡ ወጣቶች ‹‹ወንጀለኛ፣ ሌባ እና ነብሰ ገዳይ በማለት ክብራችንን እና ህገ መንግስታዊ መብታችንን የሚነካ ድርጊት ፈጽመውብናል:: በከተማዋ ያለው ድባብ ለደህንነታችን እና ጉዳያችንን በደንብ ተከታትሎ ለመከራከር እክል ይፈጥራል፤ ስለሆነም የክርክሩ ጉዳይ አዲስ አበባ ይታይልን›› ሲሉ ለችሎቱ አቅርበዋል፡፡
‹‹የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እና አመራሮች ወንጀለኛነታችን ሳይረጋገጥ ጉዳዩን በማራገብ የደቦ ፍርድ እንዲደርስብን አድርገዋል›› ብለዋል፡፡
ለአብነትም አቶ በረከት በደብረ ማርቆስ ከተማ በወጣቱ የደረሰውን ሁከት እና ግርግር አንስተዋል፡፡
የክልሉ ስነምግባርና ጸረ ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ‹‹ተመዘበረ›› ካለው የሃብት መጠን ከፍተኛነት አንጻር ዋስትና እንዳይሰጣቸውና እንዲሁም የተጠረጠሩበት ወንጀል የተፈጸመው በአማራ ክልል በመሆኑ ጉዳያቸው በባህር ዳር እንዲታይ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡
ምስክሮችን በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ስለሚያቀርብም የጉዳዩን በባሕር ዳር መታዬት ተገቢነት ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ የዋስትና መብታቸውን ከልክሎ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ በመስጠት በጥብቅ ጥበቃ በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ወስኗል፡፡
የተጠረጠሩበት ወንጀል ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ ዋስትና የከለከለው ፍርድ ቤቱ የተመዘበረው ሃብት በአማራ ክልል ስለሆነ ጉዳዩ መታዬት ያለበት በባሕር ዳር ነው ሲል መወሰኑም ታውቋል፡፡
በጥብቅ ጥበቃ እንዲቆዩ ፍርድ ቤቱ የወሰነው ከነበራቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት አንጻር መሆኑንም ችሎቱ አስታውቋል፡፡
አቃቤ ሕግም የተጠረጠሩበትን ጉዳይ አጠናክሮ በ14 ቀናት እንዲያቅረብም ፍርድቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ችሎቱ ውሎውን አጠናቋል፡፡
No comments:
Post a Comment