Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, January 19, 2019

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በናፍቆት ይጠብቁትና ሲመኙት የቆዩትን የጥምቀት በዓሉን በጎንደር እንዳያከብሩ ለምን ተፈለገ?

ቅዱስ ፓትሪያርኩን በጎንደር
እንዳይቆዩ ያደረጋቸው ማነው ?
*★★★*
~ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በናፍቆት ይጠብቁትና ሲመኙት የቆዩትን ጥምቀትን በጎንደር የማክበር ዕቅዳቸው ለምን ተሰረዘ? በዓሉን በጎንደር እንዳያከብሩ ለምን ተፈለገ?
~ "በጎንደር የጸጥታ ችግር ስላለ መንግሥት በአስቸኳይ ይዛችኋቸው ተመለሱ ስላለን ነው የመለስናቸው።" ፕሮቶኮላቸው።
~ "የለም የለም የቅዱስነታቸው ጤንነት አስጊ በመሆኑና የሰሜን ጎንደር የሀገረ ስብከቱ ሰዎችም ይዛችኋቸው በቶሎ ተመለሱ ስላሉን ነው።" ወንድማቸው አቶ ገብረመስቀል።
~ እኛ "ከፓትሪያርኩ ጋር የመጡ ሕገወጥ የልዑካን ቡድኖች በአንድ ቀን ከ100 ሺህ ብር በላይ ስላስወጡን ከእንግዲህ የእናንተ በጀት አይመለከተንም ነው ያልነው። " የሀገረ ስብከቱ ሰዎች "
 Image may contain: one or more people and people sitting
#ETHIOPIA | ~ የቅዱስ ፓትሪያርኩን ደኅንነት በተመለከተ ከስደት ያመጣቸው መንግሥት ከወዲሁ ትኩረት ሰጥቶና ጣልቃ ገብቶ በቅርበት ቢከታተላቸው መልካም ነው።
የቅዱስ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ደኅንነት በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎች ቢደርሱኝም እስከ አሁን ድረስ በቅዱስነታቸው ሕይወት ዙሪያ ምንም ነገር ላለማለት፤ ምንም ዓይነት አስተያየትም ላለመስጠት ራሴን በማግለል ቆይቻለሁ። ወደፊትም በዚህ ጉዳይ ምንም ዓይነት አስተያየት ባልሰጥ ፈቃዴ ነው። የሆነው ሆኖ ግን አንዳንድ ሾልከው የሚደርሱኝ መረጃዎች አስደንጋጭ ሲሆኑብኝ ጉዳዩን ለህዝብ ይፋ ከማድረግ በማለት ዓይኔን በጨው አጥቤ መደወል ያሉብኝና ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የሚባሉ አካላት ጋር ሁሉ ደውያለሁ። እናም ከበቂ በላይ መረጃም አግኝቻለሁ።
የቅዱስ ፓትሪያርኩ ዘመነ ፕትርክና በአስቸጋሪ ውጣ ውረድዶች የተሞላ እንደሆነ ይታወቃል። ከደርግ ሥርዓት መውደቅ በኋላ መጀመሪያ በኬንያና ኋላ በሀገረ አሜሪካ በግዞት እንዲኖሩም የተፈረደባቸው አባት መሆናቸውም ይታወቃል። በተለይ በውጭ የሚገኙት የቀድሞው የስደተኛው ሲኖዶስ አባቶች ቅዱስነታቸውን እንደመያዣ በማድረግ ከቁም እስር ባልተናነሰ መልኩ ከሰው ሳያገናኟቸው በዝግ ቤት ከርቸመውባቸው እንዳቆዩዋቸው የሚናገሩ አሉ። ከካናዳ አሜሪካ ድረስ መኪና እያሽከረከሩ በብዙ ድካም ቅዱስነታቸውን አግኝተው የመጨዋወት አጋጣሚን ያገኙ ሁለት ወዳጆቼም የነገሩኝ ይሄንኑ ነበር። በዚህ ምክንያት ግልጥ ያሉ ጴንጤ መነኮሳት ኢየሱስ አማላጅ፣ ታቦት አያስፈልግም የሚሉ አፍቃሬ ዘርፌና በጋሻው መነኮሳት በእስረኛው፣ በታጋቹ ፓትሪያርክ አማካኝነት ለማዕረገ ጵጵስና በቅተው ይኸው ዛሬ እንደ ደህና ሰው ይፍቱኝ ይባርኩኝ የሚባሉ ጳጳሳት ሆነው እያየናቸው ነው። እኛም ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ ብለን ጮጋ ብለን ተቀምጠናል። በእውነት የስዊዲኑ ሊቀጳጳስ አረጋዊው ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ብዙውን ችግር ያውቃሉ። ለብዙ ቀናትም በስልክ ያወሩኝም ይሄንኑ ነበር።
ቅዱስነታቸው በሀገረ አሜሪካ በስደት ሳሉ ልብሳቸው በላያቸው ላይ እስኪቆሽሽ፣ ከተቀመጡበት ወንበር ላይ ሳይነሱ ኩርምት ብለው ይውሉም ያድሩም ስለነበር አሁን ለገጠማቸው ችግር መንስኤ የሆኗቸውም ይኸው ነው ይባላል። የችግራቸው ምንጩ እነዚሁ ፓትሪያርኩን አግተው እንደያዙና መጠቀሚያ እንዳደረጉዋቸው የሚነገርላቸው የቅርብ ሰዎቻቸው ነን ባይ ግለሰቦች አማካኝነት እንደነበር ይናገራል። " ልጆቼ በእኔ ቲተርና ፊርማ የሚወጣው ደብዳቤ ሁሉ እኔ አላውቀውም። አይመለከተኝምም። እኔን ለሀገሬ አፈር እንዲያበቃኝ ብቻ ጸልዩልኝ " እንዳሏቸው እነዚሁ በሀገረ ካናዳ ኗሪ የሆኑ ወዳጆቼ የነገሩኝንም አልረሳም።
በፈቃደ እግዚአብሔር፣ በተለይ በዲያቆን ዳንኤል ጎትጓችነትና አሳሳቢነት፣ በኮሚቴዎች ጥረት፣ በጠሚዶኮ ዐቢይም ጉትጎታ ቀኑ ደርሶ፣ የቅዱስነታቸውም የስደት ዘመን አብቅቶ በፈቃደ አምላክ ቅዱስነታቸው ከስደት ተመልሰው በክብር ለሀገራቸው በቅተዋል። እነ ዲያቆን ዳንኤል ተጋድለው ቅዱስ ፓትሪያርኩን ወደ ሀገራቸው ባይመልሷቸው ኖሮ አይበለውና ፓትሪያርኩ እረፍተ ዘመን ቢገታቸው ቀሪዎቹ ሌላ አዲስ ፓትሪያርክ ከመካከላቸው መርጠው የቤተክርስትያንን የመከራ ዘመን ለማርዘም እንደ ነበር ይነገራል። ለማንኛውም እግዚአብሔር ያለው ሆኖ አሁን የሚታየው ሁሉ ሆነ።
#ብዥታን_ስለማጥራት
የቅዱስ ፓትሪያርኩን የአቡነ መርቆሬዎስን መመለስ ጨጓራ ያስነሳባቸው ሰዎች የሉም ማለት አይደለም። በተለይ የህወሓት ታጋይ የነበሩ ጳጳሳትና የዘመነ ህወሓት ፈላጭ ቆራጭ የቤተክህነቱ አድራጊ ፈጣሪዎች የያዘ ይዟቸው እንጂ ልክ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የመጣባቸው ያህል ነው ነስር በነስር ያረጋቸው። በስጭቷቸዋል። ነገር ግን ምንም ማድረግ የማትችሉት ነገር ሆኖባቸው እህህህ እንዳሉ ይኸው እስከ አሁን ድረስ አሉ።
ከዚህ የተነሳ ብዙው ጫና የራያ ሰው በሆኑት በጠቅላይ ቤተክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ትከሻ ላይ ነው የወደቀው። ትግሬ ጠሎቹ ግሩፖች አቡነ ዲዮስቆሮስ ትግርኛ ስለሚናገሩና አሁን ባለው አከላል ራያ በትግራይ ስር ስለሆነች እሳቸውን በትግሬነት መድበው ፓትሪያርኩን እየበደሏቸው ነው የሚል ስሞታ ያቀርባሉ። አይደለም አቡነ ዲዮስቆሮስ ዐማራ ናቸው የሚሉ የትግሬ ሰዎች ደግሞ በበኩላቸው ሊቀጳጳሱን ይኮንናሉ። በመሃል አቡነ ዲዮስቆሮስ የገና ዳቦ ሆነው ተገኝተዋል። በተለይ የቅዱስነታቸው ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ ዘመዶች ነን የሚሉ አካላት ያደረሱኝን መረጃ መነሻ አድርጌ በቀጥታ ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ደውዬ ረዘም ላሉ ሰዓታት በዚህ ዙሪያ አውርቼአቸዋለሁ።
በዚህም ምክንያት የብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስን ስቃይ ለመረዳትም ችያለሁ። " ይኸውልህ ዘመድኩን ለቅዱስነታቸው የሚደረገውን ነገር በሙሉ ማንም አያዝበትም። እሳቸው በመረጡት ወንድማቸው በኩል የጠየቁንን ከማሟላት በቀር ሌላ ነገር ውስጥ መግባት አንችልም። ጉዳዩ ስስ ነው። የእኔ ሥራ ይህን እንፈልጋለን ሲሉኝ ማሟላትና ማቅረብ ብቻ ነው። ምክንያቱም ደግሞ የታወቀ ነው። ስለዚህ ሁሉ ነገር የሚሆነው በወንድማቸው በኩል በሚቀርብ ጥያቄ መሠረት ነው የሚፈጸመው በማለት ነበር ያስረዱኝ።
አሁን ምን ተፈጠረ?
የአክሱም ካህናት በጠየቁት ጥያቄ መሠረት ቅዱስ ፓትሪያርኩ የመጀመሪያ የሀገር ውስጥ ሐዋሪያዊ ጉዞአቸውን ወደ አክሱም ጽዮን ለማድረግ ነበር ተዘጋጅተው የነበሩት። የክልሉ ፕሬዘዳንትም ተጠይቀው ዶር ደብረ ጽዮን ከ20 መኪኖች በላይ ለአቀባበሉ ፈቅደው በክብር ተቀብለው ለማስተናገድ ፈቃደኞች እንደነበሩ ይነገራል። ከአክሱም መልስ ደብረ ታቦርና ባህርዳር፣ ከባህር ዳር ጥር 9 ጎንደር ገብተው እስከ ጥር 12 ቆይተው ጥር 13 የኔታ ጥበቡ ጋር ዛራ ሚካኤል ገብተው የአብነት ትምህርት ቤቱን ጎብኝተው ከዚያም የጣና ሐይቅ ላይ የሚገኙ ገዳማትን ጎብኝተው ሊሚለሱ ነበር ዕቅድ የተያዘው ይላሉ የውስጥ አዋቂዎች።
ለዚሁ የቅዱስነታቸው ጉዞ ሲባል የተቋቋመ ኮሚቴ ቅዱስነታቸው በሚጎበኟቸው ሥፍራዎች በሙሉ ሲደርሱ ለገዳማቱና ለአብነት ትምህርት ቤቶች ድጋፍ ይሆን ዘንድ በስማቸው የሚያበረክቱት ወደ 500 ሺ ብር የሚጠጋ ገንዘብም ከባለሃብቶች እንደተሰበሰበም ይነገራል።
ነገር ግን ጉዳዩ እስከአሁን ለማንም ግልጽ ባልሆነ መልኩ ሙሉ በሙሉ ታቀደው የነበሩት ዕቅዶች ሳይፈጸሙ እንዲሰረዙ ተደርገዋል። ብሩ ተሰብስቦ የተዋቀረው ኮሚቴም ፈረሰ። የተዋጣው ገንዘብ በእነ አቶ ወርቁ እጅ ይገኛል የሚሉ አሉ። የአክሱም ጉዞም ተሠረዘ። የመርጦ ለመማርያም፣ የጣና ደሴትና የዛራ ሚካኤል ጉዞም ተሰረዘ። ከሁሉ ከሁሉ ሰፊ ዝግጅት የተደረገበት የጎንደሩ ጉዞአቸው ያለ ሀገረ ስብከቱ ፈቃድ ፕሮቶኮላቸውና የቅዱስነታቸው ወንድም ብቻ በሚያውቁት ምክንያት ተሰርዟል። ጉዳዩን ቅዱስነታቸው ባያውቁትም በመጨረሻ ለጉዳዩ ቅርበት እንዳላቸው የሚናገሩ ወገኖች እንደሚናገሩት ከሆነ በፕሮቶኮሉ ፈቃድ የመጡና ሃገረ ስብከቱ በማያውቃቸው ሰዎች #ውስኪ እንደውኃ በሚጠጡ ግለሰቦች ምክንያት ነው ቅዱስነታቸው ጎንደር በዓለ ጥምቀትን ማክበር እየፈለጉ ሳይወዱ በግዳቸው አንጠልጥለው ወደ አዲስ አበባ የመለሷቸው ተብሏል።
ለቅዱስነታቸው በጎንደር በዓለ ጥምቀትን እንዳይውሉ ምክንያት ነው ተብሎ የጠቅላይ ቤተክህነቱ የሕግ ክፍል በሆኑትና አሁን የቅዱስነታቸው ፕሮቶኮል በሆኑት በአፈ መምህር አባ ገብረሥላሴ በኩል የቀረበው ምክንያት "በጎንደር የጸጥታ ችግር ስላለ መንግሥት በአስቸኳይ ይዛችኋቸው ኑ ስላለን ነው" እንዳሉ የተነገረ ሲሆን። በወንድማቸው በአቶ ገብረ መስቀል በኩል ለቅዱስነታቸው ከጎንደር በዓል መመለስ ምክንያት ነው ብለው ያቀረቡት ነው የተባለው ደግሞ የቅዱስነታቸው ጤንነት አስጊ መሆንና የሰሜን ጎንደር የሀገረ ስብከቱ ሰዎች በአስቸኳይ ከተማውን ለቃችሁ ውጡ ብለው ስለነገሩን ነው ማለታቸው ተነግሯል።
በሀገረ ስብከቱ በኩል ደግሞ የሚቀርበው ምክንያት እኛ ቅዱስነታቸውንና ከእርሳቸው ጋር የሚመጡ ልኡካንን ለመቀበልና ለማስተናገድ አቅቶንም ቸግሮንም አይደለም ይላሉ። የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተናገሩ እንደሚባለው ከሆነ ልዑካኑ ከጠቅላይ ቤተክህነት በጀት አስበጅተው አልመጡም። ከቅዱስ ፓርትሪኩ ጋር የመጡት 5 ሊቃነ ጳጳሳት እዚያው ያሉ 2 ሊቃነ ጳጳሳት በአጠቃላይ 7 አባቶችን ማስተናገዱ አልከበደንም። የከበደን ቤተክህነቱ በጀት በጅቶ መላክ የነበረባቸው የእነ ፋንታሁን ሙጬ እና የእነ እስክንድር፣ የእነ ገብረ ጻዲቅ እና ሌሎች የማይታወቁ፣ በፕሮቶኮሉና በፓትሪያሪኩ ወንድም በአቶ ገብረ መስቀል በኩል የተዘጋጁ ግለሰቦች ወጪ ነው ከዕቅዳችን ውጪ ናላችንን ያዞረው ይላሉ።
በተለይ 10 አለቃ ፋንታሁን ሙጬ ቅዱስነታቸውን ከፍ ዝቅ አድርጎ አባ ሊባኖስ እያለ ሲያላግጥባቸውና መጽሐፍ ሲጽፍባቸው የከረመን ሰው የቅዱስነታቸው አጃቢ አድርጎ ማምጣቱ ሳይንስ በአንድ ቀን መስተንግዶ ብቻ ከመቶ ሺህ ብር በላይ በማውጣታቸውም ጭምር መከፋፈል መፈጠሩንና ከዚህም የተነሳ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በእናንተ የተነሳ እኔ ልወቀስ አይገባም። እኔ ለእናንተ በጀት መመደብም አልችልም። የራሳችሁን በጀት ከጠቅላይ ቤተክህነቱ አስመድባችሁ መምጣት ነበረባችሁ በማለት ውስኪ አውርደው በመጠጣት ላይ የነበሩትን የቅዱስ ፓትሪያርኩ ፕሮቶኮልና እነ አጃቢዎቹን እነ ፋንታሁን ሙጬን መውቀሳቸው ለፓትሪያርኩ መመለስ እንደ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ መቅረቡም ተነግሯል።
እነ ፋንታሁን ሙጬም የጎንደር ሃገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑትን "ጠብቅ እናሳይሃለን" በማለት እንደዛቱባቸውም እኒሁ የመረጃ ምንጮቼ ይነገራሉ። ሥራ አስኪያጁም መልሰው የሚመጣውን ሁል ለመቀበል ዝግጁ ነኝ። በአንድ ቀን 100 ሺህ ብር ለውስኪ አላወጣም። ፓትሪያርኩና ሊቃነ ጳጳሳቱ አይከብዱንም። የእናንተ ግን ከ ሕግ አግባብ ውጪ ነው ከማለታቸውም በተጨማሪ እኛ ይሄን ብር የምናመጣው እኮ በየገጠሩ ዞረን ከምስኪን አብያተ ክርስቲያናት ሰብስበን በስንት ስቃይ የምናመጣው ብር ነው። ስንት ጧፍ ዕጣንና ዘቢብ ያጡ አብያተክርስቲያናት እያሉ እኔ ለቸበር ቻቻ ውስኪ የሙዳየ ምጽዋት ገንዘብ ዝምብዬ በዘፈቀደ አላወጣም። ራሳቸውን ፓትሪያርኩን ሰድቦ መጽሐፍ ላወጣባቸው ግለሰብ የቤተክርስቲያንን ብር አውጥቼ ሜዳ ላይ አልበትንም። ካህናቱም ህዝቡም ይጠይቁኛል። ይወቅሱኛልም። በማለት የግለሰቦቹን በጀት ከለከሉ ይላሉ ጉዳዩን በቅርበት ስንከታተል ነበርን የሚሉት የመረጃ ምንጮቼ።
ከዚህ በኋላ የሆነው ምንድነው ሀገረ ስብከቱ፣ የቅዱስነታቸው ፕሮቶኮልና የቅዱስነታቸው ወንድም ከእነ ፋንታሁን ሙጬ ጋር ያለመስማማት ሆን ተብሎና ፀብ ያለሽ በዳቦ የሆነ ምክንያት አገኘን በማለት ቅዱስ ፓትሪያርኩ በጉጉትና በናፍቆት ከሚጠብቁት የጎንደር የጥምቀት በዓል ከማክበር አሰናክለው፤ በቅዱስነታቸው እጅም ለመባረክ ከሚጠብቋቸው በብዙ ሺ ከሚቆጠር ምእመናን ለይተውና አጣድፈው ወደ አዲስ አበባ እንደመለሷቸውም ተነግሯል።
ከሁሉ ከሁሉ ግር የሚለው ነገር ግን ቅዱስ ፓትሪያርኩ አዲስ አበባ እንደደረሱ የጠቅላይ ቤተክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ለውስኪና ለሕገወጥ ልዑካኑ የህዝብና የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ በከንቱ ሜዳ ላይ አልበትንም ብለው ሕገ ወጥነትን እንደተከላከሉ የሚነገርላቸውን የጎንደሩን ዋና ሥራ አስኪያጁ በፋክስ በተጻፈ ደብዳቤ ከሥራ አስኪያጅነታቸው እንዳስነሷቸው መሰማቱ ነው። ይሄን ለማረጋገጥ ባደረኩት ጥረት ደብዳቤውን አይተናል የሚሉ እማኞች " ደብዳቤው ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ቦታ ሲገኝላቸው ይመደባሉ፣ እስከዚያው ግን ከሥራ አስኪያጅነትዎ ተነስተዋል" ይላልም ተብሏል ለሥራ አስኪያጁ የደረሰው የሞት ደብዳቤ።
እነ ፋንታሁ ሙጬም እንደዛቱት ጉዞውንም አበላሹት፣ አሰረዙት፣ ሥራ አስኪያጁንም አስነሱት። የሆነው ይሄው ነው ተብሏል።
አሁን ጎንደር ባነር አሠርቶ ዛሬ ጠዋት በማለዳ ቅዱስ ፓትሪያርኩን ለመቀበል በጉጉት እየጠበቀ ነው። እስከ አሁን ቅዱስነታቸው መመለሳቸውን የሚያውቅ የለም። ወጣቶች የሚገርም ሠረገላ አዘጋጅተው ቅዱስነታቸውን በዚያ ላይ አስቀምጠው ጎንደርን ለማስባረክ እስኪነጋ ድረስ እየጠበቁ ነው። ነገር ግን ሁሉም ነገር ጎንደሮች እንደፈለጉት አልሄደም። ቅዱስነታቸውም ከጀርባቸው በሚሠራ ቁማር ምክንያት በናፍቆትና በስስት ይጠብቁት ከነበረው የጎንደር የጥምቀት በዓል ሳይፈልጉ በግድ ተገፍተው ነገ በጃንሜዳ ለማክበር በዚያ ይገኙ ዘንድ ተፈርዶባቸዋል።
አሁን እኔ የምፈራው በመሃል ፓትሪያርኩን በማበሳጨት የሞት ጊዜያቸውን ለማፋጠን በሚጥሩ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎችና በሌሎች ወገኖች ሽኩቻና ፍትጊያ እንዲሁም ቅዱስነታቸውን ተጠግቶ ለመበልፀግ በቋመጠ ኃይል ምክንያት በመሃል ስህተት እንዳይፈጠር ነው የምሰጋው።
ጠሚዶኮ ዐብይ ቅዱስነታቸውን ከመንበረ ፓትሪያርኩ ጊቢ አውጥቶ ካዛንችስ ቪላ ቤት ውስጥ ማስቀመጡንም አልወደድኩትም። የደኅንነታቸውም ነገር ቢታሰብበት መልካም ነው። ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እኩልም ቢከበሩ ለሁሉም መልካም ነው ባይ ነኝ። ያለ በለዚያ ግን የቅዱስነታቸው እንባ እሳት ሆኖ ብዙዎችን እንዳይበላ እሰጋለሁ።
ጠቅላይ ሚንስትሩም አካልቦ ወዳመጣቸው ፓትሪያርክ ዐይኑን መለስ ቢያደርግ አይከፋም። አለበለዚያ ግን በሆነ ስህተት፣ በድንገት በሚፈጠር ችግር ምክንያት ሁለት ብሔሮች ለዘለዓለሙ እንዳይቆራረጡ እሰጋለሁ። አበቃሁ።
ሻሎም ! ሰላም !
ዘመድኩን በቀለ ነኝ።
ጥር 11/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።

No comments:

Post a Comment

wanted officials