ይህ በእንዲህ እንዳለም ባለፉት 6 ወራት በሕገወጥ መንገድ አዲስ አበባ የገቡ ከ2ሺ በላይ የጦር መሳሪያዎች እንዲሁም 70 ሚሊየን ያህል የኢትዮጵያ ብርና ከመቶ ሺ ዶላር በላይ የውጭ ገንዘብ በቁጥጥር ስር መዋሉም ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ በወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች መሳሪያ አነስተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተዋጊዎች በከተሞች ጭምር ችግር መፍጠራቸው ሲገለጽ ቆይቷል።
መንግስት ችግሩን በንግግር ለመፍታት ከኦነግ ጋር ያደረኩት ጥረት አልተሳካም ማለቱን ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት ወደ ስፍራው ተንቀሳቅሷል።
የመንግስት ሃይሎች ይዞታቸውን እያሰፉ መሄዳቸውን ተከትሎ መከላከያ ሰራዊቱ ባልደረሰባቸው አካባቢዎች 18 የመንግስትና የግል ባንኮች መዘረፋቸው ይፋ ሆኗል።
ድርጊቱ በኦነግ ታጣቂዎች እንደተፈጸመ ቢገለጽም ኦነግ ዘረፋውን አልፈጸምኩም ሲል አስተባብሏል።
ባንክ የዘረፉት ታጣቂዎች ንብረት ጭምር በማውደም እንዲሁም መከላከያ ሰራዊቱ እንዳይከተላቸው አስፋልት መንገድ በመቁረጥ ተጨማሪ ጉዳት ማድረሳቸው ይፋ ሆኗል።
መንግስት እነዚህን ባንክ የዘረፉና ንብረት ያወደሙ ግለሰቦችን በሕዝብ ጥቆማ በቁጥጥር ስር እያዋላቸው መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።
የተዘረፈውን ገንዘብ ስለመመለሱ ግን የተገለጸ ነገር የለም።
መንግስት ከዘረፋውና ከሕገወጥ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎችን በማሰር ላይ መሆኑ ተገልጿል።
ከታሳሪዎቹ ውስጥ የኦዴፓ አባላት የሆኑ የአካባቢው ባለስልጣናት እንደሚገኙበትም ሪፖርቶቹ አመልክተዋል።
18ቱ ባንኮች የተዘረፉት በጠቅላላ በወለጋ ውስጥ እንደሆነም ታውቋል።
በጉጂ ዞን ሲንቀሳቀስ የነበረው የኦነግ ሃይል ከነመሪው በአባገዳዎች ጥሪ ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሱን ትላንት መዘገባችን ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በሃገሪቱ ውስጥ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ ህገወጥ የጦር መሳሪያና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ተበራክቷል።
በዚህም ባለፉት 6 ወራት ከሐምሌ 1/2010 እስከ ታህሳስ 30/2011 2 ሺ 383 የጦር መሳሪያ አዲስ አበባ ላይ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።
ከመሳሪያዎቹ ውስጥ 2 ቦምብና አንድ መትረየስ እንደሚገኙበትም ተመልክቷል።
ከዚህም በተጨማሪ 68 ሚሊየን 322ሺ 344 ብር እንዲሁም 88ሺ 151 የአሜሪካን ዶላር በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር መያዙንም የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።
በተጨማሪም 9 ሺ 480 ዩሮ፣12 ሺ 620 ፓውንድና የሌሎች ሀገራት ገንዘቦችም በተመሳሳይ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ተመልክቷል።
ከዚህም በተጨማሪ 163 ሺ 600 የሃሰተኛ ብር ኖቶች እንደተያዙም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ሪፖርት መረዳት ተችሏል።
No comments:
Post a Comment