ከዛሬ ጠዋት 12 ጀምሮ በዛላምበሳ በኩል ወደ ኤርትራ በመጓዝ ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ተጓዦች እንዳይገቡ ተከለከሉ፡፡
ዲደብሊውና ቢቢሲ እንደዘገቡት ክልከላው የተደረገው ፍቃድ የላችሁም በሚል ነው፡፡ የኢትዮጵያና ኤርትራ መንግስታት በደረሱት ስምምነት መሰረት ባሳለፍነው መስከረም ወር ድንበሮቻቸውን ከፍተው የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ካንዱ ወደ ሌላዉ ሲመላለሱ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
የዛላንበሳ ነዋሪዎች እንዳስታወቁት እስከ ዛሬ ድረስ የኤርትራም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥታት የይለፍ ፍቃድ አይጠይቁም ነበር፡፡ በዛሬው ዕለት ግን በኤርትራ በኩል የይለፍ ፍቃድ በመጠየቁ በርከት ያሉ መኪኖች በድንበሩ ቆመው እንደሚገኙ በትግራይ ምስራቃዊ ዞን የጉለመከዳ ኮምኒኬሽን ፅሕፈት ቤት የፕሬስ ባለሙያ አቶ የዕብዮ ሙልጌታ ለDW ተናግረዋል፡፡ የጉሎመኸዳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ገብረህይወት ገብረየሱስ በበኩላቸው የዛላምበሳ ድንበር ባልታወቀ ምክንያት ከፌደራልመንግሥት ፍቃድ ለሌላቸው ተጓዦች መከልከሉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ድንበር በኩል “ከፌደራል መንግሥት ፈቃድ መያዝ አለባችሁ” የሚል ምላሽ እንተደተሰጣቸውና ከኤርትራ በኩል ደግሞ የይለፍ ወረቀት እየተዘጋጀ መሆኑን” ነዋሪዎች ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት ግን ያለ ይለፍ ወረቀት ከሁለቱም በኩል መንቀሳቀስ የማይቻል ሲሆን በተጨማሪም በኤርትራ በኩል ድንበር ጥበቃውን እንዲያጠናክሩ በድንበር ጥበቃ ላይ ለተሰማሩ ከላይ መመሪያ እንደተሰጣቸው እየተነገረ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment