በለየለት አምባገነን ስርዓት የምትተቻቸውንና ከኤርትራ ጋር በፍጹም ጠላትነት ውስጥ የቆየችውን ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደሌላ ምዕራፍ ወስደዋል ስትል በጽሁፏ አስፍራለች።
ጋናዊቷ ኤልዛቤት ኦህኔ በአፍሪካ በዕድሜ ትንሹ የሃገር መሪ የ42 ዓመቱ አብይ አህመድ በማለት የጠቀሰቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስለሚከውኗቸው ተግባራትና እንዴት እንደሚከወኑም አስቀድሞ ለመገመት አይቻልም ብላለች።
በለየለት አምባገነን ስርዓት በምትተቸው ኢትዮጵያ በሚያዚያ ወር ወደ ስልጣን የወጡት አብይ አህመድ በአጭር ጊዜ ከወኑ ያለቻቸውን ውጤቶችም ዘርዝራለች።
የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በማንሳት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት እንዲሁም የመብት ተሟጋቾች ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ የተዘጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ድረገጾችንና ቴሌቭዥን ጣቢያዎችን በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ በመፍቀድ ተገኙ ያለቻቸውን ውጤቶች ዘርዝራለች።
በሃገር ውስጥ እየተከናወነ ባለው የለውጥ ሁኔታ ህዝቡ እየተደመመ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ጸሃይ በምዕራብ እንድትወጣ የማድረግ ያህል የማይቻለውን የኤርትራን ጉዳይ በአጭር ጊዜ ዕልባት ማስገኘታቸውን ቢቢሲ ላይ ዛሬ በቀረበው ጽሁፏ ዘርዝራለች።
በጥቂት የአውሮፕላን በረራና የስልክ ግኑኝነት ከኤርትራ ጋር ሰላም ወርዶ ጤናማ ግንኙነት መጀመሩንም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የስኬት ጉዞ ነው ስትል ገልጻለች።
ሴቶችን ወደ ስልጣን በማምጣት ረገድ ጉልህ ርምጃዎች መታየታቸውን ዘርዝራለች።
የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንዲሁም የሚኒስትሮቹ ቁጥር በግማሽ ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሳለች።
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ፣ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርትኳን ሚደቅሳ የመንግስት ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም ሁሉም እንስቶች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የስልጣን ዘመን ወደ ሃላፊነት መውጣታቸውን ጽፋለች።
አምና በሙስና ከስልጣን በወረዱት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ምትክ ሲሪል ራምፎሳ ወደ ስልጣን መምጣታቸው በአፍሪካ ሌላው ትልቅ ክስተት ነው ያለችው ኤልዛቤት ኦህኔ የቀድሞ የተባበሩት መንግስት ዋና ጸሃፊ ኮፊ አናን ህልፈትና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አፍሪካውያንን ውዳቂ ሲሉ መጥራታቸው በጉልህ ክስተትነት ተዘርዝሮ በጽሁፍ ውስጥ ተካቷል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውን ለውጥ በተመለከተ ታላላቅ የምዕራብ ሚዲያዎች ዋሽንግተን ፖስት፣ ኢኮኖሚስት፣ ብሉምበርግ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ርምጃዎቹን በማድነቅና ስጋቶቹን በመጠቆም ጽሁፍ አቅርበዋል።
No comments:
Post a Comment