ከቱርክ ኢስታንቡል ጂጂጋ ድረስ የተዘረጋው የቀድሞ ካቢኔ አባላት ኔትወርክ አዲሱን አመራር ለመጣል እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።
ሰሞኑን ጅጅጋ ላይ ቦምብ ለማፈንዳት የታቀደውን የክልሉ የጸጥታ ሃይል ማክሸፉም ታውቋል።
ከሀገር የኮበለሉት የቀድሞ ካቢኔ አባላት ክልሉን ለማተራመስ ከፍተኛ ገንዘብ መድበው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
የፌደራል መንግስቱ በሶማሌ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ትኩረት እንዲሰጠው ተጠይቋል።
የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት በሶማሌ ክልል ለውጡን ለመቀልበስ በተዘጋጁት የቀድሞ የክልል አመራሮች አንጻር የፌደራል መንግስትና የክልሉ አስተዳደር አፋጣኝ ርምጃ ካልወሰዱ ቀውስ ሊከሰት የሚችልበት እድል ሰፊ ነው።
የሶማሌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሶህዴፓ መዋቅር በቀድሞ የአብዲ ዒሌ ካቢኔ ሊዋጥ ይችላል የሚለው ስጋት እየተጠናከረ መቷል።
ከፓርቲው ውጭ በሆኑት በአቶ ሙስጠፋ ዑመር የሚመራው የሶማሌ ክልል ባለፉት አራት ወራት ሰላምና መረጋጋቱ የተሻለ ቢሆንም ውስጥ ለውስጥ እየተሰራ ያለው የለውጥ ቅልበሳ ተግባር መጪውን ጊዜ የከፋ ሊያደርገው እንደሚችል ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።
በቱርክ ኢስታንቡልና በተለያዩ ጎረቤት ሃገራት ኮብልለው ያሉት የአብዲ ዒሌ ካቢኔ አባላት ከያሉበት በኔትወርክ በመገናኘት ዳግም የሶማሌ ክልልን መቆጣጠር ስለሚችሉበት ሁኔታ ሲመክሩ መቆየታቸውም ታውቋል።
የቀድሞ የሶማሌ ልዩ ሃይል ኮማንደር አብዲራህማን ላባጎሌ በቱርክ ኢስታንቡል የሚገኘውንና የተወሰኑ አመራሮች የሚገኙበትን ቡድን በመያዝ ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ሶማሌ ክልል በመላክ የአቶ ሙስጠፋ ዑመርን አስተዳደር የማወክ መጠነ ሰፊ ተግባራትን አቅዶ በመስራት ላይ ነው ተብሏል።
የቀድሞ የአብዲ ዒሌ ጠባቂ ሚስትና የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ወይዘሮ ሱአድ ፋራህም ከኢስታንቡል ጂጂጋ በመላለስ ይህንኑ ለማወክና ለመበጥበጥ የተዘጋጀውን ገንዘብ ለሚመለከታቸው አካላት ሲያደርሱ እንደቆዩና ሰሞኑንም ለዚሁ ተግባር ወደ ሃገር ቤት መግባታቸውን ነው የመረጃ ምንጮች የሚገልጹት።
በአጠቃላይ 12 የሚሆኑትና መቀመጫቸውን ኢስታንቡል ቱርክ ያደረጉት የቀድሞ ካቢኔ አመራሮች ሀገር ውስጥ ካሉትና አሁንም በሶህዴፓ መዋቅር ውስጥ ስልጣን ይዘው ከሚገኙት አጋሮቻቸው ጋር ሆነው የአቶ ሙስጠፋ ዑመርን ክልላዊ መንግስት በማፍረስ የቀድሞውን አስተዳደር መልሶ ለመትከል መዘጋጀታቸው ታውቋል።
ለዚህም በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ አቶ ሙስጠፋን ከስልጣን የማስወገድ እቅድ ተይዞ በመከናወን ላይ መሆኑንም ከምንጮች መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ካለፈው ዓርብ ጀምሮ በጅጅጋና በአንዳንድ ከተሞች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ገንዘብ ሲበተን እንደነበርና በተለይም ከቶጎ ውጫሌ መነሻውን ያደረገው የገንዘብ ምንጭ ሲሰራጭ መቆየቱም ታውቋል።
የጥምቀት በዓልን ለማወክ ብሎም የፈንጂ ጥቃት በመፈጸም ክልሉን ወደ ለየለት ቀውስ ለመክተት እቅድ ተይዞ እንደነበር የገለጹት ምንጮች በክልሉ መንግስት የደህንነትና ጸጥታ ሃይል ሊከሽፍ ችሏል።
ጉዳዩን በተመለከተ የአቶ ሙስጠፋ ዑመር አስተዳደር የለውጥ ቀልባሾችን እንቅስቃሴ በቅርበት የሚከታተል ቢሆንም ተመጣጣኝ ርምጃ እየወሰደ ባለመሆኑ የለውጡ አካሄድ እየደፈረሰ መምጣቱ ተገልጿል።
የፌደራል መንግስቱም ከአቶ አብዲ ዒሌ መታስር በኋላ ለሶማሌ ክልል ጉዳይ ትኩረት አልሰጠውም በሚል ትችት ይቀርብበታል።
አፋጣኝና ተመጣጣኝ የሆነ ርምጃ በእነዚህ ለውጥ ቀልባሾች ላይ ካልተወሰደ የሶማሌ ክልል ወደ ትርምስ ሊገባ ይችላል ሲሉ ምንጮቹ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ የክልሉን አመራሮች ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
No comments:
Post a Comment