Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, January 22, 2019

በኢትዮጵያ ከ500 የሚበልጡ የሶሪያ ስደተኞች አሉ ተባለ


በኢትዮጵያ ከ500 የሚበልጡ የሶሪያ ስደተኞች እንደሚገኙ ተገለጸ።
እ ኤ አ ከ2011 ጀምሮ በጦርነት ከምትታመሰው ሃገር ሶሪያ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ስደተኞች በልመና እና በመለስተኛ ስራ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙም አልጀዚራ በዘገባው አስፍሯል።

የኢትዮጵያ የስደተኞችና የዜግነት ጉዳይ መምሪያ ቃል አቀባይ አቶ የማነ ገብረመስቀል ለአልጀዚራ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ደሃ ሃገር ብትሆንም ከ20 ከሚበልጡ ሃገራት ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች ብለዋል።
ከሐምሌ መጨረሻ እስከ ታህሳስ መጀመሪያ በ4ወር ከ15 ቀን ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሶሪያውያን ቁጥር በአጠቃላይ 560 ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 157ቱ በስደተኝነት ተመዝግበዋል።
50 የሚሆኑት ጊዜያዊ የመኖሪያ ፍቃድ ሲሰጣቸው የቀሩት በትራንዚትና በቱሪስት ቪዛ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ስደተኞቹ በሱዳን በኩል እንደሚመጡም አክለዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2011 ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ሶሪያውያን ቁጥር ግን አልተገለጸም።
ግጭቱ እንደተነሳ የተሰደደውና ከ5 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ የገባው አብዱላሂ መሃመድ የተባለው የ20 ዓመቱ ሶሪያዊ አዲስ አበባ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ደማስቆ በተባለ ምግብ ቤት ውስጥ በአስተናጋጅነት ያገለግል የነበረው አብዱላሂ ሙሃመድ በሱዳን በኩል በ15 ዓመቱ ኢትዮጵያ መግባቱን ለአልጄዚራ ገልጿል።
ለርሱ ኢትዮጵያ የተረጋጋች ሃገር ስትሆን ህዝቧም ለጋስ ነው ሲል ተናግሯል።
ብዙ ሶሪያውያን በቅዱስ ቁርዓን ውስጥ ኢትዮጵያ የሙስሊም ስደተኞች መጠጊያ እንደነበረች ያውቃሉ ያሉት የኢትዮጵያ የስደተኞችና የዜግነት ጉዳይ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ የማነ ገብረመስቀል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስና በሶሪያ መካከል ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ግንኙነት ብዙ ሶሪያውያን ሙሉ በሙሉ የባዕድነት ስሜት እንዳይሰማቸው ያደርጋል ሲሉም አክለዋል።
በአዲስ አበባ ጉዳዮች በተለይም በቤተክርስቲያንና በመስጊድ አካባቢ እየለመኑ የሚኖሩት ሶርያውያን በአማርኛ ቋንቋ የተጻፈ “እርዱኝ” የሚል ምልክት እንደሚይዙም ከአልጀዚራ ዘገባ መረዳት ተችሏል።
እውነተኛ ስሙን መናገር ያልፈለገውና ራሱን አህመድ በማለት የገለጸው የ18 ዓመቱ ሶሪያዊ በአዲስ አበባ ጎዳና ለልመና የተሰማራው የወንድሙን ልጅ ይዞ ሲሆን ከርሱ ጋር ከወጡት ወንድሙና እህቱ ውጭ መላ ቤተሰቡ በጦርነትቱ አልቀዋል።
“እግዚአብሔር ታላቅ ነው ኢትዮጵያውያን እየተንከባከቡን ነው” ያለው የ18 ዓመቱ አህመድ ሶሪያ ሰላሟ እስኪመለስ በኢትዮጵያ ስራ ማግኘት ካልቻልኩ ያለሁበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው ብሏል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በታህሳስ ወር 2011 በቱኒዚያ በመሃመድ ቡአዚዝ በተለኮሰው የአረቡ ዓለም አብዮት ከተናወጡት የአረቡ ሃገራት አንዷ የሆነችው ሶሪያ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2011 እስከ የካቲት 2016 በጦርነቱ 470 ሺህ  ያህል ሰው እንዳለቀባት የሶሪያ የፖሊስ ምርምር ተቋም አስታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ይፋ ባደረገው መረጃ ባለፍት 8 ዓመታት 7.6 ሚሊዮን ያህል ህዝብ ከሃገሪቱ ሲፈናቀል 5 ሚሊዮን ያህሉ ተሰደዋል።
ሶሪያ 18 ሚሊየን ያህል ህዝብ የሚኖርባት ሃገር ነች።
ከጥንታዊ የዓለም ሃገራት አንዷ የሆነችው 5 ደማስቆና አሌፓ በሚባሉት ጥንታዊ ከተሞች የምትታወቀው ሶሪያ በዋናነት ማለትም 87 በመቶ የሙስሊም ሃገር ብትሆንም ስልጣን የያዙት ከአናሳዎቹ ሺአ ሙስሊሞች የወጡ አሊዊት የሚባለውን ዘርፍ የሚከተሉ የሃገሪቱን መሪነትና የወታደሩን ክፍል መቆጣጠራቸው ለችግሩ መባባስ አስተዋጽኦ ማድረጉም ተመልክቷል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials