ወደ አንድ ግሮሰሪ ገብተው 'እስቲ የሚጠጣ ነገር?' ብለው ሲጠይቁ አልኮል አንሸጥም ብትባሉ ምን ይሰማችኋል? በአሁኑ ወቅት እንደ ኒውዮርክና ለንደን ባሉ ከተሞች ግን አልኮል የማይሸጥባቸው መጠጥ ቤቶች እየተለመዱ መጥተዋል።
ለብዙዎች አልኮል የማይሸጥበት መጠጥ ቤት ልክ አሳ እንደሌለው የአሳ ገንዳ አልያም ዳቦ የማይሸጥበት ዳቦ ቤት ይመስላል። ነገር ግን መጠጥ ቤቶች ለብዙ ሰዎች እንደ ሁለተኛ ቤታቸው በሚያገለግልበት ዘመን ምን ያክል ሰዎች በዚህ ሃሳብ ይስማሙ ይሆን?
ሳም ቶኒስና ጓደኛው ረጂና ዴሊያ 'ጌትዌይ' የተባለ አልኮል የማይሸጥ መጠጥ ቤት በኒውዮርክ ከተማ ከፍተዋል። ሳም እንደሚለው የዚህን አይነቱን መጠጥ ቤት ለመክፈት ሃሳብ የመጣለት ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር።
ሳምና ወንድሙ መጠጥ የማይሸጥበት መዝናኛ ቤት ፍለጋ ኒውዮርክን ቢያስሱም አንድ ቤት እንኳን ማግኘት እንዳቃታቸው ያስታውሳል።
''ወጣ ብለን ምንም አይነት አልኮል ሳንጠጣ መዝናናት ብንፈልግም እጅግ ከባድ ነው። ለብዙ ሰዎችንም ይህንን ጥያቄ ሳቀርብላቸው በሚያስገርም ሁኔታ አልኮል መጠጣት የማይፈልጉ እንዳሉ ተረዳሁ።''
ከዚህ ልምዳቸው በመነሳት ሳምና ጓደኛው ምንም አይነት አልኮል የማይሸጥበት አነስተኛ ግሮሰሪ ከፍተዋል። ሌላው ቢቀር የአልኮል መጠናቸው እጅግ አነስተኛ የሆኑ መጠጦች እንኳን በዚህ ግሮሰሪ አይሸጡም።
በአሜሪካ ህግ መሰረት 0.5 በመቶና ከዚያ በታች አልኮል መጠን ያላቸው መጠጦች ከአልኮል ነጻ ተብለው ነው የሚተዋወቁት። ነገር ግን የሳምና ጓደኛው ግሮሰሪ ለእንደዚህ አይነቶቹ መጠጦች እንኳን ቦታ የላቸውም።
''ከእኔ ልምድ በመነሳት አልኮል መጠጣት አይደለም የአልኮል ሽታ እንኳን የሚረብሻቸው ሰዎች ብዙ ናቸው። ምክንያታቸው ግላዊም ሊሆን ይችላል፤ ሃይማኖታዊም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የእነሱንም ፍላጎት መጠበቅ ተገቢ ይመስለኛል'' ብሏል ሳም።
ጌትዌይ ባርና ግሮሰሪ ልክ እንደማንኛውም መጠጥ ቤት ምሽት ላይ የሚከፈተው ሲሆን መብራቶቹም ቢሆኑ ደብዘዝ ያሉ ናቸው። ስለዚህ ወደውስጥ የሚገባ ሰው ከሌሎች መጠጥ ቤቶች ምንም የተለየ ነገር አይመለከትም።
እንደ ጌትዌይ ወዳሉ መጠጥ ቤቶች የሚሄዱ ደንበኞች ሁሉም አልኮል ከነጭራሹ የማይጠጡ አይደሉም። ምናልባት በቀጣይ ቀን ሥራ ኖሮባቸው ቀለል ያለ ምሽት የፈለጉ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ከስካር መንፈስና ከሰካራሞች ራቅ ብለው መዝናናት የሚፈልጉ ናቸው።
ሎሬሊ ባንድሮቭስኪ የ32 ዓመት ወጣት ነች። ኒውዮርክ ውስጥ ከአልኮል ነጻ የሆኑ መጠጥ ቤቶችን ለብዙ ጊዜ ስታበረታታ እንደቆየች የምትናገረው ሎሬሊ እንደ 'የጌትዌይ' ያሉ መተጥ ቤቶች መከፈት ለብዙዎች ደስታን ይፈጥራል።
''መጠጥ ቤቶች መዝናኛ ነው መሆን ያለባቸው። ሁሌም ቢሆን መዝናኛ ሲባል መጠጥና መስከር ይያያዛሉ። የማናስታውሳቸውና ብዙ ጊዜ የምንጸጸትባቸው ነገሮችን የምናደርገው አልኮል ስንጠጣ ነው። ይህንን ማስቀረት ከተቻለ ለእኔ ተመራጭ ነው'' ትላለች።
በቅርቡ እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በመላው ዓለም ያሉ ወጣቶች የአልኮል ፍጆታቸውን እየቀነሱ ነው። የእንግሊዙ ስታትስቲክስ ቢሮ በሰራው የዳሰሳ ጥናት መሰረት ጥያቄው በቀረበላቸው ወቅት ለአንድ ሳምንት ያክል አልኮል ያልጠጡ ወጣቶች ቁጥር 56.9 በመቶ ደርሶ ነበር።
በተመሳሳይ መልኩ በአሜሪካ የሚገኙ ጎልማሶች ላይ በተሰራ ሌላ ጥናት 52 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች የአልኮል መጠናቸውን እየቀነሱ አልያም ለመቀነስ እያሰቡ እንደሆነ ተናግረዋል።
ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ከአልኮል ነጻ የሆኑ መጠጦች መለመዳቸውና አልኮል የማይሸጥባቸው መጠጥ ቤቶች መበራከት የሚያስተላልፈው መልዕክት ያለ ይመስላል።
ሰዎች ለመዝናናት ግድ አልኮል መተጣት የለባቸውም የሚለው ሃሳብም ተቀባይነት እያገኘ ነው።
No comments:
Post a Comment