Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, November 2, 2019

ወንድሟን ለማስታመም በሰላሳ ሳንቲም ብቻ የኖረችው ቻይናዊት


ቻይናዊቷ ዉ ሁያን ላለፉት አምስት ዓመታት የኖረችው በቀን ሰላሳ ሳንቲም ብቻ እያወጣች ነበር
Image copyrightFENG VIDEO
አጭር የምስል መግለጫቻይናዊቷ ዉ ሁያን ላለፉት አምስት ዓመታት የኖረችው በቀን ሰላሳ ሳንቲም ብቻ እያወጣች ነበር
ቻይናዊቷ ዉ ሁያን ላለፉት አምስት ዓመታት የኖረችው በቀን ሰላሳ ሳንቲም ብቻ እያወጣች ነበር። ሕይወቷን በሰላሳ ሳንቲም (ሁለት ዮዋን) ትገፋ የነበረው ቆጣቢ ስለሆነች ሳይሆን ታማሚ ወንድሟን የማስተዳደር ግዴታ ስለወደቀባት ነበር።
ሰላሳ ሳንቲም (በአሜሪካ ዶላር ምንዛሬ) በቂ ምግብ ሊገዛላት ያልቻለው የ24 ዓመጠቷ ቻይናዊት፤ በምግብ እጥረት ሳቢያ ሆስፒታል ገብታለች። ዜናውን የሰሙ ቻይናዊያን ወደ አንድ ሚሊዮን ዮዋን (114,000 ዶላር) አሰባስበውላታል።
ዉ ሁያን የኮሌጅ ትምህርቷን እየተከታተለች ጎን ለጎን ወንድሟን ለማስታመም ትጥር ነበር። በያዝነው ወር መባቻ ላይ መተንፈስ ሲያቅታት ወደ ሆስፒታል የሄደችው ቻይናዊት፤ ክብደቷ 20 ኪሎ ግራም ብቻ ደርሶ ነበር።
ባለፉት አምስት ዓመታት በቂ ምግብ ባለማግኘቷ የልብና የኩላሊት ችግር እንደገጠማት ሀኪሞች ተናግረዋል።
የዉ ሁያን እናት የሞቱት የአራት ዓመት ልጅ ሳለች ነበር። አባቷ ደግሞ ተማሪ ሳለች ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። እሷና ወንድሟን ከሚረዷቸው ዘመድ አዝማዶች የሚገኘው ገንዘብ ባጠቃላይ የአዕምሮ ህመም ላለበት ወንድሟ ህክምና ይውላል።
ስለዚህም ቻይናዊቷ በቀን ማውጣት የምትችለው ሰላሳ ሳንቲም ብቻ ነበር። በሰላሳ ሳንቲም ቃርያ እና ሩዝ ገዝቶ ከመብላት ውጪ አማራጭ አልነበራትም።
ዉ ሁያን እና ወንድሟ የተወለዱበት የቻይናው ጉዋንዡ ግዛት በርካቶች በድህነት የሚማቅቁበት እንደሆነ ይነገራል።
በምግብ እጥረት ምክንያት ሆስፒታል ስትገባ ብዙዎች መንግሥት ተገቢውን ድጋፍ ሊያደርግላት ይገባ ነበር ብለው ቁጣቸውን ገልጸዋል። ቻይና የኮምኒስት ፓርቲ አገዛዝን 70ኛ ዓመት ለማክበር አላስፈላጊ ወጪ ማፍሰሷን በማጣቀስ መንግሥትን ያብጠለጠሉም አልታጡም።
የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዉ ሁያን የምትማርበት ኮሌጅ ለምን አልደገፋትም? ሲሉም ወቅሰዋል። የክፍል ጓደኞቿ ወደ 40,000 ዩዋን (5,700 ዶላር) የደጎሙ ሲሆን፤ ከትውልድ ቀዬዋም ድጋፍ ተሰጥቷታል።
የቻይና መንግሥት በየወሩ ከ300 እስከ 700 ዩዋን እንደሚለግስ አስታውቋል። አሁን በድንገተኛ አደጋ ድጋፍ 20,000 ዩዋን እንደሚሰጣትም ተገልጿል።
ምንም እንኳን የቻይና ምጣኔ ኃብት ቢመነደግም ድህነት ሙሉ በሙሉ አልተወገደም። አገሪቱ እኩልነት የሰፈነባትም አይደለችም።
ከሁለት ዓመት በፊት የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው፤ 30.46 ሚሊዮን ቻይናውያን ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ።
ቻይና በ2020 ድህነትን እቀርፋለሁ ብትልም፤ ከገቢ አንጻር በዜጎቿች መካከል የሰማይና የምድር ልዩነት ያለባቸው አገሮች ዝርዝር ውስጥ ትገኛለች።

No comments:

Post a Comment

wanted officials