ሳሃር ታባር፡ ኢራናዊቷ የኢንስታግራም 'የአንጀሊና ጆሊ የሙት መንፈስ' ታሰረች
አሜሪካዊቷን ተዋናይ አንጀሊና ጆሊን ለመምሰል ከፍተኛ ርቀት ተጉዛ በምታጋራቸው ፎቶግራፎች ዕውቅና ያገኘችው ኢራናዊቷ የኢንስታግራም ኮከብ መታሰሯን ሪፖርቶች አመለከቱ።
ሳሃር ታባር የታሰረችው በምትለጥፋቸው ፎቶች በማርከስና በማዋረድ፣ ግጭት በመቀስቀስ እንደሆነ ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።
ባለፈው ዓመት በኢንስታግራም ገጿ ላይ የምትለጥፋቸው ፎቶግራፎች በከፍተኛ ሁኔታ በኢንተርኔት የተጋሩ ሲሆን፤ በአለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ መነጋገሪያ ርዕስ ሆና ነበር።
ሳሃር ምንም እንኳን ተዋናይቷን ለመምሰል 50 ጊዜ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና አድርጋለች የሚል ወሬ ቢናፈስም፤ የምታጋራቸው ፎቶግራፎች ግን በደንብ የታደቱ [ኤዲት የተደረጉ] እንደሆኑ ተገልጿል።
የ22 ዓመቷ ሳሃር ታባር የአንጀሊና ጆሊን 'ዞምቢ' (ብዙ ጊዜ በአስፈሪ ፊልሞች ላይ የምናያቸው የሙት መንፈስ ገፅታ) ገፀባህርይ በመላበስ በፎቶግራፍና በተንቀሳቃሽ ምስል በማጋራቷ የዓለምን ሚዲያ ትኩረት መሳብ እንደቻለች የቢቢሲ የመካከለኛው ምስራቅ ምሁር ሰባስቲያን አሸር ተናግረዋል።
ምስሉ የተሰረጎዱ ጉንጮች፣ በጣም የሚያስፈራ ፈገግታ እና በካርቱን አሳሳል ስልት የተሠራ ተጣሞ ወደ ላይ ቀጥ ያለ አፍንጫ ያለው ፎቶግራፍ በመለጠፍ ተዋናይት አንጀሊና ጆሊን ለመምሰል ባደረገችው የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ሳቢያ የተፈጠረባት እንደሆነች አድርጋ ምስሉን ታጋራ ነበር።
ይሁን እንጂ በኢንስታግራም ገጿ ላይ በሚያስደንቅና በሚያስደነግጥ መልኩ የተከታዮቿ ቁጥር መበራከት ምክንያት የምትለጥፋቸው 'የመንፈስ' አምሳያ ፎቶዎች በሜካፕ እንደሆነና፤ ፎቶዎቹም በጥንቃቄ ኤዲት በማድረግ ራሷን ወደ ጥበብ ስራ መቀየሯን ፍንጭ ሰጥታለች።
የፍትህ ባለሙያዎች ሳሃርን እንድትታሰር ያደረጉት የተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍሎች በእሷ ላይ ቅሬታ በማቅረባቸው እንደሆነ ታስኒም የዜና ኤጀንሲ አስታውቋል።
ጥፋተኛ የተባለችውም በማርከስና በማዋረድ፣ ግጭት በመቀስቀስ፣ በሕገ ወጥ መንገድ ንብረት በማፍራት፣ የአገሪቷን የአለባበስ ሥነ ስርዓት በመጣስ እና ወጣት ዜጎችን ሙስና እንዲሠሩ በማበረታታት እንደሆነ ተነግሯል።
ይህንንም ተከትሎ የኢንስታግራም ገጿም ተዘግቷል።
ሳሃር በኢራን ከሕጉ ጋር የተቃረኑ ነገር ግን ተፅዕኖ ፈጣሪዎችና የፋሽን ጦማሪያን ዝርዝር ውስጥ ገብታ ነበር።
እስሯን ተከትሎ በተለያዩ የኦንላይን ተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ውዝግብ የፈጠረ ሲሆን ፤ ባለሥልጣናቱንም ማውገዛቸውን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል። በትዊተር ገጽ ላይ ከተንሸራሸሩት ሃሳቦች መካከልም "ግድያ እና ከፍተኛ ማጭበርበር ልትፈፅም ትችል ነበር" የሚል ይገኝበታል።
No comments:
Post a Comment