ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ሲባልለት የነበረውን ዋትስአፕን ሰብሮ የሚገባና የተጠቃሚዎችን መልዕክት በመለወጥ ያላሉትን እንዳሉ አድርጎ የሚያቀርብ አዲስ መተግበሪያ [አፕ] እንዳለ ተደረሰበት።
የመረጃ መረብ ደህንንት (ሳይበርሴኪዩሪቲ) ባለሙያዎች፤ አንድ መተግበሪያ የዋትስአፕ መልዕክትን በመበዝበር ተጠቃሚዎች ያላሉትን ነገር እንዳሉ በማስመሰል ማጭበርበር እንደሚችል ደርሰንበታል እያሉ ነው።
ኦዴዎ ቫኑኑ የተሰኙ ባለሙያ ለቢቢሲ ሲናገሩ መሣሪያው ተጠቃሚዎች ዋትስአፕ ላይ የተላላኩትን መልዕክት አጭበርባሪዎች እንደሚፈልጉት ማጣመም እንዲችሉ ዕድል ይሰጣል ይላሉ።
ለምሳሌ እርስዎ ለወዳጅ ዘመድዎ የላኩትን የሰላምታ መልዕክት ወደ ሐሰተኛ ዜና በመቀየር ለሌላ የዋትስአፕ ተጠቃሚ ወይም ቡድን መላክ ያስችላል።
ላስ ቬጋስ ላይ በተካሄደ አንድ የሳይበርሴኪዩሪቲ ምክክር ላይ ይፋ የተደረገው ይህ መዝባሪ መሣሪያ 'የኮምፒውተር መዝባሪዎች የዋትስአፕ ተጠቃሚዎችን መልዕክት እንዳሻቸው እንዲሾፍሩ ያስችላል' ተብሎለታል።
የዋትስአፕ ባለቤት የሆነው ፌስቡክ ስለጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠየቅም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።
«ሰዎች ዋትስአፕ ላይ የፃፉትን የትኛውንም መልዕክት መቀየር ይቻላል» ይላሉ ኦዴዎ። አልፎም የእውነተኛውን ዋትስአፕ ተጠቃሚ ማንነት መቀየር እንዲሚያስችል ባለሙያው ይናገራሉ።
አንድ መሰል አጭበርባሪ መተግበሪያ ደግሞ ለሰው 'ኢንቦክስ' ያደረጉትን መልዕክት አስተያየት [ኮሜንት] በማስመሰል ያወጣ ነበር። ነገር ግን ፌስቡክ ይህንን መተግበሪያ ማስወገድ መቻሉን ባለሙያው ይናገራሉ።
ይህኛውን የዋትስአፕ መልዕክት ቀማኛ ለመከላከል ግን ፌስቡክ አቅሙ የለኝም የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው የመረጃ መረብ ደህንንት ባለሙያው ኦዴዎ ይገልፃሉ።
ይህንን መሣሪያ የፈጠሩት ሰዎች ዓላማ ምን ይሆን? ተብለው የተጠየቁት ባለሙያው ዋነኛው ሃሳብ ዋትስአፕ ተጋላጭ መሆኑን ለማሳየትና ደህንነቱን የበለጠ ሊያጠናክር እንደሚገባ ለማሳሰብ ነው ይላሉ።
«ዋትስአፕ ከዓለም ሕዝብ 30 በመቶ ያህሉን ያገለግላል። እኛ ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን። ሐሰተኛ ዜና [ፌክ ኒውስ] ትልቅ አደጋ ጋርጦብናል። ሁለን እርግፍ አድርገን ምንም እንዳልተፈጠረ ማስመሰል የለብንም።»
ዋትስአፕ የሐሰተኛ ዜና ማስፋፊያ አንዱ መድረክ እንደሆነ ይነገርለታል፤ በተለይ ደግሞ በሕንድ እና ብራዚል። የሃሰተኛ መረጃዎቹ ሥርጭት ግጭት ከማስነሳት አልፎ የሰው ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል።
ዋትስአፕ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ መላዎችን ቢያቀርብም አደጋው ሙሉ በሙሉ የተቀረፈ አይመስልም።
No comments:
Post a Comment