Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, August 13, 2017

በባህር ዳር ከደረሰው የቦምብ ጥቃት ጋር በተያያዘ በመንግስት ዘጋቢ ፊልም በመዘጋጀት ላይ መሆኑ ታወቀ


(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 8/2009) 
ቅዳሜ ምሽት በባህር ዳር ከደረሰው የቦምብ ጥቃት ጋር በተያያዘ በመንግስት በኩል ዘጋቢ ፊልም በመዘጋጀት ላይ መሆኑ ታወቀ።
ቦምቡን ያፈነዱትና በቁጥጥር ስር የሚገኙት ተጠርጣሪዎች ከደቡብ ጎንደር ዕብናት የመጡ ናቸው የሚል መልዕክት የሚያስተላልፈው ዘጋቢ ፊልም ቀረጻው እየተካሄደ ሲሆን በቅርቡ እንደሚለቀቅ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የግብር ጭማሪውን በመቃወም በምስራቅ ጎጃም በተለያዩ ከተሞች የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ መቀጠሉ ታውቋል።
በባህርዳር ከ100 በላይ የባጃጅ ታክሲዎች ታስረዋል። በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሀረርጌ፡ በቄሌም ወለጋ፡ በጊምቢ ሱቆች ተዘግተዋል። የንግድ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ቆሟል።
በ1ዓመት ውስጥ በትንሹ ለ7ጊዜያት ተፈጽሟል። ነሀሴ 1/2008 በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ መንግስት ጥይት ከ50 በላይ ወጣቶቿን የተነጠቀችው ባህርዳር ከዛን ጊዜ ወዲህ የቦምብ ፍንዳታ በተደጋጋሚ ሲፈጸምባት ቆይቷል። የቅዳሜው ደግሞ የተለየ ነበር።
በሰሞንኛው አድማ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት በፈሰሰባት፡ ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር ባልተለያት ባህርዳር ሁለት ተከታታይ የቦምብ ፍንዳታ መፈጸሙ የስርዓቱን አቅም የተፈታተነ መሆኑ ታምኖበታል።
በአማራ ክልል ፕሬዝዳንት በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው መሪነት በህወሃት ባለስልጣናት አዘጋጅነት በጎንደር እየተደረገ ያለው ስብሰባም ይህን ለስርዓቱ አስደንጋጭ የተባለውን ክፍተት ለመነጋገር ነው ተብሏል።
ቅዳሜ ዕለት የፈነዳው ቦምብ በነሀሴ አንዱ ሰማዕታትን የማሰቡ ዘመቻ ላይ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው የንግድ ቤታቸውን ክፍት ባደረጉ ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። በፍንዳታው ሁለት ሰዎች መጎዳታቸውን መንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ይህን አደጋ ያደረሱትን ይዣለሁ ብሏል።
ሊቦ ከመከም ላይ ተያዙ የተባሉት ግለሰቦች ከደቡብ ጎንደር ዕብናት የመጡ ናቸው በሚል ዘጋቢ ፊልም እየተዘጋጀባቸው እንደሆነ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። እንደ ምንጮቹ ከሆነ የህወሃት መንግስት ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ሰዎች በመያዝ፡ የሚያመልጠን የለም ዓይነት መልዕክት በማስተላለፍ ፍርሃት ለመፍጠር በሚል የተሰራ ቲያትር እንደሆነ ነው ለመረዳት የተቻለው።
በዕለቱ አካባቢውን የሚጠብቁት የማህበረሰብ ፖሊስ አባላት በሌሎች በአካባቢው ምድብተኛ ባልሆኑ የጸጥታ ሃይሎች እንዲተኩ መደረጋቸው በባለስልጣናቱ ዘንድ የእርስ በእርስ ውዝግብን ፈጥሯል።
እነዚህ የማህበረሰብ ፖሊስ አባላት እንዲቀየሩ በተደረገበት ምሽት የቦምብ አደጋው መፈጸሙ ጉዳዩን አነጋጋሪ አድርጎታል። ቦምቡ በፈነዳበት ምሽት በርካታ ሰዎች የታሰሩ ሲሆን እስካሁን አለመለቀቃቸው ታውቋል።
ባህርዳር ከ1ሳምንት በኋላም በርካታ ሱቆች እንደተዘጉ ናችው። የሆቴል ባለቤቶች፡ ከፍተኛ ነጋዴዎች በአፈሳ ተይዘው እስር ቤት የገቡ ሲሆን ዛሬ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ታውቋል።
ከ100 በላይ ሚኒባስና የባጃጅ ተሽከርካሪዎች በአድማው ተሳትፋችኋል ተብለው መታሰራቸውንም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የዛሬ ሳምንት በስራ ማቆም አድማ የጀመረችው ደብረታቦር እስከዛሬ ሱቆቹ እና መደብሮቹ ታሽጓል የሚል ወረቀት የተለጠፈባቸው ዛሬ ድረስ ዝግ እንደሆኑ ናቸው።
የከተማዋ አጠቃላይ እንቅስቃሴ የተገደበ ሆኗል። የስራ ማቆም አድማውን አስተባብረዋል ፣ተሳትፈዋል በሚል የሀገር ሽማግሌወችን ፣ታዋቂ ሰዎችን፣ እንዲሁም ወጣቶች ታፍነው ተወስደዋል።
በስራ ማቆም አድማው ተሳትፋችኋል በሚል ሰሌዳቸው የተወሰደባቸው ባለባጃጆች ቅጣት አምስት መቶ ብር እና ግብር ሁለት ሺ አምስት መቶ ብር ካልከፈሉ እንደማይሰጣቸው የከተማው አስተዳደር መወሰኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በተያያዘ ዜና በምስራቅ ጎጃም አድማ በተጀመረባቸው ከተሞች አሁን ድረስ ወደ ስራ ያልገቡ እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።
ሱቆችና መደብሮች ተዘግተው ሁለተኛ ሳምንታቸውን እየተሻገሩ ሲሆን ግብር አንከፍልም የሚል አቋም የያዙት ነጋዴዎች ላይ እስራትና አፈና እየተፈጸመ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በሰሜን ጎንደር በመተማና በሌሎች አካባቢዎች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ አሁንም የቀጠለ ሲሆን ሱቆችና መደብሮች ዝግ መሆናቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል። በኦሮሚያም በተመሳሳይ አድማ ላይ የሰነበቱ አካባቢዎች እስካሁን ወደ እንቅስቃሴ እንዳልገቡ ታውቋል።
ከግብር ጭማሪው ጋር በተያያዘና በፖለቲካ እስረኞች ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃና ኢሰብአዊ አያያዝ በመቃወም እየተካሄደ ያለው አድማ በተለይ በምዕራብ ሀረርጌና በወለጋ በስፋት ቀጥሏል።
በጊምቢ ሙሉ በሙሉ ሱቆችና መደብሮች ተዘግተው የዋሉ ሲሆን በአጋሮም የንግድ እንቅስቃሴው በአድማው ምክንያት መቆሙን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የአድማ ጥሪ የተበተነ በመሆኑ በቀጣዮቹ ቀናት ተመሳሳይ እርምጃዎች ይጠበቃሉ ተብሏል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials