Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, August 25, 2017

አውሮፓውያን በኤርትራ ላይ የያዙትን አቋም ማለሳለስ መጀመራቸው ህወሃትን ስጋት ላይ ጥሎታል

አውሮፓውያን በኤርትራ ላይ የያዙትን አቋም ማለሳለስ መጀመራቸው ህወሃትን ስጋት ላይ ጥሎታል
(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 19/2009)
ከባድመ ጦርነት ጋር በተያያዘም ይሁን የኢትዮጵያን የነጻነት ሃይሎች ትደግፋለች በሚል ምክንያት ህወሃት በብቸኝነት የያዘው የኤርትራ ፖሊሲ እየከሸፈበት መምጣቱ ግራ እንዳጋባው በኒዮርክ የኢትዮጵያ የተመድ ቅርንጫፍ ውስጥ የሚሰሩ ምንጮቻችን የላኩን መረጃና ሰነድ ማስረጃዎች ያመለክታሉ።
የሌሎችን ብሄር ተወላጆች ባለማመን በህወሃቱ አባልና በቀድሞው የአለማቀፍ ድርጅቶች ዳይሬክተር ጄኔራል በአዲሱ ሹመታቸው የሱዳን አምባሳደር በሆኑት አቶ ሙሉጌታ ዘውዴ እና በጥቂት የህወሃት ባለስልጣናትና ምሁራን የተረቀቀው የኤርትራ ባለስልጣናትን በአለማቀፍ ፍርድ ቤት የማቆም እንዲሁም በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ የሚቀጥልበትንና አጠቃላይ አለማቀፉ ማህበረሰብ በኤርትራ ላይ የሚወስደውን እርምጃ እንዲያጠናክር የተነደፈው ፖሊሲ ውጤት አልባ እየሆነ ነው።
ለፖሊሲው መክሸፍ ደግሞ ህወሃት በተለይ የተወሰኑ አውሮፓ አገራትን ተጠያቂ እያደረገ ነው። ጄኔቭ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰኔ፣ 2008 ዓም በኤርትራ የሰብአዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን የቀረበው ምክረ ሃሳብ ተግባራዊ እንዲሆን ከፍተኛ የዲፕሎማቲክ ዘመቻ ያካሄደው የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት፣ ከአውሮፓ አገራት ውስጥ ኖርዌይ፣ ጀርመንና ስዊዘርላንድ ከኤርትራ ጋር ስደተኞችን በተመለከተ በጋራ መስራት በመጀመራቸው የአውሮፓ ህብረት ቀደም ብሎ የያዘውን አቋም እንዲያለሰልስ ግፊት ማድረጋቸው ራስ ምታት ሆኖበታል። የተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ በኤርትራ ውስጥ የሚሰሩ ባለሀብቶች የኤርትራውያንን ጉልበት እንደሚበዘብዙ ያወጣው ሪፖርት እንዲሁም ግለሰቦኡ በቡድንም ሆነ በተናጠል ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ ያስቀመጠው ምክረ ሃሳብ የአውሮፓ ህብረት አባላትን ባለማስደሰቱ ፣ ህብረቱ በኤርትራ ላይ በሚወሰደው እርምጃ ላይ የተቀዛቀዘ ስሜት እንዲይዝ እያደረገው ነው።
ከአውሮፓ አገራት በተጨማሪ የአረብ አገራት፣ ቻይና እንዲሁም የተወሰኑ የላቲን አሜሪካ አገራት፣ ከአፍሪካ ግብጽ እና በከፊል ሱዳን ለኤርትራ ድጋፍ በመስጠት በምክር ቤቱ ውስጥ ጉዳዩ እንዲቀዛቀዝ ማድረጋቸው የህወሃትን ባለስልጣናት በእጅጉ አስቆጥቷል።
ህወሃት መራሹ መንግስት በዚህ አመት ጅቡቲና ሶማሊያን በተዘዋዋሪ መንገድ በመጠቀምና ለእነሱ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ተመድ በኤርትራ ላይ ጠንካራ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካለትም። ይህንን የ2017 የተመድ የውሳኔ ሃሳብ የደገፉት አገራት ኔዘርላንድስ ፣ ክሮሺያ፣ ቤልጂየም፣ ኦስትሪያ፣ ካናዳ ፣ ፖላንድ፣ ግሪክ፣ አየርላንድ እና ሮማኒያ ብቻ ሲሆኑ፣ ተመድ በ2016 ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ከደገፉት አገራት ጋር ሲነጻጻር በእጅጉ አንሶ ተገኝቷል። በ2016 በተላለፈው ውሳኔ 2 ዋና ስፖንሰሮችና 19 ተባባሪ ስፖንሰሮች የነበሩ ሲሆን፣ በ2015 ውሳኔ ደግሞ 7 ዋና ስፖንሰሮችና 16 ተባባሪ ስፖንሰሮች ነበሩ። በአጠቃላይ የአለም አገራት በተለይም አውሮፓውያን በኤርትራ ላይ የያዙትን አቋም እያለሳለሱ መምጣታቸውን የሚያሳይ ሲሆን፣ በዚህ የተበሳጨው ህወሃት ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ህብረት በመውሰድና የአፍሪካ ህብረት የኤርትራ መንግስት ተጠያቂ የሚሆንበትን አሰራር ለመንደፍ ላይ ታች እያለ ነው።
የህወሃት ዋና ግብ የኤርትራ ጉዳይ ወደ ተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ተመርቶ ከዚያም ወደ አለማቀፍ ፍርድ ቤት ( ICC) እንዲሄድ በማድረግ የኤርትራ ባለስልጣናት በወንጀል ተጠያቄ እንዲሆኑ እንዲሁም ከኤርትራ ጋር አብረው ይሰራሉ በሚላቸው የኢትዮጰያን ተቃዋሚ ሃይሎች ላይ እርምጃ ማስወሰድ ነው።
ህወሃት የአውሮፓ አገራት የያዙትን አቋም መልሰው እንዲቀይሩ አሁንም ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነው።

No comments:

Post a Comment

wanted officials