Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, August 4, 2017

አንድ የመከላከያ ባልደረባ የሆኑ ጄኔራል በበሌብነት ወንጀል ተጠርጥረው ታሰሩ

(ኢሳት ዜና)

አንድ የመከላከያ ባልደረባ የሆኑ ጄኔራል በሌብነት ወይንም በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መታሰራቸው ይፋ ሆነ።
ፓርላማው ለነገ የጠራው አስቸኳይ ስብሰባም ለምን እንደተጠራ ሳይነገር የሰአታት ጊዜ ቀርቶታል።
የገዢው ፓርቲና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ፓርላማው የተጠራው አዳዲስ ሚኒስትሮችን ለመሾም ጭምር እንደሆነ ገልጸዋል።
የመንግስትና የፓርቲ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በቁጥጥር ስር ውለው ዛሬ ሐሙስ 27/2009 ፍርድ ቤት የቀረቡት ብርጋዴር ጄኔራል ኤፍሬም ባንጌ የተባሉ የመከላከያ ሰራዊት ባልደረባ ናቸው።
ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 የስኳር ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ እንደሆነም ተመልክቷል።
የመንግስትና የፓርቲ መገናኛ ብዙሃን ጄኔራሉ በኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 ፕሮጀክት ውስጥ ስላላቸው ሃላፊነትም ሆነ ሚና ያሉት ነገር የለም።
ሆኖም ከዚሁ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ 184 ሚሊየን ብር ለግል ጥቅማቸው አውልዋል የሚል ክስ እንደቀረበባቸው ዘገባዎቹ አመልክተዋል።
ከተጠቃሹ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት በጀት ላይ ተቀናሽ በማድረግ ካልተያዙ ደላሎች ጋር በመመሳጠር 184 ሚሊየን ብሩን ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውንም ዘርዝረዋል።
ማክሰኞ በቁጥጥር ስር ውለው ከአንድ ቀን በኋላ ሐሙስ ሐምሌ 27/2009 ፍርድ ቤት ከቀረቡት ከብርጋዴር ጄነራል ኤፍሬም ባንጌ ጋር የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የቀድሞ ስራ አስኪያጅና ከመንገዶች ባለስልጣን አንድ ሃላፊ አብረው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
የቀድሞው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ በጋሻው በአጠቃላይ ከ82 ሚሊየን ብር በላይ የመንግስት ሐብት በማባከን ሲጠየቁ የመንገዶች ባለስልጣን የእቃ አቅርቦት ቡድን መሪ አቶ ካሳሁን ካቺ ደግሞ በ26 ሚሊየን ብር መጠየቃቸው ተመልክቷል።
በሙስና በግንባር ቀደምትነት ስማቸው የሚጠቀሰው ብርጋዴር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውና ሌሎች የህወሃት ጄኔራሎች ሳይነኩ የማይታወቁና ይህ ነው የማይባል ሚና ያልነበራቸውን ጄኔራል ግንባር ቀደም ተጠያቂ አድርጎ ማቅረቡም አነጋጋሪ ሆኗል።
ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ የአቶ አባይ ጸሐዬ ባለቤት ወይዘሮ ሳሌም ከበደ ገብሩ እንዲሁም የአቶ አባይ ጸሐዬ የንግድ ሸሪክ ናቸው የሚባሉት አቶ የማነ ግርማይ በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል የሚጠቀሱ ሆነዋል።
የ77 ቢሊየን ብሩን ፕሮጀክት በበላይነት የሚመሩትና በሙስና ስማቸው ጎልቶ የሚጠቀሰው አቶ አባይ ጸሓዬ እስካሁን ለምን ተጠያቂ አልሆኑም የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል።
አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ለነገ አርብ ሐምሌ 28/2009 የተጠራው የፓርላማው አስቸኳይ ስብሰባ የአቶ አባይ ጸሐዬንና የሌሎች ተጠርጣሪዎችን ያለመከሰስ መብት ሊያነሳ ይችላል ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
የሕወሃት አመራር ወደዚህ እርምጃ መሔዱን ግን የሚጠራጠሩ ጥቂት አይደሉም።
የፓርላማው የነገ ስብሰባ የተጠርጣሪዎችን ያለመከሰስ መብት እንዲያነሳ ከተወሰነ ከአቶ አባይ ጸሐዬ በተጨማሪ የሌሎች ተጠርጣሪዎችም ያለመከሰስ መብት እንደሚነሳ ይጠበቃል።
ፓርላማው የጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ለምን እንደሆነ የፓርላማው የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ጸዳለ ረጋሳ እንደማያውቁ ቢናገሩም የፓርቲና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ፓርላማው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲሁም አዳዲስ በሚሾሙ ሚኒስትሮች ጉዳይ ላይ ድምጽ እንደሚሰጥ ዘግበዋል።
በሚኒስትር ስልጣን ላይ የቆዩትን የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትሩን አቶ ካሳ ተክለብርሃንን ጨምሮ የተወሰኑ ሚኒስትሮች በቅርቡ በአምባሳደርነት ተሹመዋል።
አዲሱ ሹመት እነሱን ከመተካት ባሻገር ብወዛና ማባረርን ሊጨምር እንደሚችልም የፖለቲካ ተኝታኞች ይገልጻሉ።

No comments:

Post a Comment

wanted officials