ከቤንሻንጉል ለተፈናቀሉና በባህርዳር ለሚገኙ የአማራ ተወላጆች እርዳታ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ የሙዚቃ ኮንሰርት ለማዘጋጀት ማቀዳቸውን ታዋቂ ድምጻውያን ገለጹ።
አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ፥ አርቲስት ፍቅርአዲስ ነቃ ጥበብ እና አርቲስት አምሳል ምትኬ ተፈናቃዮቹ ወደሚገኙበት ባህርዳር ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በማምራት የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።
በአሜሪካ የሚገኘው አርቲስት መሐሪ ደገፋውም 30 ሺህ የኢትዮጵያ ብር ለተፈናቃዮቹ ልኮ በአርቲስቶቹ በኩል እንዲደርስ ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል።
አርቲስቶቹ በቤተክርስቲያኒቱ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች ምግብ ከማብላታቸው በተጨማሪ በጠቅላላ 90 ሺህ ብር የሚገመት ገንዘብ መስጠታቸውን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም እርዳታውን የሰጡት ታዋቂ ድምጻውያን ከቤንሻንጉል ጉምዝ ተፈናቅለው በባህርዳር ለሚገኙ የአማራ ተፈናቃዮች የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ ኮንሰርት ለማዘጋጀት ማቀዳቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
ኮንሰርቱ መቼና በምን ሁኔታ እንደሚካሄድ አርቲስቶቹ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም።
No comments:
Post a Comment