የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለሕዝብ የሰጡትን የዲሞክራሲ ተስፋ ተግባራዊ የሚያደርጉ ከሆነ የትጥቅ ትግሉን ሊያቆም እንደሚችል ገለጸ።
ንቅናቄው የሰለጠነ ፖለቲካ የምንመርጠው፣የምናውቀውና የምመኘው የትግል ስልት ነው በሚል ባወጣው መግለጫ እንዳለው አርበኞች ግንቦት ሰባት የመሳሪያ ትግልን ዋነኛ የትግል ስትራቴጂው በማድረግ የፖለቲካ ስልጣን የመያዝ አላማ ኖሮት አያውቅም።
ሆኖም ግን አገዛዙ ይከተለው በነበረው ኋላ ቀር ፖለቲካ ምክንያት ዜጎች ከመንግስት ሽብር ራሳቸውን እንዲከላከሉ ሲያበረታታና እራሱንም ከጥቃት ሲከላከል ቆይቷል ብሏል በመግለጫው።
አርበኞች ግንቦት ሰባት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሰሞኑን ለፓርላማ ያደረጉት ገለጻ የሚያበረታታና የሚደነቅ ሲል አወድሶታል።
መንግስት የሽብር ተግባር ይፈጽም እንደነበር ዶክተር አብይ በይፋ መናገራቸውና የፍትህ ስርአቱ ችግር ያለበት መሆኑን ማመናቸው ሃቅን ለመናገር የሚደፍሩ መሪ መሆናቸውን ይሳያል ሲል ንቅናቄው ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።
ይህ ብቻ አይደለም እሳቸው የሚመሩት ቡድንም ለሃገራዊ መግባባት ያለውን ዝግጁነትም ያሳያል ብሏል አርበኞች ግንቦት ሰባት።
ዶክተር አብይ በቋንቋ ላይ የተመሰረተውን ክልል የሚያጠና ኮሚሽን ይቋቋማል ማለታቸውንም አዎንታዊ ነው ሲል በመግለጫው አመልክቷል።
ሕወሃትንና የትግራይን ሕዝብ ለይቶ ስለመመልከት ዶክተር አብይ አህመድ የተናገሩትም አርበኞች ግንቦት ሰባት ከልብ የሚያምንበትና በጽናት ሲያራምደው የቆየ እምነት መሆኑንም ገልጿል።
እንደ አርበኞች ግንቦት ሰባት መግለጫ ከሆነ በሕወሃት ውስጥ የለውጥ ሃይሎች መኖራቸው እሙን ነው።
እናም የኢትዮጵያን ሰቆቃ በመቀነስ ረገድ ሕወሃት ውስጥ ያሉ የለውጥ አራማጆች ሚና ከፍተኛ መሆኑን እናምናለን ብሏል አርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ በመግለጫው።
ስለሆነም ከእነዚህ የለውጥ ሃይሎች ጋር ተባብረን ለመታገል ዝግጁ ነን ሲል ንቅናቄው በመግለጫው አስታውቋል።
በመገዳደል ስልጣን መያዝም ሆነ በስልጣን መቆየት ኋላቀር ፖለቲካ ነው በሚል ዶክተር አብይ ግንቦት ሰባት የትጥቅ ትግሉን እንዲያቆም ላቀረቡት ጥሪም ንቅናቄው ምላሽ ሰጥቷል።
እንደ ንቅናቄው መግለጫ አርበኞች ግንቦት ሰባት የመሳሪያ ትግልን ዋናው ስትራቴጂው አድርጎም ሆነ በዚሁ መንገድ ስልጣን የመያዝ አላማ ኖሮት አያውቅም።
እናም ዶክተር አብይ ለዲሞክራሲ የሰጡትን ተስፋ በተግባር የሚለውጡ ከሆነ የትጥቅ ትግሉን ሊያቆም እንደሚችልም ንቅናቄው አስታውቋል።
አርበኞች ግንቦት ሰባት በዜጎች ላይ የሚደርስ ግልጽ ጥቃት እስከሌለ ድረስ በትጥቅ ትግል የምናባክነው ጊዜ፣ጉልበትና እውቀት የለንም ሲል መግለጫውን አጠናቋል።
No comments:
Post a Comment