መ/ር ታሪኩ አበራ
ሐሰተኛው ነቢይ እዩ ጩፋ በጥንቆላ ድግምት የሚዘጋጀውንና በሰዎች መንፈስ ላይ ከፍተኛ ድንዛዜ የሚያመጠውን የሟርት ዘይት በአደባባይ እየሸጠ ነው።
በሌሎች አፍሪካ ሀገራት በተዳጋጋሚ ስንመለከት የነበረው ከጥንቆላ ጋር የተያያዘው አጋንንታዊ አሰራር ሀገራችንም ውስጥ በገሃድ ገብቶ እየተተገበረ ነው።
ሐሰተኛው ነቢይ ቡሽሪ የተለያዩ ዘይቶች ላይ ከጠንቋዮች የተዋረሰውን ምትሐታዊ ድግምት እየተጠቀመ የራሱን ፎቶ በመለጣጠፍ መለኮታዊ ፈውስ ታገኙበታላችሁ እያለ ሕዝብ የሚያጭበረብርበት ሕገ ወጥ ችርቻሮ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ሐሰተኛ ነቢያት ኮፒ ተደርጎ ሕዝብ እየተጭበረበረ ነው ።ይህ ጉዳይ በመንግስት አካላት በሕግ ቁጥጥር ስር ሊውል የሚገባው ሕገወጥ ወንጀል ነው።
ሐሰተኛው ነቢይ ቡሽሪ በዘይት ችርቻሮው ዝም ሲባል የኢየሱስ ደም ነው ግዙ እያለ በ500 ዶላር እያሸገ ይሸጥ የነበረው የባዕድ ነገር ውሕድ በሕዝብ ላይ ከፍተኛ የጤና ጉዳት ሲያስከትል ነበር።በቅርቡ ይህም ወንጀል ሀገራችን ውስጥ መፈጸሙ አይቀሬ ነው።
አጭበርባሪው ነቢይ እዩ ጩፋ ፎቶውን ለጥፎ ለችርቻሮ ያቀረበው የድግምት ዘይት ቀን በአንድ ሺህ ብር አመሻሽ ላይ 50% ቅናሽ ተደርጎ በአምስት መቶ ብር ለየትኛውም ችግር ፍቱን መፍትሔ ተብሎ ሲሸጥ ነበር።
የፌደራል የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ምን እየሠራ ይሆን ?
ያለምንም ንግድ ፈቃድ ሃይማኖትን ተገን አድርገው ያልተገባን ጥቅም ለማግኘት የሚደረግ ንግድ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱ በግዙፏ አዲስ አበባና በግዙፏ ሐዋሳ በጠራራ ፀሐይ የሕግ አስፈጻሚ አካላት አላዩም ማለት አስቂኝ ነው ።
ከፍተኛ የሸማቾች ጥበቃ እናደርጋለን በሚባልባት ሀገር የምግብ ዘይቶችን በብልቃጥ በመቀናነስና መለኮታዊ ኃይል አላቸው በሚል የማጭበርበሪያ ስልት እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ መሸጥ ካላስጠየቀ ምን ሊያስጠይቅ ይሆን ??
ኮንትሮባንድ ማለት ያልተፈቀደ ንግድ እስከሆነ ድረስ ይህን ወንጀለኛ ግለሰብ በአፋጣኝ የሀገሪቱ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አለመጠየቅ የወንጀል ተባባሪ መሆን ነው።የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት በአንቀጽ ያስቀመጠው መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም የተባለው የእምነት አስተምህሮና ዶክትሪን ላይ አይዳኝም ለማለት ነው እንጂ ሃይማኖት በኮንትሮባንድ ንግድ ሲገኝ ወይም ጣልቃ ሲገባ መንግስት በዝምታ ሕዝቡን ማዘረፍ ምርጫው ነው ማለት አይደለም፤ ስለሆነም መንግስት አስፈላጊውን የቅጣት እርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነትን ሊያስከብር ይገባል።አሊያ ግን ሕዝብን መናቅ ነው።
እባካችሁ ለሌሎችም ሼር በማድረግ ሕዝባችንን እንታደግ
No comments:
Post a Comment